ተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ›› ከሚለው መጽሐፋቸው ያነበብኩት አንድ አገላለፅ ጀግኖችን ባስታወስኩ ቁጥር ትዝ ይለኛል። መጽሐፉ በትረካው ውስጥ ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ ጀግንነት ሲያትት ከቆየ በኋላ፡- ‹‹የዚህን ጀግና ታሪክ የጻፈ ጀግና ነው፤ የዚህን ጀግና ታሪክ ያነበበም ጀግና ነው›› ይላል።
አዎ! በዚህ አገላለጽ ውስጥ ብዙ እውነት እናገኛለን። ዛሬ የዓድዋ ታሪክ የመላው የጥቁር ታሪክ ሆኖ የሚወሳው ጀግኖች የታሪክ ጸሐፊዎች ባስቀመጡልን መሰረት ነው። ጀግኖች የታሪክ ዘካሪዎች ስላስተማሩን ነው። ዛሬ ላይ ያለ ወጣት ስለ ዓድዋ ታሪክ አፉን ሞልቶ ደረቱን ነፍቶ የሚናገረው ተቀምጦ ባገኘው ታሪክ ነው።
በዘመነ ኢህአዴግ ወጣቱ የአባቶቹን ታሪክ እየዘነጋ ነው የሚል ሰፊ ወቀሳ በወጣቱ ላይ ይሰነዘር ነበር። ከዚያ ይልቅ በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ ብቻ የሚያተኩርና በአገሩ ጉዳይ ላይ የማይሳተፍ ፈዛዛ ተደርጎ ሲወቀስ ቆይቷል። ያ ሁኔታ የተፈጠረውም በሥርዓቱ ታሪክ ጠልነትና ወጣቱን ሆን ብሎ የማፋዘዝ ሥራ ስለተሰራ መሆኑ በወቅቱ ምሁራንና ፖለቲከኞች ሲገለጽ ቆይቷል።
ዳሩ ግን ይህ ወቀሳ የከነከናቸው ጥቂት ወጣቶች ‹‹የአባቶቻችንን ታሪክ አንዘነጋም፤ በአገራችን ጉዳይም ፈዛዛ አይደለንም›› በማለት ዓድዋን ከተዘነጋበት ማስታወስ ፈለጉ። ሀሳባቸው ተሳክቶ፣ ልፋታቸው ፍሬያማ ሆኖ፣ የጀመሩት ጉዞ አገር አቀፍ ጉዳይ ሆነ፤ ዓድዋንም ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ አደረገ። እስኪ ታሪኩን እናስታውስ።
በ2006 ዓ.ም እንዲህ ሆነ። ‹‹ወጣቱ የአገሩን ታሪክ እየረሳ ነው›› የሚለው ወቀሳ የቆጫቸው ወጣቶች ዛሬም ጀግና መኖሩን ለማረጋገጥ አንድ ነገር አሰቡ። አስበውም አልተውትም አደረጉት። ከመሐል አገር አዲስ አበባ ተነስተው እስከ ዓድዋ ተራራ ድረስ የእግር ጉዞ ማድረግ ዓድዋን ለማስታወስ ሁነኛ ዘዴ ሆኖ አገኙት። 118ኛው የዓድዋ በዓል ሲከበር እነዚህ ወጣቶች ከቦታው በመሆንም አከበሩት። ይህ የዓድዋ የእግር ጉዞ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ተካሂዷል። በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በዚህ ዓመት ጉዞ ዓድዋ አለመካሄዱን ታሳቢ ልናደርግ ይገባል። ለመሆኑ ይህ ታሪካዊ ጉዞ በእነማን ተጀመረ?
