ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠታቸውን ተከትሎ በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች የመሪያቸውን ዱካ ተከትለው ችግኞችን በመትከልና አካባቢያቸውን በመንከባከብ ንቁ ተሳታፊ እየሆኑ መጥተዋል።
ወጣቱ በአንድ በኩል አካባቢውን እያስዋበ በሌላ በኩል የተራቆቱ መሬቶችን በማልበስ የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል። በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ደጃፋቸውን በማስዋብ ማራኪ ገጽታዎችን ሲፈጥሩ እየተመለከትን ነው።
በአንዳንድ አካባቢዎች ከቆሻሻ የጸዳ ለኑሮ ተስማሚ የሆነ መንደር ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ ይታያል። በተለይም ወጣቱ ከለውጡ ወዲህ መንግስት እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ተስፋውን የሚያለመልም ሆኖ ስላገኘው በአረንጓዴ ልማት ጽዳትና ሰላም ዘርፍ የሚጠበቅብትን እያደረገ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአሸባሪው ህወሓትን አገር የማፈራረስ አጀንዳ ለማምከን እና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎችን ፍላጎት ለማክሸፍ ወጣቶች ተደራጅተው አካባቢያቸውን በመጠበቅ በሰላምና ጸጥታው ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በመዲናዋ ላይ ያተኮረውን የጠላት እንቅስቃሴ በንቃት በመከታታል ምላሽ እየሰጡ ነው።
በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን ይዘን የቀረብነው እንግዳ በአረንጓዴ ልማትና በአካባቢ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ መልካም ተሞክሮ ያለው ነው። የወጣቱ ተሞክሮ ቢስፋፋ አዲስ አበባን እንደስሟ ለማሽሞንሞን አበርክቶው ከፍ እንደሚል በማመን እንደሚከተለው ለማቅረብ ሞክረናል።
ወጣት ናትናኤል ግርማ ይባላል። ቅጽል ስሙን ገበታ ይሉታል። ስሙን የሰጡት የሰፈሩ ልጆች ሲሆን ከምግብና ከሥራ ውጭ ምንም ነገር የማያውቅ መሆኑን ለመግለጽ ነው። መጠጥ አይጠጣም፣ ጫት አይቅምም፤ በምግብና በሥራ ግን አይደራደርም። ጋደኞቹና አብሮ አደጎቹ ሁሉ ከሱስ የጸዱ በመሆኑ ለመጥፎ ነገሮች ተጋላጭ እንዳይሆን ረድቶታል።
ናትናኤል የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ ነው። የመንደሩን ጽዳት በመጠበቅ ለአካባቢው ነዋሪዎች ምሳሌ በመሆኑ በክፍለ ከተማው የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። ቀደም ሲል የነበረውን የመንደሩ መጥፎ ገጽታ የበጎ አድራጎት ሥራውን ለመሥራት እንዳነሳሳው ይናገራል።
ጓደኞቹን በማስተባበር በደጃፋቸው አካባቢ በቆሻሻዎች የሚደፈኑ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን በማጽዳት ነበር ሥራውን የጀመረው። ናትናኤል ሥራውን እንደጀመረ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች የማይዘልቅ የወረት ሥራ በሚል ያንቋሽሹ እንደነበር ይገልጻል። አብዛኛዎቹ ግን እያበረታቱት እና እየደገፉት አገልግሎቱን እንዲያስፋፋ አድርገውታል። በዚህ ሞራል ያገኘው ወጣት ከጽዳት ሥራ ወደ ችግኝ ተከላ ይሸጋገራል።
በመጀመሪያ እራሱ በሚኖርበት ብሎክ ሃያ አራት መግቢያና መውጪያ ባሉ ክፍት ቦታዎች ላይ ችግኞችን እየተከለ መንከባከብ ይጀምራል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የአካባቢውን ገጽታ ይቀይራል። ያ ለአይን ይከብድ የነበረ ቦታ በአበቦችና በችግኞች አጊጦ የአይን ማረፊያ ለመሆን ይበቃል። የናትናኤልን ድንቅ ተሞክሮ የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎቱን እንዲያስፋፋ በሚሰጡት አስተያየት መሰረት በብሎክ ሃያ ሶስት፣ ሃያ አምስት፣ ሃያ ስድስትና ሃያ ሰባት ተመሳሳይ ሥራዎችን በመሥራት አካባቢው ማራኪ ገጽታ እንዲላበስ ያደርጋል።
ያገለገሉ የመኪና ጎማዎች እና የወዳደቁ ቁሳቁሶችን እያስጌጠ በመንገዶች ግራና ቀኝ በማስቀመጥ ለመንደሩ ልዩ ገጽታ ፈጥሯል። የመንደሩ ነዋሪዎች ሁሌም እንደሚያግዙት የሚናገረው ናትናኤል፤ አንዳንዶች በራሳቸው ፍላጎት ቀለም እንደሚገዙለት አንዳንዶችም የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ነግሮናል።
