“ጥምቀትን በጎንደር” ለማክበር መሄድ እየፈለጉ ነገር ግን በስጋትና በጥርጣሬ ሳይታደሙ የቀሩ ሰዎች በዓሉ በሰላምና በድምቀት ተከብሮ ካለፈ በኋላ እንደሚቆጩ እገምታለሁ።በእርግጥ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት የከፈተው አሸባሪው የሕወሓት (ትህነግ) ቡድን የፈጠረው ተጽእኖ ፍርሀት ማሳደሩ አይቀርም። ግን ደግሞ ተጽዕኖው ከፕሮፓጋንዳ አላለፈም።
የኃይማኖት አባቶችም ሆኑ የእምነቱ ተከታዮች እንደሚሉት “ጥምቀት የሰላም ምልክት ጭምር” በመሆኑ ነው ታዳሚው ያለስጋት በዓሉን ማክበር የቻለው። በጎንደር የተከበረው ጥምቀት ከመንፈሳዊነቱ በተጨማሪ ባህላዊና ህዝባዊ በመሆኑ የክርስትና እምነት ተከታይ ያልሆኑትንም የሚያሳትፍ በዓል መሆኑ ጭምር ነው የተለየ የሚያደርገው።
በበዓሉ የታደመው የህዝብ ብዛት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደር የሰጠው የማጓጓዝ አገልግሎት ብቻ መመልከት በቂ ምስክር ነው። በህዝብ ትራንስፖርትና በግል ተሸከርካሪ በመጠቀም በዓሉን ለመታደም ቀድሞ የገባው እንግዳ ከጎንደር ሆቴል ቤቶች አገልግሎት በላይ ነበር።
‹‹ቤት የእግዚአብሄር ነው›› ያሉ የከተማው ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነታቸውን ያስመሰከሩበትም ጭምር ነበር። የአንድ ሳንቲም ገጽታ የሆነው ጎንደርና ጥምቀት እንደወትሮው ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በደማቅ ሥነሥርአት ነበር የተከበረው።
ከኃይማኖታዊ ሥርአቱ ውጭ የነበረው መንፈስም እንዲሁ ቀልብን የሚስብ ማራኪ ነበር። ከከተራው ቀን ጀምሮ ታዳሚው የተዋበባቸው የባህል አልባሳት ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ፣ ባንዲራዋንም ከፍ የሚያደርግ፣ ‹‹ለወዳጅም ለጠላትም ደስ ይበለው›› የሚያስብል ስሜት የፈጠረ በአካባቢው ሰላም መኖሩን ያረጋገጠ ነበር።
አጠቃላይ የነበረው ድባብ በአሸባሪው ቡድን ፀብ አጫሪነት ለአንድ አመት የዘለቀው ጦርነት ያደረሰውን ጉዳት ያስረሳ እንደነበር ከበዓሉ ታዳሚና ከአካባቢው ነዋሪ ስሜት መረዳት ይቻላል።
ያነጋገርኳቸው ታዳሚዎች ፍጹም ደስታ ውስጥ ሆነው ነበር ሀሳባቸውን ያካፈሉኝ። በብዙዎችም ገጽታ ላይ ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ነበር የሚነበበው። የመጣው ቢመጣ በዓሉን ከማድመቅ ወደኋላ አንልም የሚሉ ይመስላሉ። ቅድሚያ ለእንግዳ እንደሚባለው ቅድሚያ ሰጥቼ ያነጋገርኳቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን የአንድ ሚሊየን ዲያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ ተቀብለው አገራቸው ከገቡትና ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሥፍራው የተገኙትን ጭምር ነው።
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዓለምጤና ከተማ ነዋሪ መሆኑን የነገረኝ ወጣት ብርሃኑ ሻንቆ ጥምቀትን በጎንደር ተገኝቶ ሲያከብር የመጀመሪያው ነው። በተለይም ደግሞ አሸባሪው የትህነግ ቡድን አካባቢው ላይ ትልቅ ተጽእኖ በፈጠረበት በዚህ ወቅት መገኘቱ ልዩ ስሜት ፈጥሮበታል።
ከኃይማኖታዊ ሥርዓቱ በተጨማሪ ታዳሚው በአልባሳቱ ለአገሩ ያለውን ፍቅርና ስሜት የገለጸበት መንገድ አስደስቶታል። እርሱ እንዳለው በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የተሰሩ የአገር ባህልና የተለያዩ አልባሳት ነበሩ የጎሉት። ኢትዮጵየዊነት እንደሚያሸንፍም ያረጋገጠበት እንደሆነ ሀሳቡን ሰጥቷል።
በጎንደር አካባቢ በሚዘወተረው የባህል አልባሳት ደምቃ በጥምቀተ ባህሩ ያገኘኋት በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መሆኗን የነገረችኝ ወጣት ሜሮን አፈወርቅ ከበዓሉ ሁለት ቀን ቀድማ ነው በጎንደር ከተማ የገባቸው። እንደፈለገችውና እንዳሰበችው በደስታ በማሳለፍ ላይ እንደነበረች ነው በወቅቱ የነገረችኝ። ‹‹መከላከያ ሰራዊታችን ሰላም አስፍኖልን በዓል እንድናከብር ስላደረገን እናመሰግናለን።
