ወጣት ዘካሪያስ ኪሮስ ይባላል «ንስሮቹ» የሚል የበጎ አድራጎት ማሕበር በማቋቋምና ወጣቶችን በማሰባሰብ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየከወነም ይገኛል። ወጣት ዘካሪያስ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ሲሆን የኤክስካቫተር ሹፌር በመሆን በታላቁ ህዳሴው ግድብ ግንባታ ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግሏል። በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ አካባቢ ልዩ ስሙ ዱባይ ተራ ተወልዶ ያደገው ዘካሪያስ የልጅነት ጊዜውን ወጣ ገባ በሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሳለፈ ይናገራል።
መቀሌ ከሚኖሩት አባቱ ጋር ብዙ ጊዜ ባይገናኝም እቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ከእናቱ፣ ከአክስቱና አንድ እህቱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው። ቤተሰቦቹ እሱን ለማብላት፤ ለማጠጣትና ለማልበስ የማያንሱ ቢሆንም ቤት ውስጥ መጠጥ ይሸጥ ስለነበርና እሱ ይህንን ስለማይወድ ዘካሪያስ ትንሽ ከፍ ካለ በኋላ ራሱን በመቻል ሕይወትን ለማሸነፍ የተለያዩ ይበጁኛል ያላቸውን የሕይወት አማራጮች ሲሞክር ቆይቷል። በዚህም በጎዳና ሕይወት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እስከ ድሬዳዋ ከተማ በመሄድ በተለይም ናዝሬት ከተማ ውስጥ ብዙ አሳዛኝ ሕይወቶችን አሳልፏል። ከዛ መልስም በቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረ ሲሆን በሰዋስወ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በነገረ መለኮት ትምህርት በዲፕሎማ ለመመረቅ በቅቷል።
ዘካሪያስ በዚህ ጊዜ ካገኘው የመንፈሳዊ ሕይወት የሃይማኖት አስተምህሮ የሆነው «ለሌሎች (ስለሌሎች) መኖር በውስጡ ትልቅ ቦታ ነበረው። ዘካሪያስ አሁን በሚሰራው መልኩ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በመሆን የበጎ ሥራዎችን ያከናውን ነበር። ነገር ግን ልጆቹ የሚሰሩት ሥራ እሱ በሚፈልገው መልኩ የተቃኘ ስላልነበር የራሱን በማቋቋም ይጀምራል።
በዚህ ሁኔታ ያደገውና የበጎ አድራጎት ሥራውን የጀመረው ዘካርያስ ወደ በጎ ስራ አገልግሎት የገባበትን አጋጣሚ እንደሚከተለው አጋርቶናል። አንድ ቀን እቤቱ ሳለ አንድ ችግርተኛ ለመለመን ወደ እነሱ ቤት ጎራ ይላል። ሰውየው በጣም የተጎዳ ስለነበርና የለበሳቸውም ልብሶች እላዩ ላይ የከረሙ በመሆናቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረም። እናም ዘካሪያስ ሰውየውን ምግብ አብልቶ ካደረገ በኋላ ገላውን እንዲታጠብ ያደርገውና የራሱን ልብስ አውጥቶ ያለብሰዋል። ሰውየው ገላውን ታጥቦ ልብሱን ሲቀይር ፍጹም አዲስ ሰው ሆኖ ይገኛል። በዚህች ቅጽበትም ዘካሪያስ ቢያንስ በሳምንት አንድ ሰው እንደዚህ እያደረግኩ መታደግ ብችል ለብዙዎች መድረስም ለብዙዎች አርአያ መሆንም እችላለሁ የሚል ሃሳብ በአእምሮው ብልጭ ይልበትና ስራውን ይጀምራል።
