አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከአርሶ አደር ማህበረሰብ የተገኘ እንደመሆኑ በግብርና ሥራ ተሠማርቶ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮውን ሲገፋ ይስተዋላል። ከአርሶ አደር ቤተሰብ የሚወጣው አብዛኛው የተማረ ኃይልም በሌሎች የሥራ ዘርፎች ቢሰማራ እንጂ ግብርናውን ሲቀላቀል አይታይም። ጥቂት ቁጥር ያላቸው የአርሶ አደር ልጆች ደግሞ ባደጉበት የግብርና ሥራ ተሰማርተው ሰፋፊ ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል። የዛሬው እንግዳችንም ባደገበት የግብርና ዘርፍ ተሰማርቶ እራሱንና ቤተሰቡን ብሎም በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ስኬታማ ወጣት ነው።
እንግዳችን ከአርሶ አደር ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ እንደማደጉ ሕይወቱ ለግብርና ሥራ የተሰጠች ያህል የግብርና ሥራን አጥብቆ ይወዳል። ዛሬ ላይ ለደረሰበት የስኬት ጎዳናም መሰረት ጥሎልኝ አልፏል የሚለው በግብርና ዘርፍ የተሰማሩት ቤተሰቦቹና የአካባቢው ማሕበረሰብ ስለመሆኑ ይናገራል። ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘው አቶ አዲሱ ሙሉነህ (አቢታ) ተወልዶ ባደገበት አርሲና አሰላ አካባቢ በስፋት የሚታወቀው በቅጽል ስሙ አቢታ በመሆኑ ቆይታችንም አቢታ በሚለው ቅጽል ስም እንዲሆን ወዷል።
‹‹የገበሬ ልጅ በመሆኔ የግብርና ሥራን ከልጅነት እስከ ዕውቀት እየተማርኩና ቤተሰቦቼን በተግባር እያገለገልኩ አድጌያለሁ›› የሚለው አቢታ፤ ተወልዶ ባደገበት አርሲ ትምህርቱን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል። የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ግን እርሻን ከማረስ ጀምሮ ሌሎች የግብርና ሥራዎችን በሙሉ በመሥራት ወላጆቹን አገልግሏል።
አካባቢው በስንዴ ምርት በስፋት የሚታወቅ ሲሆን ድንች፣ ሽንኩርት፣ ጎመንና መሰል አትክልቶችም እንዲሁ በስፋት ይመረታሉ። የግብርና ሥራ በአካባቢው ከዓመት እስከ ዓመት የሚቋረጥ አይደለምና ክረምቱን ተከትሎ የሚሠራው የግብርና ሥራ ሲጠናቀቅ የበጋው ሥራ የሚቀጥል በመሆኑ አቢታም ከዓመት ዓመት ጊዜውን በግብርና ሥራ ያሳልፍ ነበር። ከግብርና ሥራው ጎን ለጎንም በአካባቢው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በመኖሩ በንግዱም በኩል አቢታ ንቁ ተሳታፊ ሆኖ ነግዷል።
የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ በግብርና እንዲሁም በንግድ ሥራ የተሳተፈው አቢታ፤ በሳምንት ማክሰኞና እሁድን በሚቆመው የአካባቢው ገበያ በመሳተፍ ከአሰላ ለንግድ ከሚመጡ ነጋዴዎች የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን ለአካባቢው ገበሬ በማሻሻጥ በቀን አንድ እና ሁለት ብር ያገኝ ነበር። በዚህ መልኩ የተጀመረው ንግድ ከዝዋይ ዓሳ በማምጣት መሸጥንም አካቷል። ክፍተት ያለበትን ቦታ ሁሉ አስተውሎ በመረዳት ችግሮችን መድፈን የሚቀናው አቢታ፤ ቀስ እያለም የእንስሳት መድሃኒቶችን ከአሰላ ወደ አርሲ በመውሰድ ለገበሬው በማቅረብ የንግዱን እንቅስቃሴ አጠናክሯል።
አጠናክሮ በያዘው የንግድ እንዲሁም የግብርና ሥራ ውጤታማ በመሆኑ ዕለት ከዕለት ጠርቀም ያሉ ብሮች ወደ አቢታ መግባት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ታድያ ቆም ብሎ አሰበ። ትምህርቱን አቋርጦ የግብርናውን እና የንግዱን ሥራ በሙሉ ጊዜው ቢሠራ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚሆን ከስሜት ውጭ ሆኖ አሰላው። ስሌቱም ውሳኔ ላይ አድርሶት እስከ 12ኛ ክፍል ከሚያደርገው ጉዞ በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲ የሚኖረው ቆይታ ሲደመር ሚዛን አላነሳለትምና ትምህርቱን ከስምንተኛ ክፍል ሊያቋርጥ የግድ ሆነ።
