ሴቶች ለቤተሰባቸው፣ ለአካባቢያቸው፣ ለአገራቸው ዓለፍ ሲልም ለምድራችን ድምቀት በመሆን ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸው ስለመሆኑ በብዙ ይነገራል:: የሴቶች ቀን በሚከበርበት ማርች 8 ላይ ሆኖ ለብዙ ሴቶች ቅርብ የሆኑ እንግዶች ሃሳብን ማዳመጥ ደግሞ የሚሞላው አንድ ክፍተት እንዳለ ይታመናል:: ታድያ የዛሬዋ እንግዳችንም ከኢትዮጵያውያን ሴቶች አልፎ ለአፍሪካ ሴቶችም ቅርብ ናቸው:: የኢጋድ አባል አገራት በንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። የዛሬው ልዩ እትም እንግዳችን ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ:: በሥራቸው ምክንያት ከሴቶች ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ ለጉዳዩ ቅርብ ሆነው በሴቶች ቀን ስለሕይወት ተሞክሯቸውን እንደሚከተለው ያጋሩናል።
ወይዘሮ እንግዳዬ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ጀነራል ዊንጌት አካባቢ ነው የተወለዱት። ይሁን እንጂ በቤተሰብ የሥራ ባህሪ ምክንያት በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ባዶዋቾ ወረዳ ሾኔ ከተማ አድገዋል:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በሾኔ ከተማ ተከታትለዋል:: በወቅቱ በሾኔ ከተማ ከሰባተኛ ክፍል በላይ ትምህርት ቤት ባለመኖሮ በድጋሚ ወደ ትውልድ ቦታቸው አዲስ አበባ በማቅናት ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: የ12ኛ ክፍልን ደግሞ በደብረዘይት ተናኜ ወርቅ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል::
በነበራቸው ውጤት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቢጀምሩም ወላጅ እናታቸውን በሞት ማጣታቸው ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተገድደው ነበር:: በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሴት የቤት ድምቀት ከመሆኗ ባለፈ እናት ስትሆን ደግሞ የቤተሰቡ ሁሉ ነገር መሆኗ አይቀሬ ነው:: በተለይም የቤተሰቡ ሕልውና የሆነችው እናት ከቤቱ በጎደለች ጊዜ ሴት ልጅ እናቷን በመተካት ጎዶሎውን የመሙላት፤ ሽንቁሩን የመድፈን፤ ያዘመመውን የማቅናት ትልቁ ኃላፊነት በሷ ጫንቃ ላይ ይወድቃል:: የወይዘሮ እንግዳዬ ዕጣ ፈንታም ከዚህ ውጭ አልሆነምና የህግ ትምህርታቸውን አቋርጠው የእናታቸውን ሚና ለመወጣት መውተርተር ጀመሩ።
‹‹እረፍት አላውቅም መስራት ያስደስተኛል›› የሚሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሼል ዴፖ ውስጥ የሽያጭ ሠራተኛ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ያላቸውን ትጋትና ጥንካሬ የተረዱት የሼል ዴፖ ማናጀር በወቅቱ እንግሊዝ አገር ሄደው ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበትን ዕድል አመቻችተውላቸው የነበረ መሆኑን ያስታውሳሉ:: ይሁንና ወላጅ እናታቸው ከዚህ ዓለም በመለየታቸው የውጭ ጉዞውን ጨምሮ ሌሎች ዕድሎችንም መጠቀም አልቻሉም:: ምክንያቱም ሴት ሊያውም የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ናቸውና ነው::