ወደ ስራው ሲገባ ግን ነገሮች እሱ እንዳሰበው በቀላሉ የሚገፋ ሆኖ አላገኘውም፤ ነገር ግን ለራሱ ቃል ስለገባ ከቤቱ አንድ ባሊና አንድ ጆግ እንዲሁም የራሱን ልብሶች በመሰብሰብ ሥራውን ይቀጥላል። የራሱ ልብስ ሲያልቅበት ደግሞ ከጓደኞቹና ከሚያውቃቸው ሰዎች እየጠየቀ ገላ ማጠቡንም ምግብ መመገቡንም ይቀጥልበታል። በወቅቱ ያን ያህል ለውጥ ያመጣል ብሎ አስቦም ባይሆን በየሰፈሩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለሚሰሩና ሊሰሩ ላሰቡትም መነቃቂያ ይሆናል በማለት የሰራቸውን ሥራዎች በፌስቡክ ገጹ ያካፍል ነበር።
እናም ከፌስቡክ ገጹ የሚያገኛቸው ምላሾችም የሚያበረታቱ ነበሩ። ብዙ ሰዎችም «ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ» እንደሚባለው ለእነሱ ቀላል የሆኑ ለዘካሪያስና ጓደኞቹ ግን ብዙ ጥቅም ያላቸውን ድጋፎች ማድረግ ይጀምራሉ። በቁሳቁስ ከአንድ ሳሙና እስከ ደህና ልብስ፤ እንዲሁም በሞራል ከመደገፍ በአካል ተገኝቶ ሥራውን እስከማገዝ በርካቶች አብረውት መሆን ይጀምራሉ። በዚህ ሞራሉ የተነቃቃው ዘካሪያስም ለምን በቋሚነት ምግብ የመመገብ ሥራ አንጀምርም በማለት ከጓደኞቹ ጋር ይመክርና ወደ ትግበራው ይገባል። በዚህም ጎጃም በረንዳ ወለጋ ሆቴል ፊት ለፊት አስፋልት ዳር በየቀኑ ለአስር ሰው ሻይና ዳቦ ማብላት ይጀምራል።
በዚህ አይነት ሥራውን ያዩ ወጣቶችና ሌሎችም አጠንክረው መደገፍ ሲጀምሩ በሻይና ዳቦ የጀመረውን ምገባ ወደ መኮሮኒ በዳቦ ያሳድገዋል። ቀስ በቀስም ሩዝ… ምስርና ሌሎች አይነቶችንም እየጨመረ በርካታ ችግርተኞችን መመገቡን ይቀጥላል። የሰራው ሥራ እየታወቀ ሲመጣ የሕብረተሰቡ ድጋፍ እየተጠናከረ በመምጣቱ በቀን በሬ አርዶ ከአንድ ሺ ሁለት መቶ በላይ ሰዎችን እስከመመገብ ይደርሳል። ነገር ግን የዚህ ያህል ሰው አስፋልት ላይ ሰብስቦ መመገቡ ከጸጥታና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የራሱ ችግር ስለነበረው በፖሊስ ትእዛዝ እንዲያቆም ይደረጋል።
በወቅቱ ዘካሪያስ በጣም ቅር በመሰኘቱ ነገሩን በማሕበራዊ ሚዲያ ይፋ አድርጎትም ነበር። ቅሬታውን ሲለቅ የከተማዋን አስተዳደሮችም ፎቶ አብሮ ስለለቀቀው ከከተማ አስተዳደሩ የመጡ ሃላፊዎች ነገሩን መቀጠል እንደሚችል ያሳውቁትና ሥራውን ይቀጥላል። ነገር ግን ፖሊሶች በድጋሚ በመምጣት በዚህ ሁኔታ መቀጠል አትችልም ብለው ያስቆሙታል። ይህም ሆኖ ከጊዜ በኋላ ግን ችግር በማይፈጥር መልኩ ዛሬ እዛው ጎጃም በረንዳ አካባቢ፤ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን፤ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያንና፤ ሽንቁሩ ሚካኤል ቤተከርስቲያን የተቀመጡ ጸበልተኞችን እየመገበ ይገኛል።
