የአሁኑ ዘመን የአገራችን እግር ኳስ አፍቃሪ ከቀድሞ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ጋር በስቴድየም በአንድ ላይ ተቀምጠው ኳስ ሲመለከቱም ይሁን በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ሲያወጉ የአንድ ሰው ስም መነሳቱ አይቀርም። የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለረጅም ዓመታት በቅርበት የሚያውቁ የስፖርቱ ቤተሰቦች ብዙ ጊዜ ስለ ቀድሞ የእግር ኳስ ጨዋታ ሁኔታና ተጫዋቾች አንስተው ለአዲሱ ትውልድ ማጫወታቸው የተለመደ ነው።
እነዚህ አንጋፋ የስፖርቱ ቤተሰቦች ያለፈውን ጊዜ በሚገርም መልኩ ይተርካሉ። የተሰሙም ያልተሰሙም፣ አስደሳችም አስከፊም የነበሩ የእግር ኳሱ ገጠመኞችን መለስ ብለው ማስታወስ ይቀናቸዋል። ታዲያ እነዚህ የስፖርቱ ወዳጆች ሁሌም በአንድ ነገር ላይ ተመሳሳይ ናቸው።
‹‹በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ኣብዶ በመስራት ኢትዮጵያ ውስጥ የአስቻለው ደሴ አይነት ተጫዋች አላየንም›› ብለው መስማማት አንድ ያደርጋቸዋል። ‹‹አብዶ በአስቻለው ደሴ ጊዜ ቀረ›› ሲሉ የቀድሞ እግር ኳስ ተመልካቾች ሲያወጉ አዲሱ ትውልድ በመገረም ይሄ ሰው ማነው? እንደዚህ ሁሉም በአንድ ድምፅ ችሎታውን የሚመሰክሩለት ብለው መጠየቃቸው አይቀርም። በእርግጥ ይህ ባለድንቅ ተሰጥኦ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ብዙም አይነገርለትም። በ2000 ዓ.ም ኅዳር ወር በሐትሪክ መጽሔት ስለ አስቻለው ከተጻፈው ውስን መረጃና የቀድሞ እግር ኳስ አፍቃሪዎች አንደበት ከሚሰማው ወግ በዘለለ የተሟሉ ታሪኮችን የያዙ ሰነዶችንም እንደልብ ማግኘት ከባድ ነው።
አስቻለው ደሴ እግር ኳስን በትምህርት ቤት ደረጃ በመጫወት እንደጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ። ልዑል መኮንን በአሁኑ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት እግር ኳስን በመጫወት እንደጀመረ ይነገራል። በጊዜው የትምህርት ቤቶች ውድድር ትልቅ ፉክክርና ተመልካች እንደነበረ ይታወቃል።
አስቻለው የኳስ አብዶ ጥበብን ከልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ጀምሮ እንዳዳበረ ኃይሌ ካሴ በአንድ ወቅት ተናግሯል። ኃይሌ ሲናገር “የአስቻለው ደሴን ጎሎች ለማየት ሁሌም ከጎል ጀርባ እንቀመጥ ነበር። የሚገርመው ብዙ ጊዜ በረኛን አታሎ ነበር የሚያገባው ፤በመገረም ከጨዋታ በኋላ ያገባበትን ጫማ ለመንካት ወደ እሱ እንሄድም ነበር “ሲል በኢቢኤስ ስፖርት ዝግጅት ላይ እንግዳ በነበረበት ጊዜ ተናግሯል።
ስለ አስቻለው አብዶ ሲነሳ ኢትዮጵያ ራሷ አስተናግዳ ያነሳችው ብቸኛው የ3ኛው አፍሪካ ዋንጫ ባለታሪክ ሉቻኖ ቫሳሎ አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት የአስቻለው ደሴን አብዶ መቋቋም የሚችል ተጫዋችን እንደ መስፈርት ይጠቀም እንደነበር ይነገራል። በአንፃሩ ይሄ አብዶኛ ኮከብ ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች አገሩን ወክሎ በታላቁ መድረክ የመታየት ዕድል አለማግኘቱ ብዙዎች የሚቆጩበት ታሪክ ነው።
