እንደ መንደርደሪያ…
ላለሙት ግብ መታገል የኔ ላሉት ጉዳይ መፋለም መለያዋ ነው:: አደርጋለሁ ያለችውን ሳታደርግ እንቅልፍ በዓይኗ አይዞርም:: ግብ አስቀምጦ ህልም ጋር ለመድረስ የሚደረግ ትግልና የሚያስከፍለውን የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ቆርጣ መነሳት ደግሞ ያለፈችበት መንገድ ነው:: ሰዎች ህልማቸውን ለማሳካት የሚሄዱበት የትኛውም ርቀት የምታውቀው ጉዞ ነውና በደምብ ይገባታል::
እየሩሳሌም ነጋሽ ትባላለች:: እናቷ ወይዘሮ ሮማን ደጀኔ አባቷ ደግሞ አቶ ነጋሽ ቡኒ ይባላሉ::ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ከተማ ለገሀር ባቡር ጣቢያው ጀርባ ነው:: የመጀመሪያና መለስተኛ ደረጃ ትምህርቷን በብሔራዊ የህዝብ ትምህርት ቤት ተምራለች::
አምስት ልጆች ባሉበት ቤት ውስጥ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅ የሆነችው እየሩሳሌም ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት:: እየሩሳሌም የቀድሞ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ አምበልና የእንቁዋ ታብራ ውሜን ኢምፓወርመንት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ናት::
የልጅነት ጊዜ
ቀልጣፋና ነገሮችን ለመረዳት ቅርቧ እየሩሳሌም የልጅነት ጊዜዋን እግር ኳስን ለመጫወት በመለማድ ትምህርቷን በማጥናት ለቤተሰቦቿ በመታዘዝና በመላክ አሳልፋለች::
እንደ መጨረሻ ልጅነቷ ቀብጣ ነበር ያደገችው:: ቤት ውስጥ ከነበሩት ከአራቱ ታላላቆቿ የተሻለ ቅንጦት የተሞላበት ህይወትንም አሳልፋለች:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ውስጥ ህልምን ለመኖር የራስ ፍላጎት ብቻውን በቂ አይደለምና ቅብጠት የተሞላው ልጅነቷ ግን ያለመችውን ሁሉ እንደ ፍቃዷ ለማድረግና የፈለገችውን ለመስራት የይለፍ ቃል አልሰጣትም::
ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመኙት አድገው ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ዶክተርና ኢንጅነር ወይም ሌላ አይነት የሙያ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩላቸው ነው እንጂ አግር ኳስ እንዲጫወቱ የሚፈልጉ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ እግር ኳስ መጫወት እንደ ዱርዬነት በመታሰቡም በተለይ ሴቶች በእግር ኳስ ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አይፈለግም ነበር::
እግር ኳስና እየሩሳሌም
