ኪነጥበብ ስሜት ገዢነቱ ጥልቅ፤ መመልከቻ መነፅሩ ሰፊ ነው። ጥበብ ሁለ ገብ አይደል! ጉዳይን በጥልቀት ነገርን በስፋት ያስመለክታል። በጥበብ የማይታይ ጉዳይ፣ የማይዳሰስ አካል አይኖርም። ጥበብ ስሜተ ስስ ያርጋል፤ ለተግባር ያነሳሳል። ለልማት መንገድ ይሆናል።
አገራዊ ጉዳዮችን በተለየ መንገድ ያስመለክታል። በእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የራሱን ሃያል ሚና ይጫወታል። በእርሱ ያልተኳሸ ጣዕም አይኖረውም። ሰምተውት ልብ የሚያሞቅ፣ አይተውት ሙቀት የሚሰጥ ኪናዊ ጣዕም በከያኒው ይሰለቃል። በራሱ መንገድ አስጉዞ ሲፈልግም መልሶ ከመነሻ መድረሻው ድረስ በአጀብ … ውስጥን ይቆጣጠራል።
ጥበብን ምርኩዝ አድርገው ኢትዮጵያውያን ዓባይን ለዘመናት ሲያነሱት ኖረዋል። ወደፊትም የጉዳዩን ያህል አግዝፈው ያዩታል። እኛም ጥበብን ምርኩዝ አድርገን ብዙ እንላለን። ዓባይ የዘመናት የኢትዮጵያውያን ቁጭት ሆኖ ዘልቋል። ዛሬ ደግሞ ለዚህ ህዝብ ራሱ ተስፋ ፈንጣቂ የብርሃን ምንጭ ሆኗል። ታዲያ በሁለቱም ዘመን ጥበብ በሁለት የተለያዩ ቅኝቶች ዓባይን እያነሳ ሲጥል ኖሯል። የቀደሙት በቁጭት፣ የዛሬዎቹ ደግሞ በፌሽታና በወደፊት ተስፋ ስለዓባይ ይቃኛሉ፣ በአባይ ላይ ስለተገነባው ስለ ታላቁ ግድብ ያዜማሉ። የዚህን ዘመን ትውልድ ድፍረት ይመሰክራሉ።
ከትናንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያውያን ትልቅ ጉዳይ የነበረውና ወደፊትም የሚሆነው ታላቁ ወንዝ በቁጭትም በድልም በጥበብ ታጅቦ ዛሬ ደርሷል። የህዳሴ ግድብ እንዲህ ለመገደብና ብርሃን ለመፈንጠቅ እስኪደርስ የጥበብ ፋይዳው ጉልህ ነው። ሰዎች ያላቸውን እንዲያውቁ ሀብታቸውን እንዲጠቀሙ መሳሪያ ሆኖ ቀስቅሷል።
ስለ ዓባይ ለዘመናት በቁጭት የተንጎራጎረውን ስንሰማ፣ ዜማዎችን ስናደምጥ፣ እንደ ተራ ንግግር የማየቱ ጉዳይ አክትሞ ስለምን እኛ መጠቀም አልቻልንም? ለምንስ አናለማውም ያልነው የዓባይን ገፅ ደጋግመን በጥበብ በማየታችንም ጭምር ነበር። ዛሬም የተሻለ ውጤት ላይ ደርሶ ስናይ የወንዙን ሀያልነት የህዝባችንን የመልማት ፍላጎትና ርብርብ የተገኘውንም ስኬት በጥበብ አዋዝቶ ከእኛ ለእኛ ማድረሱን ቀጥሏል።
ዓባይ ትናንት (የቁጭት ዘመን ዜማ)
ከእናት ምድራቸው እየሸሸ ሌሎች ሀገሮችን ለዘመናት ሲያለማ የኖረውን የዓባይ ወንዝ የማስቆም አቅም አጥተው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ቁጭታቸው ጥበብን ምርኩዝ አድርገው ሲገልፁ ዘመናትን አሳልፈዋል። ስለ ዓባይ ወንዝ በብዕሩ ያልከተበ አገር ወዳድ የጥበብ ሰው የለም ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ስለእዚህ ታላቅ ወንዝ ኢትዮጵያን እየተሻገረ ርቆ መሄድ ያልተቆጨ ዜጋ አልነበረምና ነው። ደጋግመን በተለያዩ የጥበብ ውጤቶች ሰምተናል።
በእርግጥ በርካታ ከያኒያን ይህን ግዙፍ ሀብታችንን አባይን በየዘርፋቸው በኪነ ጥበብ ስራዎቻቸው አካተው ቢያስመለክቱንም ለማሳያ ያህል የተወሰኑትን ኪነጥበባዊ ስራዎች እንመልከት። በዜማዋቿ ዓብይ ጉዳዮችን እያነሳች በልዩ መልክ የምታስመለክተን ጥበበኛዋ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዘመን አይሽሬ በሆነው ሙዚቃዋ አባይን አስመልክቶ ያለውን የሕዝብ ቁጭት በታያት መልኩ ዓባይ ልብ ከመግዛቱ በፊት እንዲህ ተቀኝታው ነበር።
“የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ – በዘመን የጠና
ከጥንት ከፅንሰ አዳም – ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ – ፈልቆ ከገነት
ግርማ ሞገስ ዓባይ
አባይ ለጋሲ ነው በዚህ በበረሀ
ዓባይ – ዓባይ – ዓባይ
ዓባይ ወንዛ ወንዙ
ብዙ ነው መዘዙ
….