አብዛኞቻችን በፌስቡክ ገፁ ላይ ስለሚጽፋቸው አገራዊ ጉዳዮች እናውቀዋለን። ከዚህ ባሻገር ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ወደ ዓድዋ ስላደረገው ጉዞ ብዙ ብለውለታል። ያሬድ ሹመቴ። በ2006 ዓ.ም ጉዞው ካስጀመሩ ሰዎች አንዱ ነው። በ2009 ዓ.ም 121ኛው የዓድዋ በዓል ሲከበር ከጀማሪዎች አንዱ የሆነውን ያሬድ ሹመቴን አነጋግሬ በወቅቱ ከሰራሁት ዘገባ የጉዞ ዓድዋን አጀማመር ላስታውሳችሁ።
በመጀመሪያው ጉዞ ጋዜጠኛ ብርሃኔ ንጉሴ፣ ጋዜጠኛ ዮናስ ሐጎስ፣ ፕሮሞተር መሐመድ ካሳ፣ የፊልም ባለሙያው ሙሉጌታ መገርሳ፣ የፊልም ባለሙያ ዓለምዘውድ ካሳሁን፣ ጋዜጠኛ ኤርሚያስ ዓለሙና ያሬድ ሹመቴ ሆነው ጀመሩት። እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሳይቋረጥ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ቀጥሏል። ባለፈው ዓመት ደግሞ እስከ አላማጣ ድረስ ተደርጓል።
የጉዞው ዋና ዓላማ በወጣቱ ዘንድ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የዓድዋ ታሪክ ማሳወቅና የመገናኛ ብዙሃንን መቀስቀስ ነው። በዚህ ጉዞም ተጓዦች በሚያጋጥማቸው ውጣ ውረድና ድካም ትወስታ ይፈጠራል። ከአዲስ አበባ ዓድዋ 1 ሺ 110 ኪሎ ሜትር በእግር ተጓዙ ሲባል ‹‹ለምን?›› ተብሎ ይጠየቃል። በዚህ ውስጥም ዓድዋ ምን ነበር? እንዴት ነበር የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ይህ የሚፈጥረው መነቃቃት ዓድዋን ያስታውሳል።
በጉዞው ስለተፈጠረው መነቃቃትም ያሬድ ሹመቴ ‹‹ዛሬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚሰጠውን ቃለ ምልልስ ጨምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከዓድዋ በዓል መድረስ በፊት ጀምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ስለበዓሉ እየተነገረ ይገኛል። በማህበራዊ ድረ ገጾችም የምናወጣቸውን መረጃዎች በመቀባበል ስለበዓሉ ብዙ ተብሏል። መንግሥትም ስለበዓሉ ትኩረት መስጠት ጀምሯል›› ሲል ተናግሮ ነበር።
የዓድዋ ጉዞ የመገናኛ ብዙሃንን ከመያዝ በተጨማሪ ደግሞ በጉዞው ወቅት በየደረሱበት ቦታ ሁሉ ስለ ዓድዋ ብዙ እንዲያስተምሩና መነቃቃት እንዲፈጥሩ አድርጓል። ተጓዦችም ራሳቸው ብዙ ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲያውቁ አድርጓቸዋል።
ተጓዦቹ በጉዟቸው ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ሲደርሱ በአካባቢ ያሉ ሰዎችን በማሰባሰብና ስለዓድዋ ትምህርት በመስጠት ነበር። ባረፉበት ቦታ ሁሉ የታሪክ ንባብና የእርስበርስ ገለጻም ሲደረግ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ባለፈው ቅዳሜ የአድዋ ተጓዦችን ጉዞ የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም አስተላልፎ ነበር። በዘጋቢ ፊልሙ ላይ እንደታየውም ጉዞ ብቻ ሳይሆን ከምግብ ማዘጋጀት ጀምሮ ብዙ የማህበረሰቡን ሥራዎችም እያገዙና ለራሳቸውም እየሰሩ፣ ማህበረሰቡም ብዙ ነገር እያገዛቸው ነው። የሴቶች ድርሻ ምን እንደነበር ለማስታወስም፤ በጦርነቱ ከመሳተፍ ጀምሮ ለዘማቾች ስንቅ በማቀበል፣ የቆሰሉትን በማንሳት፣ አልባሳት በመስጠት ከወንዶች ጎን ተሰልፈው ነበር። ሴት የዓድዋ ተጓዦች ይህን ታሪክም ዘክረዋል።
