እኔም ለጣይቱ
ጣይቱ ጠቢብ ናት በገናን ደርዳሪ ግጥምም ገጣሚ፣
ማንበብን የምትችል ጥበበኛ መሪ፤
የበፊት ባሎቿን ምንም ብትፈታ፣
ንጉሡን በፍቅር በአስተሳሰብ ረታ፣
በወግ በማዕረግ በተክሊል አግብታ፣
አደብ አስያዘቺው ባፈናን አስታ፤
አዲስ አበባን ፊንፊኔን መሥርታ፣
እንጦጦ ማርያምን ቤተስኪያን ገንብታ፣
የእርሻ፣ የብርድ ልብስ የጥጡን ፋብሪካ፣
የባንክ አክሲዮኑን ማህበር አደራጅታ፣
አምስት ሺህ ጦርን ከፊት እየመራች፣
ተዋግታ አዋግታ፣
የውጫሌውን ውል ቀድማ የተረዳች፣
ቁስለኛን ያከመች ምግብ የመገበች፣
እቴጌ ጣይቱ የጀግኖች ጀግና ነች፤ በማለት ነበር የአምቦ ዩኒቨርስቲ የሕግ አማካሪ ወይዘሮ ቱሩፋት በላይነህ በግጥማቸው የዓድዋና የሴቶች ሚናን ለማስረዳት የሞከሩት። ቀጥለውም ብዙ ማብራሪያ ሰጥተውናል። የዓድዋውን ተሳትፏቸውን ብቻ ሳይሆን ከዓድዋ በኋላ የሆኑትን እስከ አሁኑ የህልውና ዘመቻ ድረስም ምሳሌ የሆኑ ሴቶችን በመጥቀስ ተሳትፎዋቸውን ዘርዘር አድርገው አንስተዋል። እኛም ቢሆን ያግዛል ያልነውን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በመውሰድ አክለንበት ለዚህ አምድ በሚመጥን መልኩ አቅርበነዋል። ስለሆነም ታነቡት ዘንድ ጋበዝናችሁ።
ወይዘሮ ቱሩፋት መነሻችን ዓድዋ በመሆኑ የዓድዋን ድል ጠንሳሽዋን፣ የውጫሌ ውል እንዳይፈረም አድራጊዋን እንስት ሲሆን፤ እርሷም እቴጌ ጣይቱ ነች። ቀድሞ አስቦ፣ ቀድሞ መርቶና በየት በኩል መራመድ እንደሚያስፈልግ እቅድ አውጥቶ የሰጠው ወንዱ ሳይሆን እርሷ እንደነበረች ያብራራሉ። ውል አለመቀበል ደግሞ የማንነት ክብር ማረጋገጥ እንደሆነ ዛሬ ድረስ ኑረንበት አይተነዋልም። ትግሉ የጀመረው አውሮፓውያኑ የአፍሪካን አንጡራ ሀብት ለመቀራመት ባደረጉት ጥረት ኢትዮጵያን ሲነኩ ነው። እንደ እቴጌ ጣይቱ አይነቶቹ ደግመው ሴራውን አውቀው አላስደፍርም አሉ። በዚህም የነጻነት መሪ ኢትዮጵያ ሆነች። የጥቁር ኩራት፣ የነጭ ሽንፈት ብስራትና ማንም የማይደፍራት መሆኗን አረጋገጠች። ከሁሉም በላይ የባርነት ቀንበርን ፈትታ የሰው እኩልነትን በዓለም ሁሉ ዘራች ይላሉም።
ጣይቱ ሦስት ባሎችን አግብታ የፈታች ብትሆንም ማንም የሚመኛት እንደሆነች አሳይታለች። ለዚህም ምስክሩ አራተኛ ባሏ ንጉሡ ናቸው። በቁርባን አግብታቸው ብዙ ኃላፊነትን ለእርሷ እንዲሰጡ ሆነዋል። ለዚህም ነው በብልሃቷ ጠላትን ድል የሚመጣ እቅድ አውጥታ ብቻ ሳይሆን ተዋግታ የዓድዋ ድል እንዲበሰር ያደረገችው የሚሉት ወይዘሮ ቱሩፋት፤ በአገሯ መብት ላይ ከንጉሡ እኩል ወስናለችም። ለዚህ ደግሞ የጣሊያን ወታደሮች ምስክር ናቸው። አልፈርምም ስትላቸው ‹‹ምኒልክ ለአንዲት ሴት ንግሥናውን ሰጥቷል›› በማለት አለቆቻቸው ፊት ተናግረዋል። ያ ወቅት ደግሞ አይደለም በኢትዮጵያ በዓለምም ጭምር ለሴት ልጅ ቦታ የሌለበት፤ ዝቅ ተደርጋ የምትታይበት ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊቷ ጣይቱ የሴት ቁንጮ በመሆን ዓለምን አስደምማለች። ከዚያም አልፋ ሴት ኃያል መሆኗን አገሯ እንድታሸንፍ ታግላ ለዓለም ጭምር መስበክ እንደቻለችም ያብራራሉ።
