በቀጣዩ መጋቢት ወር በአልጄሪያ መዲና አልጄርስ በሚካሄደው የታዳጊና ወጣቶች የፈረስ ስፖርት ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ተሳታፊ ለመሆን በዝግጅት ላይ ትገኛለች። በዚህ ቻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችም ዝግጅት ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል።
የዝግጅቱ አንዱ አካል የሆነ የኦሊምፒክ ወጣት ጋላቢዎች የአቋም መለኪያ ውድድር ከትናንት በስቲያ በጃንሜዳ የተካሄደ ሲሆን፣ ጎን ለጎን የአዋቂዎች ውድድርም ተካሂዷል።
‹‹የኦሊምፒክ ቢ-ክላስ›› በሚል ከአስራ አምስት ዓመት በታች ጋላቢዎች በተሳተፉበት ውድድር የቤካ ፈርዳ ክለብ ጋላቢዎች ከአንድ እስከ ሦስት በማጠናቀቅ በበላይነት ፈፅመዋል።
በዚህም ታዳጊው ጋላቢ ቀነኒሳ ተሾመ አንደኛ ሲሆን ፈጠነ ተሾመና ፈጠነ ንጉሱ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ውድድራቸውን ጨርሰዋል። እነዚህ ታዳጊዎች በአልጄርሱ የፈረስ ስፖርት ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚወዳደሩም ይጠበቃል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት በውድድሩ ላይ ተገኝተው ስፖርተኞቹን በማበረታት ለአሸናፊዎቹ የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት አበርክተዋል፤ በውድድሩም ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ወጣቶች እንዲሁም በአዋቂዎች የተለያዩ ውድድሮች ተከናውነዋል። አልጄርስ ላይ በሚካሄደው የፈረስ ስፖርት ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምትሳተፍ የተናገሩት የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን የፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ በአልጄርሱ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ጋላቢዎች በወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ ለመሳተፍ እንደሚፎካከሩ ገልፀዋል።
ለዚህም ከአስራ አምስት ዓመት በታችና ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ሦስት ሦስት ጋላቢዎች ተመርጠው ኢትዮጵያን ለመወከል ወደ አልጄርስ ለማቅናት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ባህላዊ የፈረስ ስፖርት ወደ ዘመናዊ በማምጣትና በማጣመር ስፖርቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ዘሪሁን፣ ለዚህም ታዋቂውን የአዊ ዞን ዓመታዊ የፈረስ ፌስቲቫል እንደ ትልቅ ግብዓት ለመጠቀም አሶሴሽኑ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በጃንሜዳ የተካሄደው ውድድር ለታዳጊዎቹ ጋላቢዎች እንደ አቋም መፈተሻ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም መሰል ውድድሮች ሲከናወኑ እንደነበር አስታውሰዋል። የአልጄርሱ ውድድር እስኪቃረብም ተመሳሳይ ውድድሮችን ለማካሄድ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአልጄርስ በሚካሄደው ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏም ስፖርቱን በአገር ውስጥ ለማነቃቃት ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዚዳንትና የቤካ ፈርዳ ክለብ ባለቤት አቶ ፀጋሁን ተሰማ በበኩላቸው፣ ታዳጊዎቹ ጋላቢዎች ለአልጄርሱ ውድድር እያደረጉ የሚገኙትን ዝግጅት ጨምሮ በጃንሜዳ የተካሄደው ውድድር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹ፈረስ ከኢትዮጵያውያን ጋር የተቆራኘ ነው፣ የራሱን ስም ትቶ በፈረሱ ስም የሚጠራ ማኅበረሰብ ያለባት አገር ናት›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያ በፈረስ ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ብትሆንም ያላትን እምቅ አቅም ወደ ስፖርቱ አምጥታ መጠቀም አልቻለችም ብለዋል።
ይህን እምቅ አቅም በስፖርቱ ለመጠቀም የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዳጊ ወጣቶችን በማዘጋጀት እንደ ቤካ ፈርዳ ያሉ ክለቦች ትልቅ ለውጥ እያመጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም እነዚህ ክለቦች እምቅ አቅሙ ያለበትን የገጠሩን ማኅበረሰብ ወደ ስፖርቱ በማምጣት ተጨባጭ ለውጥ እያሳዩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በአልጄርሱ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ታዳጊና ወጣት ጋላቢዎችም የተመረጡት ከገጠሩ ማኅበረሰብ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል። የአሶሴሽኑ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባልና የባልደራስ ፈረስ ስፖርት ክለብ አባል የሆኑት አቶ አብዱራሂም በክሪ፣ ወደ አልጄርስ ኢትዮጵያን ወክለው የሚያቀኑት ጋላቢዎች ከ12 እስከ 14 ዓመት፣ ከ15 እስከ 18 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች መሆናቸውን በመጠቆም እነዚህ ጋላቢዎች ለኦሊምፒክ የሚወዳደሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አልጄርስ ላይ የሚካሄደው ውድድር ቀደም ሲል ሴኔጋል ዳካር ላይ ሊካሄድ ታስቦ እንደነበር አስታውሰው፣ በኮቪድ-19 ስጋት ለሦስት ዓመታት ተራዝሞ በአልጄርስ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያን በአልጄርሱ ውድድር የሚወክሉ ታዳጊና ወጣት ጋላቢዎችም ከዚህ ቀደም በተደረጉ አራት ውድድሮች መመረጣቸውን ገልፀዋል። የስፖርቱ እምቅ አቅም በኢትዮጵያ እንዳለ የሚናገሩት አቶ ኢብራሂም፣ ስፖርቱ በስፋት ተደራሽ መሆን እንዳልቻለም ጠቁመዋል።
ወደ አልጄርስ የሚያቀኑትን አይነት ታዳጊዎች በብዛት ይዞ መስራት ከተቻለ ከእድሜያቸው ለጋነት አኳያ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ አስገንዝበዋል።
አሶሴሽኑ ውስን በሆነ የመንግስት በጀት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑና ከመወዳደሪያው ፈረስ አንስቶ ስፖርቱ የሚያስፈልጉት ቁሶች ውድ መሆናቸው የፈረስ ስፖርትን በትልቅ ደረጃ ማሳደግ እንዳልተቻለም አቶ ኢብራሂም ተናግረው፣ የአሶሴሽኑን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት የተለያዩ ስፖንሰሮችን ከማፈላለግ ባለፈ መንግስት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቁንም ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014