በእሱ እድሜ የዝናን ካባ የደረበ ፈልጎ ማግኘት ይታክታል። በእርሱ እድሜ ከፍ ባለ ስራና እውቅና በሰዎች ዘንድ ሲጠራ በቀላሉ የሚታወቅ እጅግ ጥቂት ነው። በእርሱ አፍላነት እድሜ በአንድ ሙያ ከጫፍ ደርሰው ስኬትን ተቆናጠው የዘርፉ ሽልማት የተበረከተላቸው ቢጠቀሱ በቁጥር ጥቂት ነው የሚሆኑት። ከዕድሜው ቀድሞ አንቱ መባልን ያተረፈ ዝነኛ በጣት የሚቆጠር ነው። እርሱ ግን ይህንን ሁሉ አሳክቷል። ክብር ዝናና እውቅና ተቀዳጅቷል።
በልጅነቱ የዝናን ካባ ደርቧል፣ በጨቅላነቱ ባሳየው የትወና ብቃት ብዙዎች ካይን ያውጣህ ብለውት ለስራው አጨብጭበዋል። በትወናው ተደምመዋል። ለ4 ጊዜ በአስገራሚ የትወና ብቃቱ ሽልማት ይገባሀል ተብሎ በትልልቅ መድረኮች ላይ በክብር ዋንጫ ተረክቧል። ወጣቱ የትወና ቁንጮ ብላቴና እዮብ ዳዊት።
ገና የ19 ዓመት ወጣት ነው። በልጅነቱ ካሳካው እውቅናና ዝና በላቀ በቀጣይ ህይወቱ መድረስ የሚፈልግበት ግብ ማሳካት የሚመኘው ህልም አለው። ለዚያም ሁሌም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ይናገራል። ወደ ህልሙ መቅረብ የሚያስችለው ትምህርት በትጋት በመማር ላይ ይገኛል። ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዶ ውጤት እየተጠባበቀ ነው፤ አርቲስት እዮብ ዳዊት።
ትውልድና እድገት
ካዛንቺስ መናኸሪያ አካባቢ ተወልዶ ያደገበት የልጅነት ውብ ጊዜውን ያሳለፈበት ነው። ፊደል በመቁጠሪያ ዕድሜው ከቀለም ጋር የተገናኘው ስላሴ ካቴድራል ሲሆን፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በኢትዮጵያ አንድነት ትምህርት ቤት መከታተል ጀመረ። ታዲያ በዚህ ጊዜ አባቱ ወደሚሰሩበት የህፃናትና ወጣቶች ትያትር ቤት ግቢ በእረፍት ሰዓቱ መሄድን ያዘወትር ጀመር። የባህላዊ ዳንስ ስልጠናም ጀመረ። ያኔ 9 ዓመቱ ነበር።
በዚያም የትወናና የዳንስ ስልጠና መውሰድ ጀመረ። ከትምህርት ቤት መልስ እና ትምህርት በሌለ ቀን ማዘውተሪያው የህፃናትና ወጣቶች ትያትር ቤት ነበር። በዚሁ ግቢ ደጋግሞ መገኘቱ አንድ አጋጣሚ ፈጠረለት። በህፃናትና ወጣቶች ትያትር ቤት ውስጥ ባህላዊ ውዝዋዜ በመማር ላይ ሳለ አንድ ቀን ፊልም ሰሪዎች እንደሁልጊዜው ተዋንያን ለመምረጥ ወደዚያ ጥበብ ቤት ያመራሉ።
አሌክሳንደር አወቀ የሚባል የፊልም ባለሙያዎችና ተዋንያን ከፊልም ሰሪ ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኝ ግለሰብ እዮብ ዳዊትን መተወን የሚፈልግ ከሆነ አንድ ስራ ላይ ሊያሳትፈው እንዳሰበ ይነግረዋል። ይህ የመጀመሪያ የሆነውና የገነነበት “ያልታሰበው”የተሰኘው ፊልም ላይ የመተወን እድል ገጠመው። በፊልም ባለሙያ አገናኙ አሌክሳንደር የተመረጠው እዮብ፣ በፊልሙ አዘጋጅ ሄርሞን ሀይሌ እጅግ በጣም ተወደደ። ለፊልም ስራው ዝግጅት ልምምድ ጀመረ።