የባለፈው ዓመት እና የዘንድሮው ጉዞ ዓድዋስ ምን መልክ አለው? ተጓዦችስ ምን አስበዋል? በሚለው ዙሪያ ከጉዞው ጀማሪዎች አንዱ የነበረውና በተለያዩ አማራጮች ጉዞውን ሲያስተዋውቀው የቆየው ያሬድ ሹመቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸው፤ ዓድዋ በአምስት ሰዎች ተጀምሮ ቁጥራቸው በየዓመቱ እየጨመረ ሄዶ እስከ 125 ሰዎች ድረስ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል። በተፈጠረው ሁኔታ ጉዞው መቋረጡም ማዘናቸውን ያሬድ አስታውቋል።
‹‹ዓድዋ የዘመን ቅብብሎሽ ነው፤ አንዱን ትውልድ ከሌላው ትውልድ የሚያስተሳስር ነው›› ያለው ያሬድ ሹመቴ፤ ዓድዋ ጦርነት ብቻ ሳይሆን ሰላምንም የሚሰብክ የአንድነት ማሳያ እንደሆነ ተናግሯል። በዓድዋ የውጭን ጠላት ማሸነፍ የተቻለው በአገር ውስጥ አንድነትና ፍቅር እንደነበር አስታውሶ፣ የአገር ውስጥ አንድነትና ፍቅር መገንባት እንዳለበትም አሳስቧል።
እንደ ያሬድ ገለጻ፤ ሥርዓት ሲቀያየር መንግሥታት የነገሱባቸውንም ሆነ ድል ያደረጉባቸውን ቀናት ሊቀያየሩ ይችላሉ። ዓድዋ ግን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝቦች ድል ስለሆነ አይቀያየርም። ለዚህም ነው ትውልድን ያስተሳሰረ ነው የሚባለው። በንጉሣዊ ሥርዓቱም፣ በወታደራዊው የደርግ ሥርዓትም፣ በኢህአዴግም፣ አሁን እያስተዳደረ ባለው መንግሥትም ዓድዋ የካቲት 23 ነው፤ ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድል ነው። ይህ ትውልድን የሚያስተሳስር የድል በዓል ለቀጣዩ ትውልድም የተከበረች አገር ማስረከብ ስላለበት ሁሉም ሰላምን ማስቀደም አለበት ብሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በዚህ ዓመት የእግር ጉዞው ባይደረግም በዓሉ ግን በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ነው ያሬድ የተናገረው። ለዚህም የራሱ የያሬድ ሹመቴ ‹‹ዓድዋስ›› የተሰኘ ቴአትር ተዘጋጅቶ ለዕይታ ቀርቧል። በቀጣይ ቅዳሜ የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምሁራን የፓናል ውይይት ይደረጋል። በዚህ ውይይትም ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ገለጻዎችና ውይይቶች ይደረጋሉ።
እንደ ያሬድ ገለጻ፤ የመንግሥት ተቋማትም ቢሆኑ በጀት ስለተያዘ ብቻ በአሉን በግብር ይውጣ ከሚያከብሩ በአግባቡ በዓሉን ለትውልድ በሚያስተዋውቅና ለቀጣይም የአንድነት ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል በሚያደርግ መንገድ ማክበር እንዳለባቸው አሳስቧል።
የጉዞ ዓድዋ አስጀማሪዎችን እያመሰገንን፤ ይህ የጋራ የድል በዓል ግን እንዳይደበዝዝ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል። ዓድዋ የኩራታችን መነሻ ነው። እንደማንኛውም ቅኝ ተገዢ አገር ‹‹የነፃነት ቀን›› ብለን አይደለም የምናከብረው፤ የድል ቀን ተብሎ ነው የሚከበረው።
ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠራበት የድል ቀን ነው። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካም ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ከነጭ እኩል መሆንን ያስመሰከረ ነው። ጥቁርን ሊገዛ የነበረን ነጭ አሳፍሮ ነጭን እኩል የማድረግ እንቅስቃሴን ያስጀመረ ነው። ስለዚህ የዓድዋ የድል ቀን በሁላችንም ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014