ማንነታቸውና ዘራቸው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሰዎች ለኢትዮጵያ ለነፃነት፣ አንድነት እና እድገት መስዋዕትነትን ቢከፍሉና አስተዋፅዖ ቢያበረክቱ ብዙም የሚያስገርም ላይሆን ይችላል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያላደጉና የዘር ሐረጋቸውም ከኢትዮጵያ የማይመዘዝ ሰዎች ለኢትዮጵያ በዋጋ የማይተመን አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ መስማት/ማየት አስደናቂ ነው። አንጋፋው እንግሊዛዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኬር ፔቲክ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ የዋሉት ውለታ የዚህ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል።
ሪቻርድ ኬር ፔቲክ ፓንክረስት ኅዳር 24 ቀን 1920 ዓ.ም ለንደን ከተማ ውስጥ ተወለደ። እናቱ የኢትዮጵያ ጠበቃና ባለውለታ የነበሩት እንግሊዛዊቷ የፀረ-ፋሺስት ንቅናቄ መሪ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ጸሐፊ ኤስቴል ሲልቪያ ፓንክረስት ሲሆኑ አባቱ ደግሞ ሲልቪዮ ኮሪዮ የተባሉ ኢጣሊያዊ ናቸው።
እናቱ ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ለኢትዮጵያ ጥብቅና የቆሙና ከፋሺስት መባረር በኋላም ለኢትዮጵያ ብዙ በጎ ስራዎችን የሠሩ የፀረፋሺስት ንቅናቄ መሪና የመብት ተሟጋች ስለነበሩ ሪቻርድ ፓንክረስት ስለኢትዮጵያ እየተነገረውና እየሰማ አድጓል።
ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ሪቻርድ ገና በዘጠኝ ዓመት እድሜው ወረራውን በመቃወም ከእናቱ ከሲልቪያ ጋር ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥቷል። በኢኮኖሚያዊ ታሪክ ጥናት (Economic History) መስክ ከለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት (London School of Economics) የዶክትሬት ዲግሪውን አግኝቷል። በ1948 ዓ.ም ሲልቪያ ፓንክረስት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግብዣ ቀረበላቸው። እርሳቸውም ግብዣውን ተቀብለው ከልጃቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መኖር ጀመሩ። ፓንክረስት ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ ‹‹ … ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሄድኩት በ1943 ዓ.ም ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ወስኜ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ ኢትዮጵያ የገባሁት ደግሞ በ1948 ዓ.ም ነው። በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበርኩ። ባለቤቴ ሪታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ትሰራ ነበር። በዚያ ጊዜ ትምህርት ቤት ሲዘጋ የበጋ እረፍታችንን የምናሳልፈው ለንደን ነበር …›› በማለት ተናግሯል።
ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (የኋላው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፤ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ማስተማር ጀመረ። ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ታሪክ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን ማድረግ ጀመረ።
በሂደትም በሌሎች ምሁራን ጭምር ያልተሞከሩ እጅግ ጠቃሚና ተደናቂ ታሪካዊ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን ቻለ። ሪቻርድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1962 ዓ.ም ከሌሎች ምሑራን ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም (Institute of Ethiopian Studies)ን መሰረቱ። ለአስር ዓመታት ያህልም የተቋሙ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
በተቋሙ ውስጥ አብረዋቸው የሰሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ስለፕሮፌሰር ፓንክረስት እንዲህ ብለዋል … ‹‹ … ከፕሮፌሰር ፓንክረስት ጋር ለስድስት ዓመታት ያህል አብረን ሰርተናል። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የኢትዮጵያን ታሪክ የያዘ ማዕከል ነው። ማዕከሉ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ነው … በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙና ስለኢትዮጵያ የተፃፉ መዛግብት ሰብስቧል … ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ኢትዮጵያን የሚወድ ሰው ነበር …›› እኚህ ሊቅ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ታሪክ ብቻ ሣይሆን ሌሎች የታሪክ ጉዳዮችንም መርምረዋል። በታሪክ ተመራማሪዎች እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠውንና ለመዘንጋት የቀረበውን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ታሪክ ዘርፍ ለማጥናት ግንባር ቀደሙ ሰው እርሳቸው ነበሩ።