ሴት ስለሆነች እንደማታደርገው ሲነግራት ‹‹የአንተ ወንድነት የሚለካው እዚያ ጦር ሜዳ ላይ ነው›› በማለት የገጠመችው ጣይቱ፤ ማድረጓን ከ10 ሺህ በላይ ሴቶችን አሰልጥና አምስት ሺህ እግረኛ 600 ፈረሰኛ ጦር እየመራች በመዋጋት፤ በማሰልጠን፣ ሕክምና በመስጠትና ስንቅ በማቀበልም የማይደክሙ መሆናቸውን አስመስክራለች። ብልጥና ምርጥ እንዲሁም ብልህ መሆናቸውንም ያረጋገጠችው በተግባር ነው። ለዚህም በአብነት የሚጠቀሰው መቀሌ ላይ ጣይቱ ያደረገችው ሲሆን፤ በቀጥታ የጠላት ጦርን ከመዋጋት ይልቅ ጥሩ ዘዴ ዘይዳ የጠላት ጦር ታጥቆና ጠብቆ ከመሸገበት በታትና አስወጥተዋለች። ለዚህ ደግሞ የተጠቀመችው ውሃ ማድረቅን ሲሆን፤ እያንዳንዱን ለመልቀም አስችሏቸዋል፤ ድባቅም መተውበታልም ሲሉ ያነሳሉ።
እንደ የሕግ ምሑሯ ገለጻ፤ የሴቶች ብልሃት በቀላሉ የሚገታና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ለዚህም ማህተመ ጋንዲ ስለሴቶች ያሉት በቂ ማስረጃ ነው። ይህም ‹‹ሴቶች ለሕግ ተገዢዎች ናቸው፣ ብርቱ ደፋር እርምጃን የሚወስዱ፣ መልካም ስነምግባርና ስነልቦና ያላቸው፣ ዱላ ለማንሳት የማይጣደፉ፣ ጀግንነታቸው ከወንዶች እኩል የሆነ ናቸው። እነርሱን አሳንሶ የሚያይ ካለ ዓይኖቹ የተንሸዋረሩ ናቸውና ይመርመሩ›› የሚለው ነው። ስለሆነም የዚያን ጊዜ ሴቶች ይህንን የተገበሩ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ሴቶች በውጊያ ብቻ ሳይሆን ጦሩን በማበረታታቱ፣ እኔ እየታገልኩ እያሉ ወኔ በመቀስቀሱ፤ ምስጢር በማቀበሉ እንዲሁም በሕክምናው ዘርፍ የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ማንም አይክደውም የሚሉት ወይዘሮ ቱሩፋት፤ ከሁሉም በላይ ከወንዱ በላይ እረፍት ሳይኖራቸው ቀንም ሌሊትም መሥራታቸው ትጉህነታቸውን ያሳዩበት ነው። የሚያበስሉበትን እቃ ጭምር በጀርባቸው አዝለው የመከተላቸው ምስጢርም ከወንዶች የማያንሱበት ነገር እንዳልነበረ የሚያሳይ መሆኑንም ያነሳሉ።
ውብና አማላይ በመሆናቸውም ብዙ ነገር ለአገራቸው አበርክተዋል። ከራሳቸው በላይ ለአገር ክብር አስገኝተዋል። በተለይ ውበታቸውን ተጠቅመው ለአገራቸው ምስጢር ጠባቂና ምስጢር አቀባይ እንዲሁም ለጠላት የውሸት አቅጣጫ በመጠቆም ለአገራቸው አሸናፊነትን እንድትቀዳጅ ያደረጉ እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል። ይህ ደግሞ ለአገራቸው የሚሰስቱት ነገር እንዳልነበረ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናልም ይላሉ።
