በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1970 ዓ.ም የወጡ የጋዜጣችን ሕትመቶች ለመቃኘት ሞክረናል። እነሆ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አገራችን እንዲህ እንዳሁኑ በሶማሊያ ተስፋፊ መንግሥት በ1969 እና 1970 ዓ.ም ወረራ ተፈጽሞባት እንደነበር ይታወሳል:: ኢትዮጵያውያን ይህን ወረራ በመቀልበስ የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር እንዲህ እንደ አሁኑ በሁሉም መስክ ርብርብ ሲያደርጉም ነበር::
ሕዝቡ ለሠራዊቱ፣ ለዘማች ሠራዊት ቤተሰብ የገንዘብና የተለያዩ ድጋፎችን ያደርግ እንደነበር በወቅቱ አዲስ ዘመን ይዟቸው ከወጣ ዘገባዎች እንረዳለን:: ጠላት በኢትዮጵያውያን እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት ተከትሎ በውስጡ የደረሰበትን መከፋፋል የሚመለከቱ ዘገባዎችም ይቀርቡ ነበር::
በዛሬው አዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችንም ከእነዚህ ዘገባዎች የተወሰኑትን ታነቧቸው ዘንድ ይዘን ቀርበናል::መልካም ንባብ::
የአዲስ አበባ ሕዝብ በወረራው ለተጐዱት ማቋቋሚያ 128‚777 ብር ሰጠ
የአድኃሪው የሶማሊያ ወራሪ በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመው ወረራ ከኑሮአቸው የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ በቀበሌና በወዛደር ማኅበራት የመንግሥት መ/ቤቶች በውይይት ክበባቸው የጀመሩትን ተሳትፎ በመቀጠል ፩፻፳፰ ሺ፯፻፯፯ ብር ለጓድ ዶክተር ዓለሙ አበበ የአዲስ አበባ ከንቲባ ትናንት አስረክበዋል::
በዚህ መሠረት በእርሻና ሕዝብ ማስፈር ሚኒስቴር ሥር ከሚገኙ ልዩ ልዩ ክፍሎች የውይይት ክበብ አባሎች ክበባቸው ውስጥ ባደረጉት አጠቃላይ ቅስቀሳ መሠረት የተሰበሰበውን ፩፻፳፭ ሺ ፫፻፯ብርና ግምቱ ፳ሺ ብር በላይ የሚሆን የወንድና የሴት ልብሶች እንዲሁም ቁሳቁሶችና ፻፴፭ ኪሎ ቡና በእርሻና ሕዝብ ሚኒስቴር ውይይት ክበቦች ማዕከላዊ ኮሚቴና ሌሎች ተወካዮች ለጓድ ዶክተር ዓለሙ አበበ አስረክበዋል::
የእርሻና ሕዝብ ማስፈር ሚኒስቴር ዋናው መ/ ቤት ፲ ሺ፱፻፴፭ ብር ሕዝብ ማስፈር ባለሥልጣን ፯ሺ፯፻፺፭ ብር የመንግሥት እርሻ ልማት ባለሥልጣን ፪ሺ፪፻፶፩ ብር የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ወዛደሮች ፬ሺ፯፻፶፮ ብር ደንና ዱር አራዊት ልማት ባለሥልጣን ፬ሺ፯፻፲፩ ብር የሸለቆዎች ልማት ባለሥልጣን ፱፻፸፪ ብር የሸዋ ክፍለ ሀገር የእርሻና ሕዝብ ማስፈር ጽ/ቤት ፪ሺ፭፻፵፩ ብር የእርሻና ሰብል ገበያ ድርጅት ፲፮ሺ፴ ብር የእርሻ መካነ ጥናት ዋና መ/ቤት ፯፻፳፩ ብር የኢ/ ፒ/ድ/ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና አገልግሎት መምሪያ ፳፩ሺ፻፲፱ ብር የአዋሽ ሸለቆ ልማት ድርጅት ፱ሺ፯፻፪ ብር ሲያወጡ የአትክልትና ፍራፍሬ ድርጅትም ፩ሺ፪፻ ብር ማዋጣታቸው ታውቋል::
ቀጥሎም እርዳታውን ያበረከቱት የከፍተኛ ፲፮ ቀበሌ ፲፰ ሊቀመንበር ሲሆኑ እሳቸውም እንደዚሁ ከቀበሌያቸው ነዋሪዎች የተሰበሰበውን ፯፻፵፪ ብር ለከንቲባው አስረክበዋል::
እንደዚሁም የከፍተኛ ፲፫ ቀበሌ ፲፩ ሊቀመንበር ከታራሚዎችና ቁርስና ምሳ የተዋጣ ፯፻፷፮ ብር አስረክበዋል:: በጐ አድራጊዎቹ በአጠቃላይ ባደረጉት ንግግር የአዲስ አበባ ሠፊ ሕዝብ በአድኃሪው ወራሪ ጦር የተደመሰሱት ከተሞችና ቤት ንብረታቸውን ያጡት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ተመልሰው እስከ ተቋቋሙ ድረስ ርዳታውና ትብብሩ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል::
