ተወልዶ ያደገው ሸዋሮቢት ከተማ ነው።ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘ እንደመሆኑ ከግብርና ሥራውም ሆነ ከንግዱ የራቀ አልነበረም።በአካባቢው የተለያዩ አትክልቶች በስፋት የሚመረት በመሆኑ ቤተሰቦቹን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንችና እና ሌሎች በየዕለቱ ከእያንዳንዳችን ጓዳ የማይጠፉ አትክልቶችን ያመርታሉ።አምርተውም ለገበያ ያቀርባሉ።
ያመረቱትን አትክልት ወደ ገበያ በማቅረብ የልፋታቸውን ፍሬ ለማግኘት ከሚተጉ አርሶ አደሮች መካከል የዛሬ የስኬት እንግዳችን ቤተሰቦችም ተጠቃሽ ናቸው።እንግዳችን ገና በለጋ ዕድሜው ንግድን መጀመር የቻለ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ውጤታማ ከመሆን ባለፈ በሰዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ታማኝነትን ማትረፍ ችሏል።
ከማህበረሰቡ ያገኘው እምነትም የበለጠ እንዲተጋና አዳዲስ ነገሮች መፍጠር እንዲችል ትልቅ አቅም እንደሆነው ይናገራል። መሰረቱን ከአርሶ አደር ቤተሰብ ያደረገው የዛሬ እንግዳችን ወጣት ዳንኤል በቀለ የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው።ወጣቱ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ለንግድ የተሰጠ እስኪመስል በንግዱ ዘርፍ ተሰማርቷል።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን በሚያስኬደው ንግድ በአካባቢው የሚመረተውን ሽንኩርት፣ ድንችና፣ ቲማቲምና ሌሎች አትክልቶችን በአቅራቢያው ወደሚገኙ ከተሞች በመውሰድ ይሸጥ ነበር።በፈጠነና በቀለጠፈ ሥራው ያስተዋሉት የአካባቢው ሰዎች በእምነት ገንዘባቸውን በማበደር ንግዱን እንዲያሰፋ አስችለውታል።
መነሻ ካፒታል ሳይኖረው በአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍና እገዛ የጀመረውን ንግድ ማጎልብት በመቻሉ ገና የ17 ዓመት ልጅ እያለ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ደብረብርሃን ላይ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች መጋዘን እንደነበረው ይናገራል። ገና ከጠዋቱ ለንግድ የተለየ ፍላጎት እንደነበረውም አጫውቶናል።
ከንግዱ ጎን ለጎን ትምህርቱን እስከ 11ኛ ክፍል መከታተል የቻለ ቢሆንም ቅድሚያ በውስጡ ለሚንቀለቀለው ፍላጎት ጆሮ በመስጠት ዘመናዊ ንግድን ማዘመን የሚችልበትን መንገድ ከመወጠን ባለፈ የተለያዩ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ውጥኑን ዕውን ማድረግ የሚያስችለው ዋናውና ቀዳሚው የኢንተርኔት ተደራሽነት ቢሆንም ቅሉ በወቅቱ በአገሪቷ ያለው የኢንተርኔት አቅም ደግሞ ደካማ ነበር።ታዲያ በዚህ ወቅት ሩቅ አሳቢው ለሆነው ዳንኤል ከአገር መውጣት ምርጫ የሌለው አማራጭ ሆኗል።ከአገር ለመውጣት በወሰነ ጊዜም መዳረሻውን የቅርብ የሚለው ሰው ባለበት በኬንያ ናይሮቢ አድርጓል።
ያገኘውን ቀዳዳ በመጠቀም እኤአ በ2016 ወደ ኬኒያ ናይሮቢ አቅንቷል።የኬንያ ቆይታውም በውስጡ የሚንቀለቀለውን ፍላጎት በተለይም ከቴክኖሎጂ የመተዋወቅና አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ጉጉቱን ለማሳካት ምቹ የሆነለት ዳንኤል፤ የሶፍትዌር ዴቭሎፕመንትና የዲጂታል ማርኬቲንግ ትምህርቱን በኬኒያ ናይሮቢ UBUNIFU COLLAGE ኮሌጅ ተከታትሏል።