ልጅነቷን ስታስታውስ በትዝታዋ ማህደር ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዘው እግር ኳስ ነው:: ቀድሞም በህፃንነት ልቧ ለኢትዮጵያና ልጆቿ ብርቅ በሆነ ነገር ፍቅር ተጠልፋ ነበር:: ነፍስ ስታውቅ ከእግር ኳስ ፍቅር ጋር ወድቃ ነው ከልጅነት እንቅልፏ የነቃችው::
በልጅነቷ የነበራትን እግርኳስን ተጫውቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማልያ የመልበስ ከፍተኛ ፍላጎትና ፍቅር ለማሳካት የተጓዘችበት ረጅም ርቀት ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር:: እነዛ ለእግር ኳስ የከፈለቻቸው ዋጋዎች እንደ እድሜ እኩዮቿ ሴቶች አይነት መንገድን ብትጓዝ ላትከፍል የምትችለው መስዋዕትነትም ነበሩ::
ከእግር ኳስ ጋር የነበራት ትስስር ከቤተሰቦቿ እስከ ሌሎች የቅርብ እስከምትላቸው ሰዎች ድረስ ተቀባይነት አልነበረውም:: የእግርኳስ ፍቅሩም ችሎታውም የነበራት እየሩሳሌም ግን የማንንም ተስፋ ማስቆረጥና ያለመፈለግ ሳታዳምጥ ለህልሟ ብዙ ዋጋ ከፍላለች::
የወንድ በሚባለው ስፖርት ላይ ሴቷ መገኘቷ ብዙ ዋጋን አስከፍሏታል:: እሷ እግር ኳስ በምትጫወትበት ወቅት ለልምምድ ስትወጣ ብቸኛ ሴትም ነበረች:: ብቸኛ መሆኗ የሚኖረው ደስ የሚል ነገር ቢኖረውም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖው ግን ይበዛል::
በሷ የተጫዋችነት ዘመን አንድ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን ሰዎች በተለምዶ ወንድ የሚሏት አይነት ሴት መሆን ባህሪያቶቿም ከሴት ይልቅ ወደ ወንድ የሚቀርቡ መሆን ይጠበቅባቸዋል:: እየሩሳሌምም እግር ኳስን ለመጫወት ስትል ብቻ እንደ ወንድ እየለበሰች እንደ ወንድ እየተራመደችና ፀጉሯን እየተቆረጠች ነበረች:: ራሷንና ማንነቷን መስዋዕት አድርጋ ነው በአስራ ሰባት ዓመቷ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የእግር ኳስ አምበል ለመሆን በቅታለች ::
እግር ኳስን ብላ ስፖርትን አስቀድማ በብዙ መውጣት መውረድ ውስጥ ያለፈችው እየሩሳሌም የሴት ብሄራዊ ቡድኑ አምበል መሆን መቻሏ በትልቁ የምትኮራበት አንገቷን ቀና አድርጋ የምትኖርበት የህይወቷ ትልቅ ድል መሆኑንም ትናገራለች:: በእግር ኳሱ ያገኘችው ስኬት አጋጣሚ ፈቅዶ ያገኘችው ሳይሆን አስባ አቅዳና አስልታ ያገኘችው ስኬት ነበር::
በንፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች ለሶስት ዓመታት ኮኮብ ግብ አግቢና ኮኮብ ተጫዋችነቷን ሳታስነጥቅ መቆየት ብትችልም በእግር ኳስ ምክንያት አስተማሪዎቿ በትምህርት ረጅም መንገድ መጓዝ እንደማትችል ተስፋ መቁረጥ ታየባቸው::
የህይወት ከባድ ቀናት
