ይህ ረድፍ የአንድ አካባቢ ወይም ቦታ ለምን እንደተባለ የሚገለጽበት ንዑስ ዓምድ ነው። በአገራችን ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን እናስተዋውቃለን። እነዚህ ቦታዎች ለምን እንደተባሉ ከታሪክ ሰነድ አጣቅሰን ምላሽ እንሰጣለን።
ማይ ሎሚን
በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ቆላ ተምቤን ውስጥ ትገኛለች። ከአዲስ አበባ 875 ኪሎ ሜትር ከክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። ከትግራይ ገደላማና ሰንሰለታማ አካባቢዎች በተለየ ረግረግና ለምለም ምድር የሚታየው በዚች ቦታ ነው። ይች ቦታ ማይ ሎሚን ትባላለች። ‹‹ማይ›› የትግርኛና የግዕዝ ቃል ሲሆን በአማርኛ ውሃ ማለት ነው። በትግርኛ ‹‹ሎሚን›› ማለት ደግሞ ያው ሁላችንም የምናውቀው ሎሚ ማለት ነው። ማይ ሎሚን ስያሜዋን ያገኘችው ውሃማ አካባቢ በመሆኗ ሎሚ በብዛት ስለሚበቅል ነው። ማይ ሎሚን ማለት የውሃ ሎሚ እንደማለት ነው።
ምንድብድብ
ታሪካዊው የዓድዋ ተራራ ነው። እዚህ ቦታ ላይ የጣሊያንና የኢትዮጵያ ወታደሮች በጥይት ብቻ ሳይሆን በጨበጣ ውጊያ ተቃምሰዋል። ጥይት ያለቀበት የኢትዮጵያ ሰራዊት ተንደርድሮ በመሄድ የጣሊያንን ወታደር ጉሮሮ አንቆበታል። አንገት ለአንገት ተናንቀዋል። የጣሊያን ወታደሮችን በጎራዴ ቆራርጠው ጥለዋል። ምንድብድብ ማለት «መቆራረጥ» ማለት ሲሆን ስያሜውን ያገኘው የኢትዮጵያ ወታደሮች የጣሊያን ወታደሮችን ቆራርጠው ስለጣሉበት ነው። በቦታው ላይ የጅምላ መቃብር ይገኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011