ሕወሓት ለሃያ ሰባት ዓመት በህዝብ ላይ የነበረው ንግሥና አብቅቶ እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተደረገው ትግል ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ከለውጥ ሃይሉ ያልተናነሰ ሚና ተጫውቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም:: በትግሉ ሂደት ሕወሓት መራሹ መንግሥት የሚታይበትን የመልካም አስተዳዳር ችግር የሚተቹና አካሄዱን እንዲያርም ሀሳብ ይሰጡ የነበሩ ወጣቶች የተለያዩ ስቃዮች ሲደርስባቸው ኖረዋል::
በተለይም ከሶስት ዓመት በፊት ሕወሓት በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያለውን የበላይነት ከስር መሰረቱ ለመንቀል በተደረገው ትግል ወጣቱ ከለውጥ አመራሩ ጋር በመሆን አገር አቀፍ ንቅናቄ አድርጎ ዛሬ የታየውን ለውጥ አምጥቷል:: በዚህ ትግል ውስጥ በተለይም የኦሮሚያና የአማራ ክልል ወጣቶች እየተናበቡ በመሥራት ለለውጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አይረሳም::
ሕወሓት እሳትና ጭድ አድርጌያቸዋለሁ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ህብረት በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት ያደረጉት እንቅስቃሴ እራሱን ሕወሓትን ሳይቀር ያስደመመው ክስተት እንደነበር የሚታወስ ነው:: በዚህ የተቀናጀ የትግል ሂደት በርካታ ወጣቶች የህይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ‹‹የአማራ ደም ደሜ ነው፤ የኦሮሞ ደም ደሜ ነው›› በሚል አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን አጋርነት እየገለጹ ዛሬ ለታየው ለውጥ አስተዋጽኦ አብርክተዋል::
ጽንፈኛው የአሸባሪ ቡድን ከስልጣኑ ተወግዶ መቀሌ በመመሸግ የአማራና የኦሮሞ ብሄረሰብን ለማጋጨት ብዙ ጥረቶችን ሲያደርግ ከርሟል:: አንዱን ጠላት ሌላውን ወዳጅ በማድረግ ለማለያየት ሞክሯል:: ግን አልተሳካለትም:: ዛሬም የኢትዮጵያ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን አጠናክረው የአሸባሪው ቡድንን ሀገር የማፈራረስ ተልእኮ እያከሸፉ ይገኛሉ::
አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በተለይም የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ወጣቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች ታቅፈው እየመከቱት ይገኛሉ:: የክልሉ መንግሥት ላስተላለፈው የክተት ጥሪ ወጣቶች የሰጡት ምላሽ ምን ይመስላል? ወረራውን ለመቀልበስ እያደረጉ ያለው ተጋድሎ ምን ይመስላል? በቀጣይስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከክልሉ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ ጌቱ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል::
እንደወጣት አባይነህ አባባል የአማራ ህዝብ በተለይም ወጣቱ በኢትዮጵያዊነቱ የሚደራደር አይደለም፤ በዚህ እይታውም እንደክልል ሳይሆን እንደ ሀገር እያሰበ የሚኖር ነው:: የቱንም ብሄረሰብ እንደጠላት ፈርጆ አያውቅም፤ በየትኛውም ብሄረሰብ እንደጠላት እፈረጃለሁ ብሎም አያስብም:: አሸባሪው የትህነግ ቡድን ግን ሀገር ማስተዳደር ከጀመረ አንስቶ በክልሉ እድገትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ በርካታ በደሎችን ፈጽሟል:: አሰራሩን የሚተቹ ወጣቶችን በየእስር ቤቱ እያጎረ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሞባቸዋል:: ጥቂት የማይባሉትን ገድሏል፤ በአንዳንዶቹ ላይም የአካል ጉዳት አድርሷል፤ ሌሎችንም ደብዛቸውን አጥፍቷል::
