በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ምዕራባውያን ተላላኪያቸውን የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ዳግም ለማንገስ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያላደረሱት ጫና የለም። በተለይም ወሮበላው ቡድኑ ደሴና ኮምቦልቻን ከያዘ በኋላ የምዕራባውያን ሚዲያዎች የተለያዩ የሀሰት ዘገባዎችን በማሰራጨት ሕዝብን ለማስበርገግ ሞክረዋል። ለአብነትም ‹‹አዲስ አበባ በአማጺው ቡድን ተከባለች፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ተግባር ሊፈጸም ይችላል፤ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በአማጽያኑ ጥቃት ስር ነው›› የሚሉና ሌሎችንም ሀሰተኛ የማሸበሪያ ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ዜጎቻቸው ከአዲስ አበባ እንዲወጡ በማድረግ ዓለም አዲስ አበባን የጦርነት ቀጣና አድርጎ እንዲስላት ብዙ ጥረዋል።
ምንም አንኳ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ እነርሱ በሚሉት ልክ ስጋት ባይኖርበትም፤ የአሸባሪ ቡድኑ ሰርጎ ገቦች ባገኙት ቀዳዳ እየተጠቀሙ የሽብር ተግባር እንዳይፈፅሙ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግ ነበር። በዚሁ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰላሳ አራት ሺ በላይ ነዋሪዎችን አሰልጥኖ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በማጣመር አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦችና ከሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲጠብቁ አድርጓል። በዚህም የውጭ ኃይሎችና የአሸባሪ ቡድኑን ድብቅ አጀንዳ ማክሸፍ ያስቻሉ ሥራዎች ተሰርተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን በሙሉ በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሉ ለሕግ አካላት የማቅረቡ ሥራ የሁሉም ኅብረተሰብ ኃላፊነት ቢሆንም በተለይም ወጣቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የታሰበው ሴራ እንዲመክን አገራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።
በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን የየአካባ ቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣቶችን አስተያየት እናስነብባለን። ወጣት በለጠ ጠሌ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፤ ወረዳ ሦስት፤ ቀጣና አምስት፤ ብሎክ ሰላሳ ሰባት አስተባባሪ ነው። በለጠ የትውልድ አገሩ ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ አካባቢ ነው። ቤተሰቦቹ በአሸባሪው ሕወሓት ምክንያት ስደትና እንግልት እንደደረሰባቸው ይናገራል።
አስራ ሁለት የሚሆኑ የቤተሰቡ አባላት አሸባሪውን ቡድን በግንባር እየተፋለሙ መሆናቸውን ገልጾልናል። እርሱም እዚህ ድረስ የተዘረጋውን የአሸባሪውን እጆች ለመቁረጥ ለተከታታይ አራት ወራት ከሰፈሩ ሰዎች ጋር ሆኖ የአካባቢውን ጸጥታ በማስጠበቅ ላይ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከተማዋን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ ሲመኙ የነበሩ የውጭ እና የውስጥ ኃይሎችን ተስፋ ያስቆረጠ ተግባር እየፈጸሙ እንዳለ ይገልጻል። በተለይም ወጣቶች ለከተማዋ የሰላም ስጋት ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በንቃት በመከታተል አዲስ አበባ ከተማ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላሟ የተረጋገጠ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን ይናገራል። እርሱም በሚኖርበት አካባቢ የመንደሩን ነዋሪዎች ከማስተባበር ጀምሮ ቀን በቀን የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
እንደ ወጣት በለጠ አስተያየት ነዋሪዎች ተደራጅተው አካባቢያቸውን መጠበቅ ከጀመሩ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ሊፈጸሙ የታሰቡ የሽብር ተግባራት ከሽፈዋል። ያም ብቻ ሳይሆን እንደ ስርቆት ጸብና መሰል የወንጀል ተግባራት ቀንሰዋል። በሥራ ምክንያት አምሽተው ወደ ቤታቸው የሚገቡ ሰዎች ከስጋት ነፃ መሆን ችለዋል። በካራ ቆሬ አካባቢ የሃይማኖት ግጭት በመፍጠር ኅብረተሰቡን ሊያውኩ የተሰናዱ አካላት እንደነበሩ የጠቀሰው በለጠ ይህንንም ችግር እልባት በመስጠት በሃይማኖት ሥም ሊፈጠሩ የታቀዱ ሴራዎችን ማክሸፍ መቻሉን ተናግሯል። በሰዓት እላፊ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን አስቁመው በመፈተሽ ወንጀል ነክ ጉዳዮችን አግኝተው ለፖሊሶች የማስተላለፍ ሥራ መሥራታቸውንም ነግሮናል።
