የዘንድሮ የገና በዓል በዲያስፖራ ደምቋል። ኢግዚቢሽን ማዕከል፣ኢምግሬሽን ቲያትርና ሲኒማ ቤቶች በዲያስፖራው ተጥለቅልቀዋል።
‹‹ሁሉም በአገር ነው›› እንዲሉት በሁሉም የአገሪቱ ሥፍራዎች በጋራ እየተደሰተና እየተዝናና በዓሉን እያከበረ ይገኛል። የውጭ ኃይሎች በአገሩ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ በመቃወም ከጎኑም ለመቆም ቆርጦ ተነስቷል።
ቋንቋውና ግብሩም ስለ አገር በአንድነት ለመዘመር አንድ አካል ሆኗል። ዲያስፖራው አገሩ በእናት ጡት ነካሾች መጠቃቷ፤ ለዘመናት የገነባችው ሀብት ንብረቷ መውደሙ አስቆጭቶታል። እናም ዲያስፖራው የውጭ ኃይሎችን ሟርት አልሰማም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቡለትን ጥሪ በመቀበል እኔ አለሁልሽ ሊላት፤ ሊደግፋትና ቀና ሊያደርጋትም ባህር አቋርጦ ወደ አገር ቤት መጥቷል።
ከዚህ ወደ አገር ቤት ከገቡ ዲያስፖራዎች መካከል ወጣት ተስፋ ታደሰ የመጣው ከአሜሪካ ኒውዮርክ ሲሆን ዘንድሮ 35ኛ ዓመቱን ይዟል። ወደ አገር ቤት ሲመጣ የመጀመሪያው ነው። አማርኛ ባለመቻሉ ሙሉ በሙሉ የሚናገረው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው።
አባትና እናቱ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም የአሜሪካ ዜግነት እንዳለውም አውግቶናል። ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በውጭው ዓለም በገና በዓል አካባቢ የሚኖረውን እረፍት አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያቀረቡትን ወደ አገር ቤት የመግባት ጥሪ ተከትሎ እንደሆነም አጫውቶናል። እሱም መምጣቱ ደስታን እንደሰጠውና በአገር ቤት ያለውን ዕውነት ለማወቅ እንደረዳውም ይገልፃል።
አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ የተረጋጋና ሠላማዊ ቢሆንም በትላልቅ ዓለም አቀፍ መረጃ ማሰራጫ ተቋማት የሚሰማው ተቃራኒውን እንደነበረ ይናገራል።
ወጣት ተስፋ ሁሉ ነገር ተቀይሯል፣ ኢትዮጵያ በጣም እያደገች ነው ይላል። በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚያዊውና በፖለቲካው የደረሰችበት ግስጋሴ ሁለንተናዊ ለውጥና እድገቷ በነዚህ ተቋማት ሽፋን ሳያገኝ መቅረቱም እንዳስገረመውና ከአሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ቢኖርም የተዘገበበት መንገድ በእጅጉ የተጋነነ እንደነበርም መታዘቡን አልሸሸገም።
‹‹አሁን ላይ አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ተሸንፎ ወድቋል ቢሆንም ስጋት መሆኑ አይቀርም›› የሚለው ወጣት ተስፋ እሱን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያለ የዲያስፖራ ወጣት ማህበረሰብ ይሄን አሸባሪ ኃይል ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ አገር ቤት ካሉ ወጣቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራም ያስረዳል።
በጦርነቱ ለተጎዱ፣ ከቀያቸው ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚያደርግም አመልክቷል። ወጣት ተስፋ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ መንግሥትን እንዲደግፍና በሁሉም መስክ የበኩሉን እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል።
ወጣት ተስፋ እንደሚለው በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራና የአፋር ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች የጎበኙበት ሁኔታ ነበር። በጉብኝቱ እንደታዘበው ቡድኑ በብዙ ቦታዎች አስከፊ ጉዳት ማድረሱን ማየቱን ጠቅሷል። አፋር ውስጥ የተሰባበሩ የጤና ተቋም መገልገያዎች በከፊል የፈረሱ ህንፃዎች ተመልክቷል።
