
አዲስ አበባ፡- በድህረ ጦርነቱ የሚዲያዎች ሚና በሁሉም አቅጣጫ የአገር ግንባታ ላይ መሆን እንዳለበት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በድህረ ጦርነት አውድ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር የተያያዙ እሳቤዎች ይንጸባረቃሉ። ሚዲያዎች ከሌሎች አጋራት ተሞክሮ በመቅሰም እነዚህ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ለአገር ግንባታ ያላቸውን ሚና በአግባቡ ሊወጡ ይገባል። እንደ ዶክተር ሳምሶን ገለጻ፤ በየትኛውም አገርና የዓለም ክፍል ጦርነት ነበረ። ከጦርነት በኋላ ደግሞ የሚዲያ ሚና በተለያየ መንገድ ሊታይ ይችላል። ከፖለቲካ አንጻር በብዙ አገራት እንደሚታየው ከጦርነት በኋላ አለመግባባቶች ይኖራሉ። ከጦርነቱ በኋላ ድርድር ከሌለ በልኂቃኑና እነርሱ በሚዘውራቸው ማህበረሰቦች መካከል የፖለቲካ ቅራኔ ይፈጠራል። ከዚህ በዘለለ ጦርነት ኢኮኖሚን ይጎዳል ያሉት ዶክተር ሳምሶን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኑሮው ውድነቱ እንደሚከሰት፤ ሥራ አጥ ዜጎችም እንደሚኖሩ አንስተዋል።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመንግሥትና የግለሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ ብዙ መሠረተ ልማቶች ስለሚወድሙና ጦርነቱ ላይም ብዙ ሐብት ስለሚፈስ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ ባሻገርም በማህበራዊ ጉዳዮች ማህበረሰቡ ውስጥ ጠባሳዎች እንደሚከሰቱና ቤተሰብ ሊጎዳ እንደሚችል እንዲሁም መፈናቀል ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ግንኙነቱ በአንድ አገር ጦርነት ሲኖር በዛው ልክ ጫናም ይኖራል
ብለዋል። ስለዚህ ሚዲያዎች በድህረ ጦርነት እነዚህን ችግሮች ማስገንዘብና መቀየር መቻል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በተለይም በአገር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራትና የተስፋ መንገድ ማሳየት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
የሚዲያው ሚና በአገር ግንባታ ይጠቃለላል ያሉት ዶክተር ሳምሶን፤ ይህ ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን፣ ማህበራዊውንና ዓለም አቀፍ ግንኙነቱን እንደሚዳስስ ጠቅሰዋል።
ከሚዲያ ሚናዎች ውስጥ አንዱ ማስተማር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተለይ በፖለቲካው ጉዳይ ላይ በሕዝብና በፖለቲካ ልኂቃኑ መካከል የሚፈጠረውን ዓለመግባባት ለመፍታትና ለመግባባት ተግባቦት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ዶክተር ሳምሶን፤ በድህረ አፓርታይድ ወቅት የደቡብ አፍሪካ ሚዲያዎች ሕዝቡ አንድ ላይ እንዲነጋገርና ያለውን ችግር ይፋ እንዲያወጣ ማድረጋቸውንና ጉዳዩም ውጤት እንደተገኘበት ለአብነት አንስተዋል።
“ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ጊዜ በኢኮኖሚ ተጎድታ ነበር። ሚዲያው በሕዝቦች መካከል አገራዊ ንግግር እንዲኖር አመቻቸ። አገሪቷም ተረጋግታ ወደ ተሻለ ኢኮኖሚ መምጣት ችላለች” ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር ይፈታል ብሎ መንግሥት ያስቀመጠው አገራዊ ምክክር ሚዲያዎች በአመቻችነት ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል። ምክክሩ ምን እንደሚመስል ህዝቡን በአግባቡ ማስገንዘብ እንደሚጠበቅባቸውም አስታውቀዋል።
የኢኮኖሚውን ጉዳይ በተመለከተም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ የተመታውን የጀርመን ኢኮኖሚ እንዲያገግም የጀርመን ሚዲያዎች በድህረ ጦርነቱ የነበራቸው ሚና ቀላል እንዳልነበር ጠቁመው፤ ከፖለቲካ ንትርክ ወጥተው ወደ ምርታማነት እንዲገቡ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚው እንዲሻሻልና ወደ ምርት መግባትና ችግርን መቋቋም እንዲቻል እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ሚዲያዎች በድህረ ጦርነቱ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በማህበራዊ ዘርፍ ጉዳይም እስራኤላዊያን ከናዚ ጭፍጨፋ በኋላ እንዴት እንዳንሰራሩ ተጨባጭ መረጃዎችን በማቅረብ ሰው ከጦርነቱ ወጥቶ ወደ መደበኛው ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴው እንዲገባ ማድረግ መቻል አለባቸው ብለዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥር 4/2014