በመጨረሻም ጓድ ዶክተር ዓለሙ አበበ ተባባሪዎችንና በጎአድራጊዎቹን አመስግነው ታሪክ ሠሪው ሠፊው ሕዝብ በአገራችን ላይ የደረሰውን ችግር ለማቃለል ያሳየውን ተሳትፎ አመስግነው ለመልሶ ማቋቋም ሕዝቡ የአደረገውን ከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት አድንቀዋል::
በከንቲባው ጽ/ቤት ውስጥ በተከናወነው በዚህ የርዳታ አሰባሰብ ስጦታ ላይ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከመገኘታቸውም በላይ ተወካዮቹ ለቁሳቁስ ተቀባዩ ኮሚቴ የሰበሰቡት ቁሳቁስ አስረክበዋል:: (መጋቢት22 ቀን 1970 ዓ.ም)
በአሰሳ በርከት ያሉ መሣሪያዎች ተያዙ
ነቀምቴ (ኢ.ዜ.አ.) በወለጋ ክፍለ ሀገር በደምቢ ዶሎ ከተማ ባለፈው ሳምንት ፷፭ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ፰፻፹፭ ልዩ ልዩ ጥይቶች በአሰሳ ተያዙ :: ከተያዙትም መሣሪያዎች መካከል ፴፯ ጠመንጃዎች ፳ ሽጉጦችና ፪ የጦር ሜዳ መነፅሮች እንደሚገኙበት ተገልጧል::
በአሰሳው ወቅት ከጦር መሣሪያዎቹ ሌላ አንድ የነብር ቆዳ እንዲሁም ግምታቸውና ዓይነታቸው ለጊዜው ያልታወቁ ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በአሣቻ ሥፍራ ተሸሽገው መገኘታቸውንም የቄለም አውራጃ አስተዳዳሪ አስታውቀዋል::
አሰሳውን በመተባበር ያከናወነው በደንቢ ዶሎ የመንገድ ሠራተኞች ከቀበሌ ማኅበራት ተወካዮች ከመለዮ ለባሾች ከገበሬና ከቀበሌ ሕዝብ ጥበቃ ደኅንነት ጓዶች የተውጣጣ አንድ ቡድን መሆኑን የአውራጃው አስተዳዳሪ ጨምረው ገልጠዋል:: (መጋቢት 15 ቀን 1970 ዓ.ም)
የፓርቲውን ሊቃነ መናብርት ትጥቅ የሞቃዲሾ ገዥ መደብ ማስፈታት ጀመረ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) የሞቃዶሾ አድኃሪ የገዥ መደብ በሶማሊያ ውስጥ በክፍለ ሀገርና በወረዳ ደረጃ ያሉትን የፓርቲ ሊቃነ መናብርት ትጥቅ ማስፈታቱን የታመኑ የዜና ምንጮች ትናንት አረጋግጠዋል ::
ከዜና ምንጮቹ ለመረዳት እንደተቻለው ፤የአገሪቱ የክፍለ ሀገርና የወረዳ የፓርቲ ሊቃነ መናብርት በአስቸኳይ ወደ ሞቃዲሾ ከተጠሩና በአልታወቀ ሥፍራ እንዲሰበሰቡ ከተደረገ በኋላ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ መደረጉ ታውቋል::
ከታመኑ የዜና ምንጮች በተጨማሪ በተገለጠው መሠረት በአሁኑ ጊዜ በሙሉ የዚያድ ባሬ ገዥ መደብ አባሎች መካከል መራራ የሆነ ልዩነትና ግጭት መፋፋሙ ተነግሯል::
የአገሪቱ የክፍለ ሀገርና የወረዳ የፓርቲ ሊቃነ መናብርት ትጥቅ መፍታት በሶማሊያ ክፉኛ የፖለቲካ ውድቀት መድረሱን አጉልቶ የሚያሳይና በተቃራኒ ኃይሎች መካከል ያለው የሰው ግጭት ፤እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መገኘቱን እንደሚያስረዳ የዜና ምንጮቹ አስታውቀዋል::
(መጋቢት 16 ቀን 1970 ዓ.ም)
የደቡብ ግንባር በዘማቹ ሠራዊት በሙሉ ነፃ ወጣ
የኢትዮጵያ መደበኛና ሚሊሺያ አብዮታዊ ሠራዊት የደቡብን ግንባር ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣቱን አንድ የብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ ቃል አቀባይ አስታወቀ::
ቃል አቀባዩ በሰጠው መግለጫ አብዮታዊ ሠራዊት ነፃ ያወጣውን የደቡብ ግንባር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አድርጎ ሕዝብ በማረጋጋትና በማደራጀት ላይ የሚገኝ መሆኑን አስታውቋል:: በደቡብ ጊኒር በኢሚ አቅጣጫ የዘመተው የደቡብ ግንባር ሠራዊታችን ኤልከሬን ባለፈው እሁድ መጋቢት ፲፬ ቀን ፲፱፻፸ ከጧቱ ፪ ሰዓት ተኩል ላይ በቁጥጥር ሥር ሲያደርግ በዚሁ አቅጣጫ ወሰን ላይ የሚገኘው ባሬን መጋቢት ፲፬ ቀን ፲፱፻፸ ዓ.ም ከጠዋቱ ፲፪ ሰዓት ላይ በቁጥጥር ሥር አድርጎ ሕዝቡን በማረጋጋትና በማደራጀት ላይ እንደሚገኝ ቃል አቀባዩ አረጋግጧል::
(መጋቢት 16 ቀን 1970 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014