አሸባሪው ቡድንና ጋላቢዎቹ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በተለያዩ ዘርፎች ግንባሮችን ከፍተዋል፡፡ የእናት ጡት ነካሽ የሆነው የትህነግ አሸባሪ ቡድን የተልዕኮ ጦርነት ተቀብሎ ኢትዮጵያን ሲወጋት፤ አይዞህ ባዮቹ አሜሪካና ምእራባውያን ደግሞ የኢኮኖሚ፣ የሚዲያ ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ ጫና በማሳደር የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማንበርከክ እየተረባረቡ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው የተከፈተባቸውን ሁሉን አቀፍ ጦርነቶች እንደአመጣጣቸው ለመቀልበስ እየተፋለሙ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ ትምህርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት ትምህርት ዘግተው የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እንዲሰበስቡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የሰብል ስብሰባው መንታ ዓላማዎችም፤ አንደኛ አዝመራዬን ልሰብስብ ሳይል ለአገሩ ሕይወቱን ለመስጠት ግንባር የከተተውን አርሶ አደር አለንልህ፤ ከጎንህ ነን ለማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው አዝመራን በወቅቱ ሰብስቦ ጎተራ በማስገባት በኢኮኖሚው ላይ የተከፈተውን ሌላ የጦር ግንባር ለመመከት ያለመ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ውድቀት የሚናፍቁት ምእራባውያንና ሚዲያዎቻቸው ታዲያ እንደለመዱት ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት ቤቶችን ዘግቶ ተማሪዎችን ለጦርነት እያዘጋጀ ነው›› በሚል ነበር የዘገቡት፡፡ የትምሕርት ሚኒስቴርን ውሳኔ ተከትሎ ህዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ቁጥራቸው ከሰላሳ ሺ በላይ የሚደረስ የአዲስአበባ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተገኝተው የሥራ መመሪያ በመቀበል አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡
‹‹ዘመቻ በትምሕርት ልማት ግንባር›› በሚል መርህ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ንቅናቄ ትኩረቱን ሰብል በመሰብሰብ ላይ ያደረገ ቢሆንም ሌሎች ተጓዳኝ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ማለትም ደም በመለገስ የዘማች ስንቅ በማዘጋጀት፣ ችግኞችን በመንከባከብ ወዘተ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል፡፡ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ ›› እንዲሉ በእጅ ያለው ሀብት እንዳይባክንና አገር የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የተከፈተውን የኢኮኖሚ ግንባር በአሸናፊነት መወጣት ያስፈልጋል፡፡
በእለቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለዘማቾቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ክብርት ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በግንባር እየተዋደቁ ያሉት ትምህርት እንዳይቋርጥና የተማረ ትውልድ እንዲኖር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የትምህርቱ ማሕበረሰብም በግንባር ለሚፋለመው የጸጥታ ሃይል እያደረገ ያለው አጋርነት የሚያኮራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከቀናት በፊት የአዲስአበባ ከተማ ተማሪዎችና መምህራን ለመከላከያ ሠራዊቱ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብ መርዳታቸውን ከንቲባዋ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ድጋፍ አሁንም በተለያዩ ተግባራት ሊጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የትምሕርት ሚኒስቴር ውሳኔን ተከትለው ተማሪዎችና መምህራን የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ለመሰብሰብ፤ ደም ለመለገስ፣ ስንቅ ለማዘጋጀትና የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀታቸው ኢትዮጵያን ለማሻገር ያላቸውን ቁርጠኝኘት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገርና ቀጣይ አገር የሚመራ ትውልድ ለማፍራት ተማሪዎች ትምሕርታቸውን መማር እንዳለባቸው የተናገሩት ከንቲባዋ ጎን ለጎን ኢኮኖሚን በሚገነቡ የልማት ሥራዎችና የኢትዮጵያን ሰላምና ጸጥታ በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ መሳተፋቸው የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተከፈተውን ዘመቻ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በሁሉም ዘርፍ የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ሊመክት እንደሚገባ ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡ የአረሶአደሩን ሰብል መሰብሰብም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመገንባት አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ሀሰተኛ መረጃ እያስተላለፉ የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሹ ሚዲያዎችን ማጋለጥም ሌላው የትግል አቅጣጫ እንደሆነ ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ተማሪዎች ብርቱና ጠንካራ ሆነው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ መታጠቅ የሚያስችል እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ትምሕርት ሚኒስቴር ተማሪዎች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ ኢኮኖሚውን እንዲገነቡ ያስተላለፈውን የአንድ ሳምንት ዘመቻ፤ የውጭ ሚዲያዎች መንግሥት ትምህርት ዘግቶ ተማሪዎችን ለጦርነት እያዘጋጀ ነው በሚል መዘገባቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎችና ከጀርባ ያሉ ጋላቢዎቻቸው ተማሪዎች የተቀደሱ ተግባራትን ለማከናወን በተዘጋጁ በዚህ ሰዓት የሀሰት ዘገባ እያሰራጩ መሆኑ ምን ያህል ስም የማጠልሸት ዘመቻ ላይ እንዳሉ የሚሳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተማረ ትውልድን ለማስቀጠል የዘመተ የጸጥታ ሃይል እያላት ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ወደ ጦር ግንባር የሚዘምቱበት ምክንያት እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ዘገባ አገሪቱ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንዳለባት ለማሳየት የተፈለገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘርፈ ብዙ ጦርነት ለመቀልበስም ሁሉም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን ሊያከናውን ይገባል ብለዋል፡፡ የተዘጋብንን የኢኮኖሚ ግንባር በጠነከረው ክንዳችን በላባችንንና በድካማችን ለመገንባት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች የሚደረግላቸው ሽኝት በምግብ ራስን ለመቻል፣ የዘማች ቤተሰቦችን ለማገዝ፣ ሰብል ለመሰብሰብ፣ ደማቸውን ለመለገስና ኢትዮጵያም እንደማትፈርስ ለማሳየት ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትገነባው በተባበረው የልጆቿ ክንድ እንጂ በልመና አለመሆኑንም መልእክት የሚያስተላልፍ ዘመቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክብርት ከንቲባዋ በንግግራቸው ወርቅ በእሳት ተፈትኖ የሚያስደንቅ ውብ ጌጥ እንደሚሆን ሁሉ በፈተናው የምንወድቅ ሳንሆን የምንቆም ሕዝቦች ነን፡፡
ፈተናው የሚበትነን ሳይሆን ከብረት ይልቅ ጠንክረን እንድንቆም የሚያደርገን፤ የበለጠ አገራችንን እንድናበለጽጋት እልህ ውስጥ የሚያስገባን፤ አርቀን እንድናይና እንድንሰባሰብ የሚያርገን ነው ብለዋል፡፡
መሪያችሁ የዘመተላችሁ እድለኛ ትውልዶች ስለሆናችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል ያሉት ከንቲባዋ፤ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና የጸጥታ ሃይሎች በግንባር የሚፋለሙት እናንተ ትምህርታችሁን እንዳታቋርጡ ነው ብለዋል፡፡ ትምህርት ዘግተን ወደ ጦርነት የሚያስገባን ምክንያት አለመኖሩን የውጭ ሚዲያዎች ሊረዱ ይገባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትምሕርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለጦርነት ትምህርት ዘጋ ብለው የተሳሳተ መረጃ የሚያስተላልፉ የውጭ ሚዲያዎችን በማውገዝ ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ የትምሕርት ሚና በእውቀት የሚመራ ማሕበረሰብ መፍጠር እንዲሁም ሕይወት በማስቀጠልና የእለት ተእለት ኑሮን ማቅለል የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁንና ትምህርት ያለሰላም ሰላምም ያለትምህርት ህልውና ሊኖራቸው አይችልምና የትምህርት ማሕበረሰቡ የሚያበረክተው የሰላም አስተዋጽኦ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አሁን ያለንበት ጊዜ ከየትኛም ጊዜ በተለየ አገር የማዳን ሃላፊነት በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የተጣለበት ወሳኝ ወቅት እንደመሆኑ በተደራጀ ሕብረትና አንድነት ሆነን አገር የማዳኑን ተግባር የምንፈጽምበት ሰዓት ነው ብለዋል፡፡
መምህራን ተማሪዎችና በአጠቃላይ የትምሕርት ማሕበረሰቡ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና መወጣት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ማሕበረሰቡ ባለፉት ጊዜያት መከላከያ ሠራዊቱን ሲደግፍ እንደነበረና አሁንም የዘማች ቤተሰቦችን ለመርዳት ለአንድ ሳምንት ትምህርት በመዝጋት በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ በእውቀት የበለጸገ የሰው ሀብት ከማፍራት አንጻር ትምህርት ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት ሃላፊው አገርን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መማር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የትምህርቱ ማሕበረሰብ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የዘማች