በግንባር ለተገኘው ድል የደጀኑ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የገለጸው በለጠ የአሸባሪው ሕወሓትና የተላላኪው ሸኔ አባላት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያነጣጠረው የሽብር ተግባራቸው እውን እንዳይሆን በተለይም ወጣቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ትግል ከአካባቢያቸው አልፎ የአገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ‹‹ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት›› በድል እንዲቋጭ ያገዘ ነው፤ ግንባር ተሰልፈው የሕይወት መስዋዕትነት ከሚከፍሉ ወገኖች ጋር ሲነጻጸር ግን ያደረጉት ትንሽ እንደሆነ ወጣት በለጠ ተናግሯል። የአዲስ አበባ ወጣቶች አካባቢያቸውን ከመጠበቅ ባለፈ የተደረገላቸውን የእናት አገር ጥሪ ተከትሎ አንዳንዶቹ በስልጠና ላይ እንዳሉና አንዳንዶቹም በግንባር እየተፋለሙ መሆኑን ገልጿል።
ማህበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ቀንና ሌሊት መንደሩን እየጠበቀ ነው የሚለው በለጠ የሁሉም ሰው ተሳትፎና ንቃት ግን ተመሳሳይ አለመሆኑን ይጠቅሳል። አንዳንድ ግለሰቦች ከአጥር ግቢያቸው ውጪ መንደሩን ወጣ ብሎ የመቃኘት ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራል፤ በዚህ ወቅት ማሰብ ያለብን እንደ ግል ሳይሆን እንደ አገር መሆኑን የጠቀሰው በለጠ በቀበሌው አስተዳደር በኩል ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ ሊጠናከር ይገባል ይላል።
አስፈላጊውን ግብአት የማሟላት ችግር መኖሩንም ይጠቅሳል። ለአብነትም ሌሊት በጥበቃ ሥራ የሚሰማሩ አካላት ያለምንም ትጥቅ የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሶ አስተዳደሩ ከታጠቀ ኃይል ጋር ሊያሰማራቸው እንደሚገባ ይናገራል። ይህ ልምድም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ወጣት በለጠ አስተያየቱን ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ጸጥታ ለማረጋገጥ የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰድ ሲጀምርና ጸረ ሰላም ኃይሎች መፈናፈኛ ሲያጡ ያሰቡት አልሰምር ያላቸው ምዕራባውያንና ሚዲያዎቻቸው የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸት ሥራ መሠማራታቸውን አስታውሷል። ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንዲሉ ምዕራባውያን ሚዲያዎች የጸጥታ ችግር የሌለባትን አዲስ አበባ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ወድቃለች ማለታቸው አስቆጭቶት እንደነበር የገለጸው በለጠ አሁን የከተማዋ ሰላም በወጣቱ የነቃ ተሳትፎ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ መገኘቱ አስደስቶታል።
ሌላው አስተያየቱን የሰጠን ሳሙኤል እንባይብል ይባላል። የሚኖረው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት፤ ቀጣና አምስት፤ ብሎክ ሰላሳ ስምንት ነው። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አቅዶ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወረራውን ከአማራና አፋር ክልሎች ቢጀምርም መዳረሻው አዲስ አበባ ነው ይላል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ደግሞ ይህን አሸባሪ ቡድን በናፍቆት የሚጠብቁና ወደዚህ የሚያደርገውን ግስጋሴ እያዩ ከተማዋን ለመበጥበጥ ያሰፈሰፉ ጥቅመኞች መኖራቸው ይገልጻል። ምዕራባውያንና አሸባሪ ቡድኑ በመዲናዋ ላይ ያላቸውን ፍላጎት የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተደራጅተው አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ያመቻቸውን ስልጠና ሳሙኤል ያለምንም ማመንታት እንደወሰደ ይናገራል። ኅብረተሰቡ ውስጥ ተደብቀው ለጥፋት የተዘጋጁ ኃይሎችን በአይነ ቁራኛ በመከታታል የአካባቢውን ሰላም ሲያስጠብቅ መክረሙን ይገልጻል።
ምዕራባውያንና ሚዲያዎቻቸው አዲስ አበባን ኢላማ አድርገው የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማስተላለፋቸው ወጣቱ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ እልህ ያስያዘው ጥሩ አጋጣሚ ነው። በዚህም የጸጉረ ልውጦችን ማንነት በመጠየቅ፤ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን በመጠቆም፤ በመፈተሽ፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት፣ አንዳንዴም ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እስከ አስራ አንድ ሰዓት ቅኝት በማድረግ አካባቢያቸውን ይጠብቁ እንደነበር ይገልጻል። ጥበቃው እንኳንስ ለአጥፊ ሰዎች ይቅርና መጠጥ ቤት ለሚያመሹም ምቹ ስለነበር የመንደራቸው ሰላም ከመቼውም በላይ አስተማማኝ ነበር።