እዮብ ተዋናይ የመሆን ራእይ ኖሮት አያውቅም ነበር። በትምህርት ቤት ህይወቱም በትወናና ስነ ጽሁፍ ዘርፍ ተስጥኦውና ፍላጎት እንዳላቸው ተማሪዎች በትምህርት ቤት የኪነጥበብ ቡድኖች ተሳትፎ እንዳልነበረውም ያስረዳል። ወደ ትወና የገባው ዕድል እና አጋጣሚ ተገጣጥመውለት ነው።
የጥበብ ጅማሮ
እዮብ ከዚያ የመጀመሪያ ፊልሙ እንዲሰራ ከመጋበዙ በፊት ስለ ፊልም አሰራር ምንም እውቀት አልነበረውም። ፊልሙን እንዲሰራ የተመረጠው ከትልልቅና ስመ ጥር ከሆኑ ተዋንያን ጋር በመሆኑ ጅማሮው ላይ ግራ ተጋባ። ነገር ግን ሁሉም በፊልሙ ላይ የተሳተፉ የፊልም ስራ ባለሙያዎች ቀርበው ይረዱት ያዙ። በተለይ ዳይሬክተሯ ሄርሞን ለእዮብ በፊልሙ ላይ ጎልቶ እንዲወጣ ያስቻለውን የትወና ቴክኒክ እና አተዋወን ጥበብ ጊዜ ወስዳ አስተማረችው።
ልጅነቱ ይህን ለመቀበል ጊዜ አልወሰደበትም። በመጀመሪያ ፊልሙ “ያልታሰበው” ላይ ሲሰራ በፊልሙ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ባለሙያዎች በሙሉ አስተማሪዎቹ እንደነበሩና በደንብ ይተውን ዘንድ እንደነገሩት ደጋግሞ ያነሳል።
በመጀመሪያ ፊልሙ “ያልታሰበው” ላይ የጎዳና ልጅ ሆኖ ሊያሳድጉት ወደ ቤት ያመጡትና እጅግ በጣም አሳዛኝና አዕምሮ ብሩህ ልጅ ሆኖ ሲተውን ያየ በሚያወራቸው ንግግሮቹ ፍፁም ሊረሳው የማይችለው፣ በሳቅ ታጅቦ በእዮብ የትወና ብቃት የማይደመም የፊልም አፍቃሪ ማግኘት ይቸግራል። ለዚህ ፊልም 5 ሺ ብር ተከፍሎት እንደሰራ ይናገራል።
ስለ ፊልም እቤቴ ቁጭ ብዬ እንደማየው ቀላል እንዳልሆነና ሙያ ጥበብና ልዩ ክህሎት ከታታሪነት ጋር እንደሚያስፈልገው ሙያውን ቀርቦ ሲያየው የተመለከተው ሀቅ መሆኑን የመጀመሪያ ስራው ሲጀምር ከተመለከተው ገጠመኝ ጋር እያነፃፀረ ያስረዳል። ያልታሰበውን ለመስራት አሌክሳንደር እና ሄርሞን አግኝተውት እስኪያወሩት ድረስ አንድም ቀን ፊልም የመስራት ፍላጎት ኖሮት አልያም ደግሞ እተውናለሁ የሚል ህልም ኖሮት አያውቅም ነበር።
የስኬት መንገዱ የተለያየ ነው። በአንድ ሙያ አንቱታን ለማግኘት የበዛ ጥረት፣ ያልተቋረጠ ውጣ ውረድ፣ የማይታክት ሙከራ ወሳኝ ሊሆን ይችላል። አንዱ ስኬት እድል ፈጥኖ ከበሩ ሲያደርስለት ሌላው ደግሞ ምን አልባትም ዕድሜውን ሙሉ ለፍቶና ደክሞ ያሰበውን የማያሳካ፤ የወጠነውን ከግብ የማያደርስ ይሆናል። እዮብ ግን አድለኛ ነበረና ወደ ስኬት ደጃፍ የሚያደርሰው ይህ አጋጣሚ ተፈጠረ። በዚህም ተመልካች አይን ውስጥ ገብቶ ተወዳጅ ሆነ።