ትህነግ ለሃያ ሰባት ዓመት ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም በአማራ ወጣቶች ላይ የፈጸመው ግፍ ይለያል:: ቡድኑ ገና በርሃ እያለ አማራን በጠላትነት ፈርጆ የተነሳ እንደመሆኑ በዚያው ልክ ህዝቡ ላይ መከራ አድርሶበታል:: በተለይም ሃምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ከኮሌኔል ደመቀ ዘውዱ ጋር ተያይዞ በጎንደር ከተማ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከነሐሴ አንድ ጀምሮ ባህርዳር እና ሌሎች በርካታ የአማራ ከተሞችን ያደረሰ የተቃውሞ ንቅናቄ ሲደረግ ነበር:: በዚህ ሂደትም በርካታ ወጣቶች በየአደባባዩ በግፍ ተገድለዋል:: ይህ ትግሉ በከፍተኛ ደረጃ የተቀጣጠለበት ወቅት ይሁን እንጂ ከዚያም በፊት ወጣቱ ትግል ያደርግ ነበር:: እንግዲህ ትህነግ በመላው ሀገሪቱ እያደረሰ ያለው ግፍ ነው እያደገ መጥቶ ወጣቱ በተደራጀ መልክ ታግሎ ሊያስወግደው የበቃው::
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከስልጣን ተወግዶ መቀሌ ከከተመ በኋላ ከዚህ በፊት በአማራ ህዝብ ላይ በደብቅ ይሠራ የነበረውን ወንጀል በአዋጅ ለፍፎ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ፈጥሯል:: ቡድኑ ከአማራ ህዝብ ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ በማለት ከኢትዮጵያ ህዝብ የዘረፋቸውን የጦር መሳሪያዎች ታጥቆ ክልሉን በመውረር እግሩ በረገጠባቸው ቦታዎች ሁሉ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል:: የአማራ ህዝብ እንደጠላት የሚፈርጀው አካል ባለመኖሩ እራሱን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችለው ጠንካራ አደረጃጀት ባላደረገበት ሰዓት ወራሪው ቡድን በታጠቀው የጦር መሳሪያ ታግዞ በክልሉ ላይ በርካታ ጥቃቶችን ሰንዝሯል::
በዚህም የተነሳ አሸባሪ ቡድኑ በርካታ ንጹኋንን በጅምላ ጨፍጭፏል፤ የግለሰብ ድርጅቶችንና የመንግሥት ተቋማትን አውድሟል፤ ንብረቶችን ዘርፏል፤ እንሰሳትን ከመዘረፍ አልፎ ረሽኗል፤ ቤተእምነቶችን እንደምሽግ ተጠቅሞባቸዋል፤ አንዳንዶቹንም በከባድ መሳሪያ አውድሟቸዋል፤ ነዋየ ቅድሳትን ዘርፏል፤ ቅዱሳት መጻህፍትን አቃጥሏል፤ ህጻናትና የመነኮሱ እናቶችን ሳይቀር ደፍሯል፤ የአርሶ አደሩን ሰብል እያጨደ ወስዷል፤ ቀሪውንም አቃጥሏል፤ በአጠቃላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጆሎችን ሠርቷል::
የአሸባሪ ቡድኑ አድራጎት ያስቆጣቸው የአማራ ክልል ወጣቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ አደረጃጀቶች ታቅፈው አሸባሪ ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ትግል አድርገዋል:: በግንባር ተሰልፎ ከመዋጋት አስከ ደጀንነት አኩሪ ገድል እየፈጸሙ ይገኛል::
የክልሉ መንግሥት የህልውና ዘመቻውን ከማወጁ አስቀድሞ አንዳንድ ንቁ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ጥቃት ለመሰንዘር የሚንቀሳቀሰውን አሸባሪ ቡድን እየተደራጁ ይመክቱ ነበር:: በኋላም የክተት አዋጅ ሲታወጅ በሁሉም ዞኖች የሚገኙ ወጣቶች የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ምላሽ ሰጥተዋል::
በመጀመሪያ አካባቢ በተለይም በሰሜን ጎንደር ደባርቅ የነበረው የወጣቶች ተጋድሎ መላውን አማራ ያነቃቃ ነበር:: ከዚያም ወዲህ በደብረ ታቦር፣ በራያ ቆቦ፣ በወልዲያ፣ በደሴ በሸዋሮቢት በሰሜን ሸዋ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የወጣቶች ትግል አሸባሪውና ተስፋፊው ቡድን ያሰበውን ሁሉ እንዳይፈፅም አድርጎታል:: በዚህ ሁሉ ሂደትም በርካታ ወጣቶች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ የወጣቱ መነቃቃትና አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ በሚያደርጉት ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ታይቷል:: በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ግንባር ተገኝተው ማዋጋት መጀመራቸው የአማራ ክልል ወጣቶችን በከፍተኛ ሁኔታ አነቃቅቷቸዋል:: ለተገኘው ድልም ድርሻቸው የጎላ ነው::
