ወቅቱ በ2007 ዓ.ም በተደረገ ምርጫ ሰሞን ነው። በወቅቱ ራሴን ዘና ለማድረግና በዚያውም ለጤና ጠቃሚ ነው በሚል ህሳቤ ምሽቱን በራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ የእግር ጉዞ በማድረግ ላይ ነበርኩ። ያን ሰሞን የተደረገውን ምርጫ ተከትሎም በየመንገዱ፣ ድልድዩ፣ የመብራትና የቴሌ ምሰሶዎች ላይ የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮች ተለጣጥፈው እዚህም እዚያም ይታያሉ። የተለመደ ነገር ነበርና ብዙም ትኩረት ሳልሰጣቸው የቀስታ ጉዞዬን ቀጥያለሁ።
በዚሁ አጋጣሚ ነበር መንገድ ያገናኘን አንድ ወጣት ጉዳዬ ብዬ ቦታ ያልሰጠሁትን ነገር እንዳሰላስለው ያደረገ ንግግር ጣል ያደረገው። ይህ ወጣት ጣቱን ወደ ፖስተሮቹ ቀስሮ በስሜት እየተወራጨ “አያችሁ…አያችሁ..አያችሁት ፖለቲካችን ጭልጥ ብሎ እኮ የጡረተኞች ሙዚየም ሆኗል። አይገርምም እንዲያው ለመፎገር ብለው እንኳን አንድ ሁለት ወጣት ጣል አያደርጉም ኧረ ምን ሼም የሌላቸው ናችሁ በእናታችሁ…” በማለት። የወጣቱን ንግግር ተከትሎ እኔም ሆንኩ እንደኔ በአጋጣሚ በዚያ ቦታ የተገናኘን መንገድ ተጋሪዎች ዓይናችንን በቅጽበት ጣቱ ወደሚያመለክተው ፖስተር ወረወርን።
በአንዲት ብጣሽ ወረቀት በጥቁርና ነጭ ቀለም በተጻፈ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተር ላይ የአንድ ፓርቲ ተወካይ ሆነው የቀረቡ 6 ሰዎች ፎቶ ጉብ ብሎ ይታያል። ለወጣቱ እንዳስገረመው አስደናቂው ነገር ስድስቱም ሰዎች በእርግጠኝነት ከ70 እስከ 80 ባለ ዕድሜ ውስጥ ያሉ አዛውንቶች መሆናቸው ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እስካሁን ድረስ ወጣቶቻችን በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ለምን ተቀዛቀዘ? ለምንስ ፖለቲካችን በጡረተኞች ተዋጠ? የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ ይመላለስብኛል። የነገ ኢትዮጵያን ተረካቢ የሆኑና ከኅብረተሰቡ ከግማሽ በላይ የሆነ ቁጥር ያያዙትን ወጣቶችን ያላሳተፈ ፖለቲካስ እውነት ፖለቲካ ሆኖ የአገራችንን መጻኢ ዕድል መስመር ያስይዘዋልን ስልም እብሰለሰላለሁ።
በእኔ እምነት ወጣቱን ከፖለቲካ አርቆ መድረኩን የጡረተኞች መዘክር ያደረገው አንድም ገዥው ፓርቲ ቀደም ሲል ከእሱ የተለየ አመለካከት በሚያራምዱ አካላት በተለይም፣ በወጣቶች ላይ ሲያደርግ የነበረው ማዋከብና እስር ሲሆን በሌላም በኩል ፖለቲካን ከግል ጥቅም አንጻር የሚቃኙና ለጥቅም የተሰለፉ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች አላስጠጋ ስላሉት ይመስለኛል። ስለሆነም ቅድሚያ ለወጣቶች በሚል ህሳቤ መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፖለቲካው መድረክ ሰፊውን ሥፍራ ለወጣቱ ይስጡት ፖለቲካችንም ከጡረተኞች መዘክርነት ቢላቀቅ አይበጅም ትላላችሁ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በናታን ከጉለሌ