በዚህ ሁኔታ ቀጥለው ጠዋት አንድ ሺ አምስት መቶ፣ ማታ አንድ ሺ አምስት መቶ፣ በድምሩ ሶሰት ሺ ግለሰቦችን አስከመመገብ ደርሰው ነበር። ከዚህ ውስጥ አንድ ሺው በማህበራዊ ሚዲያ ተዝካር ሰርግና ፍላጎትን አካቶ በትእዛዝ ሲሆን፤ አምስት መቶው ግን በቋሚነት ምገባ የሚደረግላቸው ናቸው። ዘካሪያስ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ከሃሳብ እስከምክርና እስከ ቁሳቁስ ያላቸውን ለጋስነት «እስካሁን ያልረዳን ግለሰብና ድርጅት የለም» ሲል ይገልፃል።
ዘካርያስ ከዚህም ባለፈ ሶስት መቶ ሃምሳ አንድ ተንቀሳቃሽ የብረት ቤቶችን በመስራት ሕይወታቸውን በጎዳና ለሚገፉ አቅመ ደካሞች ማድረስ ተችሏል። ሥራውን ሲጀምር እነዚህ ቤቶች እያንዳንዳቸው ከአንድ ብርድልብስና ፍራሽ ጋር ሰባት ሺ አምስት መቶ ብር ያወጡ ነበር። በአሁኑ ወቅት የእያንዳንዱ ቤት ወጪ አስራ ሁለት ሺ ብር ደርሷል። የእነዚህ ቤት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ግማሾቹ ይህንን ክረምት እንዴት እንወጣለን ብለው ከዛሬ ነገ ሬሳችን ከመንገድ ዳር በማዘጋጃ ሰራተኞች ይነሳል ብለው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ሴቶቹ ደግሞ በእያንዳንዷ ሌሊት የሚያሰጋቸውን የመደፈር አደጋ የዳኑ ናቸው።
እነዚህ ቤቶች በመንገድ ዳር የሚቀመጡ ቢሆንም እነዘካሪያስ የትራፊክና የእግረኛ መንገድ እንዳይዘጋ፤ ቤቶቹ የወንጀል መፈጸሚያ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄና ክትትል እያደረጉ ይገኛል። እነዚህ የብረት ቤቶች በቅድሚያ በቆርቆሮ ከሃያ በላይ ያሰሯቸውን ቤቶች አይጨምሩም። ከዚህም በተጨማሪ እነዘካሪያስ መንግሥት በሚያውቃቸው የቀበሌ ቤቶች የሚኖሩ አዛውንቶችንም በቁሳቁስና በቤት ማደስ መርሃ ግብር ይደግፋሉ። በዚህ ሁኔታ ከሚደገፉት መካከልም 2013ዓ.ም ሃያ አንድ ቤቶችን በማደስ ለአቅመ ደካሞች ማስረከብ ችለዋል። እነዚህ ቤቶች ከፊሎቹ ግማሽ እድሳት የተደረገላቸው ሲሆኑ አብዛኞቹ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ፈርሰው የታደሱ ናቸው።
ዘካሪያስ ላለፉት ሁለት ዓመታት በስሩ ከሃያ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በመያዝ ለወገን ደራሸ ወገኖችንም ሆነ ድጋፍ የሚሹትን የሚያገኘውም ሆነ ድጋፍ የሚደረግላቸውን የሚለየው ማሕበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ነው። በእነዚህ ጊዜያት ከሰራቸው ስራዎች መካከልም የእማማ ዝናሽ ታሪክ በሕዝብ ዘንድ አድናቆት ያተረፈለትና ቀዳሚውም ነው።
ዛሬ የማሕበራዊ ሚዲያ አንድ አነጋጋሪ ግለሰብ እስከመሆን የበቁት እማማ ዝናሽ እንዴት ለዚህ እንደበቁ ዘካሪያስ እንደሚከተለው ያስታውሳል። በአንድ ወቅት አዲስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት አንዲት እናት ለሁለት ዓመታት ያህል ላስቲክ እየለበሱ ጎዳና ዳር በረንዳ ላይ ይተኙ ነበር። ዘካርያስ እኚህን እናት ለማንሳት ሲንቀሳቀስ እቤት ወስጥ ያሉ በተመሳሳይ ችግር ወስጥ የሚገኙ እናት መኖራቸውን በወረዳው የሚሰራ አንድ ወጣት ይነግረውና ወደሳቸው ያቀናል።