የአማራ ክልል ወጣቶች በፋኖ፣ በልዩ ሃይል፣ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ታቅፈው ከጠላት ጋር እየተፋለሙ ከሚከፍሉት የህይወት መስዋዕትነት በተጨማሪ ትጥቅና ስንቅ በማቀበል፣ ቁስለኛ በማግለል፣ ደም በመለገስና የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ግንባር ቀደም ፈጻሚ በመሆን በህልውና ትግሉ ታሪክ የማይረሳው ሥራ ሠርተዋል::
ወጣቱ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች በመጠበቅና ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ጸጉረ ልውጦችን እያደኑ ለጸጥታ አካለት በማስረከብ ሊደርሱ የነበሩ ጉዳቶችን አስቀርቷል:: ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ ወደ ግንባር የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ሰብል በመሰብሰብና ቤተሰቦቻቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች በመርዳት ጭምር በህልውና ዘመቻው የጀርባ አጥንት መሆናቸውን አሳይተዋል::
በአንድም በሌላም መንገድ የክልሉ ወጣቶች ጠላትን አሳፍሮ ለመመለስ ከመንግሥት ሲታወጁ የነበሩ የክተት ጥሪዎችን ተቀብለው እንደ አንድ ሰው ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን አመርቂ ሥራዎችን ሠርተዋል::
በየአካባቢያቸው የመጣባቸውን ወራሪ ጠላት በመመከቱ ሂደት አኩሪ ጀብድ የፈጸሙ በርካታ ወጣቶችም ተፈጥረዋል:: አንዳንዶቹ ጀብድ ፈጽመው ለህይወታቸው ሳይሳሱ መስዋዕት ሲሆኑ አንዳንዶችም ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በጠላት ላይ አስገራሚ ድሎችን ተቀዳጅተዋል:: እጅግ በርካታ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ያልተነገሩ ጀብዶችን ፈጽመዋል:: ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በየአካባቢው የተደረገው ተጋድሎ በታሪክ ማስታወሻ ላይ ሰፍሮ ለመጪው ትውልድ የሚቀመጥ፤ የታጋዮቹን ጀብድም የሚዘክር ሆኖ ይሰነዳል::
አሸባሪው ቡድን አማራን እንደጠላት ፈርጆ ጥቃት በመክፈት የክፋት ሥራዎችን ይሥራ እንጂ የትኛውንም ብሄረሰብ በአቅራቢያው ቢያገኝ መሰል የሽብር ሥራ ሳይፈጽመበት ይቀራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው:: ለዚህም በአፋር ክልል ላይ የፈጸመውን ወንጀል ማስታወስ በቂ ነው::
ዞሮ ዞሮ አሸባሪው ቡድን መከላካያ ሰራዊት ላይ ጫና በማሳደር ዳግም ወደ ሃላፊነት ለመምጣት ያደረገውን ግስጋሴ የአማራ ወጣቶች በተለያዩ አደረጃጀት ታቅፈው በጥምር የጸጥታ ሃይሉ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለክልላቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገራቸው ህዝቦች ነጻነት ሲሉ ተዋድቀዋል:: የአፋር ወንድሞቻችንም ተመሳሳይ ሥራዎችን በመሥራት የዚህን የህዝብ ጠላት ቅስም መሰባበር ተችሏል::
አሸባሪ ቡድኑ የሚሠራው የራሱን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ፍላጎት ለማሟላት ነው:: ሱዳን፣ ግብጽ፣ አሜሪካና ከፊል አውሮፓውያን ከጦርነቱ ጀርባ አሉበት:: ይህንን ፍላጎት የአማራ ወጣቶች በደንብ የተረዱ በመሆናቸው የተልዕኮ ጦርነት በመያዝ መንደራቸው ድረስ መጥቶ ሊያጠፋቸው የተነሳውን ባንዳ ለመደምሰስ ቁርጠኞች ሆነዋል::
የአማራ ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከሌሎች የክልል ልዩ ሃይሎችና ሚሊሻዎች ጋር በመሆን በዚህ የህልውና ትግል ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ናቸው:: ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ይህንን ወራሪና ቅጥረኛ ቡድን ያሰበውን እንዳይፈፅም አድርገውታል::
