ኢትዮጵያ ለደን ሀብቷ ትኩረት በመስጠት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን ተክላለች፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያደረገች ትገኛለች።
ደን አፈርን ቆንጥጦ ከመያዝ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅና የዱር አራዊት መጠለያ ከመሆን ባለፈ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ከደን የሚገኘውን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስቀጠል ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ለአፍታም ትኩረት ሊነፈገው የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑንም መገንዘብ ተገቢ ነው። ከላይ ከዘረዘርናቸው በተጨማሪ፣ የደን ሀብት ለሥራ እድል ፈጠራ ምንጭ እንደሚሆንም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ነገር ግን እንደ ቀርከሃ ያሉ በአጭር ጊዜ ጥቅም መስጠት የሚችሉ የደን ሀብቶችን በመትከል በእንጨት ቴክኖሎጂ ለተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ በገጠርም በከተማም ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻል የሚያስረዱ ሲሆን፤ የኤሺያን፣ በተለይም የቻይናን ተሞክሮም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። በአገራችን ከፍተኛ የቀርከሃ ሀብት ያለ ቢሆንም ይህንን ሀብት በቴክኖሎጂ ታግዞ የተለያየ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረጉ ሥራ ሲሠራበት አይታይም።
ይህ የሥራ ዘርፍ ትኩረት ቢሰጠው ከገጠር እስከ ከተማ ያሉ ወጣቶችን በገበያ ሰንሰለት በማስተሳሰር አዲስ የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል። በአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይም የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሌሎች አገራትን ተሞክሮ መነሻ አድርገው ቀርከሃን ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
ደንን መትከልና ከደን የሚገኘውን ትሩፋት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ይመክራሉ። ሶዞ አማካሪ ድርጅት የኢትዮ-ስዊዲሽ ጥምረት ያለው ሲሆን ለስድስት ዓመታት ያህል በሥራ እድል ፈጠራና የተለያዩ የማማከር ሥራዎችን ሠርቷል። አሁንም በደን ሀብት እንክብካቤና አጠቃቀም ዘርፍ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ የአሰልጣኞች ስልጠናም ይሰጣል።
የድርጅቱ ጀነራል ማናጀር ወይዘሮ አሜን ሁልትስሮም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ድርጅታቸው ትኩረቱን በፕሮጀክቶች ትግበራና በእውቀት ሽግግር ላይ አድርጎ፤ በተለይም፣ ወጣቶች የደን ሀብታቸውን እንዴት መንከባከብ እንደሚገባቸውና እንዴት ለሥራ እድል ፈጠራ መጠቀም እንዳለባቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ ስልጠና ማድረጋቸውን ተናግረዋል። እንደ ጀነራል ማናጀሯ ገለጻ ሶዞ አማካሪ ድርጅት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረቱን በደን በተለይም በቀርከሃ ላይ አድርጎ እየሠራ ነው።
በአፍሪካ ከሚገኘው የቀርከሃ ምርት ሰባ በመቶ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት ማናጀሯ ኢትዮጵያ ይህን የተፈጥሮ ሀብት ለሥራ እድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ምንጭነት መጠቀም የሚያስችል ትልቅ አቅም አላት ብለዋል። ይሁንና ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አለመሆኗን ገልጸዋል።