ወላጅ አባታቸውን በልጅነታቸው ያጡት ወይዘሮ እንግዳዬ እናታቸውን በሞት ባጡ ጊዜ ትምህርታቸውን አቋርጠው ታናሽ ወንድማቸውን ጨምሮ ቤተሰቡን የመምራት ኃላፊነትን ተረክበዋል:: በዚህ ወቅት እናታቸው ይሰሩት የነበረውን ሥራ ተረክበው ሕይወት እንዲቀጥል አድርገዋል:: ከወላጅ እናታቸው የተረከቡትን ጠጅ ቤት ወደ ምግብ ቤት በመቀየር ደቡብ ክልል ሾኔ ከተማ ውስጥ እናትዓለም ሆቴል በማለት ሰርተዋል:: የሆቴል ሥራውን በማጠናከር በተለያዩ የትምህርት ቤት ክበቦች ውስጥ ሰርተዋል:: ከሆቴሉ በተጨማሪም በተለያዩ የንግድ ሥራዎች አልፈዋል:: ከእነዚህም መካከል የእህል ወፍጮ ቤት፣ ከፋብሪካ ተረክበው ሲጋራ ማከፋፈልና በቡና ንግድም ተሳትፈዋል::
ወላጅ እናታቸው በጥቂቱም ቢሆን ፊደል የቆጠሩ መሆናቸውን ሲናገሩ ‹‹እናቴ ለእኔ ትምህርት ትልቅ ድርሻ ነበራት፤ እናቴ ለኔ ተምሳሌቴ ናት መብራት በሌለበት አካባቢ ስንኖር ኩራዝ አብርታ ለትምህርቴ ትኩረት ሰጥታ ትከታተለኝ ነበር›› በማለት የእናታቸውን አበርክቶ የሚገልጹት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው ቁጭት የገባቸው በመሆኑም ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ በ1994 ዓ.ም ወደ ትምህርት ዓለም በመመለስ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማና የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተው ቁጭታቸውን እንደተወጡ ይናገራሉ::
በማህበረሰብ ውስጥ የሚንጸባረቀው ለሴቶች ያለው አመለካከትና ጎጂ ባህል በአብዛኛው ሴቶችን ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን በማንሳትም ሴቶች በራሳቸው መቆም የሚችሉ እንዳልሆነ ይታመን እንደነበር ይናገራሉ:: ነገር ግን አሁንም ሴት አትችልም ብሎ የሚያምን መኖሩን በመግለፅ፤ ማህበረሰቡ ለሴት ልጅ ያለውን አመለካከት ይኮንናሉ:: “እችላለሁ” ብላ አደባባይ የምትወጣ ሴትም እምብዛም መሆኗን በመግለፅም ይህ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ይገልፃሉ። ከቀደመው ጊዜ በተሻለ እራሷን ለስኬት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት የምታደርግ ሴት ልጅ እንዳለች ቢያምኑም በቂ እንዳልሆነ ግን ይናገራሉ።
‹‹ሴት ልጅ እናት፣ ሚስት እህትና ጓደኛም ጭምር በመሆኗ ወንዶች ከሴቶች ብዙ ይማራሉ›› የሚሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ የወለዷቸውን ሶስት ሴት ልጆቻቸውን ጨምረው በኢትዮጵያ የሚገኙ 320 ሺ ነጋዴ ሴቶች እንዲሁም ከስምንት አገራት የተውጣጡ ስድስት ሚሊዮን ነጋዴ ሴቶችን ያስተዳድራሉ::
ከደቡብ ክልል ዞን ጀምረው ደረጃ በደረጃ በመሸጋገር የኢትዮጵያና የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችም ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው:: አፍሪካን ወክለው የዓለም አባል በመሆናቸውም ከወለዷቸው ሴት ልጆቻቸው ባለፈ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ በንግድ ላይ ለተሰማሩ አፍሪካውያን ሴቶች ቅርብ ናቸው::
በንግዱ ዘርፍ የተሰማራች ማንኛውም ሴት የማህበሩ አባል ሆነችም አልሆነች ለማገዝ በራቸውን ክፍት አድርገው የሚጠብቁት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ በተለይም ሴቶችን በማማከርና የሥራ አቅጣጫ ለመስጠት አይደክሙም አይሰለቹም:: ምክንያቱም ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ ሲችሉ በውስጣቸው ያሉት ወንዶችንም ማሳደግ ይችላሉ:: በዚህም የአገር ኢኮኖሚ ያድጋል ብለው ያምናሉ:: ጉልት ላይ ከምትቸረችር አንዲት ሴት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ንግድ ድረስ ያለው በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው እምነታቸው ነው::