ጦርነቱ ከአስከፊነቱ ጎን ለጎን ይዟቸው ከመጣው መልካም ነገሮች ውስጥ አንዱ በክልልም ይሁን በሀገር ደረጃ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ አንድነቱን አጠናክሮ ጠላቱን ለመመከት ሆ ብሎ እንዲወጣ አድርጓል:: በአሁኑ ሰዓት የክልሉ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን አጠናክረው ጠላታቸውን እንዲመክቱ አስችሏቸዋል::
ህግ የማስከበሩ ሂደት አሽባሪው የሕወሓት ቡድን የኢትዮጵያ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ፤ ኢትዮጵያን ለመውረር ያሰፈሰፉ የውጭ ሃይሎች እጃቸውን እስከሚሰበስቡ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል:: የአማራ ክልል ወጣቶችም እስከመጨረሻው ድረስ የትግሉ አካል ናቸው::
አሸባሪው ቡድን በወረራ በያዛቸው ቦታዎች በመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል ይህንን ከነበረበት በተሻለ ደረጃ ለመገንባት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል:: በመልሶ ግንባታው የክልሉ ወጣቶች የሚያደርጉት ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የወደሙ ተቋማትን ወደነበሩበት ለመመለስ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይታመናል:: አሸባሪ ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልል ላይ ያደረሰው ጥቃት በሀገር ላይም እንጂ በክልሎቹ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት አይደለም::
ዓላማው ኢትዮጵያን የማፈራረስ እስከሆነ ድረስ ሌሎች አጎራባች ክልሎች ቢኖሩ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም:: እንደውም ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳን ሃይል የአፋርና አማራ ክልል ወጣቶች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ተጋድሎ ማድረጋቸው ለክልላቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦች የከፈሉት መስዋዕትነት ነው:: ስለዚህ የወደሙትን መሰረተ ልማቶች ወደ ነበሩበት መመለሱ ለአማራና አፋር ክልሎች የሚተው ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው::
የክልሉ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች በሙሉ መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል ሀገራቸውን ከገጠማት አደጋ መታደግ ይጠበቅባቸዋል:: መከላከያ ሠራዊት እጅግ ግዙፍ ተቋም ነው:: የቴክኖሎጂ እውቀትን የሚጠይቁ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የሚገኙበት ነው፤ ከዚያም ውጭ በርካታ ሙያዎች በስሩ አሉ:: ለዚህ ደግሞ የተማሩ ወጣቶች ያስፈልጋሉ:: ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ብቻቸውን የሰራዊቱን ቁመና ምሉዕ ሊያደርጉት ስለማይችሉ ወጣቱ የዚህ እድል ተጠቃሚ በመሆን በአንድ በኩል ሀገሩን ከጠላት መከላከል ይችላል፤ በሌላ በኩልም ከቴክኖሎጂዎች ጋር እየተዋወቀ አቅሙን ያሳድጋል::
የክልሉ ወጣቶች አሁን እያደረጉ እንዳለው በየአካባቢያቸው ያሉ የዘማች ቤተሰቦችን በሁሉም ዘርፍ በማገዝ ደጀንነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው፣ አካባቢያቸውን በንቃት መጠበቅ እንደሚገባቸው ወጣት አባይነህ ጥሪ አስተላልፏል:: በወራሪው ቡድን ተይዘው ነጻ በወጡ አካባቢዎች እየተቆረጡ ቀርተው በየጉራንጉሩና በየገበሬው ቤት ተሸሽገው ያሉትን ተዋጊዎች ወጣቱ እየተከታተለ ለጸጥታ ሃይሉ ማሳወቅ ይጠበቅበታል ብሏል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2014