አስቻለው በ7ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንደሚጓዝ ተነግሮና ሁሉን ነገር አሟልቶ በመጨረሻ ሰዓት እነ ሸዋንግዛው አጎናፍር ከውጪ መጥተው ብሔራዊ ቡድኑን ስለተቀላቀሉ በመጨረሻ ሰዓት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መቀነሱን ብዙዎች በቁጭት ይናገራሉ።
አስቻለው ብዙዎች የሚደመሙበት የአብዶ ችሎታውን ይዞ የአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ብቃቱን ለዓለም ማሳየት አለመቻሉ ብቻም ሳይሆን በክለብ ደረጃ የተጫወተው ለአንድ ክለብ ብቻ መሆኑም ነው። አስቻለው አንድነት ለሚባል የነጋዴዎች ቡድን ብቻ በመጫወት ነው የኳስ ሕይወቱን የቋጨው።
ክለቡ በጊዜው በመርካቶ ነጋዴዎች የሚደገፍ የዘመኑ ክለብ የነበረ ሲሆን በ1960/70 ዎቹ ጠንካራ የነበሩት ክለቦች ብዙ ጊዜ ሊያስፈርሙት አስበው ነበር። ይሁን እንጂ የአንድነት ክለብ ሰዎች ባለመፍቀዳቸውና ‹‹አንተ ሌላ ክለብ የምትሄድ ከሆነ ቡድኑን እናፈርሰዋለን›› በማለታቸው በሌሎች ትልልቅ ክለቦች ማልያ ሳይታይ ቀርቷል።
አስቻለው ለሚወደው ክለብ ተጫውቶ እግር ኳስን ያቆመ ታማኝ ተጫዋች በመሆኑም ብዙዎች አሁንም ድረስ ይደነቁበታል። አስቻለው የእግር ኳስ ህይወቱ አልፋና ኦሜጋ የሆነውን ክለቡን ከመውደዱ የተነሳ እንዲያውም የሁለተኛ ልጁን ስም በቀድሞ ክለቡ መጠሪያ ‹‹አንድነት አስቻለው›› በማለት መሰየሙ ይነገርለታል።
ብዙ አስገራሚ ታሪኮች የሚወራለት አስቻለው ተመልካቾች ጭምር በእሱ አብዶ ተማምነው ይወራረዱ እንደነበረ ይነገርለታል። ከዚህ ጋር በተያያዘም አንድ አጋጣሚ እንደታሪክ ይነሳል። በአንድ አጋጣሚ አንድነትና ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ፣ እናም መርካቶ የሚገኙ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ይወራረዳሉ፣ ውርርዱ ይሄ ክለብ ያሸንፋል ፤ ይሸንፋል ብቻ አልነበረም፣ ጨዋታው በዚህ ውጤት ያልቃል የሚልም አልነበረም። አስቻለው ደሴ ጌታቸው ዱላን አልፎ ግብ ያስቆጥራል፤ አያስቆጥርም ነበር። የሚገርመው ነገር አስቻለው ሁለት ግቦችን ጌታቸው ዱላን አልፎ አስቆጠረና አስገራሚውን ታሪክ ፈፀመ።
ይሄ ብዙ የሚወራለት ነገር ግን ታሪክ እየዘነጋው የመጣው አብዶኛ ተጫዋች በውፍረቱም ይታወቃል። ይህ የሆነውም ክትፎና ቢራ ስለ ሚያዘወትር እንደሆነ ይነገራል። ያም ሆኖ ያለፈው ዘመን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቹን በአብዶው ሲያስታውሰው ይኖራል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የ2009 ዓም የሊጉን እጣ አወጣጥ ሥነሥርዓት ሲያከናውን ይህን አብዶኛ ተጫዋች በክብር እንግድነት አቅርቦት ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17/2014 ዓ.ም