የተሳተፈባቸው የፊልም ስራዎች፤ ስኬት
የመጀመሪያው ከሆነው “ያልታሰብው” ፊልም በኋላ ፊልም ሰሪዎች እዮብን በጥብቅ ይፈልጉት፤ለፊልም ስራቸው ቅመም ሆኖ ያጣፍጥላቸው ዘንድ ያስተውኑት ጀመር። ካልታሰበው ቀጥሎ ብላቴና የተሰኘ ድንቅ ፊልም ላይ ተውኖ ዝናው ይበልጥ ናኘ።
ገና በዘጠኝ ዓመቱ “ያልታሰበውን” ሀብ ብሎ የጀመረው እዮብ አፄ ማንዴላ፣ ደስ ሲል፣የልጅ ሀብታም፣ እስክትመጪ ልበድ፣ የአራዳ ልጅ፣ ይመችሽ(የአራዳ ልጅ ሁለት)ያበደች (የአራዳ ልጅ 3)እና የአራዳ ልጅ 4ን ተውኖ እጅግ ከገነነባቸው ፊልሞቹ ከፊት ቀዳሚዎቹ ናቸው።
በልጅነቱ የማታመን የትወና ክህሎት ተላብሶ የተወነባቸው ከ30 በላይ ፊልሞች አሉት። ፖለቲካ አይደለም፣ሳቅልን ሄሮል ተውኖ ከፍ ያለባቸው ስራዎቹ ናቸው። አምስት ጊዜ በተለያዩ የፊልም ሽልማት ዘርፎች ታጭቷል። ጉማ የፊልም ሽልማት ላይ በተደጋጋሚ ተስፋ የተጣለበት ተብሎ ኢትዮ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆኖ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል።
ቁጥራቸው በርካታ ፊልሞች ላይ እንደመተወኑ ፊልሞቹን ሲሰራ በየራሳቸው የተለያየ ክህሎትና እውቀት ቀስሞባቸዋል። ነገር ግን የመጀመሪያ ፊልሙ፣ ያልታሰበውና ብላቴና የተሰኙ ፊልሞቹ የፊልም ትምህርት ቤቶቼ ብዙ የተማርኩባቸውና ከልቤ የምወዳቸው ስራዎቼ ናቸው ይላል። በእያንዳንዱ የፊልም ስራ ገጠመኙ ችሎታውን እያሻሻለና አሁን ላይ ቀለል አድርጎና በተሻለ መልክ የሚሰራቸው ስራዎች በመምረጥ እየሰራ ይገኛል።
ቀጣይ ህልም
ልጅ ሆኖ ተዋናይ መሆንን ፈፅሞ አስቦም ተመኝቶም የማያውቀው እዮብ፣ በአጋጣሚ የገባበት የትወና ሙያ ወደፊትም አጠንክሮ በመስኩ ታላቅ የመሆን ህልም አለው። በእርግጥ በልጅነት ይመኘው የነበረውን የጠፈር ሳይንቲስትነት ወይም ተመራማሪነት ለማሳካት የቀለም ትምህርቱን አጥብቆ ይዟል።
አሁን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዶ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ያለው ተዋናይ እዮብ፣ በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ በሚኖረው ቆይታ ከትወናው ጎን ለጎን የልጅነት ህልሙ ሊያሳካበት የሚያስችለውን የትምህርት አይነት መርጦ ወደፊት መገስገስን ይመኛል።
የእዮብ አርዓያ
