የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ እያገለገለ ያለውና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚደረገው ልዩ ልዩ የአፍሪቃ መንግሥታት ጉባኤዎች መሰብሰቢያ እንዲሆን በሚል የተገነባው ይህ ቀደምት አዳራሽ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመርቆ የተከፈተው በ1950 ዓ.ም በዚህ ሳምንት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አንዳንድ መረጃዎች ህንጻው የተመረቀው ጥር 30 መሆኑን ይጠቁማሉ። አብዛኞቹ መረጃዎች የሚያሳዩት ይህ ሁነት የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ብቻ መሆኑን ነው። ለማንኛውም ወደ ታሪኩ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሁለት ዓመት በፊት ‹‹የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ታሪክ›› በሚል በሰራው ፕሮግራም፤ ሕንጻው የተሰራው ለአፍሪካዊ ጉዳዮች ነው። ይህ ሕንጻ በወቅቱ በስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተገነባና በ1950 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር የተፈረመውም በእዚሁ ህንጻ በተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቤተ መጻሕፍት እና ሌሎች ሰፋፊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ያሉት ይህ ግዙፍ ህንጻ፤ የአርክቴክት ባለሙያውም ኢትዮጵያዊው ኢንጂነር ጌታቸው ማህተመሥላሴ ናቸው። የህንጻው የወንበሮች አቀማመጥ፣ ለሊቀመንበር 8፣ ለአማካሪዎች 36፣ ለተመልካች 48፣ ለአስተርጓሚ 8 ለጋዜጠኞች 225፣ ለልዩ እንግዳ 37 ወንበሮች እንዲኖሩት ተደርጎ ነው የተገነባው።
በመግቢያው ላይ በሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተሳለ 150 ስኬየር ሜትር ስፋት ያለው በመስታወት ላይ የተሳለ ስእል ይገኛል። ስእሉም የቀደመችውን፣ የአሁኗንና መጪዋን አፍሪካ የሚያመላከት ይዘት ያለው ነው።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የግቢውን ይዞታ ከመንግስት በተለያዩ ጊዜያት በተሰጠው ተጨማሪ ቦታ በማስፋፋት ግዙፍ ግንባታዎችን በማድረግ በርካታ አዳራሾች እንዲኖሩት አርጎ ገንብቶበታል፤ በእዚህም በርካታ አለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ሀገር አቀፍ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ። የተባበሩት መንግስታት በርካታ መስሪያ ቤቶችም በእዚሁ ግቢ ውስጥ ይገኛሉ።
ኢዮቤልዮ ቤተ መንግሥት
ኢዮቤልዮ ቤተ መንግሥት፣ ከደርግ ስርአት አንስቶ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በመባል ይታወቃል። ኢዮቤልዮ ቤተ መንግሥት የተባለው በዚያ ዘመን የሀገሪቱ መሪ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ነው። ቤተመንግስቱ የተገነባውም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን 25ኛ ዓመት የንግሥና በዓል አስመልክቶ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን ታሳቢ በማድረግም ነው ኢዮቤልዮ (25ኛ ዓመት) የተባለው ይባላል።
ይህ ፍል ውሃ በመባል በሚታወቀው አካባቢ የሚገኝ ቤተ መንግሥት ከደርግ ወዲህ ደግሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መኖሪያ እና እንግዶች መቀበያ ነው። ቤተ መንግሥቱ ከዛሬ 66 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 30 ቀን 1948 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ይነገርለታል።
ቤተ መንግሥቱ ለሙዝየምነት የሚያበቁት በቂ የቅርሳቅርስ ክምችት እንዳለውም ይገለጻል። የነገስታት አልባሳትን፣ ከልዩ ልዩ አገራት የተበረከቱ ስጦታዎችን፣ የዱር እንሰሳት ማቆያ፣ የዚያን ዘመን ልዩ ልዩ ዘመናዊና ቅንጡ አውቶሞቢሎችን እንዲሁም የትም የማይገኙ ታሪካዊ ቁሳቁስን ይዟል።
ቤተ መንግሥቱ በአገር በቀል ዛፎች የተሞላና የተዋበ ሲሆን፣ አንበሳን ጨምሮ የተለያዩ የዱር እንስሳት ግቢም ያለው ነው። የቤተ መንግሥቱ ውስጣዊ ክፍልም እንዲሁ በተለያዩ ውብና ውድ ዕቃዎችና ጌጣጌጦች የተዋበ መሆኑ ይታወቃል።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የቀድሞውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ለቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በስጦታ ከማስረከባቸው በፊት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓለ ሲመታቸውን ሲያከብሩ ያሠሩት ይህ ቤተ መንግሥት፣ ዘመን ተሻጋሪ ውብ የአርክቴክቸር ጥበብ የተንፀባረቀበትም ነው።
ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት የሀገሪቱ ርእሰ ብሄሮች የነበሩት ለቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና አሁን ደግሞ ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በመኖሪያነት ያገለገለ ከመሆኑ በተጨማሪ የሀገሪቱን እንግዶች አስተናግደውበታል።
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተሠራላቸው ቤት መኖራቸው አይዘነጋም። ለአንዳንድ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ብዙም አልተገለገሉበትም። ንጉሡ በብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ከተመራውና ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን ለቀው ከ1954 ዓ.ም. ጀምሮ ለ13 ዓመታት እስከ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ድረስ በዚህ ቤተ መንግሥት ውስጥ ኖረዋል። በኋላም ወታደራዊው መንግሥት ንጉሡን ከሥልጣን አውርዶ ይህንን ቤተ መንግሥት ተረክቧል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኮሎኔል መንግሥቱ የሚመራው ደርግ ይህንን ቤተ መንግሥት ኦፊሴላዊ ዝግጅቶችን ለማካሄድና እንግዶችን ለመቀበል ተጠቅሞበታል።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው አዲሱ መንግስት ይህን ቤተመንግስት ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር እየሰራ ነው። ከጊዮን ሆቴል፣ ከፍል ውሃ እና በአቅራቢያው ካለው ከፍት ቦታ ጋር በማስተሳሰር ልዩ የመስህብ ስፍራ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ለእዚህም ሲባል የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መኖሪያ ወደ ሌላ ስፍራ ተዛውሯል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014