ነጋዴ ሴቶች ለኢኮኖሚው ትልቅ ድርሻ አላቸው የሚሉት ወይዘሮ እንግዬ፤ በተለይም የአገራችን ሴቶች ወጥተው መነገድ እንዲችሉ እቴጌ ጣይቱ ፈር ቀዳጅ የነበሩ መሆኑንም አንስተው አጫውተውናል:: የመጀመሪያውን ሆቴል መክፈት የቻሉ ቀዳሚ ሴት በመሆናቸው በዘመናቸው የነበሩ ሴቶችም ይህን ፈለግ በመከተል ወደ ንግዱ ዓለም መቀላቀል እንደቻሉ አስታውሰው የሴቶች ቀንም በአድዋ ድል ማግስት መከበሩ ደስታ የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል::
በሥራቸው ከሚተዳደሩ ነጋዴ ሴቶች መካከልም በርካቶች ውጤታማ ሆነው መመልከት በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታና ኩራት የሚሰማቸው እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ይህም በሕይወታቸው ያገኙት ትልቅ እርካታ እንደሆነ ይገልፃሉ። ከዚህም በላይ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ እንደሚቻልም እምነታቸው ነው:: ምንም እንኳን የተመቻቸ ነገር ባይኖርም ከሁኔታዎች ጋር በመጋፈጥ በመስራት ሴቶች ጉልበትና ጥንካሬያቸውን መጠቀም አለባቸው ይላሉ::
ምንም ያልነበራቸውን ሴቶች በማበረታታት፣ ወደ ኋላ እንዳይመለሱ በማገዝ፣ በንግድ የተዋጣላቸው ሆነው እንዲነግዱ የተለያየ ስልጠናዎችና የምክር አገልግሎት በመስጠት ሰፊ አበርክቶ እንዳላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ቢሮ ድረስ ለሚመጡ ነጋዴ ሴቶች የምክር አገልግሎት በመስጠት አቅጣጫ በማሳየት መንገዱን ይመራሉ:: ታድያ ለዚህ ሁሉ አገልግሎታቸው አንድም ክፍያ አይጠይቁም:: ሴቶች ሰርተው ገቢ ማግኘት ከቻሉ አልያም እራሳቸውን ከቻሉ ትልቅ ክፍያ ነው:: ከሁሉ በላይ ደግሞ ‹‹የኔ ሴቶች ልጅ ወልደው ማበርከት መቻላቸው በራሱ ትልቅ ክፍያ ነው›› በማለት የሴቶችን የጎላ አበርክቶ ይገልጻሉ::
በዕለት ማርች 8 ስለ ሴቶች ሲነሳ ‹‹የኔ ሴቶች ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ናቸው›› በማለት ኢትዮጵያዊ ሴቶች በተፈጥሮ የተሰጣቸው ልዩ ተሰጥኦ እንዳለ ሲናገሩ፤ በሥራ ምክንያት በተጓዝኩባቸው ከ40 በሚልቁ አገራት የሴቶችን ጥረት የመመልከት ዕድል ገጥሞኛል ይላሉ:: ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ሴት ከሁሉም ትበልጣለች በማለት ስለኢትዮጵያዊ ሴቶች ጥንካሬ ያስረዳሉ::
“ሴቶች ወደ ውጤት እንዲሄዱ ቀስቃሽ ሳያስፈልጋቸው ብዙ ማድረግ ይችላሉ:: ስለዚህ ሴቶች በቅድሚያ እራሳቸውን ማየት አለባቸው:: ሴቶች በተፈጥሯቸው በፍጥነት ሀሳብ የማመንጨትና ሌላውን የማየት ከፍተኛ ችሎታ አላቸው:: በተለይም ኢትዮጵያዊ ሴቶች በጣም ጠንካሮች ናቸው:: ይህን ታዝቤያለው” የሚሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ኢትዮጵያዊ ሴቶች ማንም የማያገኘውን ተፈጥሮ ያደለቻቸው በርካታ ችሎታ አላቸው:: የውጪዎቹ ሳይንሳዊ የሆነ መንገድ ይከተላሉ:: ኢትዮጵያውያን ሴቶች ግን ተፈጥሮ አድላቸዋለች:: ስለዚህ ይህን ታላቅ ስጦታ ተረድተው ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ያስረዳሉ::
