አዲስ አበባ አራት ኪሎ ከተወካዮች ምክር ቤት አጠገብ የሚገኘው መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተመረቀው ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም ነበር። ይህም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ንጉሠ ነገሥት በተባሉ በመጀመሪያው ዓመት ያስጀመሩት ግንባታ ነው።
ካቴድራሉን ለማሠራት የመሠረተ ድንጋዩ ተጥሎ ግንባታው የጀመረው ታኅሣሥ 15 ቀን 1924 ዓ.ም የግብፁ ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስ እና ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት በተገኙበት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠው ነው።
ቤተክርስቲያኑ ሲታነፅ ለአገራቸው ነፃነት ሲታገሉ ለተሰው አርበኞች መካነ መቃብር እንዲሆን ታቅዶ መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ። በመሀል በጣልያን ወረራ ምክንያት ግንባታው ቆሞ ነበር።
የካቴድራሉ ስም መንበረ ጸባዖት መባሉም ይህንኑ ያመላክታል፤ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መንበር የሚለው ቃል በቁሙ ወንበር፣ መኖሪያ፣ ማረፊያ፣ መቀመጫ፣ ዙፋን፣ አትሮንስ፣ እርፍ መደብ፤ ለመቀመጫ ከፍ ያለ ቦታ በሚል ይገልጹታል። ጸባዖት ፍቺው ሠራዊት፣ ጭፍራ፣ የጦር ሕዝብ ፣ ብዙ ወታደር፣ ያርበኛ ጉባኤ፣ የጀግና ማኅበር ማለት ነው።
የሥላሴ ካቴድራል የሕንፃው ግንባታ ልዩ መልክ ባለው እቅድ ተገንብቶ በሮችን መገጣጠምና ጌጣ ጌጥ ነገሮች ሲቀሩት በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ጣልያን አገራችንን በግፍ ለመውረር ስለተነሳ ሥራው መቆም ግድ ሆነበት። የፋሺስት ጣልያም ጠቅላላ ሃሣብ የኢትዮጵያን ሙሉ ክብር ፈጽሞ ለመግፈፍ እና የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ስለነበር፣ ካቴድራል የአሠራር ጥራት እና የቦታውንም አቀማመጥ ምቹነት በመገንዘብ የጣልያን ካቴድራል ለማድረግ ወስኖ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።
ሆኖም በግድ እና በግፍ ወሰደው ላለመባል ግምቱን ሰጥቶ መውሰድን መርጦ የጊዜውን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በማስፈራራት ግምት ከፍዬ ልውሰደው ሲል ጠየቀ። ያገኘው መልስ ግን “ዛሬ መብቱ ያንተ ነው።
በግድ ለመውሰድ ትችላለህ፤ ግን በፈቃዳችን አናደርገውም” የሚል ቆራጥ መልስ ያገኘ በመሆኑ ተስፋ ቆረጠ፣ ካቴድራሉም ከጠላት እጅ ሳይገባ ቀረ። በ1933 ዓ.ም በተገኘው ድል ንጉሠ ነገሥቱ ሲመለሱ፣ የሕንፃው ሥራ እንደገና ተጀምረ፤ በፍጥነት ተሠርቶ ካለቀ በኋላ “መንበረ ጸባኦት” ተብሎ በቅድስት ሥላሴ ስም ተሰይሞ ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሊቃውንት፣ የሴት ወይዛዝርት፣ የጦር ሠራዊት በተገኙበት ተመረቀ።
ከላይ እንደተገለጸው ካቴድራሉ መታሰቢያነቱም በአምስቱ የጠላት ወረራ ዓመታት ለተዋጉት አርበኞች ሆነ። ቅዳሴ ቤቱ ከተባረከ በኋላ በባህር የተጣሉትን፤ በገደል የወደቁትን እና በማይታወቅ ቦታ የረገፉትን አርበኞች ዐጽም ተሰብስቦ በዚሁ ዕለት በልዩ የጸሎት ሥነ ሥርዓትና በታላቅ የሰልፍ አጀብ ተቀበረ።
በ1936 ዓ.ም የተመረቀው የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የአዲስ አበባ ሕዝብ እየጨመረ ሲሄድ በመጥበቡ በ1939 ዓ.ም አዲስ ቅጽል ሥራ ተጀምሮ አሁን ያለውን መልክና ሥፋት ሊያገኝ ችሏል። የአሁኑ ሕንፃ ወለል ስፋት ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ 37 ሜትር ሲሆን ከሰሜን ወደ ደቡብ 27 ሜትር ነው።
ቁመቱም መካከሉ ላይ 35 ሜትር ነው። በውስጡ ካሉት ዓምዶችና ከቅድስቱ ጀምሮ ያለው ሕንፃ በመጀመሪያው ጊዜ የተሠራው ያልተነካ ነው። በሰሜንና በደቡብ ያሉት ግንቦች ግን በ1939 ዓ.ም የተቀጠሉት ግንቦች መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ። የካቴድራሉ ሥዕሎች በአቶ አገኘሁ እንግዳ፤ በአቶ እምአላፍ ኅሩይ፤ አቶ አለፈለገ ሰላም እና አቶ መዝሙር ዘዳዊት የተሣሉ ናቸው።
ከ90 ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባው መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ከተገነባ ጊዜ አንስቶ እንደ ቀለም መቀባት ካሉ አነስተኛ ዕድሳቶች ውጪ ሙሉ ጥገና አልተደረገለትም።
የደረሰበትን ጉዳት አስመልክቶ የተደረገው ጥናት ሕንፃው አሁን ባለበት ሁኔታ የአገልግሎት ዘመኑን መጨረሱን ማመላከቱም ተገልጿል። ዕድሳቱ ሲጀመር በዓይን የማይታዩና የጉዳቱን ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳቶች ይገኛሉ የሚል ሥጋት አለ። በካቴድራሉ በቅርቡ ይጀመራል የተባለው ዕድሳት ለማከናወን ሲባል መቃብሮቹ ሊነሱ ይችላል።
በቅጥር ግቢው ውስጥ የሚገኙትን የሃይማኖት አባቶችን መቃብር ወደ ‹‹ክብር ቦታ›› በማዛወር ግቢውን ‹‹ጠዋትና ማታ የሚቀደስበት የሚጸለይበት›› የማድረግ ሃሳብ እንዳለም መረጃዎች ያሳያሉ። ቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመለየት ፋሲል ጊዮርጊስ በተባለው አማካሪ ድርጅት አማካይነት ዘጠኝ ወራት የፈጀ ጥናት መደረጉን ከካቴድራሉ ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ከካቴድራሉ አሠራር የተነሳ ወደ ዕድሳት ሥራ እንዲገባ የሚያስችል ሰነድ የተገኘው ለዘጠኝ ጊዜያት የጥናት ሰነድ ከቀረበ በኋላ መሆኑም ታውቋል።
በተደረገው ጥናት በሕንፃው መሠረት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የውኃ ሥርገት እንዳለ፣ እንዲሁም ሕንፃውን በያዙት ምሰሶዎችና በቤተ ክርስቲያኑ ጣሪያ ላይ ከፍተኛ ስንጥቅ እንዳለ ነው። በቤተ ክርስቲያኑ ጣሪያ ላይ በተከሰው ስንጥቅ ምክንያት ውኃ ወደ ውስጥ እየገባ በመሆኑ፣ በሕንፃው ምሰሶ ላይ ያሉት ቅርፃ ቅርፆች እየወደቁ መሆናቸውን ሲሆኑ ዕድሳቱ ቢያንስ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅና ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ በቅርቡ የወጣ መረጃ ያሳያል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014