በዚህ በኩል የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብቷል። ድጋፉን ዘላቂና የተጎጂዎችን ችግር ፈቺ እንዲሆን ለማስቻልም በክልሉ በኢንቨስትመንቱ መስክ በሂደት የመሰማራት ሀሳብ እንዳለውም ገልጿል።
የ22 ዓመቷን ወጣት ሮዳስ ዮናስን ያገኘናት ከእናቷ ጋር ተዝናንታ ወደ ቤቷ (ማደርያ ሆቴል) ስትመለስ ኤግዚቢሽን ማዕከል አካባቢ ነው። ሮዳስም ከአሜሪካን ሉሳንጀለስ የመጣችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዲያስፖራው ያደረጉትን ጥሪ ተቀብላ ነው። ከእናቷ ጋር ብዙም የዕድሜ ልዩነት የሌላቸው ጓደኛሞች ነው የሚመስሉት። እንደነገረችን የወለደቻት በ22 ዓመቷ ነው።
አሁን ላይ ደግሞ 44 ዓመት ሆኗታል። አጋጣሚ ሆኖ እናቷም እሷም አሜሪካ ውስጥ በተለያዩ ግዛቶች ነው የተወለዱት። የአሜሪካን ዜግነትም አግኝተዋል። ሆኖም ሁለቱም ያደጉት የኢትዮጵያ የሆነውን ነገር በሙሉ ሳይዘነጉ ነው።
አማርኛ ቋንቋ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በመማራቸው አቀላጥፈው ይናገራሉ። በሙሉም ከአለባበስና ከስርዓት ጀምሮ ባህላዊ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ተግብረው እንዲያድጉ በመደረጉ አልዘነጓቸውም አሁንም እየተጠቀሙባቸው ይገኛል። የለበሱት የሀበሻ ቀሚስ ማሳያ እንደሆነም መገንዘብ ችለናል።
ወጣቷ ወደ አገር ቤት ሲገቡ ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸው ትገልፃለች። ሲገቡ የነበረውና እና እስካገኘናት እስከ በዓሉ ዋዜማ የነበረው እንክብካቤ መረጃ አሰጣጡ፣ መዝናኛ ቦታዎቹና የሚመገቧቸው ምግቦች ደስ የሚሉ እንደነበሩም ትጠቅሳለች።
‹ ‹በተለይ አዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ አበባ መስላ ተውባለች›› የምትለው ወጣቷ እናቷ የነገረቻትን ዋቢ በማድረግ ባለፉት ከሁለት 10 ዓመታት በላይ ታጥረው በመቀመጣቸው ለቆሻሻ ማከማቻና የወንጀል መፈፀሚያ የነበሩት ሰፋፊ ቦታዎች ወደ ማራኪና መዝናኛ ፓርክነት መለወጣቸው እንዳስደሰታትም አጫውታናለች። ‹‹ትምህርቴን ስጨርስ መጥቼ የምሰርገው አንድነት ፓርክ ውስጥ ነው›› ብላናለች።
መስቀል አደባባይ ከመዲናችን ውብ ሥፍራዎች አንዱ መሆን መቻሉን ማየቷን የጠቀሰችው ሮዳስ፤ በተለይ በአደባባዩ ያለው የአንድ መስኮት አዲስ የዲያስፖራ ጊዜያዊ ማዕከል ዲያስፖራው ቀድሞ ገና አገር ቤት ሳይገባ የሚፈራውን የአገልግሎት መጓተት እንዲሁም የእንግልትና የጊዜ ብክነት ችግር አስቀርቷል ብላ ታስባለች። የቅሬታ ምንጮችን መዝጋቱንም ተናግራለች።
ማዕከሉ ቋሚ ቢሆን ከመረጃ ጋር የተያያዙ የዲያስፖራውን ችግር ለዘሌቄታው እንደሚፈታም ሀሳብ ታቀርባለች። እናቷም እሷም መላውን የዲያስፖራ ማህበረሰብ ባሳተፈውና በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መሳተፋቸውንም አውግታናለች።
‹‹አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በገዛ አገሩና ወገኑ ላይ ጦርነት መክፈቱና ብዙ እልቂት ማድረሱ እጅግ አሳዝኖ እና አስቆጥቶኛል›› የምትለው ሮዳስ በተለይ አገር ቤት ያለው ወጣት ተደራጅቶ ይሄን ኃይል ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ በማድረስ ማስወገድ እንደሚገባውም መልእክቷን አስተላልፋለች።
ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት ከመጣበት አንዱ ምክንያትም በዚህ ቡድን የተጎዱ ወገኖችን መደገፍ በመሆኑ እሷም በዚሁ በኩል እንዲሁም የአሸባሪውን ቡድን ተግባር ተረድተውም ሆነ ሳይረዱ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረጉ ያሉ የውጭ ኃይሎችን በመቀነሱ ረገድ እንደምትሰራ ታስረዳለች።
በተለይ ደግሞ በውሸት እየተፈበረኩ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች በመሰራጨት የአገሪቷን ገጽታ የሚያጠለሹ ፕሮፓጋንዳዎች በመቀልበሱ ረገድ የምታደርገው አስተዋጽኦ የጎላ ይሆናል።
በአጠቃላይ ወጣት ሮዳስ የአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባም ሆነ የአገሪቱ ክልሎች ዲያስፖራው ለሚሳተፍበት ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ምቹ ሆነው ማየቷን ገልፃልን ሀሳቧን አሳርጋለች።
‹‹ሁሉም ነገር ሊሳካ የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው›› ያለን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሐመድ ነው። ወጣቱ ዲያስፖራ ቀድሞ መሥራት ያለበት እዚሁ የሰላም ጉዳይ ላይ መሆኑንም ወጣት ይሁነኝ ያሳስባል።
በሰላም በኩል እየሰራና ሰላሙን እየጠበቀ በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣውን የውጪ ኃይሎች ተፅዕኖ መቀነስ እንደሚገባውም ያሰምርበታል። ሰላም መጠበቅ ወታደር መሆን ማለት እንዳልሆነም ይጠቅሳል።
ሠላም መጠበቅ ማለት የጎረቤትና አካባቢ ግጭትን መጠቀም ለሚፈልጉ አካላቶች አሳልፎ ከሚሰጥ ድርጊት ራሱም መቆጠብ፣ መታቀብና መጠንቀቅ እንደሆነም ያስገነዝባል።
ወጣቱ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች የሚቀየሩት በመንግሥት ዕቅድና ተግባር እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በውጭ አገር ድጋፍና እገዛ ብቻ ሳይሆን በራሱ በወጣቱ ተነሳሽነት እውቀትና ተግባር ጭምር እንደሆነም ያመላክታል። ወጣቱ ዲያስፖራ በእያንዳንዶቹ የአገር ቤት ጉዳዮች ውስጥ በንቃት መሳተፍ መቻል እንዳለበትም ይጠቁማል።
ይሄ ማለት እራሳችውንና ወገናቸውን ለመቀየር መነሳት መቻል ማለት እንደሆነም ያስረዳል። አገር የምትለወጠው እኛ ስንለወጥ ነው የተለወጠች አገር ደግሞ እኛን ትለውጠናለች በማለትም አስተያየቱን ቋጭቷል ወጣት ይሁነኝ።
‹‹ዲያስፖራው በውጭው ዓለም ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ጫና የመመከት ኃላፊነት አለበት›› ሲል ሀሳቡን የጀመረው ወጣት አብይ ኃይለመለኮት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በወጣት ዘርፍ የወጣቶች ግንዛቤና ንቅናቄ ከፍተኛ ባለሙያ ነው። አብይ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሕግ ማስከበር ዘርፍ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ የነበረ መሆኑን ያስታውሳል።
በጦርነቱ ወጣቶች የአገር ፍቅር ስሜታቸው የተጋጋለ እንደነበርና ራሳቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት መድረሳቸውንም ይጠቅሳል።
‹‹አሸባሪው ኃይል ስጋት ነው›› የሚለው ወጣቱ ለስጋቱ የተጋጋለው የአገር ፍቅር ስሜቱ ሳይቀዛቀዝ ምንጊዜም ቢሆን መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት በሚገኘው ብሄራዊ አገልግሎትና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በመታገዝ የበለጠ ተጠናክሮ ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅበት ያስረዳል።