የግብርና እንዲሁም የንግድ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ትምህርቱን ሲያቋርጥ ታድያ ያሳደጉት አያቱ ተቃውሞ አልነበራቸውም። እንዲያውም ሀሳቡን ያከብሩለትና ይደግፉትም ነበርና ይሄ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለታል። በጥቃቅን የንግድ እንቅስቃሴ ያገኛትን ሁለት ሺ ብር የማይሞላ ገንዘብ ይዞ ትልቁን ህልም ለማሳካት በአቅራቢያው ወደምትገኘው አሰላ ከተማ በማምራት የተለያዩ አትክልቶችን ወደ ክልል ከተሞች የማከፋፈል ሥራ ሰርቷል።
እስከ ሻሸመኔ ድረስ የሚገኙ የአካባቢው ገበሬ ጋር ወርዶ ገበሬው የሚያለማውን ድንች፣ ሽንኩርትና ጎመን የመሳሰሉ አትክልቶችን ወደተለያዩ የክልል ከተሞች በማከፋፈል መሸጥ ቀጠለ። እሱ ልጅ በነበረበት ወቅት በአካባቢው የሚመረተው አትክልት ከአዳማ እስከ አዲስ አበባ ብቻ ተጉዞ ይሸጥ እንደነበር አስታውሶ አሁን ግን ምርቶቹ በመላው ኢትዮጵያ መዳረስ አለባቸው በሚል ጥናት በማድረግ የማከፋፈል ሥራ በመጀመር አርሲ ላይ የሚመረተውን በቀጥታ ወደ ሁመራና መተማ እንዲሁም ሻሸመኔ አካባቢ የሚመረተውን ደግሞ ወደ ሀረር፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ በማራዘም ነግዷል። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልም እንዲሁ መቀሌ፣ ጎንደርና ባህርዳርን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ማለት በሚቻል መልኩ አትክልቶችን የማከፋፈል ሥራ ሰርቷል።
በአካባቢው የሚመረቱት አትክልቶች በአብዛኛው ገበያ አጥተው ሲበላሽ መመልከቱን መነሻ በማድረግ ወደ ንግዱ ያዘነበለው አቢታ፤ በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው ገበሬው በተሻለ ጥራት አምርቶ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆንና ይታይ የነበረውን የገበያ እጥረት ለመቅረፍ ከዛም ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ነው። በመሆኑም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር በመፍጠር አትክልቶችን በሚፈልጉት መጠን የማቅረብ ሥራን በስፋት መስራት ችሏል።
የገበሬውን ችግር ልፋትና ድካም ጠንቅቆ የሚረዳው አቢታ፤ ወደ ሥራው ለመግባት ምንም አይነት ችግር አልገጠመውም። እንዲያውም ከአርሶ አደር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥሮ ገበሬው ያመረተውን ምርት ከማሳው ላይ አንስቶ በመሸጥ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በፈጠረው የገበያ ትስስር የጋራ ተጠቃሚ ሆኗል። አርሶ አደሩም በተፈጠረለት ምቹ የገበያ ትስስር በመነሳሳት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግና የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ተነሳሽነትን ፈጥሮለታል። በተለይም ምርጥ ዘርን ጨምሮ የተለያዩ አቅርቦቶችን ለገበሬው በማድረስ የገበሬውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ችሏል።