ቤተሰቦችን ለማገዝ እንዘምታለን ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን፣ የዘማች አርሶ አደር ሰብል መሰብሰብ እና ቤተሰቦቻቸውን ማበረታታት፣ የደም ልገሳ ማድረግ፣ ችግኞችን መንከባከብ፣ ቆሻሻ አካባቢዎችን ማጽዳት ትኩረት አድርገው የሚሠሯቸው ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የትምህርቱ ማሕበረሰብ ላሳየው በጎ ምለሻም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመጡ ተማሪዎችን አስተያየትም ተቀብሏል፡፡ ተማሪ ቢኒያም ደምሴ የኮከበ ጽብዓ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡ የአገርን ህልውና ለማስከበር ግንባር የተሰለፉ አርሶ አደር ወገኖቹን ሰብል ለመሰብሰብና የደም ልገሳ ለማድረግ መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡
ይህን በማድረጉም አገሩን ከገጠማት አደጋ ለማውጣት የራሱን አሻራ እንዳስቀመጠ ይሰማዋል። አገርን ለማዳን ሁሉም ሰው ጦር ግንባር መገኘት እንደሌለበት የገለጸው ቢኒያም የደጀንነት ሥራዎችን በመሥራት ለኢትዮጵያ አሸናፊነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻል፡፡
በሰላም ወጥነትን የምነገነባውና የምንማረው የጸጥታ ሃይሉ በሚከፍለው መስዋዕትነት ነው ያለው ቢኒያም እነርሱን ማገዝና ማበረታታት የደጀኑ ሕዝብ ሃላፊነት ነው ይላል፡፡ የትምህርቱ ማሕበረሰቡም የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱ አገርን ለማዳን የሚደረገውን ርብርብ የሚያግዝ ነው፡፡
መንግሥት ትምህርት ዘግቶ ተማሪዎችን ለጦርነት እያዘጋጀ ነው የሚለው የውጭ ሚዲያዎች ዘገባ ሀሰተኛ መረጃን እያስተላለፉ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሠሩ መሆኑን በሚገባ ያረጋገጠበት ሁኔታ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
ሀሰተኛ ሚዲያዎችን ማጋለጥም ከተማረው ክፍል የሚጠበቅ ሌላው ግንባር ሊሆን እንደሚገባ ገልጿል፡፡
ሌላዋ አስተያየቷን የሰጠችን ከእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የመጣችው ሂክማ ሲራጅ ነች፡፡ አገር ማለት ሰው ነው የምትለው ሂክማ በግንባር ለሚፋለመው የጸጥታ ሃይል ደጀን መሆን ማለት የራስንም ህልውና ማረጋገጥ ነው ትላለች፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ዘመቻው መሳተፍም ነው፡፡
ምዕራባውያን ሚዲያዎች እንደሚያራግቡት ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠን ወደ ጦር ግንባር ልንሄድ ሳይሆን፤ ለእኛ ሰላምና ለአገራችን ክብር ሲሉ በግንባር የሚፋለሙ የጸጥታ ሃይሎችን በቻልነው ሁሉ በመደገፍ አጋርነታችንን ለማሳየት ኢኮኖሚያችንንም ለመገንባት ነው፡፡
ትምህርትን ለመማር ሰላም ያስፈልጋል፤ የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ውስጥ ተማሪዎች አስተዋጽኦ አበረከቱ ማለት ሰላማዊ የመማር ማስተማር አውድን ፈጠሩ ማለት እንደሆነም ትገልጻለች፡፡ አሁን አገር እየረበሹ ያሉት አካላት በቅጡ ያልተማሩና ተምረውም ቢሆን የአስተሳሰብ ለውጥ ያላመጡ ናቸው ትላለች፡፡
ለዚህም በአፋርና በአማራ ከልል ያወደሟቸው የትምህርት ተቋማትና ግፍ የፈጸሙባቸው ንጹኋን ማሳያ መሆናቸውን ትጠቅሳለች፡፡ ሕዝብን እየገደሉ፣ እያፈናቀሉ፤ ንብረት እያወደሙ፤ ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርጉት ሩጫ ግቡ ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው ትላለች፡፡
ካሊድ ሙራድ የፊታውራሪ አባይነህ መተኪያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡ በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግንባር ተገኝተው እያዋጉ ያስመዘገቡት ድል እንዳስደሰተው ይናገራል፡፡ እርሱም ‹‹ዘመቻ ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት››ን ‹‹በዘመቻ በትምህርት ልማት ግንባር›› ታቅፎ የራሱን አሻራ ማስቀመጡ ደስተኛ አድርጎታል፡፡
ትምሕርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት ትምህርት ዘግተው የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እንዲሰበስቡና ሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንዲሠሩ መወሰኑ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነም ያምናል፡፡ ግንባር ተሰልፈው ከጠላት ጋር መፋለም ያልቻሉ ተማሪዎች ደጀን ሆነው ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ መልካም አጋጣሚ ማግኘታቸውን ይናገራል፡፡ መማር የአስተሳሰብ አድማስን ያሰፋል ተብሎ እንደሚታመን የገለጸው ሙራድ አሁን አገራቸውን እየወጉ ካሉት አካላት አብዛኛዎቹ የተማሩ መሆናቸው ሲታይ ያለፉበት የትምህርት ሥርዓት ጥሩ ሥብዕና እንዲላበሱ ያላደረጋቸው መሆኑን ይናገራል፡፡ የመማር ግቡ በሥራ የሚተረጎም ፍሬ ማፍራት እንደሆነ ሙራድ ይናገራል፡፡ ትምሕርት ሚኒስቴር አገር ወዳድ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችል የትምህርት ፖሊሲ ሊቀርጽ ይገባልም ብሏል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014