‹‹አሸባሪው ያፈረሰውን መልሶ መገንባትም ሌላ ጦርነት ነው›› ሲልም ለዚህኛውም የቤት ሥራ እንዲሁ እንደ ስጋቱ ታጥቆ መነሳት እንደሚኖርበትም ይገልፃል።
ከዳያስፖራው የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ሌላ በርካታ ነገር መኖሩንም ያወሳል። ቆይታቸው ለአንድ ሳምንትም ሆነ ለወር መንግሥት ከነሱ የሚጠብቀውን የማገልገል ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም ያሳስባል። ቤተሰባቸው የሚገለገሉበት አገር የምትደገፍበት የኢንቨስትመንት ሥራ ላይም መሰማራት ይጠበቅባቸዋል።
ዕድሉም የተመቻቸ ነው ብሏል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ ዓላማ አንዱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንቱ ዙሪያ በስፋት እንዲሳተፉ ማስቻልን መሰረት ያደረገ መሆኑን የሚገልፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ ናቸው።
በዓለም ዙሪያ ባሉ የውጭ አገራት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያኖች እንደሚኖሩ የሚጠቅሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ የዘርፉን የዲያስፖራ ተሳትፎ አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዲያስፖራ መካከል ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተሰማርተዋል።
የሚያንቀሳቅሷቸው ኢንቨስትመንቶች ከፍ እያሉ መጥተዋል። ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ የሚወስዱባቸው ዘርፎች መጠንም ዕድገት እያሳዩ መጥተዋል። ከሦስት ዓመት በፊት 54 ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ የተከፈቱ ቢዝነሶች የነበሩ መሆናቸውንም ያስታውሳሉ።
በቅርብ ወራቶችም 84 ፈቃድ የወሰዱበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰዋል። ለአብነት ያህል ኮቪድ የበርካታ ዘርፎችን እንቅስቃሴ ባስተጓጎለበት ባለፈው ዓመት ብቻ እንኳን ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የነበራቸው ወደ ዘርፉ የመሰማራት ተሳትፎ ሲቃኝ 35 ፈቃዶችን ወስደዋል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 5 ሺህ 100 ኢንቨስትመንቶች በዲያስፖራው ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። 30 ሺህ ያህል የሥራ ዕድሎችን መፍጠር መቻላቸውንም አመልክተዋል። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዲያስፖራው የአገር ቤት ተሳትፎ በኢንቨስትመንቱ ብቻ ሳይሆን ከባህር ማዶ ወደ አገር ውስጥ በሚላከው ገንዘብም እያደገ መጥቷል።
እነዚሁ ከአገር ውጪ በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እ.እ.አ በ2020 ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ማንቀሳቀሻ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላካቸው አብነት ይሆናል።
እኛም ወደፊት የሚመጡትም ሆነ ለገና በዓል ወደ አገር ቤት የመጡት የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ሁኔታዎችን ምቹ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ወጣቱ ዲያስፖራ በመልሶ አገር ግንባታው የሚያደርገው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥል በማለት ጽሑፋችንን ደመደምን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 29/2014