ክለቦችና የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚያሰለጥኗቸውን ወጣት አትሌቶች ብቃት የሚፈትሹት በተለያዩ ውድድሮች ነው:: አትሌቶች ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከመሸጋገራቸው አስቀድሞም የክልልና አገር አቀፍ ውድድሮችን እንደመንደርደሪያ ይጠቀማሉ::
በመሆኑም ፌዴሬሽኖች በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ውድድሮችን በማዘጋጀት አትሌቶች ያላቸውን አቅምና ብቃት ይመለከታሉ:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ እንዳለፉት ዓመታት በስሩ ለሚገኙ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር አዘጋጅቷል:: በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ የክለቦች አቋም መለኪያ ውድድር ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ በሚካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮችም ይጠናቀቃል::
በሞሃ መጠጦች አክሲዮን ማህበር ድጋፍ ‹‹የፔፕሲ አዲስ አበባ ክለቦች አቋም መለኪያ ውድድር›› በሚል ስያሜ በሚካሄደው በዚህ አትሌቲክስ ውድድር ላይም ከከተማው ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች በመም ሩጫዎች እንዲሁም በሜዳ ላይ ተግባራት ውድድሮች ተካፍለዋል:: ውጤታማ በመሆን ውድድራቸውን የፈጸሙ አትሌቶችም በፌዴሬሽኑ የተዘጋጀውን የወርቅ፣ ብርና ነሃስ ሜዳሊያዎች ይወስዳሉ:: የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራሁ ገብሬ፤ ክለቦች አሁን ካለው የአገሪቷ ወቅታዊ ችግር ጋር በተያያዘ አትሌቶች ልምምድ እንጂ አገር አቀፍ ውድድሮች ባለመኖራቸው አቋማቸውን መመዘን እንዳልቻሉ ይገልጻሉ::
በመሆኑም የአትሌቲክስ ቤተሰቡ በዜግነቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ አትሌቶችን ለማነቃቃት ውድድሩ ተዘጋጅቷል:: በዚህ የአቋም መለኪያ ውድድር ላይ በከተማዋ የሚገኙ አትሌቲክስ ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን፤ በአንደኛ ዲቪዚዮን 7 ክለቦች እንዲሁም ከሁለተኛ ዲቪዚዮን 9 ክለቦች በጥቅሉ 16 ክለቦች አቋማቸውን በተዘጋጀው ውድድር መለካት ችለዋል:: ውድድሩም የአትሌቶችን አቋም ከመመዘን ባለፈ ከሁለት ሳምንት በኋላ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሚዘጋጀው አገር አቀፍ የአጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ ሜዳ ተግባራትና ርምጃ ቻምፒዮና ተካፋይ ለመሆን የሚጠቅም መሆኑን ወይዘሮ እታፈራሁ ተናግረዋል::
ክለቦች በተለይም የሚያደርጓቸውን የውድድር ዝግጅቶችና ልምምዶች አስቀድመው ይህንን በመሰለ ውድድር መለካታቸው የውድድር ስነ ልቦናቸውን ከማጠናከር ባለፈ ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን ለይተው ለውጤታማነት እንዲቀርቡ እንደሚያግዝም አብራርተዋል::
ለሶስት ቀናት የተካሄደው ውድድር እየተደረገ ያለው በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲሆን፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በከተማዋ ያሉት ሁለት ስታዲየሞች (አዲስ አበባ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየሞች) በእድሳት ላይ ስለሚገኙ መሆኑን ኃላፊዋ ይጠቁማሉ::
በከተማዋ ባለው የመሮጫ መም እጥረት ምክንያት በአካዳሚው የሚደረገው ውድድር መሙ በአካዳሚው ሰልጣኞች ለልምምድ የሚፈለግ በመሆኑ እነርሱ እስኪጨርሱ ድረስ ጠብቆ ከሶስት ሰዓት በኋላ ማካሄድን አስገዳጅ አድርጓል:: የሜዳ ተግባራትን እንዲሁም እንደ መሰናክል ያሉ የውድድር ቁሳቁሶችንም በአካዳሚው ማግኘት ባለመቻሉ በአዲስ አበባ ስታዲየም የነበረውን ወደ አካዳሚው በማጓጓዝ ውድድሩ ተደርጓል:: ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ነባራዊውን ሁኔታ በመረዳት በትዕግስት በውድድሩ ሲሳተፉ ቆይተዋል:: ይሁንና የመወዳደሪያ ሜዳ ችግሩም በቀጣይ የሚታረምበትን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑን እንዳመላከተ ኃላፊዋ ይጠቁማሉ::
በስፖርት ሜዳዎች ላይ ውድድርን ከማካሄድ ባሻገር መልካምና የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራትን መከወን የተለመደ ተግባር መሆኑ ይታወቃል:: በኢትዮጵያም ይኸው ተግባር በስፋት የሚተገበር ሲሆን፤ በዚህ ውድድር ላይም መሰል ስራዎች ከአቋም መለኪያው ውድድር በተጓዳኝ መካሄዱን ኃላፊዋ ገልፀዋል::
ይኸውም አገር ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ክለቦችን በማነቃቃት ከሚያገኙት ገቢ ላይ ለአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ለተፈናቃዮች ድጋፍ በማድረግ ደጀን እንዲሆኑ ስራዎች በስፋት ሲከናወኑ መቆየት ነው:: በዚህ እንቅስቃሴም በተለይ እንደ ንግድ ባንክ ያሉ ክለቦች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ሌሎች ክለቦችም እንደ አቅማቸው በመስጠት በአጠቃላይ ወደ 217ሺ ብር ተሰብስቧል::
ከገንዘብ ባሻገር ከ400ሺብር በላይ የሚያወጡ አልባሳትና ምግብ ለተፈናቃይ ወገኖች ማሰባሰብ ተችሏል:: ፌዴሬሽኑና ሥራ የአስፈጻሚዎች በጋራ በመሆንም 300ሺ ብር ለአገር መከላከያ ሠራዊት የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግ መቻሉንም አክለዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014