ጀነራል ማናጀር ሶዛ በኢትዮጵያ የቀርከሃ ደን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከሲውዲሽ አጋሮች ጋር በመተባበር እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ስዊድን የተሰነጠቀ እንጨት በማቅረብና ከዛፎች ወረቀት በማምረት የካበተ ልምድ አላት ያሉት ማናጀሯ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በዓመት ከአስራ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአገራቸው ገቢ ያስገባሉ ብለዋል።
እንደዚያም ሆኖ ጥቅም ላይ የሚያውሉትን ዛፍ መልሰው እየተከሉ የአገራቸውን መሬት ሰባ በመቶ በደን እንደሸፈኑና እንዲያውም በመቶ ዓመት ውስጥ የደን ሀብታቸውን በእጥፍ ማሳደጋቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያም ይህንን ተሞክሮ ለማስፋፋት FREP (forest Restoration Enterpreneur program) በሚል ስያሜ የተቋቋመው ድርጅታቸው ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስልጠና እያደረገ ነው። FREP ዛፍን መትከል፣ መንከባከብና ጥቅም ላይ ማዋል የሚል መርህን ይከተላል። የደን ሀብት በአግባቡ ከተሠራበት ልክ እንደ ማዕድን የአንድን አገር ኢኮኖሚ የማሳደግ
አቅም እንዳለው FREP ያምናል። የደን ሀብትን ከኢኮኖሚ ጋር ማስተሳሰር፤ ለዚህም በርካታ ዛፎችን በመትከል የደን ሽፋንን ማሳደግ፤ በደን ሀብት የበለጸገች አገር ከተፈጠረች በኋላ በእንጨት ቴክኖሎጂ የረቀቁ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት የዘርፉን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መርሁ ነው። ኢትዮጵያም በዓመት ወደ አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የእንጨት ምርት ከውጭ እንደምታስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አገሪቱ እያደገች በሄደች ቁጥር የእንጨት ምርት ፍላጎቷም እየጨመረ ስለሚሄድ ከወዲሁ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ባለሙያዎች ይናገራሉ። FREP በዘርፉ የሥራ እድል ፈጠራ እንዲኖር በተለይም በገጠርና በከተማ የሚኖሩ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የተዘረጋ መርሃ ግብር ነው። በዚሁ መሠረት የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ስልጠና ይሰጣል። በአሁኑ ሰዓትም ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው የአሰልጣኞች ስልጠና የተለያዩ ዳራ ያላቸውን አሥር ሰዎች አሰልጥኖ አስመርቋል።
ሰልጣኞቹ ያገኙትን እውቀት ለወጣቶች በማጋራት የእውቀት ሽግግር እንዲስፋፋ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ከሰልጣኞቹ አንዳንዶቹ የደን ባለሙያዎች ቢሆኑም ስለሥራ ፈጠራ የጠለቀ እውቀት የሌላቸው፤ የተቀሩት ስለ ሥራ ፈጠራ የሚያውቁ ቢሆኑም በደን ዘርፍ ለመሥራት የሚያስችል ምን ዓይነት እድል እንዳለ የማያውቁ ናቸው።
ሁሉም ሰልጣኞች በዚህ ዘርፍ ላይ ያለውን አቅም ማየት የቻሉበት አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው ማናጀሯ ተናግረዋል። FREP በቋሚነት የኢትዮጵያን የደን ሀብት ለማሳደግ እና ሀብቱ በሥራ እድል ፈጠራ ተካቶ ወጣቶች ኢኮኖሚ የሚያመነጩበት እንዲሆን አልሞ የሚሠራ ድርጅት ነው። ኢትዮጵያ የሌሎች አገራትን ልምድ ብትከተልና በትክክል ሥራ ላይ ብታውለው የደን ሀብቷን አሳድጋ ለዜጎቿም የሥራ እድል መፍጠር ያስችላታል የሚል እምንትን አሳድሯል።
ደኖች ለከሰል፣ ለማገዶ፣ ለቤት መስሪያና የእርሻ ቦታዎችን ለማስፋት ሲባል እየተጨፈጨፉ ጉዳት እያስከተሉ በመሆኑ አርሶ አደሩ ዛፎችን ከመቁረጥ በፊት መትከል እንዳለበት፤ እንደ ቀርከሃ ያሉ ዛፎችን በመትከል ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የገቢ ምንጩን ማሳደግ አለበት ብሎ የሚያምን ተቋም ነው። ዛፎችን በመትከል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት
እንደሚቻል የተረዳ ትውልድ ሁል ጊዜም ዛፎችን እየተከለ ይንከባከባል። ለተያዘው የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ውጤታማነትም አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ኢትዮጵያ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሟ እያደገ በሚሄድ ጊዜ ደኖችን ለማገዶ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ይቀንሳል።
የኃይል አቅርቦትን ተከትሎ ኢንዱስትሪዎች ሊስፋፉ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ከያዘችው የእድገት አቅጣጫ አንጻር ወደፊት ደኖች ከማገዶነት ይልቅ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚፈለጉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ ዛፎችን መትከል መጪውን የኢንዱስትሪ ዘመን በማሰብም የሚደረግ ቅድመ ዝግጅትም ተደርጎ ሊታሰብ ይገባል።
ዛፎችን እየተከሉ በገጠርም በከተማም ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ እድልና የገበያ ትስስር መፍጠር ከአሁኑ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። FREP ከመንግሥት ጋር በመተባበር በተለይም ዓለምአቀፍ የእንጨት ቴክኖሎጂን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ወጣቱ ዘመን ያፈራውን የእንጨት ቴክኖሎጂ እንዲተዋወቅና የሥራ እድል እንዲፈጠርለት ማድረግ ዋና ትኩረቱ ነው። ኢትዮጵያ ለደን ልማት ያላትን አመቺነት ተጠቅማ በርካታ ዛፎችን በመትከል በአንድ በኩል ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ እንደትችል ግንዛቤ የማስጨበጥና የማሰልጠን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሶዞ አማካሪ ድርጅት ጀነራል ማናጀር አሜን ሁልትስትሮም ገልጸዋል።
ድርጅቱ የእንጨት ቴክኖሎጂ ስልጠና ለመስጠት ሲያስብ ለሰልጣኞቹ የመጀመሪያ መስፈርት ያደረገው ፍላጎትን ነው። በዘርፉ ፍላጎት አለን ያሉ ሰዎች መጥተው ሰልጥነዋል። ፍላጎት ያለው ሰው በስልጠናው እራሱን አበልጽጎ የተሻለ ሥራ መስራት ይችላል። ኢትዮጵያ የደን ሀብቷን ማሳደግ የሚያስችል መልክዓ ምድርና የአየር ንብረት አላት። እስከ አሁን የቀርከሃ ሀብቷን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እያዋለች አይደለም።
ሶዞ አማካሪ ድርጅት ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚሠራ እንደመሆኑ የእንጨት ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል እንዲፈጠር አገሪቱም ከዘርፉ ኢኮኖሚ እንድታገኝ የሚሠራ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት መንግሥት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ በርካታ ችግኞችን እየተከለ መሆኑ ሲታሰብ የእንጨት ቴክኖሎጂ አስፈላጊ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
የሚተከሉት ዛፎችየደን ሽፋንን በማሳደግ ከሚያበረክቱት ተፈጥሯዊ አስተዋጽኦ ባሻገር ኢኮኖሚ አመንጪነታቸውን እያሰቡ መትከል እንደሚስፈልግም ጀነራል ማናጀሯ ተናግረዋል። አቶ ወንድማገኝ በቀለ በዓለምአቀፍ የቀርከሃ ልማት ድርጅት ውስጥ የቴክኒክ ባለሙያ ሆነው ይሠራሉ። ሶዞ አማካሪ ድርጅት በሰጠው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ተሳትፈዋል።
ስልጠናው የሙያ ክሂሎትን እንዳሳደገላቸውና በሥራ እድል ፈጠራ በርካታ ወጣቶችን የዚህ እድል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የእንጨት ቴክኖሎጂና እውቀት የቀሰሙ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