ይህች ድንቅ የጥበብ ሰው በዜማዋ ስለ ዓባይ የተቀኘችውን ጠንከር ያለ ስንኝንም እዚህ ላይ ማንሳት መልካም ነው። በተለይ የመልዕክቱን ጥልቀት ለሚረዳ ያኔ የዓባይ ግብር ምን ያህል በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ቁጭት እንደፈጠረ ማሳያ ነው።
ስለ ዓባይ ጥናቶች ተሰርተዋል፤ እነዚህ የጂጂ ስንኞች ደግሞ ግዙፉን ዓባይ በጥቂት ስንኞች ከመጻሕፍት በላይ ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል። ‹‹እውነተኛ ጥበብ ዓይን ገላጭ ነው›› የሚባለውም ለዚህ ነው። ጂጂ ‹‹ዓባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ›› ስትል የዓባይን ፖለቲካዊ ጣጣ ሁሉ በአንዲት ስንኞች ገልጻለች። አዎ! ዓባይ ከጥንት እስከ ዛሬ ብዙ ፖለቲካዊ መዘዞች ነበሩበት!
“ፍልቅልቅ ፍልቅልቅ…አንች ውብ ከተማ
‘ዓባይ’ ባልሽ ነው ወይ..ሰማሁኝ ሲታማ፡!!”
እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በዚያ በማይነጥፈው ብዕሯ ስለ ዓባይ ስትቀኝ፤ በስርቅርቅ ድምፅዋ ስሜት በሚነካ መልኩ በሚገርም ቁጭት ስታዜም ቁጭቱ ሁላችንም ዘንድ ሰርጾ ተብሰልስለናል። ስለዓባይ ብዙ እንድናስብ አድርጋናለች። ድምፃዊቷ የአባይን ሃያልነት ከውበቱ እና ግርማ ሞገሱ ጋር “ የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና….የማይደርቅ የማይነጥፍ – በዘመን የጠና” በማለት አንስታ ትልቅነቱን አስመልክታናለች። በጥበብ ስለ ወንዙ ሃያልነት አጋብታብናለች።
ዓባይን እንኳን ለምናውቀው ለእኛ የአገሩ ልጆች እሩቅ ያለውም ምንነቱን እንዲመረምር ከታሪካዊነቱ አንፃርም በጥበብ ምርኩዝነት አድርሳለች። ዓባይ እኛን ትቶ አፈራችንን ተሸክሞ ወደ ባዕድ መፈርጠጡ አስቆችቷታል። ቁጭቷንም እኛ ላይ አስተጋብታለች። እኛም ዜማዋን እያዜምን ተቆጭተናል፤ እያሰብን ተክዘናል። ዛሬ ቀን ወጥቶልን ዓባይን ማሞገስ ከመጀመራችን በፊት በጥበብ ብዙ ታዝበነውም እያዜምን አስቆጭቶን ነበር። አሁንም የጂጂን ስንኞች እንመለክት እስቲ።
ብነካው ተነኩ አንቀጠቀጣቸው
መሆንህን ሳላውቅ ሥጋና ደማቸው
የሚጠጡት ውሃ
የሚበሉት ውሃ
ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሃ
ጂጂ ‹‹የበረሃው ሲሳይ›› ያለችውን ዓባይን ከላይ በቀረቡት ስንኞች ብቻ ከአንድ መጽሐፍ በላይ ትንታኔ በሚወጣው ሃሳብ ገልጻዋለች። አዎ! ዓባይ ለግብጾች ውሃና ደማቸው ነው። ሲነካ ይነካሉ፤ ያንቀጠቅጣቸዋል።
ጂጂ በዓባይ ላይ የጥበብን ልክ አሳይታበታለች፤ ተራቀቀችበት ማለት ይቻላል። ‹‹የሚበሉት ውሃ›› ትለናለች። ውሃ በባህሪው የሚጠጣ እንጂ የሚበላ አይደለም፤ ለግብጹቹ ግን ውሃ ብቻ አይደለም። ይበላል፤ ይጠጣል። ምግባቸው ነው፤ መጠጣቸው ነው፣ ‹‹ደማችን ነው›› ሁሉ ይላሉ። ይህን ባህሪውን የተረዳችው ጂጂ ውሃን ከመጠጥነት አውጥታ ምግብ ሁሉ ታደርገዋለች። ጥልቅ ጥበብ እንዲህ ነው!