ሴቶች ከዓድዋ ድል በኋላም ቢሆን ታግለው አገራቸውን የለወጡ ናቸው። ከነበረው ጦርነት ብዙ ልምድ በመቅሰም አዳዲስ ነገሮች በአገር ውስጥ እንዲጀመር አስችለዋል ያሉን የሕግ አማካሪዋ፤ ለዚህም ዳግመኛ ጣይቱን ያነሳሉ። ከባለቤታቸው ጎን ሆነው ትምህርት እንዲስፋፋ፣ ከተማ እንዲፈጠር፣ ፋብሪካዎች እንዲጀመሩ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ፤ ሆቴል እንዲመሠረትና አክሲዮን መሥርተው ባለሀብቶች በገዙት አክሲዮን አቢሲኒያ ባንክ እንዲከፈት ያደረጉ ናቸው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ድሃውም ተበድሮ እንዲሠራ አስችለዋል። ታሪካዊ ቤተ እምነቶችን በመገንባትም የማይተካ ሚናን ተጫውተዋል።
ማንኛዋም ሴት ጦርነት አይወድም። ምክንያቱም የመጀመሪያው ተጠቂ እርሱና ቤተሰቡ እንደሆነ ያውቃል። ይሁን እንጂ በአገር ከመጣ ግን የሚሰሰት ነገር እንደማይኖር የዓድዋ ድል ሴት ተሳታፊዎች በትክክል አስመስክረዋል። ለዚህም አሁንም ጣይቱን መጥቀስ ይቻላል። ‹‹እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን በአገሬ ከሆነ ሞትን እመርጣለሁ›› በማለት ነበር ብዙ ነገሮቿን ከመሰል ሴት የአገሯ ልጆች ጋር ዘምታ ድሉን ያመጣችው። እናም የእናቶች ድርሻ ዓድዋ በብዙ ነገር እንዲሞሸር አድርጎታልም ብለውናል።
በሴቶች ተሳትፎ ዓድዋ ነጻነታቸውን ለሚፈልጉ የጥቁር ሕዝቦችና የሰው ልጆች ምልክት እንዲሆን ያደረገ ነው። ለእውነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት የተከፈለ መስዋዕትነትም መሆኑን ያሳዩበትም ነው። በዚያ ላይ ኢትዮጵያውያን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሞራልም ከፍ ያሉ እንዲሆኑም እድል የሰጡበት ነው። ከሁሉም በላይ ዓድዋ የይቻላል ነጸብራቅን ያበሰረ፤ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መሥራት እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑንም አስመስክረውበታል ይላሉ።
እንደ ወይዘሮ ቱሩፋት ማብራሪያ፤ ሴቶች ሥዕል ባይችሉ እንኳን አስለው የኢትዮጵያ አሳሳል ጥበብን ለታሪክ ያስቀመጡ ናቸው። ስለሆነም ዓድዋና ሴቶችን ስናነሳ በአጠቃላይ በዘመቻው ከ20 ሺህ እስከ 30ሺህ የሚደርሱ ሴቶች ተሰልፈው ለአገራቸው እንደታገሉ፤ ጦር ሜዳ ሲባል የወንድ ብቻ እንዳልነበር ያስመሰከሩ፤ ቁስለኛውን ከማከም እስከ መመገብ እንደደረሱ፣ የሴትን ኃያልነት እንዳስመሰከሩና መሪ መሆን እንደሚችሉ ያረጋገጡ እንዲሁም ሀሳብ ሰጪ፣ ወኔ ሰናቂና ደስታ ቀማሪ መሆናቸውን ለዓለም ጭምር ያበሰሩ እንደሆኑ በዋናነት ማንሳት እንችላለን።