‹‹በኬንያ ቆይታዬ ኢንተርኔቱን በበቂ መጠን በማግኘቴ ቴክኖሎጂውን በሚገባ ተዋውቄዋለሁ›› የሚለው ወጣት ዳንኤል፤ ሶፍትዌር ማጎልበትን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በርካታ ሥራዎችን መሥራትና ዲዛይን ማድረግ ችሏል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ወደ አገር ቤት መመለስና የራሱ የሆነ ካምፓኒ ማቋቋም እንዳለበት ስሜቱ በተሰማው ቅጽበት ወደ አገር ቤት በመምጣት በተለይም ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችለውን ኢኮሜርስን በአገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ ቻለ። ቴክኖሎጂውን በአገር ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጀበት ወቅት ብዙዎች የሚመከረ አይደለም፤ ይቅርብህ በማለት ወደኋላ ሊጎትቱት ሞክረዋል።
ነገር ግን እርሱም ተጠቅሞ ለብዙዎች መትረፍ እንደሚችልና በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችል ዘርፍ ስለመሆኑ ሙሉ እምነት የነበረው ዳንኤል የውስጡን ሀሳብ ብቻ በማዳመጥ ጉዞውን ቀጠለ።በጉዞውም ማመን የቻለውን አሳምኖ ማመን ያልቻለውንና የማይፈልገውን በመተው ፍላጎትና ሀሳቡን አስቀጠለ።
ወደ አገር ቤት ሲመለስ አንድ ጓደኛውን ይዞ በመመለስ አሸዋ ቴክኖሎጂ የሚል ካምፓኒ በማቋቋም የኦንላይን ግብይትን ጀምሯል።በወቅቱ የአገር ባህል አልባሳትንና የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ለገበያ በማቅረብ የጀመረ ሲሆን የገበያ መዳረሻውን በቅድሚያ ለሚውቃቸው ሰዎች በማድረግ በሂደት ደግሞ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ለሚኖሩ ሰዎች አድርጓል።
ከኦንላይን ግብይቱ ጎን ለጎንም በተቋሙ ውስጥ የተለያዩ ትምህርቶችን ማስተማር የሚችሉ ባለሙያዎችን በመቅጠር ግራፊክ ዲዛይንና የማርኬቲንግ ትምህርት ከ300 ለሚልቁ ተማሪዎች ይሰጥ ነበር። ሲስተም መፍጠር የሚያስደስተው ወጣት ዳንኤል፤ በኬንያ ቆይታው የቀሰመውን በርካታ ዕውቀት ተግባራዊ በማድረግ በኢኮሜርስ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።በዓለም አቀፍ ያለውን ተሞክሮ እንደ አሊባባ፣ አማዞንና ሌሎችም ባጠረ ጊዜ ተአምር መሥራት የቻሉትን በምሳሌነት በማንሳት እኛስ ለምን? የሚል እልህ ይተናነቀዋል።ይሁን እንጂ በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በፈለገው ፍጥነት እንዲበር አላስቻለውምና በቻለው መጠን ሁሉ ወደፊት ገሰገሰ።ግስጋሴውን ፍሬያማ ለማድረግም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በቅድሚያ ያለውን ክፍተት በመለየት በአገሪቱ ያለውን ችግርና ማኅበረሰቡ የሚፈለገውን ነገር በማጥናት ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ መስጠት ያስችላል ያለውን ውሳኔ በመወሰን የአሸዋ ቴክኖሎጂ ካምፓኒን ወደ አክሲዮን ማህበርነት አሳደገ። ሀሳብን ወደ ተግባር ለውጦ መሬት ላይ ማውረድ በመቻላቸው በአሁን ወቅት ያለው ኢኮሜርስ ቀድሞ ከነበረው እጅጉን የተሻለና ቀዳሚ መሆን ችሏል።ይህ ሙሉበሙሉ በኢትዮጵያውያን የተመሰረተው ግዙፍ ካምፓኒ በአሁን ወቅት በአክሲዮን ደረጃ 100 ሚሊዮን ብር በላይ መሸጥ መቻሉንና ከ52 ለሚበልጡ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለና 12 አባላት ያሉት መሆንን አቶ ዳንኤል ይናገራል።
ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ አክሲዮን መሸጥ በራሱ እጅግ ፈታኝ ነው የሚለው ዳንኤል፤ ለቴክኖሎጂው መነሻ የሚሆን ነገር ካለመኖሩም ባለፈ ከመንግሥት ፖሊሲዎች ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች የገጠሙት መሆኑን ጠቅሷል።