ኢትዮጵያውያን ባህር ተሻግረውም አገራቸውን ማሰባቸው ውቂያኖስ አቋርጠው ኢትዮጵያዬ ማለታቸው አይቀሬ ነው። በአንድ በሆነ አጋጣሚ ግብፅ ርዕሰ ከተማ ላይ የተገኘው አንድ ኢትዮጵያዊ ብዕረኛ ቁጭቱን ከኪሱ ብእር አውጥቶ ስንኝ በመቋጠር እንዲህ የሚል ማስታወሻ አኑሮም ነበር።
ሁሌም እየቆጨኝ፣ ያኗኗርህ ዕጣ፣ የጉዞህ ፍጻሜ፣
ወንድሜ የናቴ ልጅ፣ ልጠይቅህ መጣሁ፣ ወሬህን ቃርሜ፤
እንዴት ነህ ባያሌው? ተስማማህ ወይ ኑሮ?
በሀገረ-ምሥር፣ ከተማ ካይሮ!
ከዚያ ሰላም ምድር፣ ከዚያ ሰላም አምባ፣ ስትደነፋ መጥተህ፣
የመኪናው መአት፣ የጡሩምባው ጩኸት፣ የሰዎች ትርምስ…
እንዴት ሰላም ሰጠህ?!
እንደምነህ ዓባይ?!
የዘር ግንዴ ክፋይ።
የናታችንን ሀብት፣ ቅርሷን አግበስብሰህ፣
ፋታ ሳትሰጣት፣ በኃይል ደንፍተህ፣
ሸክምህን ሁሉ፣ ለባዳ አራግፈህ፣ ጸጥ-ለጥ ብለህ፣
ገራም ሆነህ ሳይህ፣ ካይሮ ተኝተህ፣
ባጣሙን ተገረምኩ..!
………
ይህ ግጥም የጌታቸው አበራ ሲሆን፣ (ካይሮ-ግብጽ “ኮርኒሽ ኤል-ኒል”- ከዓባይ ወንዝ ዳርቻ) ጥቅምት 1991 ዓ/ም እዚያው ግብፅ ሆኖ ቁጭቱን በብዕሩ ያሳረፈበት የዓባይ ወንዝን በኪናዊ እይታው የቃኘበት ነው። በእርግጥም ቦታ ፈቅዶ ሙሉውን ለማቅረብ አይመችም እንጂ ሙሉ ስንኙ ላይ ያሉ እያንዳንዱ የቁጭት ስንኝ አንባቢ ዘንድ በመቅረብ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፤ ቁጭትና እልህ ያስተጋባል።
ከግንባታው ጅማሮ በፊት በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ ይሰማ የነበረ አገራዊ ቁጭት አንፀባራቂ በእያንዳንዳችን ጆሮ እየገባ ከራሳችን ጋር እየጠቀላቀለ ብዙ ያስተከዘን ኪነ ጥበባዊ ዜማ ዓባይ ዓባይ… የነበረ ዜማ ነው።
ዓባይ ዓባይ አባይ ዓባይ
የአገር ሲሳይ የአገር አዋይ
ያለ አገሩ ዘምሮ
ያለ ግብሩ ዘምሮ
ኣባይ ያለ አሻራ ኖሮ
እህ እህ እህ እህ
…
እጅጉን ደጋግመን የሰማነው የቁጭት ዜማ። ከሁላችን ልቦና ውስጥ የማይጠፋ ኪነት የወለደው ስሜት ገላጭ ዜማ ነው። ያን ጥቁር ውሃ ተሻግሮ ሲሄድ የተቆጨንበት እህ እህ እያልን ያነጎራጎርንበት ነበር። ጊዜ ልብ አስገዝቶት ዛሬ ብርሃን ከመፈንጠቁ ትንሽ ቀደም ብሎ ዓባይን ያየ ያገሬ ሰው በቁጭት አገሬው እንዲህ አዚሟል።
በተለይም የዓባይ ቁጭት ዜማዎችን ስናነሳ መጥቀስ ተገቢ የሆነውን የገነት ማስረሻ “ጭስ አልባ ነዳጅ” ብላ የሰየመችው ዜማ ዓባይን አወድሳ ነገር ግን አገሩን ትቶ ባዕድ አገር ላይ ቤቱን መስራቱን በቁጭት ያነሳችበትን ዜማዋን የማያስታውስ አይኖርም።
“… ዓባይ ወርዶ ወርዶ ወርዶ ሲሳይ ለሰው
ዛሬስ ለወገኑ ስላልሆነ ቆጨው
ዓባይ እኔና አንተ ያለነው ቅርብ ነው
ከተስማማንማ ሙያ በልብ ነው… ”
በማለት ቁጭትና ተስፋዋን በውዳሴም በእልህም አዚማዋለች። ለአብነት እነኚህ አየን እንጂ የዓባይ ልጅ ውሃ በጠማው ጊዜ ኪነጥበብን በብዙ ተመርኩዞ ውስጣዊ ስሜቱን ገልጿል። በድራማ፣ በቲያትር በፊልምና ሙዚቃ ስለ ታላቁ ወንዝና የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት ዓባይ ብዙ ተብሏል።