ደንን የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ መጀመሪያ አስተማማኝ የደን ሽፋን እንዲኖር ማስቻል፤ ለዚህም እንደ መልክዓ ምድሩና እንደ አየር ንብረቱ ተስማሚነት ችግኞችን መትከል ከሚል የተነሳ ስልጠና ነበር። ስልጠናው በንድፈ ሀሳብ (ቲዮሪ)ና በተግባር የተካሄደ፤ የእንጨት ቴክኖሎጂ አሁን የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳዩ ማሽኖች የታገዘ፤ በኦንላይንም ጭምር ከስዊድን ሙያተኞች በተሰጠው ማብራሪያ ሰልጣኞች መሠረታዊ እውቀት ያገኙበት እንደነበር ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በደን ሀብት የመበልጸግ እድል ላላቸው አገራት እንዲህ ዓይነቱ ስልጠና ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ጀነራል ማናጀሯ ማብራሪያ የደን ሽፋንን በማሳደግ ጥቅም ላይ የሚውለውን በመተካት እና በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ዘርፍ ነው።
ከወጣት ሰልጣኞቹ መረዳት እንደ ተቻለው፣ በተለይም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሰውን የቀርከሃ ዛፍ በስፋት በመትከል ለፋብሪካዎች ግብዓት ማዋል ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ባላቸው እውቀት ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ ጨብጠዋል።
በደን ሀብት ዙሪያ የንግድ ሀሳብን ለመንደፍ መነሻ እውቀት አግኝተዋል። ቀርከሃ በአገራችን ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ይሸፍናል። ይህንን የሚያህል ቦታ የያዘ ሀብት በርካታ ወጣቶች ያለሥራ እየተቀመጡ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት ሲሰጥ አለመታየቱ የሚያስቆጭ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ከቀርከሃ የተሠሩ ምርቶችን ከውጭ ማስገባቷ የሚያሳፍር ነው።
እንደ ሰልጣኞቹ ምስክርነት ከሆነ፣ ቀርከሃ በቴክኖሎጂ ሲታገዝ ጣውላ ሊወጣው ይችላል። ቀርከሃ ጣውላን የሚተካ ከሆነ ደግሞ በጣውላ ፍላጎት ምክንያት የሚጨፈጨፉ ረዥም እድሜ ያላቸውን አገር በቀል ዛፎች መታደግ ይቻላል።
በኤሺያ አገሮች ቀርከሃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም እየሰጠ ነው። ለምሳሌ ቻይና በዓመት ከሰላሳ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የቀርከሃ ምርት ንግድ ታንቀሳቅሳለች። ኢትዮጵያ የቀርከሃ ደን ቢኖራትም ለሥራ እድል ፈጠራ እና ለኢኮኖሚ ምንጭነት አልተጠቀምንበትም።
እስካሁን ባለው መረጃ፣ በኢትዮጵያ ተሞክሮ ቀርከሃ ለቤት ቁሳቁስ፣ ለመኖሪያ ቤት ሥራና ለአጥር አገልግሎት ከመስጠት አይዘልም። ሰልጣኞች ሥልጠናም ቁጭት የሚያሳድርና ዘርፉ ቢሠራበት በርካታ የሰው ኃይል ሊሸከም የሚችል መሆኑን ስለመገንዘባቸው ተናግረዋል።
በተለይም ወጣቶች ጥሬ ሀብት ከማቅረብ እስከ ማምረት ባለው የሥራ ሂደት ቢሳተፉ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንዛቤ የጨበጡበት ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት የሰልጣኞች አሰልጣኝ አቶ አለማየሁ ገብረየስ ይባላሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ስልጠናው በደን ሀብት፤ በተለይም በቀርከሃ ላይ አዳዲስ የቢዝነስ እቅዶችን አቅዶ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል፤ ክሂሎትና እውቀትን ያጣመረና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና ነው።
ቀርከሃ ማንኛውም እንጨት የሚሠራቸውን ሥራዎች ሁሉ ሊተካ እስከቻለ ድረስ እድሜ ጠገብ ዛፎችን ከመቁረጥ እንድንቆጠብ ያደርጋል። መንግሥት ለአረንጓዴ አሻራ በሰጠው ትኩረት መሠረት ወደ ፊት የደን ሽፋናችን ሊያድግ ይችላል።
ሀይድሮ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅማችን ሲያድግ ደኖችን ለማገዶነት የሚጠቀመው ሰው ቁጥር ይቀንሳል። መጪው የኢትዮጵያ እድገት በደን ሀብታችንም ጭምር የሚደገፍ እንዲሆን ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ዓይነት ስልጠናዎች ያስፈልጉታል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥር 13/2014