ከድልና ጦርነት ጋር በተያያዘ ስለሴቶች ተሳትፎ ከ40 ዓመት በኋላም ብዙ የምናነሳው ነገር አለ። ምክንያቱም ይህ ወቅት የጣሊያን ጦር ዳግም የተመለሰበትና ኢትዮጵያን ለማሳፈር የተንጠራራበት ጊዜ ነው። ይህንን ደግሞ የታገሉ ሴቶች በርካታ ናቸው። በአምስት ዓመት ቆይታው ብዙ አሲረው ድባቅ ከአስመቱት መካከል ብዙ ሴቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ጎልታ የምትወጣው ደግሞ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ ነች።
‹‹የምታስፎክር ሰንጋ ገለሌ
በጦር መካከል ሳይሆን አያሌ
በጥይት ገዳይ ነጭ ብር ገድሌ
የሴት ወንድ ናት ሸዋረገድ ገድሌ›› ተብሎ የተገጠመላት ይህች አርበኛ የጣሊያን ጦር ሊጎርሰን ማሰፍሰፉ ሲሰማ በአዲስ አበባ ከተማ በአገር ተቆርቋሪ ዜጎች በተቋቋመው የአገር ፍቅር ማኅበር አባልነት መጀመሪያ የተመዘገበች ከዚያም አዲስ አበባ ሲገባ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ የጣሊያን ባንዲራ ሲተካ ስቅስቅ ብላ ያለቀሰችና ለምን አለቀሽ ተብላ ስትጠየቅና ስትከሰስ ያለምንም ፍርሃት ‹‹አዎ አልቅሻለሁ፤ ያገሬን መወረርና መዋረድ ያወቅሁት የኛ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ የእናንተ ሲውለበለብ በመታየቱ ነው። ሰው ለእናት አገሩ ቢያለቅስ ነውሩ የት ላይ ነው?›› ብላ የመለሰች ጠንካራ ሴት ነች።
አርበኛ ሸዋረገድ ለአርበኞች ስንቅ በማቀበል፣ መሣሪያ በመግዛት፣ መረጃ በማሰባሰብ፣ መድኃኒት በመላክና ሞራል በመስጠት አምስቱን ዓመት ሙሉ በተጋድሎ ያሳለፈችም ነች። በዚህ ተግባሯ ደግሞ ተከሳ ‹‹ለአርበኞች ስንቅ ማቀበሌ እውነት ነው፤ ይህንንም ያደረግኩት ለአገሬ ክብር ብዬ ነው። ሰው እንኳን ለአገሩ የእናንተ ወይዛዝርት አገራቸው ያልሆነችው ኢትዮጵያን ለመውረር የጣታቸውን ቀለበት ሳይቀር መስጠታቸውን ትናገራላችሁ። እኔም ለአገሬ የሠራሁት ሲያንሰኝ እንጂ አይበዛብኝም›› በማለትም አስረግጣ የተናገረች አገር ወዳድ ሴት ነበረች።
ለአገሯ ልጆች ምስጢር በማቀበል የምትታወቀው አርበኛዋ፤ ይህን በማድረጓ የሞት ፍርድ ተፈርዶባታል። ሞቱ ባይፈጸምም በእስር ከአንዱ ወደ አንዱ ተንከራታለችም። ግን ታስራም የአገሯ ጉዳይ ከልቧ አልወጣም። በዚህም ምግብ በአሳሪዎቿ ፊት እየደፋች ተቃውሞዋን ስታስረግጥ የቆየች አይበገሬ ሴት ነች። የአዲስ ዓለም የጣሊያን ምሽግ በአርበኞች ሲሰበር ዋናውን መረጃ የሰበሰበችውና እቅድ የነደፈችውም እንዲሁም ደጀን መሆኑን ትታ ወደ መዋጋቱ የገባች እንደነበረች ታሪክ ይመሰክርላታልም።