በወቅቱ ባዶ ቤት ያገኛቸው እማማ ዝናሽ የነበሩበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፤ ጥፍራቸው አድጎ ቤታቸው በእጅጉ ቆሽሾና ተጎሳቁሎ፤ ለነፍስ ያሉ ሰዎች ያመጡላቸውም ምግብ በየቦታው ተበታትኖ የአይጥ ራት ሆኖ ነበር። ዘካሪያስ ባየው ነገር በእጅጉ እንዳዝነ እሳቸውን ፎቶ አንስቶ በማህበራዊ ሚዲያ ለመላው ኢትዮጵያዊ እጅ ከምን ሲል ይለቀዋል። ወዲያውም እሱ ካሰበው በላይ ያልጠበቀውን ምላሽ ማግኘት ይጀምራል። በተለይም ቀዳሚዋ የሆነችው የኢትዮ ኢንፎ-ዩ-ትዩብ ባለቤት መሰረት የምትባል ግለሰብ መጥታ በመቅረጽ ለሕዝብ ይፋ ስታደርጋቸው ነገሮች ሁሉ መለወጥ ጀመሩ።
እማማ ዝናሽ በወቅቱ አቅማቸው በርትቶ አብሰለው መመገብ ባይችሉም በሰላ አንደበታቸው ያሰቡትንና ያሳለፉትን በግልጽ ይናገሩ ነበር። ከዚህም ውስጥ በተለይ በሕይወት እንዲቆዩ ትልቁን ሚና የተወጡላቸውን እማማ ስሉስን (አደይን) ከአፋቸው አውጥተዋቸው አያውቁም። እማማ ስሉስ (አደይ) ከእማማ ዝናሽ ጋር የነበራቸው ትውውቅ በምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም በየቀኑ እየመጡ አቅማቸው የፈቀደውን ምግብ በማብላትና እማማ ዝናሽ የሚወዱትን ቡና በየቀኑ በማፍላት ይንከባከቧቸው ነበር።
እማማ ዝናሽም ዘካሪያስን የክፉ ቀን ደራሼ እያሉ «ተገኘ ወርቅ» በማለት ስያሜ አውጥተው የሚጠሩት ሲሆን እማማ ስሉስን ደግሞ እናቴ እህቴ በማለት ከአፋቸው ለይተዋቸው አያውቁም። ዛሬ እማማ ዝናሽ ከምግብና ከሰው ፍቅር ባለፈ እንደ አዲስ ጎጆ ወጪ ባለ አስራ አንድ ሺ ብር ፍራሽ ላይ እየተኙ ፍሪጁ ቁምሳጥኑ ሁሉም ነገር በተሟላበት ቤት ወስጥ እየኖሩ ይገኛሉ።
እነ ዘካርያስ ዛሬም ድረስ ከየመንገዱ እየለመኑና እያግባቡ በማንሳት ገላቸውን የሚያጥቧቸው አሉ። ሆኖ ሥራው እንዲህ በቀላሉ የሚገፋ አይደለም ከእነዚህም መካከል በአንድ ወቅት ለማጠብ ሲያነሷቸው ዘካርያስን በጭንቅላታቸው ጥርሱን የገጩትን አባት ያስታውሳል። በእርግጥ ነገሩ ካለፈ በኋላ እንደተረዳው አዛውንቱ ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ ጉዳት ያደረሱበት በኪሳቸው በልመና ያገኙት ከፍተኛ ብር ስለነበር እሱን ይወስዱብኛል በሚል የተሳሳተ ስሜት ነበር። ሁሉን ካወቁ በኋላ ግን አዛውንቱ ለነዘካርያስ አባታዊ ምስጋናቸውን ከማድረግ አልቦዘኑም ነበር።
በተመሳሳይ በአንድ ወቅት ደግሞ አንዲት የጡት ካንሰር ታማሚ የነበረች እናት ከልጇ ጋር ትኖር ነበር። በወቅቱ ሴትየዋ ቪዲዮ ስትቀረጽ እናቴን አድኑልኝ እያለች ትማጸን ስለነበር ከፍተኛ ገቢ ማሰባሰብ ተችሎ ነበር። ነገር ግን እናትየው ሕይወቷ ሊቆይ አልቻለም። ይህም ሆነ ልጅቷ ታማ ስለነበር እንድትታከም ከተደረገ በኋላ አባቷ ስለነበር ከእሱ ጋር እንድትሄድ ተደርጓል። ዘካርያስ ለዚህ ሥራው መቀጠል ደግሞ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማራውና መርካቶ አካባቢ በተለምዶ አሜሪካን ጊቢ የሚገኘውን ወጣት አስመሮም አርአያ እንደሆነው ይናገራል።
