የስፖርቱን ዓለም ሰላማዊነት በመጥፎ ተግባር ከሚያደፈርሱና ንጹህ የውድድር መድረኮችን ከሚያራክሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የስፖርተኞች አበረታች ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚነት ነው። ብርቱ ጥረትና ጽናትን በሚጠይቀው የስፖርተኝነት ህይወት በአቋራጭ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ የብዙዎችን ዕድል ከመዝጋት ባለፈ የስፖርትን ተአማኒነትን ያጎድላል። በዚህም ምክንያት አትሌቶች አውቀው የማይገባቸውን ዝና ለማጣጣምም ይሁን ሳያውቁ በአሰልጣኞቻቸውና ሌሎች አካላት ንጥረ ነገሩን ተጠቅመው ከተገኙ ክብራቸውን ከመግፈፍ ባለፈ ከስፖርቱ አለም እስከ ዘላለም ድርሽ እንዳይሉ ቅጣት ይጣልባቸዋል።
አትሌቶች በውድድር ወቅት የተለየ ብቃት የሚጨምርላቸውን ንጥረ ነገር መጠቀማቸው ቀድሞም የነበረ ልማድ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጥንታዊ ግሪካዊያን እንደ በለስ እና እንጉዳይ ያሉ ምግቦችን ለአትሌቶቻቸው በመመገብ ብቃታቸውን ለመጨመር ይሞክሩ ነበር። ግብጾች ደግሞ የበቅሎ ኮቴ በአትሌቶች ብቃት ላይ ተጨማሪ ኃይል ይሆናል የሚል እምነት ነበራቸው።
ይኸው ተግባር በህግ ክልክል እስኪሆን ድረስ በተለያዩ ሃገራት በተለያየ መልክ ተከውኗል። እ.አ.አ 1807 እንግሊዛውያን አትሌቶች ‹‹ሉዳነም›› የተሰኘ መድሃኒት በመውሰድ ንቃታቸውን እንደጠበቁ ለመቆየት ጥረት ያደርጉ እንደነበር ዘገባዎች ያመላክታሉ። እአአ በ1904ቱ የሴንት ሉዊስ ኦሊምፒክ ማራቶንም አንድ ተወዳዳሪ ‹‹ስትሪክኒን›› የተባለ የመድሃኒት ዓይነት፣ ጥሬ እንቁላል እንዲሁም ብራንዲ የተባለ አልኮል መጠጥ አቀላቅሎ በመጠጣት በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ችሏል።
እ.አ.አ 1930 ደግሞ በእንግሊዝ የሚገኝ አንድ የእግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾቹ የፍራፍሬ ጭማቂን ከአልኮል ጋር በመቀላቀል የሚፈጠር መጠጥ እንዲጠቀሙ ማድረጉም ተደርሶበታል። አሁን አሁን ይህ የአበረታች ንጠረነገር አዘገጃጀት ስልት እጅግ የዘመነና የረቀቀ ሲሆን፤ አትሌቶች የሚደረግባቸውን ከፍተኛ ቁጥጥርና ምርመራ ማለፍ በሚችሉበት መልኩ ይዘጋጃል። በደም በሚሰጡ እንዲሁም ዘረመልን በመጨመርም የአትሌቱን ህይወት አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እየተሰጠም ይገኛል። በአበረታች ንጥረነገሮች ዙሪያ በርካታ ታሪኮችን ማንሳት ቢቻልም አስገራሚው ነገር ግን አትሌቶች በነፍስ ወከፍ ውጤታማ ለመሆን ከሚያደርጉት ተጠቃሚነት ባለፈ ሃገራት ለብሄራ ቡድናቸው ሙሉ ፈቃድ በመስጠት ሁኔታውን ማበረታታቸው ነው።
ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን የመሳሰሉ ታላላቅ ውድድሮችን ጨምሮ በሌሎች ቻምፒዮናዎች ላይ ብሄራዊ ቡድኗ እንዳይሳተፍ በመታገዱ ለዓመታት በውድድሮች ላይ የማትታየው ሩሲያ ለዚህ ማሳያ ናት። ይህ ሁኔታ አሁን የተፈጠረ ብቻም ሳይሆን በቀደመው ዘመንም በዚህ ረገድ የሚነሱ ሃገራት እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል።
ከእነዚህ ለዘላለም ከሚኖሩ የስፖርቱ ዓለም ጠባሳዎች መካከል ስሟ የሰፈረው የቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ናት። እአአ በ1970ዎቹና 80ዎቹ ሃገሪቷ አትሌቶቿን አበረታች ንጥረ ነገርን እንዲጠቀሙ ታስገደድ ነበር። የኮሚኒዝምን ፖለቲካዊ ርዕዮት አሸናፊነት ለማመላከት በሀገሪቷ ከሚደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ በስፖርት ሜዳዎች ላይ ስፖርተኞቻቸው ልቀው እንዲታዩ የማብቃት እሳቤ ነበር። በመሆኑም ለአትሌቶች የሚቀርብላቸው ምርጫ ‹‹አበረታች ንጥረነገሮችን ትወስዳለህ ወይስ ትሞታለህ?›› የሚል መሆኑን የጽሁፍ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ጀርመን በዚህ መልኩ የተዘጋጁ አትሌቶቿንም እአአ በ1976ቱ የሞንትሪያል ኦሊምፒክ ላይ ማሳተፍ ችላለች። በዚህም አስደናቂ ውጤት አስመዝግባበታለች። በሌሎች ተወዳዳሪዎች ዘንድ የሚሆኑ የማይመስሉ ክስተቶችም ታይተዋል። ለአብነት ያህል በሴቶች የውሃ ዋና ውድድር ከተዘጋጁ 13 የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል 11 የሚሆኑት የተወሰዱት በጀርመናዊያኑ ነው። በአጠቃላይም በኦሊምፒኩ ሃገሪቷ 40 የወርቅ ሜዳሊያዎችን 25 የብር እንዲሁም 25 የነሃስ በአጠቃላይ 90ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሩሲያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ ችላለች።
በመሆኑም ውጤቱ በአወዳዳሪዎች በኩል ጥያቄን ያስነሳ ሊሆን ችሏል። በመጨረሻም አትሌቶቹ አበረታች ንጥረነገር መጠቀማቸው ተደርሶበት ለቅጣት ሲዳረጉ ነገሩ በሃገር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቶና ድጋፍ ተደርጎለት የተከወነ መሆኑ ታውቋል። በተደረገው ማጣራትም በሃገሪቷ የሚገኙ ከ9ሺ በላይ አትሌቶች አበረታች ንጥረነገሩን እንዲጠቀሙ መደረጉ ተደርሶበታል።
እአአ በ1990 ጀርመን በድጋሚ ስትዋሃድም በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት ወንጀለኛ ተብለው የቅጣት ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ተደርጓል። ይህ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድ እንጂ ከፍተኛውን የህይወት ዋጋ የከፈሉ አትሌቶችን ሊክስ የሚችል አልሆነም። ምክንያቱ ደግሞ ሊያስተካክሉት አሊያም ወደኃላ ተመልሰው ሊፍቁት የማይቻላቸውን መሰዋዕትነት በእድሜ ልክ በሽታ ተቀብለዋልና። በአበረታች ንጥረነገሮቹን የተጠቀሙት አትሌሎች በኋላ ላይ ለልብ ህመም፣ ለመካንነት እንዲሁም ካንሰር በሽታ ተዳርገው የአብዛኛዎቹ ህልምና የመኖር ተስፋ ሲጠወልግ ታይቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2014