ከጣሊያን ዳግም ወረራ በኋላ ደግሞ ሸዋረገድ ገድሌ አርበኞችን ወደ መርዳትና የበጎ አድራጎት ሥራ መከወን ተግባር ገብታለች። ከምትጠቀስበትም ውስጥ አንዱም ለቀይ መስቀል ማኅበር የነበራት ድጋፍ ነው። በጦርነቱ ዋዜማ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ንብረቷን ጭምር ሸጣ የሰጠች አርበኛ ነች። ከመጀመሪያዎቹ የባንክ ተጠቃሚዎች፣ የአክሲዮን ገዥዎች፣ የፋብሪካ ተካዮች መካከልም ትጠቀሳለች።
ወደ አሁኑ ሴቶች ስንመጣ ደግሞ ጉዳያችን አሸናፊነት በመሆኑ ከቀደመው የጦርነት ሁኔታ የተለየ ትግል ቢገጥመንም የእናቶቻቸው ልጆች የሆኑ ሴቶች እንዳሉ አይተናል። በተለይም በህልውናው ዘመቻ ለአገር ብዙ መስዋዕትነትን የከፈሉ ሴቶች ነበሩ። አሁንም እየታገሉ ያሉ እንዲሁ ጥቂት አይደሉም። ምክንያቱም ሴቶች ከማጀት እስከ ግንባር ደርሰው ማንነታቸውን አሳይተዋል።
አሁን የተደረገው የሕልውና ጦርነት የውጪ ኃይሎች ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም በእኛ ላይ ያደረጉት ሴራ እንደሆነ የሚጠቁሙት ወይዘሮ ቱሩፋት፤ ይህንን አውቀው ሴቶች እንደቀደመው ጣይቱ ለዘመቻ ተሰልፈዋል፤ ጀብዱ ፈጽመውም ከቤተሰባቸው ጋር የተቀላቀሉ አሉ። አሁንም ውጊያ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ እየተፋለሙ ይገኛሉ። ለዚህም ማሳያው ልጆቻቸውን፣ ባለቤታቸውን ትተው የዘመቱና የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ እንደ አፋር ላይ ጦሩን እየመራች ስትዋጋ የነበረችው እንስትን እናቶችን ማንሳት በቂ ይሆናል ይላሉ። በእርግጥ ከወንዶች እኩል ላይሆኑ የሚችሉበት ብዙ ሁኔታ አለ። ማኅበራዊ ጫናውን ብንተወው እንኳን ተፈጥሯዊ ጫናው በምንም መልኩ እኩል አያደርጋቸውም። ይሁን እንጂ ይህንንም ተቋቁመው መታገል ላይ ናቸው።
አንችልም አንልም የጣይቱ ልጆች፤
ዛሬም እንሆናለን ታሪክ ደጋሚዎች። በማለት የተነሱ ሴቶች ብዙ ናቸውና ታሪክን እንደሚደግሙ እምነት አለኝም ብለውናል።
ሴቶች በቀጥታ ባይዋጉ እንኳን በተዘዋዋሪ የሚያደርጓቸው ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ፡- የባላቸውን ኃላፊነት ተሸክመው ባላቸውን አበረታተው ለአገሩ እንዲዋደቅ ማድረጋቸው፤ ስንቅ ማቀበላቸው፤ ከመቀነታቸውና ከልጆቻቸው አፍ ወስደው ለመከላከያ፣ ለተፈናቀሉት እያሉ መስጠታቸው፤ በጸሎታቸው ዓይናቸው እስኪጠፋ ድረስ ስለአገራቸው የሚጸልዩም ጥቂት አለመሆናቸው በዋናነት የሚጠቀስ ነው። እናም የቀደመውን ታሪክና እውነት ተረክበው እነርሱም ለማስረከብ እየታተሩ ይገኛሉም ብለውናል።