ከገጠሙት ችግሮች ባለፈ የፖለቲካ አለመረጋጋት ባሉበት በዚህ ወቅት 100 ሚሊዮን አክሲዮን መሸጥ መቻል ትልቅ ስኬት መሆኑን በማንሳት ለዚህ ውጤትም በውስጡ ያለው ዕውቀትና ጥልቅ ፍላጎቱ መሆኑን ይናገራል። አሸዋ ቴክኖሎጂ አዲስ ቴክኖሎጂ ቢሆንም አሁን ያለበት ደረጃ እጅግ የሚያኮራና ውጤታማ መሆን የቻልንበት ነው የሚለው ዳንኤል፤ እንደችግር የሚያነሳቸው በርካታ ነገሮች አሉ።
በተለይም ማኅበረሰቡ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀብት ሲባል የሚዳሰስና የሚጨበጥ እንደ ቤትና መኪና ብቻ የሚመስለው ሰው እንደሚበዛና፤ አሸዋ ቴክኖሎጂ ደግሞ ይዞ የመጣው ሶፍትዌር በመሆኑ ሀርድዌር የሚገባው ባለመሆኑ በካምፓኒውና በማኅበረሰቡ መካከል ሰፊ ክፍተት ተፈጥሯል በማለት በዚህ ሰፊ ክፍተትም ገበያ ውስጥ ሰብሮ መግባት ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳል፤ ይሁን እንጂ ሁሉም ችግሮች አሸዋ ቴክኖሎጂ ይዞት ከመጣው ዓላማ ጋር ሲወዳደሩ እዚህ ግባ የሚባሉ አልነበሩምና ሁሉም ችግሮች ካምፓኒው ከተነሳበት ዓላማ
አንጻር በድል መወጣት መቻሉን ይገልጻለ። በአሁን ወቅትም በአገሪቱ ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ የመጣ በመሆኑ በተለይም የገባቸው ሰዎች ወደ ቴክኖሎጂው እየቀረቡ እንደሆነ በመጠቆም ከገባቸው ሰዎች ባሻገር ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ረሃብ ያለባቸው በርካታ ሰዎች እንዳሉም ይናገራል።
እነዚህ ሰዎች በተለይም በኢኮሜርስ ላይ የሚሰሩ መሆናቸውን ሲያውቁ በከፍተኛ ፍላጎት ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ በአገር ውስጥ የሚገኙና በውጭው ዓለም ያሉ ዲያስፖራዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው ይላል። ኢኮሜርስ እና መሰል የኦንላይን ግብይት በተለየ ሁኔታ የሚገባው ዲያስፖራው አሊባባና አማዞንን የመሰሉ ካምፓኒዎች በስንት ዓመት እንደተቀየሩ ያውቃሉ።
በ20 እና በ25 ዓመታት ቢሊዮኖችን አልፈው ወደ ትሪሊየን እየተሻገሩ እንደሆነ የሚያነሳው ወጣት ዳንኤል፤ በተለይም ዲያስፖራው ቴክኖሎጂን የተራበ ስለመሆኑና የተጋባባቸው መሆኑን ይናገራል።ስለዚህ በአገሪቱ የሚገኙት የኢኮሜርስ ካምፓኒዎች ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ካላቸው ፍላጎት በመነጨ መንገድ በከፍተኛ መጠን ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ኢንቨስት እያደረጉ በመሆኑና አሸዋን በመቀላቀላቸው ምስጋናውን አቅርቧል።
‹‹አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር በአንድነት ለአንድ ዓላማ በመሰለፍ የተሻለ ነገር እናምጣ›› የሚል ሰፊ ሀሳብ ያለውን የሥራ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን የጠቀሰው ወጣቱ፤ ድርጅቱ በያዘው ዓላማ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር እንዲችል ከፍተኛ ጥረት እያደረገና አመላካች ነጠብጣቦች ላይም እንዳለም ተናግሯል።
ማህበሩ በቅርቡም “ሥራ ለሁሉም” የተባለ የቢዝነስ ሞዴል በይፋ የከፈተ ሲሆን ይህ ሥራ ለሁሉም የተባለው ቢዝነስ ድህንትን ከምናስወግድባቸው መንገዶች መካካል አንደኛው መንገድ ይሆናል የሚል ዕምነት አለው፤ በመርሃ ግብሩም በርካቶችን ተሳታፊ በማድረግ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግሯል።