ዓባይ ዛሬ
ትናንት በኪነ ጥበብ ባለሙያ ስንኝ ተቀኝቶ በዜማ ሰው ተበጅቶ በቁጭት ዋ! ያሰኘን ዓባይ አልል ያሰኘን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 2003 ዓ.ም አንስቶ ደግሞ ዓባይ እጅ ሊሰጥ መሆኑን ማደሪያ ሊያገኝ መሆኑ ተዜሞለታል። ይህ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያውያን በግንባታው ላይ አሻራቸውን ማኖራቸውን እንዲቀጥሉም ተዜሞለታል። ለእዚህም ‹‹እንጉርጉሮ ይብቃ›› የሚለው በታዳጊዎች የተዜመው ይጠቀሳል። የትናንት ኪነት በፈጠረው ቁጭታዊ ዜማ ለምን ያሰኘን የዓባይ መንጎድ በኢትዮጵያውያን ርብርብ ለፍሬ መብቃት ጀምሯልና የድል ዜማ ማስደመጥ ይዟል።
“ እንጉርጉሮ ይብቃ፤ ይገባል ውዳሴ
ጉዞውን ጀምሯል ዓባይ በሕዳሴ
ትውልድ እንደ ጅረት የተቀባበለው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ዛሬ ሊቋጭ ነው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ሀይ ባይ ሊያገኝ ነው…”
ይህ ዜማ ጅማሮው ላይ የተዜመ ዓባይን መገደብ እንደጀመርን የተቀኘ ተስፋ የጣልንበት ግድባችን እውን ሆኖ ማየትን ያስናፈቀን ደጋግመን ያዜምነው ጥዑም ዜማ ነው። ብርሃን ማመንጨት መጀመሩን የተመለከተ የብስራት ዜና ከመስማታችን ከዓመታት በፊት መዜም የጀመረው።
አሁን ላይ ደግሞ ውዳሴው ተበራክቷል። አገሬው ከቁጭት ተላቆ በላብና በጥረቱ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ እያጠናቀቀ ነው። ዓባይም ማደሪያ አግኝቷል፤ ብርሃን መፈንጠቅ ጀምሯል፤ እናት ምድርሩን የማልማት ጉዞውን ጀምሯል። ይህም የቁጭት እንጉርጉሮው ወደ ድል ዜማ እንዲለወጥ ያደርገዋል። ኪነትም ይህን ድል ባማረ ውዳሴ፣ በደመቀ ዜማ እያጀበ ነው። የዓባይን ልማት ላይ መዋል አጉልቶ በራሱ ጥበብ እንዲህ ተቀኝቶታል።
እናም የዓባይን ጅማሮ ጥበብ የተመለከቱ የቀድሞውን ዜማ ለውጠው ወጣት ድምፃዊያኑ (ቅድስት ዘሪሁን እስጢፋኖስና ማህደር (ዓባይ)በተሰኘው ዜማቸው እንዲህ ብለው የአባይን ልብ መግዛት አዚመውታል።
“ዓባይ ዓባይ ዓባይ ዓባይ
በአገሩ ዘምሮ
ወገኑን አክብሮ
መዞሩን ሲያበቃ
ለቁም ነገር በቃ….”
እነሆ ዓባይ በኢትዮጵያውያን ጥረት ለውጤት በቅቶ ብርሃን መፈንጠቅ ጀምሮ ተስፋችንን እውን አድርጎታል። ይህ እሸቱ ነው። ብዙ አለ ገና። ከ13 የሃይል ማምንጫዎቹ አንዱ ነው ስራ የጀመረው። ድሉ ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭታቸውን ወደ ድል ዜማ እንዲለውጡትና በአዲስ ቅኝት ዓባይን ከመውቀስ ወደ ማወደሱ በስፋት እንዲገቡ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የዓባይ ትናንትናና ዛሬ ኪነታዊ ዳሰሳችንንም በዚሁ አሳረግን። መጪው ጊዜ የኢትዮጵያን ብስራት ዜና የምንሰማበት እንዲሆን ተመኘን። ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2014