በርካታ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች ስለመኖራቸው በማንሳት በተለይም ማርች 8 ሲነሳ በተለያየ መንገድ ሰፊ አበርክቶ ያደረጉ የአገራችንን ሴቶች ማንሳት ቢቻል መልካም ነው የሚሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ለአብነትም እቴጌ ጣይቱን፣ የቃቄ ውረዶትንና ንግስት ሳባን ያነሳሉ:: ታድያ ማርች 8 ወይም የሴቶች ቀንን ስናከብር የእነዚህንና መሰል ጀግና ሴቶችን ታሪክ በማስታወስ ቢሆን በእጅጉ የሚያስደስታቸውና ትውልዱም የሚማርበት እንደሆነም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል::
‹‹ለጠንካራ ወንድ ሴት ወሳኝ ናት አንድ ወንድ ፍንትው ብሎ መውጣት የሚችለው ከበስተጀርባው ባሉ ሴቶች ምክንያት ነው›› የሚሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ እያንዳንዱ ወንድ እናት፣ እህት፣ ሚስትና ጓደኛ ያለው በመሆኑ ከእያንዳንዳቸው የሚያገኘው ቁምነገር አለ:: እነዛ ቁምነገሮች በእርሱ ማንነት ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው:: ብዙውን ጊዜ ግን ይህን አይረዱትም በማለት ወንዶች ጋር ያለውን ክፍተት ይጠቁማሉ::
በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ “የኔ ሴቶች” በትራንስፖርት ዘርፉም ሆነ በማንኛውም ዘርፍ ለሚደርስባቸው እንግልት ቀዳሚ ሆኜ ጉዳያቸውን እንደ ጉዳዬ በማየት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸውና ከችግራቸው እንዲወጡ ባለኝ አቅም ሁሉ እሠራለሁ የሚሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ከመሆን ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት የህዝብ ክንፍ ሆነው ያገለግላሉ:: ነጋዴ ሴቶች በሚያልፉበት መንገድ ሁሉ እንደሚያልፉ ባነሱ ጊዜም የዝግጅት ክፍላችን “ጊዜው እንዴት ይበቃዎት ይሆን” በማለት ላነሳላቸው ጥያቄ ‹‹ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም›› በማለት መልሰውልናል::
በኢትዮጵያ በ14 ማህበራትና በ260 ቅርንጫፎች የታቀፉ 320 ሺ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ጋር ተደራሽ ለመሆን በማህበራቱ አማካኝነት የሚገለገሉት ወይዘሮ እንግዳዬ፤ ሴቶች ባላቸው ትርፍ ጊዜ ሁሉ መሥራት እንዲችሉና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያላቸውን ዕውቀት ሁሉ ሳይሰስቱ ያጋራሉ:: በንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በአብዛኛው ለራሳቸው ደመወዝ የሌላቸው በመሆኑ ካናት ካናቱ በመብላት ኪሳራ እንዳያጋጥማቸውም የተለያየ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ስልጠና ይሰጣሉ::
ላለፉት 16 ዓመታት ከዞንና ወረዳ ጀምረው እስከ ፕሬዚዳንትነት ነጋዴ ሴቶችን በመምራት ሕይወታቸውን ሙሉ ለነጋዴ ሴቶች ሰጥተው እየሰሩ የሚገኙት ወይዘሮ እንገዳዬ በተለያየ ጊዜያት ከአገር ውስጥንና ከተለያዩ አፍሪካ አገራት 50 የሚደርሱ ሽልማቶችን አግኝተዋል:: በመጨረሻም ሴቶች በኢኮኖሚ መፈርጠም እንዲችሉና ያላቸውን እምቅ ችሎታ አሟጠው እንዲጠቀሙ በሚያበረታታ መልዕክታቸው ሀሳባቸውን ሲቋጩ ‹‹ሴቶች ውስጣችሁ ብዙ አቅም አለና ተመልከቱት፤ እኔ ማነኝ በማለትም ቆም ብላችሁ እራሳችሁን ጠይቁ፤ እራሳችሁን አግኝታችሁም ተጓዙ›› በማለት ነው::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2014