ናትናኤል ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በአካባቢው ያገኘውን የጉልበትም ይሁን የቴክኒክ ሥራ ሳያማርጥ ሠርቷል። የግለሰቦችን ግቢ እያስዋበ፣ ዛፎችን እየከመከመ ቢያንስ በወር እስከ ሁለት ሺህ ብር ያገኝ እንደነበር ገልጾልናል። ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ እየቆነጠረ ችግኞችን ገዝቶ ይተክላል። በአመዛኙ ግን ችግኞችን የሚገዛው እናቱ በሚያደርጉለት ድጋፍ እንደሆነ ይናገራል። በእናቱ ድጋፍ በርካታ ችግኞችን እየገዛ ተክሏል። የቀበሌው መስተዳድርም እንዲሁ ቀለምና ሌሎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችን እንደሚደግፉት ተናግሯል።
ናትናኤል አካባቢውን አረንጓዴ አልብሶ መንከባከብ ከጀመረ በኋላ እንደከዚህ ቀደሙ በድፍረት መንገድ ዳር የሚሸኑና ቆሻሻ የሚጥሉ ሰዎች አለመኖራቸውን ይገልጻል። እንደውም መንገዶች የአይን ማረፊያና መዝናኛ ሥፍራዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራል።
ናትናኤል አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው አካባቢውን በማጽዳትና የተከላቸውን ችግኞች በመንከባከብ ነው። ናትናኤል ዛሬ ጠንክሮ በመሥራት አካባቢውን ቀይሯል፤ በሰፈሩ ሰዎች ዘንድ ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። ለወረት ነው ሲሉት የነበሩ ሰዎችንም በሥራ አሳምኗቸዋል። ለዚህም የአካባቢው ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት የመንደራቸውን አንድ መንገድ ናትናኤል ጎዳና ብለው በስሙ ሰይመውለታል። በዚህም የበለጠ ኃላፊነት ስለጣሉበት የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጨምሮ ቢያንስ ከአንድ ኪሎሜትር በላይ በሚሸፍን ሥፍራ የተከላቸውን ችግኞች ሲንከባከብ ይውላል። የመንደሩ ሰዎችም በየደጃፋቸው ላይ ያሉ ችግኞችን ውሃ በማጠጣት ይተባበሩታል።
ናትናኤል የአረንጓዴ ልማቱን በሰፈሩ ተደራሽ ለማድረግ ተግቶ መሥራቱን ተከትሎ ሌሎች ወጣቶችም የእርሱን ተሞክሮ በመመልከት ግቢያቸውን በችግኞች የመሸፈን ዝንባሌ እየታየባቸው እንደመጣ ይናገራል። አሁን አካባቢው ከሌሎች መንደሮች በተሻለ የአረንጓዴ አሻራ ሽፋን የሚታይበት፤ ሞዴል መንደር እየሆነ መጥቷል።
ናትናኤል ከቀበሌ እስከ ከተማ አስተዳደር ባለው መዋቅር አምስት ጊዜ ያህል የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል። በተለይም በ2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዓለም ዓቀፍ የጽዳት ቀንን ሲያከብር ከክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እጅ የዋንጫ ሽልማት እንደተከበረለት ይናገራል።
የሰፈሩ ሰው በየሳምንቱ ረቡዕና ቅዳሜ እለት በሚያደርገው የጽዳት ዘመቻ ናትናኤል ሰዎችን በማስተባበርና ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ይህ የጽዳት ዘመቻ ሰዎች ለአካባቢያቸው ንጽህና ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል ይላል። የእርሱን ሥራ የሚደግፉ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ይናገራል።
ናትናኤል ከአረንጓዴ አሻራ እና መንደር ጽዳት ተሳትፎው በተጨማሪ ስልጠና ወስዶ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ እያስከበረ መሆኑን ይገልጻል። ለውጡ ለወጣቱ ተስፋ ይዞ እንደመጣ የሚናገረው ናትናኤል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሃያ ሰባት ዓመት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጫነውን ቀንበር ዳግም በህዝብ ጫንቃ ላይ ሊያሳርፍ የሚያደርገውን መፍጨርጨር መታገል እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
የአሸባሪ ቡድን ደጋፊዎች አዲስ አበባ ከተማን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚጎነጉኑትን ሴራ በማክሸፉ ሂደት እርሱም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ይገልጻል። ከልማት በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለጸጥታ ጉዳይ ነው። ችግኝ መትክል አካባቢን ጽዱና አረንጓዴ ማድረግ የሚታሰበው ቅድሚያ ሰላም ሲኖር ነው። ባለፉት አራት ወራትም ከየትኛውም ሥራ በላይ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አተኩሮ ሲሠራ እንደነበር ጠቅሷል። በዚህም በአካባቢው ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳይከሰት እዚህ ተደርሷል ይላል።
በከተሞች አካባቢ ወጣቶች አካባቢያቸውን በንቃት መከታተል ከጀመሩ ወዲህ ጥፋት ለመፈጸም ሲሰናዱ የነበሩ የአሸባሪው ቡድኑ ደጋፊዎች ተስፋ ቆርጠዋል፤ ስርቆት እና ህገወጥ ወንጀሎችንም ማስቀረት ተችሏል። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መልካም ተሞክሮ እንደሆነ ናትናኤል ተናግሯል።
በዚህ ወቅት ወጣቱ የአዲስ አበባ ከተማን ንጽህና እና ሰላም እያስጠበቀ መሆኑ ዲያስፖራ ወገኖችን በሚፈለገው ደረጃ ለማስተናገድ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው። አዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ችግር አለባት በሚል የሀሰት ዘገባ ሲያሰራጩ የነበሩ የውጭ ሚዲዎችንም ትዝብት ውስጥ የሚጥልና የሚያጋልጥ ነው።
አቶ ዳምጤ ማናየ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ጽዳት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የግንዛቤና ህብረተሰብ ተሳትፎ ቡድን መሪ ናቸው። የወጣት ናትናኤልን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ሲናገሩ፤ አካባቢን ማጽዳትና ማስዋብ ሲታሰብ ናትናኤል እና መንደሩ በሞዴልነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ስለአካባቢ ንጽህና ለህብረተሰቡ በቃል ግንዛቤ ከመስጠት ይልቅ የናትናኤልና የአካባቢውን ተሞክሮ ማስጎብኘት ስለጉዳዩ በደንብ ለማስረዳት ይጠቅማል ይላሉ።
ናትናኤል የአካባቢን መጥፎ ገጽታ መቀየር እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው። ወጣቱ የለወጠው መንደር ከዚህ በፊት ቆሻሻ ይበዛበት እንደነበርና በተለይም የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በቆሻሻ እየተሞሉ አላፊ አግዳሚውን የሚረብሽ መጥፎ ሽታ እንደነበራቸው ተናግረዋል። ናትናኤል ጓደኞቹን እያስተባበረ ማጽዳት ከጀመረ ወዲህ ግን ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል። እንደውም በየመንገዱ ዳር ችግኞችን እየተከሉ በመንከባከብ የአካባቢው ማህበረሰብ የሰፈሩን ንጽህና እንዲጠብቅ ጫና አሳድረዋል። ከዚህ በፊት ለአካባቢ ንጽህና ግድ የሌላቸው ሰዎች ትምህርት አግኝተው የመንደራቸው ተቆርቋሪ እንዲሆኑ ተጽእኖ ፈጥሮባቸዋል። አካባቢው በአሁኑ ሰዓት ለሌሎች መንደሮች ምሳሌ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
የወረዳው ጽዳት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የናትናኤልን የሥራ እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተለ አስፈላጊ የሆኑ የቁሳቁስ ድጋፎችን እንደሚያደርግለት ተናግረዋል። እስከ አሁንም በርካታ ያገለገሉ ጎማዎችን ከግለሰቦች በመሰብሰብ ለናትናኤል አስረክቦታል፤ ማስዋቢያ ቀለሞችንም እየገዛ መስጠቱን የጽህፈት ቤቱ የግንዛቤና ህብረተሰብ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ዳምጤ ተናግረዋል።
የሰፈሩን የጽዳትና እንክብካቤ ተሳትፎ በደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲ እንዲታወቅ በማድረግ የመንደሩ ወጣቶች በየጊዜው ያላቸውን አበርክቶ በማስተዋወቅ በናትናኤል አማካኝነት የምስክር ወረቀቶችን እንዲያገኙ ተደርጓል።
የመንደሩ ወጣቶች ከጽዳት ሥራቸው በተጨማሪ የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ አስተማማኝ ጸጥታ ያለው መንደር ፈጥረዋል። የአዲስ አበባ ከተማን ለማተራመስ ያሰፈሰፉ ጸረሰላም ሃይሎች እንዲህ አይነቱ የወጣቶች አደረጃጀት ተስፋ ያስቆረጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቱ በጽዳትና በጸጥታው ዙሪያ ተጨባጭ ለውጦች ማምጣቱ ወደ እናት አገራቸው እየገቡ ያሉት ዲያስፖራ ወገኖች ያማረ ቆይታ እንዲኖራቸው የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል። ለናትናኤል ንቃት የአካባቢው ወጣቶች ቅን ትብብርና የበጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ አጋዥ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ዳምጠው አካባቢን በማስዋብም ይሁን ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጡ ሂደት የመንደሩ ሰዎች ላደርጉት ንቁ ተሳትፎ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
እኛም እንዲህ አይነቱን ተሞክሮ ስናቀርብ በርካቶች ይማሩበታል ብለን በማመን ነው። በተለይም ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላምና ጽዳት በመጠበቅ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይገባቸዋል እንላለን። ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥር 6/2014