በዳግማዊ ዓድዋው የሴቶቹ ተሳትፎ እንደቀደመው ሁሉ ማንነታችንን ያስከበረ እንደነበር የሚያብራሩት የሕግ አማካሪዋ፤ የህልውና ዘመቻውን ዘር፣ ቀለም ሳይለዩ ተሳትፈዋል። የሰውን እኩልነት አረጋግጠዋል። ምክንያቱም በዚህ ዘመቻ ውስጥ ባለስልጣን፣ አርሶአደር፣ ድሃ፣ ሃብታም፣ ትንሽ ትልቅ አላሉም። ሁሉም የቻሉትን ነው ያበረከቱት። ስለሆነም ድሉም የሁሉም ሆኗል። የቀረውም እንዲሁ ይሆናል እምነታቸው ነው።
እንደ ወይዘሮ ቱሩፋት ገለጻ፤ የሴቶች አገራዊ አበርክቶ ብዙ ቢሆንም አሁንም ብዙ እገዛን ግን ይፈልጋል። ጥያቄያቸው ከወንድ በላይ እንሁን ሳይሆን እኩል እንሁን ነውና መልስ ሊያገኝ ይገባዋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ በሁሉም መስክ እድሉ ሲመቻችላቸው ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሴቶች ከወንድ እኩል ለመሆን መቶ ዓመታትን መሥራት ያስፈልጋል። እናም ዛሬ ካልተጀመረ አደጋው የከፋ ነው። ስለሆነም እንደ አገር የተግባራቸው ፍሬ እንዲታይ መሥራት ይገባል።
የእስከዛሬ ሥራቸው ተጽፎ ለትውልድ መድረስ አለበት። ምክንያቱም አሁንም ድረስ ያልተቀረፈ ሴቶችን አሳንሶ የማየት ችግር አለ። ጠንካራ ሴቶች እንዳሉ መንገርና ሌሎችን ማበረታታም ይገባል። አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ በዚህ በዳግማዊ ድሉ በማስረገጥ ማስተማርም ተገቢ ነው። ሴትን ልጅ ማስተማሩ ላይም ከፍተኛ ሥራ መከናወን አለበት። በተለይም ቤተሰብ ሴቶችን በማበረታታት ዙሪያ ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚገባ አበክረው ይመክራሉ።
ሴቶች በራሳቸውም ሊከውኗቸው የሚገባ ጉዳዮች አሉ የሚሉት የሕግ ምሁሯ፤ እንደ ዓድዋው ሁሉ ድልን አብሳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ መጀመሪያ ራሳቸውን በሁሉም መስክ ማብቃት አለባቸው። ለአብነት በትምህርት፤ የሰውነት ብቃት እንቅስቃሴና በሥራ ከሌላው ልቀው ሊወጡ ይገባል። ሳይሞክሩት አልችለውም የሚለውን አመለካከት ከአዕምሯቸው ማስወጣት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ይህንን የማይሉ ሴቶች የት ላይ እንዳሉና እንደደረሱ በሁሉም መስክ እያየን ስለሆነ። እናም በመሞከር ውስጥ ብዙ ድል እንዳለ ማመን አለባቸውም ሲሉ ይመክራሉ። በአገር ጉዳይም ተግባራቸው በፍጹም ልብ የሚተገበር በመሆኑ ሁሌም አጠናክረው ሊቀጥሉበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። እኛም ምክራቸው ይተግበር እያልን ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያው
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014