በተለይም መንግሥት ‹‹ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት›› በሚል የመጨረሻ ርምጃ መውሰድ ሲጀምርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በግንባር ተገኝተው ውጊያውን ሲመሩ ወጣቱ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሮበት እንደነበር ይገልጻል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከሰሜን ሸዋ እስከ ደሴ ያሉ ከተሞች ነፃ ሲወጡ የትግሉ ፍሬ መታየት በመጀመሩ እኛም ሥራችንን በደስታና በከፍተኛ ሞራል ነበር የምንሠራው ይላል ሳሙኤል። የአገር ሰላም ደፍርሶ፤ አንድ የአገር መሪ ከወታደሮች ጋር አብሮ እየዋለ፣ አብሮ እያደረ ሲያዋጋ እያየ እቤቱ ቁጭ የሚል ወጣት አይኖርም። በዚህ ምክንያት የአካባቢያችን ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ሰርጎ ገቦች ያሻቸውን እንዳያደርጉ መንደራቸውን በንቃት ጠብቀዋል። ዛሬ አሸባሪው ቡድን ከአማራና አፋር ክልሎች ተጠራርጎ መውጣቱ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የነበረውን ጫና ቀንሶታል። እንደዚያውም የከተሞች ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ በግንባር ለተሰለፈው የጸጥታ ኃይል ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን አዲስ አበባን ለመቆጣጠር መቃረቡን ሲገልጽ የነበረውና የውጭ ሚዲያዎችም መከበቧን ሲናገሩ የነበረው የአዲስ አበባ ፖለቲካዊ ጥቅም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። የአዲስ አበባ ወጣቶች በከተማዋ ኮሽታ እንዳይኖር በማድረግ ጠላትን ተስፋ የማስቆረጥ ሥራ መሥራታቸውን ወጣት ሳሙኤል ተናግሯል። ከተሜው በከተሞች አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን ጸረ ሰላም ኃይል መቆጣጠር መቻሉ የጸጥታ ኃይሉን ጫና እንደቀነሰለትና ድሉን እንዳፋጠነው ያምናል።
አዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ካሉ ትላልቅ ከተሞች የተሻለ ጸጥታ እንዳላት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ የተገለጸው እውነትነት ያለው ነው ብሏል። በግንባር ለተገኘው ድል የደጀኑ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን በመጥቀስም አንድ መሆን ከተቻለ ማንኛውንም ጠላት መመከት እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው መንደራቸውን መጠበቅ ከጀመሩ ወዲህ ከዚህ በፊት ይፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎች እየቀነሱ መሆናቸውን ሳሙኤል ተናግሯል። ይህ መልካም ተሞክሮ ተጠናክሮ ቢቀጥል የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ማስጠበቅ እንደሚቻልና በየጊዜው እየረቀቀ የመጣውን ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ለማስቀረት እንደሚረዳ ሳሙኤል ገልጿል።
የአገሪቱ ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ከማንም በላይ የሚጠቅመው ለወጣቱ ነው ያለው ሳሙኤል ወጣቱ የተፈጠረለትን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞ ፊቱን ወደ ልማት በማዞር የራሱንና የአገሩን ኢኮኖሚ የሚያሳድግበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈትለታል ብሏል።
ሰላምና ጸጥታን በማስከበር የታየው ውጤት በልማቱም እንዲደገም ወጣቱ የተጠናከረ አንድነቱን ጠብቆ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የመንግሥት ክትትልና እገዛ ያስፈልገዋል ብሏል።
ይትባረክ ቤኛ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ ወረዳ አራት ነዋሪ ነው። እርሱም ቀደም ብለው ሀሳባቸውን እንደገለጹት ወጣቶች የአዲስ አበባን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ከመሰሎቹ ጋር ተደራጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ ነው። አዲስ አበባ ከተማ በአሸባሪው ቡድን ተከባለች የሚለውን የውጭ ኃይሎች ቅዠት ከሰማ በኋላ ሰላሟን ለማስጠበቅ በእልህ እየሠራ መሆኑን ይትባረክ ይገልጻል። ወጣቱ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ በመሆኑ የትኛውም ሰርጎ ገብ ጥፋት ለመፈጸም እድል እንዳያገኝ አድርጎታል ይላል። ለውጡን ከማምጣት ጀምሮ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ እንደነበር የሚጠቅሰው ይትባረክ የአገሪቱን ሰላም በማረጋገጥ ሂደትም ከግንባር እስከ ደጀን ባሉ አደረጃጀቶች ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል።
ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አንድነታቸውን አጠናክረው ጠላቶቻቸውን እየመከቱ ባሉበት በዚህ ሰዓት እርሱም የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ እየሠራ ያለው ሥራ እንደሚያኮራው ተናግሯል። የአዲስ አበባ ሰላም መረጋገጥ ኢትዮጵያን በወሬ ለማፍረስ በየጊዜው የሀሰት ዘገባ ሲያሰራጩ የነበሩ የውጭ ሚዲያዎችን ያሳፈረ ነው ብሏል። ወጣቱ የጀመረውን አንድነት አጠናክሮ በመቀጠል ከኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ በኋላ በሚገኘው የልማት ትሩፋት ራሱንም አገሩንም ማሳደግ ይጠበቅበታል ብሏል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 15/2014