ዜማ ብዙ ማረፊያ አለው። ኪነ ጥበብ በርካታ ስፍራ አላት። ዜማ ማረፊያው አገርና ህዝብ ሲሆን ደስ ይላል። ኪነ ጥበብ ስፍራዋ ትውልድ ግንባታ ሲሆን እሰየው ያስብላል።
በርካታ ሀገርኛ ዜማዎቻችን ፍቅርና ሴትነት ላይ ያተኮሩ ነበሩ፤ አሁን ጊዜው ደርሶ ስለ አገራችን የምናዜምበት ሆኗል። በድሮው ስርዐት እያንዳንዱ ድምጻዊ ስለአገሩ የማዜም ግዴታ ነበረበት። አሁን ላይ ከነፍሳችን ተጋብተው አካል ስጋችንን የሚያላውሱ አገረኛ ሙዚቃዎች በዛን ሰሞን ተዚመዋል። ኢትዮጵያ ሲባል እንባችንን የሚያመጡ፣ የአገር ፍቅር የወለዳቸው ዜማዎች ወጥተዋል።
ስለ አገር ማዜም ስለምንም ነገር ከማዜም በላይ ነው። ሁሉም ነገር አገርን ተደግፎ የቆመ፣ ትውልድን ይዞ የጸና ነው። በህይወት ውስጥ ክብርና ቦታ የምንሰጣቸው ማናቸውም ነገሮች ከአገር ቀጥሎ የሚመጡ ስለሆነ በዜማውም ሆነ በማናቸውም ነገር ላይ የአገር ጉዳይ ሁሌም ከፊት የተቀመጠ ይሆናል።
ዜማ አፍ አለው፣ ኪነ ጥበብ ሀይል አላት። ዜማና ዜመኛ፣ ጥበብና ጠቢብ በአገር ጉዳይ ላይ በአንድ ላይ ሲቆሙ ውጤቱ ያምራል። ኪነ ጥበብ ማረፊያዋ አገር፣ ጉዳይዋ ትውልድ ሲሆን የምንፈልገውን ውጤት እንድናመጣ መንገድ ይጠርግልናል።
አገር በኪነ ጥበብ ይሰራል። ትውልድ በዜማ ይገነባል። ጥበብ ኃይሏ ሁለት አፍ እንዳለው ስለት ነው። ባስቀመጥናት ቦታ ሁሉ ታብባለች። አበባዋ ግን በእኛ እውቀትና ማስተዋል ልክ የሚያፈራ ነው። እውቀታችንን ለመልካም ነገር ስንጠቀመው መልካሙን ያፈራል። ለመጥፎ ነገር ካዋልነው ደግሞ እንደዚሁ መጥፎውን ይወልዳል። በእውቀታችሁ ለራሳችሁም ሆነ ለአገራችሁ ፍሬ እንድታፈሩ ይሁን።
ኪነ ጥበብ የአገር ሀኪም፣ የማህበረሰብ ወጌሻ ናት። ከትላንት እስከዛሬ በጠላቶቻችን ላይ የበላይ ሆነን በማሸነፍ የተራመድንው የኪነጥበቡ ሀይልም ደግፎን ነው እላለሁ። በኪነ ጥበብ ያልተነቃቃንበት ጊዜ የለም። በችግር በደስታችን ማህበረሰቡን ስናነቃቃበት ኖረናል። በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ዙሪያ እንኳን የኪነ ጥበብ ድርሻ ምን ያህል እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን።
ጥበብ በብዙ መንገድ ትፈጠራለች። የጥበብ መፈጠሪያ ከሆኑ አጋጣሚዎች አንዱ ደግሞ ተጋድሎ ነው። የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የጉዳቱን ያህል ኢትዮጵያዊነትንም በብዙ ነገር ጠቅሞታል ብዬ አስባለሁ። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አንድነታችን ጠንክሯል፣ ድሮነት እየተመለሰ ይገኛል።
ከኪነ ጥበብ ረገድም በርካታ ሀገርኛ ሙዚቃዎች ወጥተዋል። ሁሉም ሰው አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ሀገሩን እየጠቀመ ነው። አሁን ላይ ሀገራችንን ከወራሪው ሀይል ለመታደግ አገራችንን ከአሸባሪ ቡድን ለማላቀቅ ብዙዎቻችን በብዙ መንገድ በመታገል ላይ ነን።
ከዚህ ህዝባዊ ትግል ውስጥ ደግሞ ኪነ ጥበብ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ጥበብ ለኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ለጥበብ አዲስ አይደሉም። እንዳውም ጥበብ ሆይ የትውልድ ቀዬሽ ወዴት ነው ብትባል ኢትዮጵያ የምትል ይመስለኛል። ለዚህ እንዲሆነን በአለም አቀፍ ደረጃ ዜማ ፈጣሪ የሆነውን ቅዱስ ያሬድን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል።
ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በልጆቿ እንደኮራች ነው። አገር ችግር ላይ ስትሆን የሚያዜሙ፣ የሚገጥሙ፣ የሚያቅራሩ ታማኝ ልጆች ሞልተዋታል። በጥበበኛ ልጆቿ ከትናንት እስከዛሬ ስትወደስ ኖራለች። በየጦር ሜዳው፣ በየግንባሩ ሰራዊታዊታቸውን በዜማና በግጥም በሽለላም ያገዙ በርካታ አርበኞች ነበሩ፤ አሁንም አሉ።
አድዋ ሲነሳ አዝማሪ ጣዲቄን አለመጥቀስ ንፉግነት ነው። የጣዲቄን የጀግንነት ግጥሞችና ዜማዎች የአድዋን ድል ለማምጣት ወሳኝ ነበሩ። ልክ እንደ ጣዲቄ ሁሉ አሁንም አገራችን ከሕወሓትና ከምዕራባውያን ጋር ለገባችበት ጦርነት በኪነጥበቡ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ያሉ ዜጎች ጥቂት አይደሉም። ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ማሸነፍና ጀግንነት፣ ስለ ነጻነትና አንድነት በርካታ ሙዚቃዎችን እየሰማን ነው።
ከዚህ ሁሉ በመነሳት አገር በመፍጠር ረገድ ኪነ ጥበብ የጎላ ድርሻ እንዳላት እንረዳለን። አሁን ላይ በየትኛውም ስፍራ ስንሄድ የምንሰማው ሙዚቃ አገራዊ መንፈስ የተላበሰ ነው። ይሄ መሆኑ አገራዊ መነቃቃትን ከመፍጠር ባለፈ የኪነ ጥበቡንም እድገት አንድ እርምጃ የሚያሻግረው ነው። ጀግኖቻችንን ጨምሮ ኢትዮጵያ አገራችን በአርቲስቶቻችን የተሞገሰችበት እንደዚህ ያለ ጊዜ ያለ አይመስለኝም።
ሙዚቃ ኃይል አለው በተለይ ጀግኖቻችንን የሚያወድስ፣ ስለ አገር መስዋዕት የሆኑ አርበኞችን የሚዘክሩ ሲሆኑ ደግሞ ጣዕማቸው የትየሌለ ይሆናል። አሁን ላለችው ኢትዮጵያም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ አገራዊ ለዛ ያላቸው ዜማዎች ያስፈልጉናል። በተለይ እንዲህ እንደ አሁኑ አገር ችግር ላይ ስትሆን፣ ህዝብ ስጋት ላይ ሲሆን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉሙዚቃዎችን ጆሯችን ይናፍቃል።
ኢትዮጵያ አገራችን በእውቀታችን፣ በጥበባችን የሳልናት ስዕላችን ናት። የእኔና የእናንተ አሻራ በአገራችን ገጽ ላይ የሆነ ቦታ ላይ እየተንጸባረቀ ነው። ኢትዮጵያን ለመሳል በእጃችሁ ያለው ቀለም ምን አይነት ነው? ቀለማችሁን ምረጡ፤ .ኢትዮጵያዊነት ላይ አርፎ የሚደበዝዝ ሳይሆን የሚጎላና የሚደምቅ ሀሳብና እውቀት ያስፈልጋችኋል።
ትውልድ ላይ አርፎ መከራ የሚሆን ሳይሆን ክብር የሚሆን ማንነት ግድ ይለናል። ዛሬ ላይ ለአገራችሁ እየሆናችሁት ያለው ማንኛውም ነገር ነገ ላይ ልጆቻችሁን የሚጠብቅ ነውና እውቀታችሁንና ሀሳባችሁን ምረጡ። የሰው ልጅ ብዙ የሀሳብ ማረፊያ አለው፤ ዘር መሬት ላይ እንደሚበቅል ሀሳብም አገር ላይ ያፈራል። አገራችሁን በሀሳባችሁ አክሙ፣ በዜማችሁ አንጸባርቁ፣ በእውቀታችሁ አርነት አውጡ።
አገር አስተሳሰብ ናት። አገር የግለሰቦች አሻራ ናት። በምንጽፈው ድርሰት፣ በምንገጥመው ግጥም፣ በምንሰራው ሙዚቃ አገር ትፈጠራለች። በምንስለው ስዕል፣ በምንሰራው ፊልም ትውልድ ይፈጠራል። የዛሬዋንም ሆነ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ባለአደራዎች ነን። አገር ለመፍጠር ከምንም በፊት ራሳችንን መፍጠር አለብን። ራሱን የፈጠረ ዜጋ አገር ለመፍጠር ወይም ደግሞ አገር ለመፍጠር በሚደረግ ትግል ውስጥ ሚና ለመጫወት አይቸግረውም። ራሱን ያልፈጠረ ዜጋ ግን ለአገር ሸክም ከመሆን ባለፈ ጥቅም አይኖረውም። ሕወሓት ራሱን መፍጠር ቢችል ኖሮ ዛሬ ላይ በዚህ ልክ አገሩን አያወድማትም ነበር። ራስን መፍጠር ማለት መልካም ዜጋ መሆን ማለት ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014