
የከሰል ድንጋይ እንደ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላሉ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አማራጭ ሆኖ በማገልገል ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ይታወቃል።
የምርት አቅርቦቱ በሀገር ውስጥ ሲሸፈን ደግሞ ለግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ ያድናል። የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ደግሞ ለውጪ ገበያ በማቅረብ ገቢ በማስገኘት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲገኝ ያስችላል።
ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር በሚይዘው የሰው ኃይልም የሥራ አጥነት ጫናን ይቀንሳል።እንዲህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኘው የድንጋይ ከሰል ሀብት ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲቃኝ ሀብቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ በኦሮሚያ፣በአማራ፣በቤኒሻንጉል፣በደቡብ ክልሎች በስፋት መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሀብቱ በተወሰነ ደረጃ ጥቅም ላይ ቢውልም በአብዛኛው ግን በግዥ ከውጭ ሀገር በሚገባው የድንጋይ ከሰል ነው አምራች ኢንዱስትሪዎቹ በመጠቀም ላይ የሚገኙት። ይህ የሚያሳየው ሀብቱን ለማልማት የሚያስችል ቴክኖሎጂ በማሟላትና በዘርፉም የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ማፍራት ካልተቻለ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነው።
ግብአቱ በስፋት ከውጭ ገብቶ ጥቅም ላይ ለመዋሉ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ በባህላዊ የአመራረት ዘዴ መከናወኑ ነው። ይህ ደግሞ ሙቀት የማመንጨት የኃይል ጥራቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። አመራረቱ አለመዘመኑና ለዘርፉ የተሰጠውም ትኩረት አናሳ መሆን የከሰል ድንጋይ ምርትን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት ሳይቻል ቆይቷል።እንዲህ ያለው አካሄድ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ወጪ እያስወጣት ይገኛል።
የሀገር ውስጥ ሀብትን በማልማት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ካልተቻለ ሀብቱ ጥቅም ላይ ሳይውል መቅረቱ ብቻ ሳይሆን ፣ አሁን ሀገሪቱ በጦርነትና በተለያየ ምክንያት እያጋጠማት ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የአቅርቦት ፍላጎት የማታሟላበት ደረጃ ላይ ልትደርስ የምትችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
ሀብቱን በማልማት በሀገር ውስጥ ለመተካት በተለያየ ጊዜ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ሀብቱን አልምቶ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ የሚችል ፋብሪካ አለመኖሩ በቁጭት ይነሳል። የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ በአጠቃላይ የማዕድን ዘርፉን ለማሻሻል ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ኢኮኖሚውን እንደሚያነቃቃ ተስፋ አሳድሯል።
በቁጭት ይነሳ የነበረው የከሰል ድንጋይ ፋብሪካ የማቋቋሙ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በመልካም ጅምር የተወሰደው ፋብሪካ የማቋቋም ስራ ሀብቱ በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች መሆኑ ደግሞ ውጤታማነቱን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ሆኗል። የከሰል ድንጋይ ፋብሪካ ለማቋቋም የመሠረት ድንጋይ ከተጣለባቸውና ከፍተኛ የሀብቱ መገኛ ከሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች በደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ይጠቀሳል።
ፋብሪካዎቹ ተገንብተው ወደ ማምረት ተግባር ሲሸጋገሩ ሀገራዊ የማምረት አቅም በመፍጠር በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ለውጥ ያስመዘግባል። ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በጉራጌ ዞን ‹‹ሰን ማይኒግ›› በተባለ ኩባንያ የሚገነባው የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ ፤ ግንባታው ተጠናቅቆ ማምረት ሲጀምር በወር ስምንት መቶ ሺ ቶን የከሰል ድንጋይ የማምረት አቅም ይፈጥራል።
በዚህ ሚናውም የውጭ ምንዛሪን በማዳን የበኩሉን ድርሻ ይወጣል። ከአንድ ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። የፋብሪካ ግንባታው የሚገኝበትን ደረጃና የዞኑን የከሰል ድንጋይ ሀብት በተመለከተ የጉራጌ ዞን ውሃ መስኖና ማእድን ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ዳምጠውን አነጋግረናቸዋል።