ያለስጋት በጎንደር የተገኘሁትም። በፀጥታው እርግጠኛ ስለሆንኩ ነው። በአካልም ተገኝቼ አረጋግጫለሁ›› በማለት ነግራኛለች። ከአውስትራሊያ ከአምስት አመት ቆይታ በኋላ አገራቸው ያቀረበችላቸውን ጥሪ ተቀብለው መምጣታቸውን የነገሩኝ አቶ ደሳለኝ ጥጋቡ እንዳጫወቱኝ፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ለሁለት ጉዳይ ነው የመጡት። በአንድ በኩል ይመኙት በነበረው በጎንደር ጥምቀት ላይ ለመታደም ሲሆን፣ ዋናው የመጡበት ጉዳይ ግን አሸባሪው
ቡድን የኢትዮጵያን ድንቅ ኃማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያለውን የጥምቀት በዓል ለማደብዘዝና ኢትዮጵያ የምትባል አገርም እንዳትኖር ጦር ሰብቆ የተነሳው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ያደረሰውን ጉዳት ለመቃወምና ከህዝባቸው ጋር መሆናቸውን፣ ጥምቀትን በጎንደር መገኘታቸውም ቡድኑ ስጋት በመፍጠር በበዓሉ ላይ ታዳሚ እንዳይኖር ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ለማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል።
በጎንደር በነበራቸው ቆይታም ሆነ ከተራውና ጥምቀቱ ሰላማዊ ሆኖ ማለፉንና ያጋጠማቸው ችግር አለመኖሩንም ነው የገለጹት። ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ መኖሩና በዓሉም በደመቀ ሁኔታ መከበሩ ቢያስደስታቸውም፣ ከበዓል በኋላም ያለው ሰላም የበለጠ ተረጋግጦ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በአካባቢው እንዲኖር ተመኝተዋል።
በተለይ ደግሞ ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሆነ በአጭር ጊዜ ቆይታቸው ተገንዝበዋል።
ኢኮኖሚው የሚያስከትለው ችግር ከጦርነቱ ያልተናነሰ ስለሚሆን መንግሥትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ መረዳታቸውንም ተናግረዋል። እርሳቸውን ጨምሮ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አገርን የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸውና በየሚኖሩበት አገር ሆነው በገንዘብ፣ በሀሳብና በተለያየ መንገድ ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ ማጠናከር እንዳለባቸውና እርሳቸውም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
የታዘቡትን አግባብ ያልሆነ ግብይትን በተመለከተም በንግዱ ላይ የሚገኙት በዚህ ወቅት ትርፍ ብቻ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሌለባቸውና ዜጋን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይም የበዓላት ወቅት ማትረፊያ ሳይሆን ሁሉም እንደአቅሙ መጠቀም እንዲችል መደረግ እንዳለበትም ሀሳብ ሰጥተዋል። በአሜሪካን አሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ 22 አመታት መቆየታቸውንና ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነው ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ሲመኙት የነበረው ተሳክቶላቸው በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹልኝ ወይዘሮ ዙሪያሽወርቅ እሱባለው፤ በነበረው ጦርነት የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ እንዴት እንዳላሰጋቸው ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ‹‹በአገሬ ውስጥ ሆኜ እንዴት እሰጋለሁ። ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ ነን›› ነበር ምላሻቸው።
ወይዘሮ ዙሪያሽ ከአውሮፕላን ማረፊያው ከተደረገላቸው አቀባበል ጀምሮ የነበረውን ሥርአት አድንቀዋል። ይህም ኃይማኖት፣ ታሪክና ባህልን በጎንደር ለማየት እንዳስቻላቸውም ነግረውናል። ጥምቀት በጎንደር አገር በችግር ውስጥ ሆናም የደመቀ መሆኑ አስደሳች እንደነበር በሥፍራው የተገኘው ሁሉ መስክሯል።
ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ ሰላምን እያረጋገጡ ኢኮኖሚው ላይ እንዴት መበርታት እንደሚቻል በተለይም ከዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚጠበቀውን ወይዘሮ ዙሪያሽወርቅ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ድጋፍና እርዳታው አልተቋረጠም።
አሁን ደግሞ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለን የመግባታችን ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ የፀጥታ ስጋት እንደሆነች ይናፈስ የነበረውን፣ እንዲሁም ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡና ወደ ኢትዮጵያም እንዳይገቡ ይደረግ የነበረው ቅስቀሳ ከንቱ እንደነበር ምስክር ለመሆን ነው የመጡት።
በተግባርም አረጋግጠዋል። በልማቱም ቢሆን በጋራም ሆነ በግል አገራቸው የምትጠብቅባቸውን ለማድረግ ወደኋላ እንደማይሉና በአገራቸው እንደማይደራደሩ ተናግረዋል።
ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም አብዛኞቹ ያነጋገርኳቸው እንዳሚሉት ከሁለት ወር በፊት የነበረው ስጋት ከፍተኛ ነው፤ ግን ደግሞ በዓሉ እንደወትሮው እንደሚከበር እርግጠኞች ነበሩ። ሀሳባቸውን ካካፈሉኝ መካከል በጎንደር ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሁለት ነዋሪ የሆነችው ወጣት የሰሜንወርቅ ሲሳይ እንደተናገረችው፤ በነበረው ጦርነት ፍርሀትና ስጋት ውስጥ ከተለያየ አቅጣጫ ሰው እንደቀደመው ሁሉ በበዓሉ ላይ ተገኝቶ በማክበሩ ተደስታለች።
በጦርነቱ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ይሰሩ ከነበረበት የመንግሥት ሥራ ለቀናት ቤታቸው ለመቆየት ተገደው እንደነበር ያስታወሱት በከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው በረከት፤በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ወደ ሥራቸው ተመልሰው የጥምቀት በዓልንም ማክበር መቻላቸው ስሜታቸው ከሌላው የተለየ እንደሆነ ነው የነገሩኝ።
የዘንድሮው ጥምቀት በጎንደር ዘርፈ ብዙ ትርጉም እንዳለው የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰመስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ናቸው። አጠቃላይ የክልሉ ሰላም እየተረጋገጠ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቱሪዝም ከተማዋን እያነቃቃ፣ የሥራ እድልም እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ነው የገለጹት። ጎንደር እንደቀደመው ሁሉ ደምቃ እንግዶችዋን ተቀብላ በዓሉ መከበሩ ከማስደሰትም በላይ የሆነ ስሜት እንዳለው ተናግረዋል። እንደአገር ከገጠመው ጦርነት የተገኘው አንፃራዊ ሰላም በተጨማሪ ዘመናዊ ኢትዮጵያን የመሰረተው፣የቴክኖሎጂ ልማትን በማምጣትና ፍላጎትን በማንፀባረቅ የብዙ ተምሳሌት የሆነው፣ በቅርቡ ከእንግሊዝ አገር የተመለሰው የአፄቴዎድሮስ ሹሩባ (ቁንዳላ) በኤግዚቢሽን ለህዝብ እይታ መቅረቡ ሌላው የበዓሉ ድምቀት መሆኑን ነው የተናገሩት።
በጎንደር ጥንታዊ ቤተክርስቲያኖች፣ አብያተ መንግሥታት፣ ስዕሎች መኖራቸውን ያስታወሱት ዶክተር ይልቃል፤ እነዚህ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ግብአት የሆኑት ሀብቶች በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከተፈለገ፣ ሰላምን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ቱሪስቱ ለደህንነቱ ሳይሰጋ በነዚህ ሀብቶች ተደስቶ እንዲመለስ ጎንደር ከተማ ተኩስ የማይሰማባት የሰላም ከተማ እንድትሆን ከአካባቢው ነዋሪ ጀምሮ የሚቻለው ሁሉ እየተደረገ ነው። ይሄ ጥረት ለውጤት በቅቶ የታሰበው ሰላም እንደሚረጋገጥም ዶክተር ይልቃል ተስፋቸውን ይገልጻሉ።
ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱና ቀዳሚው የአካባቢ ሰላም እንዲጠበቅና የዜጎች ደህንነት እንዲከበር ማድረግ እንደሆነ፣የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት እንዲቀጥልና ኢኮኖሚውም እንዲያድግ የክልሉ መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው።
አሸባሪው ትህነግ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከፈተው ጦርነት ከፍተኛ በሚባል ደረጃ በከተሞች ይሰማ እንደነበርና ይህ ጠቃሚ እንዳልሆነ መሳሪያ ከያዙ አካላት ጋር በንግግር ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።
የቱሪዝም ኢንደስትሪው ለምቶ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ከተፈለገ፣ ሰላምን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም የተናገሩት አጽንኦት ሰጥተው ነው።
“ገናን በላልይበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር ማክበር ለዓለም ሰፊ ትርጉም አለው” ያሉት ዶክተር ይልቃል፤ ከሌላው ዓለም ጋር በትብብር መስራት ቢያስፈልግም የውስጥ አቅምን ማጠናከር፤በተለይም በቱሪዝም ኢንደስትሪው ላይ በርብርብ መሰራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ዶክተር ይልቃል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀደም ሲል ፋሲለደስ ባህረ ጥምቀት ተብሎ ይጠራ የነበረው ስያሜ እንዲመለስላት ያቀረበችውን ጥያቄ በበዓሉ ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ለቱሪዝም ኢንደስትሪው አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ይደረጋል ብለዋል።
የጎንደርን የጥምቀት በዓል ደማቅ ካደረጉት አንዱ በፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ ለህዝብ እይታ የቀረበው የአፄቴዎድሮስ ሹሩባ (ቁንዳላ) ነው። በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መንግሥት መካከል በተደረገ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተለያየ ጊዜ ተወስደው ወደ አገር ቤት ከተመለሱት መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የአፄቴዎድሮስ ሹሩባ (ቁንዳላ) ለባለቤቱ ኢትዮጵያ መመለሱ እንጂ ህዝቡ በአካል እንዲያየው የተደረገበት አጋጣሚ አልነበረም።
ቁንዳላቸው በክብር በኢትዮጵያ ባንዲራ ተሸፍኖ ነው ለእይታ የቀረበው። ጎንደር አፄቴዎድሮስ የኖሩባት፣ የነገሱባት በመሆኑ ልዩ ስፍራ እንደሚሰጣቸው በቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ከፍተኛ የትምህርት ክፍል ባለሙያ ከሆኑት አቶ ኃይለየሱስ አባተ ለመረዳት ተችሏል።
በሙዚየሙ ውስጥ ለእይታ የቀረቡት የተለያዩ ቅርሶች ሰፊ ታሪክ የያዙ መሆናቸውንም እንዲሁ ለጎብኝው ገለጻ አድርገዋል። ከከተራ ጀምሮ በጎንደር በዓል ለማክበር የተገኘው ታዳሚ በተከታታይ የሚጎበኛቸው መንፈሳዊና ታሪካዊ እንዲሁም ባህላዊ እሴቶች ከጎንደር ውጭም በአማራ ክልል የበዙ ናቸው።
የበዓሉ ታዳሚ ከጎንደር ታላቁ የዓባይ ግድብ መነሻ ምንጭ በሆነው ሰከላ የግዮን በዓልን ታድሞ በተመሳሳይ መንፈሳዊ ሥርአቱን ተካፍሎ ታሪክን አውቆና ተዝናንቶ ደግሞ በአገው የፈረሰኞች ማህበር በየአመቱ ጥር 23 ቀን የሚካሄደውን በዓል በመታደም በፈረስ ጉግስ ወይንም ግልቢያ አስደናቂ ትርኢት የማየት እድሉን ያገኛል። የዘንገና ሐይቅም ሌላው መስህብ በመሆኑ ቆይታን ያማረ ያደርጋል።
የሰሜን ኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህብ በማልማት የቱሪስቱን ቆይታ በማራዘም አካባቢንና አገርን ተጠቃሚ ለማድረግ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ዓባይን ተሻግረን በሰሜኑና በምእራቡ የአማራ ክልል ያደረግነው አስደናቂ ቆይታ በልብ ውስጥ ተመዝግቦ የሚቀመጥ አይረሴ ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014