እየሩሳሌም ከትምህርቷ ይልቅ ሙሉ ትኩረቷን እግር ኳስ ላይ ማድረጓ በ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤቷ ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባትን ነጥብ ማምጣት ሳትችል መቅረቷ የህይወቷ ከባድ ጊዜ ሲሆን እግር ኳስን ለኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ክለብ በመጫወት ላይ ባለችበት ወቅት ልምምድ እየሰራች በእግሯ ላይ ያጋጠማት ጉዳት ሌላው ነው::በኢትዮጵያውያኑ የጊዜ ቀመር በትልቁ የሚታወሰው ሚሌኒየም ላይ ከእግር ኳስ ጋር የነበራትን ግንኙነት ቋጨችና ጫማዋን ሰቀለች::
በህይወቷ የምታውቀው ብቸኛ ነገር እግር ኳስ ነበርና ነገሮች የተደበላለቁባት ሰማይ የተደፋባትም ወቅት ነበር፤ ለእግር ኳስ ጨዋታ ብላ ባዳበረችው ወንዳወንድ ባህሪይዋ ምክንያት የሴት ጓደኛ አልነበራትም ፤አብዛኛው ሰውም እግር ኳስ ተጫዋች በመሆኗ ደስተኛ ስላልነበር ማህበራዊ ህይወቷም የተጎዳ ነበር:: ይህ ደግም ህይወትን አከበደባት ::
በዚህ ጊዜ ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ትምህርቷ ላይ መበርታት እንደነበረባት ተሰማት ጸጸትም በረታባት፤ ካለፈ በኋላም ቢሆን እግር ኳስ እየተጫወተች መማርና በትምህርቷም መበርታት ትችል እንደነበር ገባት::
ቢረፍድም በትንሿ እየሩሳሌም ላይ አስተዋይ ያለመሆን እንዲሁም ለአንድ እግር ኳስ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ሌሎችን የህይወቷን ጉዳዮች መተው ታይቶባት እንደነበርና ህይወቷን ከዚህ በተለየ መንገድ መቅረፅ ትችል እንደነበር ተረዳች::
የትዳር ህይወት
እግር ኳስ መጫወት ካቆመች በኋላ ወደ እምነት ስፍራዎች ማቅናትን ልምድ አደረገች፤ ባለቤቷ የሰፈሯ ልጅና አዘውትራ የምትሄድበት ቤተክርስቲያን መምህር ነው:: በጊዜ ብዛት በመቀራረብ ለትዳር መብቃት ቻሉ:: እዮሲያስ ቴዎድሮስና ዮሀና ቴዎድሮስ የተባሉ ሁለት ልጆች ያሏት እየሩሳሌም ከባለቤቷ ከፓስተር ቴዎድሮስ ጋር ለአስራ ሁለት ዓመት የዘለቀ ትዳር አላቸው::
የትዳር ህይወቷ እየሩሳሌምን ከብዙ ውጣ ውረድ ከብዙ ስህተት ታድጓታል፤ ከትዳር በኋላ ህይወቷ ሌላ መልክ ያዘላትና ትምህርቷን ደግማ ተፈትና የማለፍያ ውጤት ማምጣት ቻለች:: ድሮ ከእግር ኳስ ውድድሮቿ ጎን ለጎን ማድረግ ያቃታትን ነገር ሁሉ አሁን ከትዳር ጋር ማከናወን ቻለች::
ትምህርቷ ላይ በመግፋት በማማከር አገልግሎት የመጀመርያ ዲግሪዋን ማግኘት እንዲሁም ኢቫንጄሊካል ቲዎሎጂ ኮሌጅ ውስጥ የሶስተኛ ዓመት ተማሪም መሆን ቻለች::
ባለቤቷ በህልሟ ማመኑና ማድረግ ትችላለች ብሎ ማሰቡ ህይወትን ቀለል ያለ እንዲሆን እንዳደረገላት ትናገራለች :: በትዳር ህይወቷ ሲበዛ ደስተኛና አመስጋኝ ናት፤ እየሩሳሌም በነበሯት ስኬቶች ላይ ሁሉ አሥራ ሁለት ዓመታትን ያሳለፈችበት ትዳሯ ነው ምክንያቱ :: ስለ ባለቤቷ ቴዎድሮስ ተናግራ አትጠግብም::
እንቁዋ ማናት?