እንደ አቶ ፍሰሀ ማብራሪያ ፤ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተብሎ ከተያዘው ዘርፍ አንዱ የማእድን ልማት ሲሆን ፣ ዞኑም የተቀመጠውን የልማት አቅጣጫ በማሳካት ረገድ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በአካባቢው የሚገኝ የማእድን ሀብትን ከመለየት ጀምሮ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በማመቻቸት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። በተለይም ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ዞኑ ከዲላ ፣ ሀዋሳና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ስላለው የማዕድን ሀብት ጥናት ሀብቱን ለመለየት ችሏል።
የጥናቱ ግኝትም በስምጥ ሸለቆ ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙ ሶዶ፣ ደቡብ ሶዶ፣በከፊል መስቃን እንዲሁም በጊቤ ተፋሰስ አብሽጌና እነሞር ወረዳዎች የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለተለያየ ጌጣጌጥ የሚውሉ የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች መኖራቸው ተረጋግጧል። እንደ አሸዋ ፣ ነጭና ጥቁር ድንጋይ ያሉ ለግንባታ ሥራ የሚውሉ ማዕድናት በስፋት መኖራቸውም ተለይቷል። የግንባታ ማእድናቱ ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፣ ወጣቶች ተደራጅተው በመሥራት የኢኮኖሚ አቅም እየፈጠሩበት ይገኛል።
በጥናት ተለይቶ ይፋ የሆነውን የማእድን ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል የአካባቢውንም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ድርሻ ለማበርከት በሚደረገው እንቅስቃሴ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያና ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ከጥቂት ወራት በፊት በዞኑ አበሽጌ ወረዳ ጊቤ ቀበሌ ውስጥ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል።
በአሁኑ ጊዜም የማሽን ተከላ ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት አከናውነዋል። ፋብሪካው የሚያርፍበት መሬት የአፈር ጥናት ምርመራ ሥራም ተጠናቅቋል።
የአፈር ምርመራው የተከናወነው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኝ ታዋቂ ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት ሲሆን፣ የግንባታ ሥራውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው እቅድ የተያዘው።
በአሁኑ ጊዜ እንደሀገር ያጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የግንባታ ቁሳቁስ ግብአት ዋጋ መናር በተወሰነ ደረጃ የግንባታ ጊዜውን ሊያራዝመው እንደሚችልና ቀድሞ የተያዘለት የግንባታ ወጪ ወይንም ኢንቨስትመንት መጠነኛም ቢሆን ለውጥ እንደሚኖረው ይጠበቃል ።
ፋብሪካው መቋቋሙ ስለሚኖረው ፋይዳና ለአካባቢው ማህበረሰብ ስላሳደረው ተስፋ አቶ ፍሰሐ እንዳስረዱት ፤ ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታ ለመፍታት ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ግብአቱ በሀገር ውስጥ መመረቱ መንግሥት ከውጭ በግዥ ለማስገባት የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪም ያድናል ።
እንደ ሀገር ከሚያስገኘው ጠቀሜታ በተጨማሪ የዞኑን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ጉልህ ሚና አለው ። የፋብሪካው መሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በቁጥር በዛ ያሉ ባለሀብቶች በአካባቢው በማዕድን ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ ።
አሁን ግንባታውን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ካለው ኩባንያ በተጨማሪ አንድ ሁለት ኩባንያዎች በድንጋይ ከሰል ላይ ምርምር ማድረግ ጀምረዋል። በሌሎች የማእድን ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍቃድ የወሰዱም ይገኛሉ። ተስፋ ሰጭ የሆኑ ጅምሮች እየታዩ ናቸው።
የፋብሪካው መኖር እያስገኘ ያለውን ዕድል ለመጠቀም በዞኑ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ፣ እድሉን ለመጠቀም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ፋይዳው ከፍ ያለ ሲሆን፣ በትንሹ ለአንድ ሺ 500 ዜጎች ሥራ ይፈጥራል።
እንዲህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለሚያስገኘው ፋብሪካ ዞኑ ስላመቻቸው ነገር አቶ ፍሰሐ እንደገለጹት ፤ ዞኑ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የሚያሳይ ባለሀብት እራሱን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ፣ አልፎም ሀገርን ይጠቅማል የሚል እሳቤ በመያዝ ነው ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኙት።
ይህን አስተሳሰብ መሠረት በማድረግም የተለያዩ የአሰራር የማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደዋል።ክፍተቶች እየታዩም እርምጃዎቹ ይቀጥላሉ ። በዚሁ መሠረትም ዞኑ ባካሄደው የቅድመ አዋጭነት ጥናት ለግንባታ የሚውል መሬት ለይቶና ነፃ አድርጎ በማመቻቸት፣ያለውን የማዕድን ሀብትና መገኛ ስፍራ በማመላከት፣ባለሀብቱ የሚፈልጋቸውን መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኝ ከማድረግ ጀምሮ የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርአት በመዘርጋት ባለሀብቱ በአካባቢው መዋዕለ ነዋዩን እንዲያፈስ፣ ዞኑ ደግሞ አስፈላጊውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የጋራ የሆነ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት በማድረግ የቻለውን እያደረገ ይገኛል።