ስራዎች ሲመጡ መርጠው ይሄን ስራ ይሄ ደግሞ ከአንተ ጋር ፈፅሞ አይሄድምና ተወው ላንተ መልካም ያ ነው እያሉ በስስት የሚንከባከቡት አባቱን “የህይወቴ አርዓያ” ሲል ይገልጻቸዋል። አባቱ በእያንዳንዱ የህይወት መስመሩ እየተከታተሉ ልጃቸው ለስኬት ይቃረብ ዘንድ አቅጣጫ ያስይዙታል። ለህይወቱና ለወደፊት ኑሮው የተሻለን ያመላክቱታል። በስራው ይረዱታል። እዮብ ስለ አባቱ ብዙ ይላል። የህይወት መምህርና አርዓያዬ በማለት ያወድሳቸዋል። ጥልቅ የአባትነት ፍቅሩን ይገልፃላቸዋል።
ወደ ትወናው አለም ሲገባ ያማከረው አባቱን ነው፤ዛሬም ድረስ በእያንዳንዱ ስራውና የትምህርት ቤት ቆይታው የእሳቸው ክትትልና ድጋፍ አይለየውም። ከትምህርት ቤት ውጪ የሆኑትን የፊልም ስራዎቹን ከትምህርት ጋር በማይጣረስ መልኩ መርሀ ግብር ነድፈው ሁለቱም ላይ ስኬታማና ውጤታማ እንዲሆን ያደረጉት አባቱ መሆናቸውን ይናገራል።
እርሱ በትወና ስራ ውስጥ የሚያደንቃቸው ሁሌም ስራቸውን የሚከታተልላቸው ታላላቅ የሙያ አጋሮች እንዳሉትም ይጠቅሳል። ከወንድ ተዋንያን ግሩም ኤርሚያስና አማኑኤል ሀብታሙን፣ ከሴት ተዋንያን ደግም እድልወርቅ ጣሰውና ሰላም ተስፋዬ እጅግ የሚያደንቃቸው መሆናቸውን ያስረዳል። ከግሩም ኤርሚያስ በስተቀር ከሶስቱ ጋር የመስራት እድልም ገጥሞታል።
የእረፍት ጊዜ
ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አብዛኛውን ጊዜውን ሙዚቃ በመስራት ያሳልፋል። ልብ አንጠልጣይ ድራማ እጅግ በጣም የሚወደው የፊልም ዘውግ ነው። የሚገርመው ግን አብዛኛዎቹ የሰራቸው ፊልሞች ከአስቂኝ ዘውግ የሚመደቡ ናቸው። ጊታር መጫወት እና ከቤተሰቡ ጋር ጥሩ የዕረፍት ጊዜውን በመዝናኛ ቦታዎች ማሳለፍን ይወዳል።
ፊልሞች ሳያመልጡት በወጡ ቁጥር እየተከታተለ ያያል። ለትወና ስራው የሚያግዙትንና ጥሩ ታሪካዊ ልቦለድ ይዘት ያላቸውን መፅሀፍት ማንበብ የዕረፍት ጊዜ ተግባሩ ነው። ፊልም መስራትና ስለ ፊልም የተለያዩ መረጃዎችን መለዋወጥና ስለ ፊልም ስራ ማንበብም ይወዳል።
መልዕክት
በሀገር ጉዳይ ላይም አስተያየቱን ሰጥቶናል። “ከአገር የበለጠ ትልቅ ጉዳይ የለም። ሁላችንም በአንድነት ተፋቅረን ከሆነ ሀገራችን በቂያችን ናት፤ እንኳን ለእኛ ለልጆቿ ለሌሎችም ትተርፋለች። አሁን ካለችበት ፈተና እንድትወጣ ሁላችንም በያለንበት ሀይማኖት አጥብቀን እንለምን።›› ሲል ያሳስባል።
‹‹ሰላም እንድንሆን በጎ ነገር ላይ እናተኩር” በማለት ኢትዮጵያዊያን ካሉበት እርስ በርስ ከመጠራጠርና ከመናቆር ወጥተው የአብሮነት ጉዟቸውን ይቀጥሉ ዘንድ ይማፀናል። በአንድነት ተቆሞ የማይታለፍ ችግር፣ በአብሮነት ፀንቶ የማይፈቱት ችግር የለምና የአገሬ ልጆች ሆይ በአንድነት በአንዲት ሀገራችሁ አፅኑ፤ የሚል ሀያል መልዕክቱን እንካችሁ ብሏል። አበቃን፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014