ከዓመታት በፊት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ያልተዘጋው ዶሴ የተሰኘና የወንጀል ታሪኮች የሚቀርቡበትን ዝግጅት ማየት ታዘወትር እንደነበር ያወሳችው እየሩሳሌም ከእለታት በአንዱ ቀን ያንን ዝግጅት ስትመለከት የታየው ነገር ልቧን ነካት ፤ ባየችው ዝግጅት ውስጥ እንቁዋ ታብራ “ውሜን ኢምፓወርመንት “ን ማቋቋም እንደ መፍትሄ ሆኖ አገኘችው::ለድርጅቱ መመስረት ትልቁ ድልድይ የሆናት በእግርኳሱ ውስጥ የነበራት የመታገልና የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ ነው::
በሁሉም የዓለማችን ክፍል ላይ ሴቶችን አንኳሶ የማየት ችግር እንዳለ ታዝባለች፤ ይህንን አስተሳሰብ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ አምጥታ ስታየው ከዚህ ያለው የገዘፈ ሆነባት:: ሴቶች ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል መፍትሔ ብላ ያሰበችው ደግሞ ወንዶችን አጋር አድርጎ መስራት እንዲሁም ራሳቸው ሴቶች ውስጣቸው ያለውን ችሎታ እንዲያወጡት ማገዝ ነው::
እንቁዋ ታብራ ሁለት ትርጉሞች አለው፤ አንደኛው ማህበረሰቡን እንቁዋ ሴት ልጅ ታብራ ተዋት ውስጧ ያለውን ችሎታ ታውጣ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ራሷ ሴቷ ውስጧ ያለውን እንቁ በማውጣት ለሌሎችና ለራሷ ጥቅም ታውል እንደሆነ ትናገራለች ::
በእንቁዋ ታብራ “ውሜን ኢምፓወርመንት “ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጣሉ:: ከነዚህም መካከል ሴቶችን በተለያዩ ማህበራዊና ፆታዊ ጉዳዮች ላይ ስልጠና መስጠት፣ በዓላትንና ሌሎች ቀናትን ምክንያት በማድረግ የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ይገኙበታል :: በሌላ በኩል እንቁዋ ምሽት የተለያዩ የሀሳብ ውይይቶችና የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማምጣት ጥረት የሚደረግበት ዝግጅት ነው:: ሴቶች ወንዶች እንዴት ከጎናቸው መሆን ይችላሉ የሚሉና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ እቅድ ያወጣሉ ::
እየሩሳሌም ከውጭው ዓለም ቀጥታ መጥተው ኢትዮጵያ ካለው አሁናዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱ የፆታ መብት እንቅስቃሴዎችን አትደግፍም፤ የኢትዮጵያ ሴቶችና የውጭ ሀገራት ሴቶች ችግሩም መፍትሄውም የተለያየ በመሆኑ ሴቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ኢትዮጵያዊ ቁመና ሊኖራቸው እንደሚገባም ታምናለች::
መልእክት
ለሴቶች ትዳር መስርቶ ቤተሰብ ማፍራት መልካም ነው፤ ነገር ግን ለእየሩሳሌም ትዳር መስርቶ ልጆች ወልዶ ማሳደግ የስኬቷ መጨረሻ አልሆነም :: የሴት ልጅ የስኬት ህይወት ቤት ከመምራትም ያልፋል ማለፍም አለበት ትላለች::
እየሩሳሌም በህይወትም በልምድም የራስን ፍላጎት መከተል፣ የኔ የሚሉትን ነገር ለራስ መወሰን ራስን ማስተማር የራስን ጉድለቶች በራስ ጥንካሬ ማሸነፍ ህይወት ላይ ትልቁ ስኬት እንደሆነ ታምናለች::
“ህልሜ ህልሟን ኖራ ለሌላዋ ህልም መፈፀም የምትተጋ እንደ እንቁ የምታበራን ሴት መፍጠር ነው::” የምትለው እየሩሳሌም ለዚያ የሚሆናትን የብዙ ኪሎ ሜትሮች ጉዞ በትንሽ እርምጃ ጀምራለች::
ከሀምሳ ሚሊዮን ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መድረስ ትልቁ ህልሟ ቢሆንም እነሱ ጋር ለመድረስ ግን አጠገቧ ካሉት እንዲሁም በእንቁዋ ታብራ “ውሜን ኢምፓወርመንት “አማካኝነት ልትደርስላቸው ከቻለቻቸው ጀምራለች ::
የምስጋና ችሮታ
በህይወቷ ብዙ ጥሩ ሰዎች አሉና እየሩሳሌም ለነሱ ሰዎች ምስጋናዋን ታቀርባለች:: በማወቅም ባለማወቅ ፈልገውም ይሁን በገጠምኝ ላበረቷት ሰዎች በሙሉ ምስጋናዋን አቅርባለች:: የህይወትን ብርቱ ሰልፎች አብሯት ተሰልፎ ክፉ ቀናትን ከሷ ጋር ለረታው በፀሎት በገንዘብ በሞራልና በሀሳብ ለሚደግፋት ባለቤቷ ምስጋና አቅርባለች::
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2014