ሰነዶችንም ሰብስበዋል። ይህ ደግሞ ከሌሎች የታሪክ ተመራማሪዎች ሁሉ ልዩ ያደርጋቸዋል። ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የነበረውን የኢትዮጵያን ታሪክ በዘርፍ በዘርፍ የመረመሩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ፣ ያልዳሰሱት ርዕሰ ጉዳይ እንደሌለ በቅርብ የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸውና ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።
የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ወደ እንግሊዝ ተመልሰው የነበሩት ፕሮፌሰር ፓንክረስት፣ ከጥቂት ዓመታት የእንግሊዝ ቆይታቸው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በምርምር ስራቸው በመቀጠል የኢትዮጵያ ባለውለታ ያደረጓቸውን ተግባራት አከናውነዋል። ፕሮፌሰር ፓንክረስት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ
(ስለ ጦር መሣሪያዎች፣ በሽታና ድርቅ፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ ንግድና እርሻ፣ ገንዘብ፣ የኢትዮጵያውያን የእጅ ሙያዎች፣ እንስሳትና አገልግሎቶቻቸው፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶችና ጥንታዊ ሥነ-ጥበብ …) 22 መጽሐፍትን ጽፈዋል፤ ከ17 በላይ ለሚሆኑ መጽሐፍት የአርትዖት ስራ ሰርተዋል፤ ከ400 በላይ የሚሆኑ ምሑራዊ ጽሑፎቻቸው ደግሞ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚገኙ ጋዜጦችና የጥናት መጽሔቶች ላይ ታትመዋል።
እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት የፋሺስት ኢጣሊያን አውግዘው ለኢትዮጵያ እንደተከራከሩ ሁሉ ፕሮፌሰር ፓንክረስትም ወረራ የኢትዮጵያን ነገሥታት ተግባራት ከሚዘረዝሩ መጻሕፎቻቸው ባሻገር የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሰራውን ግፍ የሚያሳዩ መጽሐፍትንና ጽሑፎችንም አበርክተዋል።
ፕሮፌሰር ፓንክረስት ለሥራ በተዘዋወሩባቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ከመናገር ቦዝነው አያውቁም ነበር። የኢትዮጵያን የጥናት ጉባዔዎች በማሰናዳት ተሣታፊ፣ አዘጋጅ፣ አርታኢ፣ አደራጅና አቅራቢ በመሆን የኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እንዲታወቅና ተቀባይነት እንዲኖረው ብዙ ደክመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክን ጨምሮ ሌሎች የማኅበራዊ ሳይንስና የስነ-ሰብዕ የትምህርት መስኮችን ከማቋቋም አልፈው የጥናት መስኮቹ ጠንካራ መሠረት እንዲይዙ ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል። ብዙ የውጭ አገር የታሪክ ጸሐፍትና ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ በማዛባትና በማመሳቀል ይታማሉ። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ግን በዚህ ዓይነቱ ተግባር ፍጹም የማይታሙና የኢትዮጵያን ታሪክ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጥልቀት የፃፉ የኢትዮጵያ ባለውለታ እንደሆኑ ለረጅም ዓመታት ያስተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መስክሮላቸዋል። ፕሮፌሰር ፓንክረስት ለኢትዮጵያ የነበራቸው ተቆርቋሪነት የአገሪቱን ታሪክ በማጥናትና በመፃፍ ብቻ የተገደበ አልነበረም። በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱ ብዙ ጥረት አድርገዋል።
ከነዚህም መካከል በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ወደ ኢጣሊያ ተወስዶ የነበረው የአክሱም ሐውልት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ክታብ፣ መስቀሎችና ሌሎች ቅርሶችም ለኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርገዋል።
ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ‹‹ … ፕሮፌሰር ፓንክረስት የአክሱም ሐውልት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ትልቅ ጥረት አድርጎ ተሳክቶለታል። ምንም እንኳ ውጤቱ እርሱ በሚፈልገው ልክ ባይሆንም ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱት የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱም በብርቱ ታግሏል። በተለያዩ አካባቢዎች ተዘርፈው ያገኛቸውን የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱም አድርጓል … ›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ለፕሮፌሰር ፓንክረስትና ለባለቤታቸው ወይዘሮ ሪታ ፓንክረስት ክብር በተዘጋጀ መጽሔት ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ‹‹ … የፓንክረስት ስም በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ዝግጅቶችና ሁነቶች በግንባር ቀደምትነት ተነስቷል። በሴቶች የመምረጥ መብት፣ የሠራተኛውን መደብ መብት በማስከበርና በፀረ-ፋሺስት ንቅናቄዎች እንዲሁም በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ስሙ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ አንፃር የፓንክረስት ቤተሰብ፤ እናት ሲልቪያ፣ ልጅ ሪቻርድና የልጅ ሚስት ሪታ ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ላይ በነበራት አይበገሬነት ተሳትፏል።
በድኅረ ጦርነትም ኢትዮጵያና ኤርትራ አብረው እንዲሆኑ ብዙ ጥሯል … ሪቻርድ ፓንክረስት ሙሉውን የሕይወት ዘመናቸውን ለኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ማዋላቸው እድለኞች ያደርገናል … ሪቻርድ የከፈቱት መስኮት በርካታ ኢትዮጵያውያን ታሪክን ሰፋ ባለ መልኩ መመልከት እንዲችሉ ያደረገ ነው … ›› ብለው ነበር። አንጋፋው መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ በበኩላቸው፤ ፕሮፌሰር ፓንክረስት ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይወለዱ ስለኢትዮጵያ በጥልቀት የሚያውቁ ታላቅ ሰው መሆናቸውንና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፕሮፌሰር ፓንክረስትን ማክበርና መዘከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የ‹‹ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት›› መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ከፕሮፌሰር ፓንክረስት ጋር ስለነበራቸው ትውውቅ እንዲሁም ስለባህርያቸውና አበርክቷቸው ሲናገሩ ‹‹ … ከፕሮፌሰር ሪቻርድ ጋር የምንተዋወቀው ገና በልጅነቴ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለሁ ነው። የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ሲቋቋም እርሳቸውና እኔ ከመስራች አባላቱ መካከል ስለነበርን በይበልጥ የመተዋወቅ እድል ያገኘነው በዚያ ወቅት ነው … በጋዜጠኝነትም ሆነ በአሳታሚነት በሠራሁባቸው ዓመታት ከበርካታ ኢትዮጵያውያንንና የውጭ አገራት ምሑራን ጋር የመተዋወቅ እድል አግኝቻለሁ፤እንደፕሮፌሰር ፓንክረስት ዓይነት ሰው ግን አጋጥሞኝ አያውቅም።
እስከመጨረሻዋ እስትንፋሳቸው ድረስ ሥራ እየሠሩ ነበር። ከሕልፈታቸው አምስት ቀናት ቀደም ብለው እናታቸው ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት ስለፋሺስት ኢጣሊያ ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በመጽሐፍ መልክ ለማሳተም እየሰሩ እንደሆነ የሚገልፅ መልዕክት ልከውልኝ ነበር። በአንድ ወቅት ጀርመን ውስጥ የሚኖር አጎቴ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን መጽሐፍ እንድልክለት ጠይቆኝ መጽሐፉን ገበያ ላይ አጣሁት።
መጽሐፉን እንዴት ማግኘት እንደምችል እርሳቸውን ስጠይቃቸው ‹መጽሐፉን አላውቀውም፤ማን ነው የፃፈው› ብለው ጠየቁኝ። እርሳቸው እንደፃፉት ስነግራቸው አስታወሱትና መጽሐፉ ማለቁን ነገሩኝ። ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ፕሮፌሰር ፓንክረስት ገና ወደፊት ስለሚሰሩት እንጂ ‹ይህን ሰርቻለሁ› ብለው እንደማያሰላስሉና እንደማይኩራሩ ነው … ፕሮፌሰር ፓንክረስት የቴዎድሮስን ዓይነት ወኔ እና የምኒልክን ዓይነት ብልሃት ያላቸው ታላቅ ምሁር ነበሩ …›› በማለት ተናግሯል።
የታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በፊልምና በፎቶ በመቅረፅ የሚታወቁትና በለንደን የኢትዮጵያ ቅርስ ማበልጸጊያ ማዕከል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ አለባቸው ደሳለኝ ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር የረጅም ጊዜ ትውውቅ እንዳላቸው ይናገራሉ። ‹‹ … ከእኔ ጋር የተዋወቅነውና ልብ ለልብ የተግባባነው የአክሱም ሐውልትን ለማስመለስ ዘመቻ ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት ነው። እኔም የዘመቻው ተሳታፊ ስለነበርኩ ተገናኝተን ተነጋግረናል። ሪቻርድ ፓንክረስት ረጋ ያሉና ነገሮችን በጥልቀት የሚመለከቱ ሰው ነበሩ። በወቅቱ መጽሐፎቻቸውን በስጦታ መልክ አበርክተውልኝ የኢትዮጵያን ቅርሶች በመጠበቅና በማሰባሰብ ላይ እንድበረታ ነግረውኝም ነበር።