ዘካርያስ ከአመት በፊት ያገባት የትዳር አጋሩንም ያገኛት በዚሁ የበጎ አድራጎት ሥራው እማማ ዝናሽን ልትደጉም መጥታ ነበር። ከመንደር ሃሜት እስከ ግልጽ ትችት የገጠሙት ዘካርያስ በሥነ መለኮት ትምህርቱ የተማረውን በመተግበር ሁሌም ለበጎ ሥራ መቅናት እንዳለበት በመናገር ሥራውን በመስራት ላይ ይገኛል።
ዘካርያስ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት ያስተማሩትን አሳዛኝና አስደሳች ገጠመኞች እንደሚከተለው ይገልጻቸዋል። በአንድ ወቅት አንድ ወጣት በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ታሞ ወድቆ የተገኘ ነበር። እነሱ አንስተውት በራሳቸው አስታማሚነት በራስ ደስታ ሆስፒታል የአራት ሰው ደም ተሰጥቶት ለአንድ ሳምንት ቆይቶ እንዲድን ቢያደርጉትም ተመልሶ ወደ ሱስና ጎዳና ሕይወት ሊመለስ በቅቷል።
በሌላ በኩል አንድ ወጣት በጣም በትልቁ ጸጉሩን ያሳደገና በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የነበረ በጎዳና አግኝተው ነበር። ወጣቱ የመኪና ረዳት ሲሰራ የነበረ ሲሆን በኮንትሮባንድ ሥራ ተጠርጥሮ አሽከርካሪው ሲያመልጥ እሱ ተይዞ ለረጅም ጊዜ በእስር በመቆየቱ ለጎዳና ሕይወት የተዳረገ ነው። ይህም ሆኖ ወጣቱ ጸጉሩን ያሳድግና ኮፍያ ያደርግ የነበረው ጭንቅላቱ ላይ ትልቅ እጢ ስለነበረበት ነበር። ወጣቱ ህክምና የጀመረ ቢሆንም በገንዘብ እጦት ማቋረጡን ለእነዘካርያስ ስለነገራቸውና እነሱም በማሕበራዊ ሚዲያ ስለለቀቁት አንዲት ሴት ባደረገችው የስድስት ሺ ብር ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ለመዳን ችሏል።
በተመሳሳይ አንዲት የሶስት ልጆች እናትና ከኤች አይቪ ጋር የምትኖር በዘሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነች ለሕዝብ እንዲደርስ በመደረጉ ስምንት መቶ ሺ ብር ተሰብስቦሏት ቤቷ ታድሶላት መኪና ለመግዛት እስከ ማሰብ ደርሳ በማይገመት ሕይወት ውስጥ ትገኛለች።
በመጨረሻም ዘካሪያስ እንደገለፀው፤ ዲግሪ ይዞ ተመጋቢ የነበረ፤ ነገር ግን ዛሬ በአንድ ወረዳ የሰው ሀብት አስተዳደር ሰራተኛ የሆነ ወጣትም ተጠቃሚ ሆኗል። እኛ ሥራ ለሚሰሩ ክብር አለን ለእርዳታውም ቅድሚያ እንሰጣለን የሚለው ዘካርያስ ሊስትሮ ለሚሰሩ፤ ሀይላንድ ለሚሰበብስቡና ሌሎችም እስከ አምስት መቶ ብር ድጋፍ ያደረግንበት ጊዜ አለ። ነገር ግን እንኳን አለሁ ባይ የሌላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ይቅርና ረሃብ ብዙ ያሳስባል፣ ወንጀል ያሰራል ከቤተሰብ ያራርቃል። በመሆኑም ከምንም በፊት በተቻለ አቅም የተራቡትን መርዳት የተጠሙትን ማጠጣት ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ሲል ወጣታዊ ምክሩንም አስተላልፏል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2022