በብዙ ልፋትና ጥረት ከሚታወቀው አርሶ አደር መሀል በመገኘቱ በርካታ ሥራዎችን ቀንና ሌሎት ሳይል ይሰራል። ጠቃሚ መስሎ የታየውን እና ክፍተት አለ ብሎ ባመነበት ዘርፍ ሁሉ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ይንቀሳቀሳል። በመሆኑም ከአትክልቱ በተጨማሪ እህል ገዝቶ የመሸጥ ሥራም ይሠራል። ለአብነትም ሄኒከን ቢራ ለተሰኘው ካምፓኒ የቢራ ገብስ ከገበሬው ገዝቶ ያቀርባል። ካምፓኒው የተሻለ የምርት መጠን ከጥራት ጋር ማግኘት እንዲችል ከካምፓኒው ጋር በጋራ በመሆን በአርሲ ዙሪያ ለሚገኙ ገበሬዎች ምርጥ ዘርን በማቅረብ አራብቶ እንዲጠቀም ይደግፋል፤ የመድሃት አቅርቦትና ሌሎችንም ድጋፎች በማድረግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
ከአርሶ አደሩ ጋር ባለው ጥብቅ ቁርኝት ንግዱን ማሳለጥና ስኬታማ መሆን ችሏል። በአሁኑ ወቅት አሰላ ከተማ ላይ አቢታ ቁጥር አንድ፣ ሁለትና ሶስት የተሰኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት ሆቴሎችን አስገንብቶ ለስራ አብቅቷል ። ብዙዎች ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ያላቸውን ፍላጎት በመረዳትም በቅርቡም ወደ ትምህርት ሥራ በመግባት ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥራት ያለውን ትምህርት መስጠት የሚችል ተወዳዳሪ የግል ትምህርት ቤት እያስገነባ ይገኛል ።
ከዚህ በተጨማሪም ነብሱ አብዝታ የምታደላው ለግብርናው ነውና በደቡብ ክልል ስልጤ ውልባረክ ወረዳ ሰፊ የመስኖ እርሻ እያለማ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በ10 ሄክታር ቦታ ላይ ብርቱካንና ማንጎን አልምቷል። እንዲሁም መንግሥት ትኩረት በሰጠበት መስክ በመሰማራት በ70 ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የሚለማ የበጋ ስንዴን ዘርቶ የምርት ውጤቱን እየተጠባበቀ ነው። አቢታ፤ በቀጣይም ክፍተት ባለባቸው ዘርፎች ሁሉ በመሰማራት በተለይም ባልተነኩ ዘርፎች ላይ በመሰማራት የወጪ ንግዱን መቀላቀል አሁናዊ ፍላጎቱ መሆኑን ይናገራል።
ይህን ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ ታድያ የቀርከሃ ምርትን ቀዳሚ አድርጓል። ቀርከሃ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት የሚገኝ ቢሆንም በተገቢው መንገድ እየተጠቀምንበት እንዳልሆነ የሚያምነው አቢታ፤ ለሥራ ወደ ዱባይ ባቀናበት ወቅት ቀርከሃ በርካታ ነገሮችን ሆኖ በማየቱ ተገርሞ ዘርፉን ለመቀላቀል አሰበ። በዚህ ጊዜ ታድያ በአገር ውስጥ የሚባክነው ቀርከሃ ወደዚህ ቢመጣ አገር ትጠቀማለች ብሎ በማሰብ ገበያ አፈላልጎ ጥሬ ሃብቱን ወደ ዱባይ ለመላክ ከአንድ ኩባንያ ጋር ስምምነት ፈጽሟል። በአሁኑ ወቅትም አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን ሁሉ አልፎ ቀርከሃን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ሂደት ውስጥ ይገኛል። ይህም አገሪቷ ላለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዱ መፍትሔ እንደሚሆን ይታመናል።
በቀጣይም የተለያዩ ምርቶችን ከቀርከሃ የማምረት ዕቅድ አለው። በተለየ ሁኔታ ለግብርናው ዘርፍ ቢያደላም በትራንስፖርት ዘርፍም የጎላ ተሳትፎ ያደርጋል። በተለይም ከገበሬው የሚገዛቸውን ምርቶች በሙሉ ከማሳው ላይ የሚያነሳው በግሉ ተሽከርካሪዎች ሲሆን ተሽከርካሪዎቹ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም የጭነት አገልግሎት በመስጠት ገቢውን ማሳደግና የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