ከዓመታት በኋላ ወደ ለንደን በመጡበት አጋጣሚ ከሊቀ መምህራን አበባው ይግዛው ጋር በመሆን ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል … በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ፎቶዎችንም አንስቻቸዋለሁ … በእኔ ግንዛቤ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ያጠና ሰው የለም። የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ በጥልቀት በመመርመር ጥናታዊ ስራዎችን ያበረከቱ ታላቅ ምሁር ናቸው። ከጽሑፍ ሥራዎቻቸው ባሻገር በባዕዳን የተዘረፉ የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ ጥረት ያደረጉና ለውጤትም የበቁ ሰው ናቸው። የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ አባል ሆነው ሐውልቱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ አድርገዋል።
የመቅደላ ታሪካዊ ቅርሶች አስመላሽ ማኅበርን በመመስረትም በከፍተኛ ቁርጠኝነት ይንቀሳቀሱ ነበር …›› በማለት ስለፕሮፌሰር ፓንክረስት ምስክርነት ሰጥተዋል። ፕሮፌሰር ፓንክረስት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ናቸው። የሦስተኛው ዓለም አገራትና ሕዝቦች ያጋጠሟቸውንና ወደፊትም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጥልቀት አስረድተዋል። ፕሮፌሰር ፓንክረስት ከትዳር አጋራቸው ወይዘሮ ሪታ ፓንክረስት ጋር አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቻቸውን ኢትዮጵያዊ በሆኑ ስሞች በመሰየምም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።
ወንዱን ልጃቸውን አሉላ፤ ሴቷን ደግሞ ታሪክ ብለው ሰይመዋቸዋል። [ታሪክ አሁን የምትታወቀው ሔለን በሚለው ስሟ ነው] … በጀግናው ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ ራስ አሉላ ስም የተሰየሙት የፕሮፌሰር ፓንክረስት ወንድ ልጅ፣ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ባለቤታቸው ኢትዮጵያዊት ናት። በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ፓንክረስት ‹‹ልጄ ኢትዮጵያዊት ሴት በማግባቱ በጣም ኩራት ይሰማኛል፤ ደስተኛም ነኝ።
በግማሽ ኢትዮጵያውያን የሆኑ የልጅ ልጆች አሉን›› ብለው ተናግረው ነበር። ስመ ጥሮቹ ኢትዮጵያውያን እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እና መንግሥቱ ለማ የሪቻርድ ሚዜዎች ነበሩ። ፕሮፌሰር ፓንክረስት የኢትዮጵያንና የእንግሊዝን ወዳጅነት ለማጠናከር የኢትዮ-እንግሊዝ ማኅበር (Anglo-Ethiopian Community)ን መስርተዋል። ላከናወኗቸው ወርቃማ ተግባራት ከኢትዮጵያና ከእንግሊዝ መንግሥታት እንዲሁም ከሌሎች አካላት ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።
ለኢትዮጵያ መቆርቆርንና መሥራትን ከእናታቸው ከወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት የወረሱት፣ ከ50 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ የደከሙት … ታላቁ የኢትዮጵያ ወዳጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ከእናታቸው የተቀበሉትን ኢትዮጵያን የማገልገልና ለኢትዮጵያ ጥብቅና የመቆም አደራ ታማኝ የኢትዮጵያ አገልጋይ በመሆን አደራቸውን ተወጥተው የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም፣ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ልጃቸው ዶክተር አሉላ በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ … አባቴ ሪቻርድ ፓንክረስት ከእግዚአብሔር የተሰጠው ተልዕኮ ኢትዮጵያን ማገልገል ነበር … አያቴ ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለማስከበር ያደረገችውን ተጋድሎ ለዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ለማሳወቅ ስትጥር አባቴ ከጎኗ ነበር። ለኢትዮጵያ ያላትን ታላቅ ፍቅርና አክብሮት ለልጇ እንዳስተላለፈችው ሁሉ አባቴ እኔንና እህቴን ሲያሳድገን ስለኢትዮጵያ ታሪክና ባሕል ያለውን አክብሮት አስተላልፏል።
እኔን ‹አሉላ› ብሎ ሲሰይመኝ እህቴን ደግሞ ‹ታሪክ› ብሎ ስም አወጣላት … አባቴ የኢትዮጵያን ታሪክ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ኅብረተሰብ ቀለል ባለ አቀራረብ ማቅረቡን ስላመነበት መጽሐፍትና የምርምር ሥራዎችን በተለያዩ መንገዶች አቅርቧል … በኃያላን የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስመለስ ያላሰለሰ ጥረት ያደርግ ነበር። የአክሱም ሐውልት ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ከደስታ ብዛት አልቅሶ ነበር …›› ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ ጠበቃና ባለውለታ የነበሩት የአንጋፋው እንግሊዛዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሰሯቸው በጎ ስራዎች እንዲሁም ያሳዩት ፍቅርና ክብር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖር ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2014