
አዲስ አበባ፡- የማሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ቹጉኤል ማይጋ ፈረንሳይ በልዩ ተልዕኮ የተሰማሩ ወታደሮቿን በመጠቀም የምዕራብ አፍሪካን አገራት ለመከፋፈል እየሞከረች ነው ሲሉ ወቀሱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዲፕሎማቶች ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ማሊ ከጽንፈኛ ታጣቂዎች ጋር በተደረገው ጦርነት ለተሰዉ የፈረንሳይ ወታደሮች ትልቅ ክብር እንዳላት አውስተዋል።
ይሁን እንጂ ፈረንሳይ ማሊን ለመርዳት በሚል ተልዕኮ አሸባሪዎችን እየረዳች መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
በማሊ ውስጥ በልዩ ተልዕኮ ወታደሮች ልጆቻቸውን ያጡ ፈረንሳውያን የአገራቸው መንግሥት ማሊን ከመርዳት ይልቅ አገሪቱን ለሁለት ለመከፋፈል እየሰራ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል ነው ያሉት ።
የተዳከሙ አሸባሪዎች ተመልሰው አገራችንን እንዲወሩ ለሁለት ዓመታት ያህል እንደገና እንዲደራጁ እና አቅም እንዲኖራቸው ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች ሲሉም ፈረንሳይን ወንጅለዋል።
በፈረንጆቹ 2013 ላይ የፈረንሳይ ጣልቃ ገብነት በማሊ በጀመረበት ወቅት የፈረንሳይ ጦር አሸባሪዎችን በማሰልጠን እና የቱዋሬግ ተገንጣዮችን ይደግፋል በሚል ክስ አቅርበው እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲም ሆነ የፈረንሳይ መንግሥት በወቅቱ ምንም አይነት ምላሽ አለመስጠቱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ሰርቫል በመባል የሚታወቀው የፈረንሳይ ወታደራዊ ዘመቻ ሰሜናዊ ማሊን ከጽንፈኛ ታጣቂዎች ለመመለስ እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱን አፍሪካን ኒውስ በዘገባው አስታውሷል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014