አሸዋ ቴክኖሎጂ በ2030 ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር በቀጣይ ከያዘው ስትራቴጂካዊ እቅድ መካከል የመጀመሪያው ምዕራፍ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ኢንተርኔትን ተጠቅሞ የተለያዩ ቢዝነሶችን መሥራት የተለመደ አይደለም።
በአሁን ወቅት ግን ማህበሩ ባደረገው ጥናት መሠረት ከ50 የሚልቁ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ገቢ እያስገቡ እንደሆነ አንስቷል።በተለይም ኢንተርኔትን ሥራ ላይ ከማዋል አንጻር አጥጋቢ የሆነ ሥራ አልተሠራም።ስለዚህ በቀጣይ ይህን ችግር በመቅረፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂው ከፍተኛ ቦታ ላይ የደረሱ አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ዘርፉን ማሳደግ የግድ መሆኑንና ለነገ የሚተው ሥራ እንዳልሆነም አስረድቷል።
ማኅበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን መንገድ እየፈጠረ ይገኛል ፤ በተለይም በአሁን ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የዲጅታል ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ በመሆኑ ይህንንም በአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ላይ ይበልጥ ለማሳለጥ ወጣቶች በእጅ ስልኮቸቻውም ሆነ በአካል በአካባቢያቸው በሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮችን በማነጋጋር ማህበሩ ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን መሸጥ እንደሚችሉና ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንደሚፈጠርም አስረድቶናል።
ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የራሳቸው ቢዝነስ ባለቤት እንዲሆኑና አንድ ሚሊዮን ሚሊየነሮችን የመፍጠር እንዲሁም ሌሎች በርካታ ራዕዮችን ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አሸዋ ቴክኖሎጂ በተለይም ወጣቱ ኢንተርኔትን ሲጠቀም ለበጎ ዓላማ በማዋል የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ይገልጻል።
በቀጣይም ቴክኖሎጂውን በማስፋት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉት የክልል ከተሞችም ቴክኖሎጂውን ተደራሽ በማድረግ የክልል ከተሞችን የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን አስረድቷል። በመጨረሻም ማንኛውም ሰው ከአሸዋ ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ በመሥራት ቢዝነሱን ማሳለጥ የሚችል መሆኑን ይናገራል።
በይበልጥ ግን የሽያጭ ክህሎት ያላቸውና ለቴክኖሎጂው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ቢሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግሯል።ስለሆነም ዓላማውን የተረዳችሁና ዝንባሌና ፍላጎቱ ያላችሁ ወጣቶች በእጅ ስልካችሁ የምታደርጉትን የኢንተርኔት ቁርኝት ከአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር ጋር በማድረግ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘባችሁን ቆጥባችሁ ከዘርፉም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ በመሆን የዓላማው ተጋሪ መሆን ትችላላችሁ በማለት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014