በተለያዩ ቢዝነሶች ውስጥ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆን የቻለው ስኬታማው እንግዳችን ፤ በአሁኑ ወቅት የበጋ ስንዴ በስፋት እየተሰራ መሆኑ በአትክልት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ መኖሩን ይጠቅሳል። ማህበረሰቡን ግን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርገው የበጋ ስንዴ መሆኑን ይናገራል። በርካታ ያልተሰራባቸውና ውሃ ባላቸው አካባቢዎች ላይ በበጋም ሆነ በክረምት የግብርና ሥራን በሰፊው መሥራት ከተቻለ ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ በብዙ ዘርፈ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል የሚለው አቢታ፤ ይሁንና ለግብርና ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በእጅጉ አናሳ በመሆኑ ይሄ መሻሻል እንዳለበት ይናገራል።
በእርሻ ሥራ ተሰማርቶ ለሥራ ማስኬጃ ብድር ከሚጠይቀው ይልቅ ለህንጻ ሥራ ብድር የሚጠይቀውን የሚያስቀድሙት ባንኮች ቅድሚያ ለግብርናው ዘርፍ በመስጠት ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎች እንዲሰሩ ቢደረግ መልካም መሆኑን ሳይጠቅስ አላለፈም። ሰፊውን የግብርና ሥራ መስራት ከተቻለ ሌላውን ማግኘት ቀላል እንደሆነም ያምናል። ስለዚህ ወጣቱ ወደ ከተማ መፍለሱን ገታ በማድረግ በግብርናው ዘርፍ ቢሰማራ እሱም ተጠቅሞ አገርን መጥቀም እንደሚችል ነው አጽንኦት ሰጥቶ የተናገረው ።
አዋጭ ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የሚሰማራው አቢታ፤ በተሰማራባቸው የግብርና፣ የሆቴልና የትራንስፖርት ዘርፍ ከ300 ለሚልቁ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከፈጠራቸው የሥራ ዕድሎች መካከልም 10 የሚደርሱት ከጎዳና አንስቶ መንጃ ፈቃድ በማውጣትና የተለያዩ የሙያ ትምህርትን በማስተማር ብቁ ያደረጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም አቢታ በርካታ አበርክቶዎችን ለአገሩ እያደረገ ይገኛል። ለአብነትም አሰላ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አደባባይ ላይ ባህልን የሚያስተዋውቅ የከተማው ድምቀት የሆነ የአርሲ ባህላዊ ምግብ ጭኮ ወይም ገንፎ ማቅረቢያ ጮጮ አሰርቷል። እንዲሁም የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤት አሰርቶ ለመንግሥት ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ለተለያዩ አገራዊ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።
‹‹ሰርቶ ከማግኘት የበለጠ ለተቸገሩት መድረስ፣ ማገዝና መርዳት ትልቅ እርካታን ይሰጣል›› የሚለው አቢታ፤ ሁሌም ቢሆን በሥራ የሚያምን ለሥራ የተፈጠረ በመሆኑ ዛሬም ድረስ በግብርና ሕይወት ውስጥ ሆኖ ቢቆፍር፣ ቢያርስና ቢጎለጉል እርካታን አያገኝም። ሁሌም መስራትና ባለው አቅም ሁሉ ደግሞ የደከሙትን ማበርታት፣ አቅም ላጡት አቅም በመሆን የተቸገረን መርዳት ያስደስተዋል።
ጠንካራ የሥራ ባህልን ውርስ ያደረገው አቢታ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለሥራ ባለው ትልቅ ክብር ሰርቶ የተለወጠውና ከራሱ አልፎ ለብዙዎች መትረፍ የቻለ ብርቱ ወጣት ነው። ከልጅነት ጀምሮ ንግድና ግብርናን አጣምሮና አጠናክሮ በመጓዙ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት መቻሉን ይናገራል። በቀጣይም የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት ከአገር ውስጥ አልፎ በአፍሪካ ተደራሽ በመሆን የውጭ ገበያውን ለመቀላቀል አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በመጨረሻም ‹‹ወጣቱ ሰፊ ዕድል ባለው የግብርና ዘርፍ ቢሰማራ ከራሱ አልፎ ማህበረሰቡን እንዲሁም አገርን መለወጥ ይችላል›› ብሎ ለወጣቱ ባስተላለፈው መልዕክት ሃሳቡን አጠቃለልን፤ ሰላም!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም