አባባ መርድ መንደሩ ውስጥ የታወቁ ህልም ፈቺ ናቸው..። እሳቸው ጋ ሄዶ ህልሙን ያላስፈታ አንድም ሰው አይገኝም። ስለእሳቸው የህልም ጥበብ ወሬ ነጋሪ ሆነው ለመንደሩ ሰው ወሬ የሚነዙ በርካታ ወሬኞች አሉ። ወሬኞች እሳቸውን በማስተዋወቃቸው ብቻ ለሳምንት ህልማቸው በነጻ ይፈታላቸዋል.።
የዚህ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ እትዬ ትብለጥ አንዷ ናቸው። እትዬ ትብለጥ ከመንደር መንደር፣ ከከተማ ከተማ እየዞሩ ስለ አባባ መርድ የሚመሰክሩ ናቸው። ‹የተናገሩት መሬት ጠብ አይልም፣ ቢበዛ በሶስተኛው ቀን አልያም በነጋታው ትንቢታቸው ይፈጸማል፣ በዚህ ጥበባቸው የመንደሩ ሰው ሁለተኛው እግዜር የሚል ስም ሰቷቸዋል› እያሉ በበሬ ወለደ የሚያወሩና የሚያስወሩ ናቸው።
አባባ መርድ እንደ እድሜአቸው መካሪና አስታራቂ ሳይሆኑ ዋሽቶ በማጣላት ምንዳ የሚፈልጉ ናቸው። አባትነታቸውን ለበጎ ሳይሆን ለነውር የሚጠቀሙ በበሬ ወለደ የቆሙ አዛውንት እንዲህም ናቸው።
በሽምግልናቸው ውስጥ ዘልቆ የገባ አንድ ነውር አለ፤ እሱም የገንዘብ ፍቅር ነው። ከእርጅናቸው ጋር የተስማማው ሸበቶ ጸጉራቸው እብለታቸውን ደብቆ ከእግዜር ጋር የቀረበ ወዳጅነት ያላቸው ጻድቅ ሰው አስመስሏቸዋል። በእድሜ ነቁጥ የተዋጀ አንቱነታቸው በእውነት እንጂ በግፍ የሚሞግተው አንድም ሰው የለም። ግን አባባ መርድ እንዲህ አይደሉም፤ በሽምግልናቸው ውስጥ እውነትና ፍትህ የለም።
ለገንዘብ ካላቸው ስር የሰደደ ፍቅር ህልም ሊያስፈታ ወደ ታዛቸው የመጣን ደንበኛ የሚጠይቁት የመጀመሪያ ጥያቄ ‹ምን ያህል ህልም ይዘህ መጣህ? ከትላንት ማታ ጀምረን አንድ ህልም ብቻ ይዞ የመጣን ደንበኛ ማስተናገድ አቁመናል› የሚል ነው። ይሄው የነዋይ ፍቅራቸው ራሳቸው ላይ ወጥቶ ከሰሞኑ ደግሞ በአዲስ ውሸት ተከስተዋል።
ወደ እሳቸው የመጣን ህልመኛ ሁሉ ‹ምን ላይ ሆነህ ነው ያለምከው? አልጋ ላይ ነው መደብ ላይ? ሲሉ መጠየቅ ጀምረዋል። በሰሞነኛው የእሳቸው ህግ መሰረት አልጋ ላይ ሆኖ ያለመና መደብ ላይ ተኝቶ ያለመ እኩል አይዳኝም።
አባባ መርድ ፍትህን አያውቁም..የእውነት ስፍራው የት ጋ እንደሆነ አልደረሱበትም። ከትላንት እስከዛሬ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ያልሰሩት ሸር የለም። ሲያልቅ አያምር እንዲሉ ዛሬም በመቁረቢያ እድሜአቸው በስተርጅና ህልም ፈቺ ሆነው ብቅ አሉ..። እንዴት ብዬ ሌሎችን ላግዝ ሳይሆን እንዴት ብዬ በሌሎች ላትርፍ የሚል የሽምግልና ቆፈን የተጠናወታቸው የእድሜ ነውረኛ ናቸው።፡
አዳፋ ብሉኳቸውን ወደ ትከሻቸው እያጣፉ..ከጸሀይ መውጫ ትይዩ በጎለቱት ባለመደገፊያ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ህልመኛ ይጠብቃሉ።
ህልመኛ ይመጣል..
‹ህልም እንዴት ነው? ይጠይቃሉ።
‹ምንም አይል ጥሩ ነው› ህልመኛ ይመልሳል።
‹ምን ላይ ሆነህ ነው ያለምከው? ማለቴ አልጋ ላይ ነው ወይስ አሊቤርጎ ሴት ጉያ ውስጥ? ህልም ሲፈታ ይሄ ሁሉ መታወቅ ይኖርበታል..ያለዛ ጥበቤም እሺ አይለኝ። ሲሉ የባጥ የቆጡን ለፈለፉ።
‹ሶፋ ላይ ሆኜ ነው› ህልመኛ መለሰ።
‹እንደዛ ከሆነ በምኞት ያለምክበትን አምስት ብር ያስጨምርሀል። ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ነገሮች ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርገናል። ፍንጭት ጥርሳቸውን እያሳዩት። ይቺ ንግግራቸው የተለመደች ናት፤ መደብ ላይ ሆኜ ነው ያለምኩት ቢባሉ እንኳን ያለምቾት እየተወራጨህ ያለምከው ህልም ውስጠ ግንዱን ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን ያስጨምርሀል ይላሉ እንጂ ካለምኞት የታለመ ስለሆነ ቀንሼልሀለው አይሉም። ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ዋሽተው ያተርፋሉ እንጂ ታምነው አያጎድሉም።
‹ህልሜን ይፍቱልኝ እንጂ ለብሩ ችግር የለውም› ህልመኛው መለሰላቸው።
አባባ መርድ እጅጉን አዘኑ..አስርና ሀያ ብር ትጨምራለህ ባለማለታቸው ተቆጩ።
እማማ ያሸርግዱ ከእትዬ ትብለጥ ቀጥለው የአባባ መርድ የህልም ደንበኛ ናቸው። አንዱም አይስመርላቸው እንጂ ከትላንት እስከዛሬ ያላስፈቱት ህልም የለም። ጠዋት..በጣም ጠዋት ገና ሰማይና ምድር ሳይላቀቅ፣ በውርጩ የአባባ መርድን ቤት ከሚያንኳኩ እንስቶች አንዷ እማማ ያሸርግዱ ናቸው።
‹‹እንዳው ዛሬ ምን ሊያሳየኝ ይሆን እንዲችው ሲያቃየኝ ነው ያደረው› ይላሉ እማማ ያሸርግዱ፤ አባባ መርድ ፊት ላይ ተነጥፈው። እግዜራቸው ይመስል ከጉድ እንዲያወጧቸው በመማጸን አይነት።
እማማ ያሸርግዱ ቀን ተኝተው ያለሙትን ሁሉ ያስፈታሉ ይባላል። ለህልም ካላቸው ፍቅር የተነሳ በቀን ሀያ አራት ሰዐት ነው የሚተኙት እየተባለ ይታማሉ። አባባ መርድ ቤት ሲመላለሱ እንዲችው ነግቶ ይመሻል።
የእማማ ያሸርግዱን እግር ተከትለው ሊነጋጋ ሲከጃጅለው እትዬ ትብለጥ ይመጣሉ። ሶስተኛው ሰው ሆነው የአባባ መርድን ደጅ በማለዳ ከሚረግጡት ውስጥ አቶ መንገሻ አንዱ ናቸው። አባባ መርድ ይሄን ስራ የጀመሩት በእኚህ ሶስት ሰዎች ህልም ላይ ተለማምደው ነው ይባላል።
እማማ ያሸርግዱ አባባ መርድ ቤት በመመላለስ ያተረፉት ነገር የለም፤ የጫማቸውን ሶል በከንቱ ነው የጨረሱት። በሁለት ዓመት ውስጥ ሀያ ስምንት ጥንድ ጫማዎችን ጨርሰዋል። ቀንና ለሊት እያለሙ፣ ቀንና ማታ እያስፈቱ..ብርድ ሳይሉ ውርጭ ከአባባ መርድ ደጅ እየቆሙ በሀብትና በሲሳይ ትሽቆጠቆጫለሽ፣ ይሄ ነው የማይባል ተድላ ቤትሽ ይገባል የሚለው ትንቢታቸው ግን የምጻት ቀንን ያክል ርቋቸው በተስፋ ስብራት ውስጥ ወድቀዋል።
በተስፋ ስብራታቸው ውስጥ ትላንትን ሲዳብሱት አጡት፤ ዛሬን ሲፈልጉት የለም። ነገም ለታሪካቸው ባዳ ሆኖ አገኙት። በአባባ መርድ ውሸት ታሪክ አልባ ሴት መሆናቸው ቆጫቸው። ለሀገርሽ ምን ሰራሽ? ለትውልድ ምን አደረግሽ? ብሎ ህሊናቸው ለሚያቀርብላቸው ጥያቄ መልስ መመለስ እንዳለባቸው ያወቁት ቆይተው ነበር።
ከስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ ሀገርና ህዝብን በታማኝነት ማገልገል ነው የሚለው ሀሳብ ወደ አእምሯቸው መጣ። በቀሪ ዘመናቸው አንድ መልካም ተግባር በመፈጸም በአባባ መርድ እብለት የባከነ ታሪካቸውን ለመመለስ ቆርጠው ተነሱ…። ሀገርና ህዝብ ለማገልገል ጊዜው አሁን እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተረዱ። በማስመሰል ትብታብ ተሸርበው ነበርና ካጎነበሱበት ቀና አሉ። የመጀመሪያ ተግባራቸው አባባ መርድን ማጋለጥ ይሆናል፤ ከዛም በምኞት ሳይሆን በትጋት የሚያምን ትውልድ መፍጠር።
‹ሰው በእስተርጅና..ዋሽቶ ማስታረቅ ሲገባው እንዴት ዋሽቶ ያጣላል? አበስ ገበርኩ እያሉ..ወደ ቤታቸው ሄዱ።
አዲስ አበባ፣ ቻይና በአምስት አሜሪካውያን ላይ አጸፋዊ ማዕቀብ ለመጣል መወሰኗን የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ገለጹ፡፡
ቃል አቀባዩ የአሁኑ የቻይና ማዕቀብ አሜሪካ በሐምሌ ወር በቻይና ባለሥልጣናት ላይ ለጣለችው ማዕቀብ ምላሽ መሆኑን አስታውቀዋል።
አሜሪካ የቻይና ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ የጣለችው ከሆንግ ኮንግ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል ባለችው ፖለቲካዊ ሴራ ውስጥ ተሳትፋችኋል በሚል መሆኑን ም አስታውሰዋል፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 22/2014