የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በሕልውና ዘመቻው ተሳታፊ ለነበሩ አትሌቶች ዕውቅና ሰጠ።
ፌዴሬሽኑ የተቋሙን እንዲሁም የስፖርቱን ታሪክ የሚዘክሩ ሁለት መጽሐፍትንም በጠቅላላ ጉባኤው አስመርቋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ ቆይቷል።
በጉባኤው ላይም አገር የገጠማትን የሕልውና ፈተና ተከትሎ አንጋፋ አትሌቶች ግንባር ድረስ በመሄድ እንዲሁም በሞራልና በስንቅ ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።በኦሊምፒክ መድረክ እንዲሁም በሌሎች የዓለም ቻምፒዮናዎች አገራቸውን ወክለው ባንዲራዋን ያውለበለቡት አትሌቶች የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን ዳግም በጦር ግንባር ተገኝተው በማስመስከራቸው ጠቅላላ ጉባኤው የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።
በጠቅላላ ጉባኤው ተሸላሚ የሆኑትም በፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነው የማራቶን ጀግናው አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮማንደር ማርቆስ ገነቴ እንዲሁም ዋና ኦፊሰር ፋንቱ ሜጌሶ ናቸው።
በግንባር ተገኝቶ ለሰራዊቱ ድጋፍ ያደረገው ሌላኛው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በመድረኩ አልተገኘም።ከፌዴሬሽኑ ጎን ለጎንም የአፋር ክልል አትሌት ፋንቱ ሜጌሶ በአፋር ግንባር በአካል ተገኝታ እርዳታ በመለገስ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ልዩ ሽልማት አበርክቶላታል።ፌዴሬሽኑ ከአትሌቶች ጎን ለጎን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰራጨውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ አትሌቶችን በመመርመር ድጋፍ ሲያደርግ ለቆየው ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪም የምስጋና ዕውቅና አበርክቷል።
በጠቅላላ ጉባኤው ሌላው የቀረበው ፌዴሬሽኑ ያዘጋጃቸው ሁለት መጽሃፍት ሲሆኑ፤ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ ሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም በጠቅላላ ጉባኤ አባላቱ አስመርቋል።
መጽሐፍቱ ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድድሮች ዝክረ ታሪክ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዝክረ ታሪክ›› የሚሉ ሲሆኑ የፌዴሬሽኑን ታሪክና ያለበትን ሁኔታ የሚያንጸባርቁ መሆኑን በመድረኩ ተጠቁሟል።መጽሐፍቱ በፌዴሬሽኑ ባለሙያዎችና አንጋፋ አሰልጣኞች አስተባባሪነት በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የአትሌቲክስ ስፖርትን የዘመናት ታሪክ፣ የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ውድድር ውጤቶች እንዲሁም የአትሌቶችን ታሪክ የሚዘክሩም ናቸው።
መጽሐፍቱ የመጀመሪያ እትሞች ሲሆኑ፤ ለተጨማሪና ለማስተካከያ የሚሆኑ ታሪኮች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ለማሻሻያ ጉባኤው ለሕልውና ዘመቻ ተሳታፊዎች ዕውቅና ሰጠ ስፖርት እትም እድል የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል።በስፖርቱ ዙሪያ የጥናትና ምርምር ስራ ለሚሰሩ እንዲሁም መረጃዎችን ለሚፈልጉ አካላት ቀጥተኛ ምንጭ ሊሆን ይችላል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በምርቃቱ ወቅት፤ በመጽሐፍቱ ዝግጅት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት ምስጋናዋን አቅርባለች።የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በስራ ላይ በቆየባቸው ጊዜያት የራሱን አሻራ ለማኖር በማለም የተቋሙን ታሪክ በመጽሐፍ መልክ እንዲዘጋጅ አድርጓል።
የጽሁፉ ዝግጅት ሶስት ዓመታትን ሲፈጅ፤ አትሌቶችንና ለስፖርቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ጭምር በፎቶግራፍ አስደግፎ የሚገልጽ መሆኑንም ለጉባኤው አስረድታለች።የጉባኤው ተሳታፊዎችም መጽሐፍቱ ከሽፋናቸው ጀምሮ ለአንባቢ ሳቢ መሆናቸውን እንዲሁም ለስፖርቱም ጠቀሜታ ያለው እንደሆነም በሰጡት አስተያየት አንጸባርቀዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው፤ አትሌቲክስ በኢትዮጵያ ስፖርት ትልቁና አገሪቷም ስሟ የሚነሳበት በመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመዋል።ስፖርቱ የተደራጀና ውጤታማ ቢሆንም እንደ አገር እየታየ ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ እንዳይዳከም መስራት ተገቢ ነው።
እአአ ከ2020 ጀምሮ የአገሪቷ ስፖርት መዳከም እየታየበት በመሆኑ ምክንያቱን በመፈተሸና በመመርመር ችግሩን ለመቅረፍ ሚኒስትሩ እየሰራ ይገኛል።በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ዝናውን እንደያዘ እንዲቀጥል የአሰራር ደንብና ሌሎች አሰራሮችን በማጠናከር እንዲቀጥልም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014