አካባቢው በልማት የተጎዳና ሥራ የሌላቸው ወጣቶችም በመኖራቸው ኢንቨስተሮችን ወደ አካባቢው ለመሳብ በዞኑ በኩል ያለው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነም አቶ ፍሰሐ ይናገራሉ ።
በዞኑ የከሰል ድንጋይ ማጠቢያና ማምረቻ ፋብሪካ እስከ ማቋቋም ደረጃ መድረሱ አካባቢው ያለውን እምቅ ሀብት ያሳያል። በዚህ ላይ አቶ ፍሰሐ እንደገለጹት፤ በቂ የሆነ ሀብት ስለመኖሩ ዞኑ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥናት ለማረጋገጥ ካደረገው ጥረት በተጨማሪ ፋብሪካውን የሚያስገነባው ኩባንያም በራሱ በቂ የሆነ ሀብት መኖሩን በጥናት በማረጋገጥ ነው የግንባታ ስምምነት ውል ተፈራርሞ ወደ ግንባታ ሥራው የገባው።
“ዞኑ በማእድን ዘርፍ እንዲህ እምቅ ሀብት እያለው ግን ጥቅም ላይ ሳይውል ገና አሁን እንቅስቃሴ መጀመሩ ምክንያቶቹ ምን ይሆኑ?” አቶ ፍሰሐ ለዚህ በሰጡት ምላሽ፤ ዋናው ሀብቱ ጥቅም ይሰጣል ብሎ ያለመገንዘብ ችግር ነው።
ግንዛቤ ባለመኖሩ ሀብቱን ለይቶና አደራጅቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ሥራ አልተሰራም። አሁን ግን እንደ ሀገር ንቅናቄ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ ዞኑም እድሉን ማግኘት ችሏል።
ከዚህ በኋላ በእድሉ መጠቀም የዞኑ ተግባር ይሆናል። ዘርፉ በእውቀት መመራት ስላለበት በዞኑ ውስጥ ከሚገኘው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። የአስፈጻሚውን አቅም በማጠናከርና የሰው ኃይልንም በማሟላት በኩልም ሥራዎችን በመስራት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረቶች ይጠናከራሉ።
እንዲህ እራስን በማዘጋጀት በዞኑ ከሚገኘው የድንጋይ ከሰል ሀብት በተጨማሪ ኬላ በሚባለው ስፍራ ለብርጭቆ ፋብሪካ ግብአት የሚውል፣ አበሽጌ፣ሶዶ፣ ኢነሞር አካባቢዎች ደግሞ ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ ማዕድናት ስለሚገኙ እነዚህንም ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል። የሀገር ጥሪ ተቀብለው ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር የገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመጋበዝ በዘርፉ እንዲሰማሩም ዞኑ በያዘው እቅድ መሰረት እንደሚሰራም ይገልፃሉ።
እቅድ በመንደፍ የሚደረግ እንቅስቃሴና አካባቢ ላይ የተፈጠረን እድል መጠቀም ከወቅታዊነት ያለፈ የማይሆንበት አጋጣሚ የበዛ በመሆኑ ዘላቂ ማድረግ ላይ ስላለው ነገር ሲነገሩም፤ ‹‹እኔ ከምመራው ተቋም ጀምሮ ከላይ እስከታች ያለው አመራር ቁርጠኛ ሆኖ በመምራት፣የአካባቢው ማህበረሰብም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆኑን እንዲገነዘበው በማድረግ ረገድ ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ›› ብለዋል። ማዕድን ሚኒስቴር በቅርቡ ለስምንት ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል ምርት ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።
ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ከሚገኙ ክምችቶች የከሰል ድንጋይ ማዕድንን አዋጭ በሆነ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ በማምረት እና በማበልጸግ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ለማቅረብ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ያሟሉ በመሆናቸው ነው።
ኢቲ የማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር እና ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስ ኩባንያዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ ሰን ማይንኒግና ትሬዲንግ ፒ ኤል ሲ ኩባንያ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ኦሮሚያ ማይኒንግ አክሲዮን ማኅበር፣ ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን እና ሪያልማይን ትሬዲንግ ፒ ኤል ሲ ኩባንያዎች በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ሻቃና ልጆቹ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ኤልኔት ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርት ፈቃድ ወስደዋል። ኩባንያዎቹ ስድስት ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል አስመዝግበዋል።
የድንጋይ ከሰል ፕሮጀክት በዘርፉ ከሚከናወኑ አጠቃላይ የማዕድን ዘርፉን የማልማት፣ የማዕድናትን ሀገራዊ ምርት የማሳደግ፣ በዘርፉ ሰፊ የስራ ዕድል የመፍጠር፣ አምራች ሀገራዊ ባለሀብቱን በማበረታታት በዘርፉ ዕሴት እንዲጨምሩ፣ ወጣቶች ከባለሀብቶች ጋር በመስራት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥራል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014