የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት ክትባቶች በአዲሱ ኦሚክሮን ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ከባድ የጤና እክል እንዳይገጥማቸው መከላከል እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ ተናገሩ።
ኃላፊው ይህን ያሉት በደቡብ አፍሪካ በተደረጉ ሙከራዎች ይህ ቫይረስ በተለይ የፋይዘር ክትባትን ማሸነፍ እንደሚችል ምልክቶች አሉ መባላቸውን ተከትሎ ነው። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሰዎች በአዲሱ ቫይረስ ሲያዙ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች በሰውነታችን የሚፈጥሩ የመከላከል አቅም በእጅጉ ይቀንሳል መባሉን የዘገበው ቢቢሲ ነው። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ማይክ ራያን ኦሚክሮን ክትባቶችን ሙሉ በሙሉ የመገዳደር አቅም እንዳለው የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት አልተገኘም ብለዋል።
“እስካሁን ድረስ ሁሉንም አይነት ቫይረሶች መከላከል የሚችሉ ውጤታማ ክትባቶችን አግኝተናል። በኦሚክሮን ምክንያት ከባድ የጤና እክል የሚገጥመው አልያም ሆስፒታል እስከ መግባት የሚደርስ ሰው ይኖራል ብሎ መገመት በጣም ከባድ ነው” ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊው ዶክተር ማይክ ራይን።
ኃላፊው አክለውም ኦሚክሮን ከዚህ በፊት ከታዩት ሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች አንጻር እንደውም ሰዎችን የማሳመም አቅሙ ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተሰርቶ እስካሁን በሌሎች ተመራማሪዎች ባልተገመገመ አዲስ ጥናት መሰረት ግን የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት ከኦሚክሮን ጋር ሲገናኝ ውጤታማነቱ 40 በመቶ እንደሚቀንስ አመልክቷል።
ነገር ግን ኦሚክሮን ሙሉ በሙሉ ከክትባቱ እንደማያመልጥ ደርሰንበታል ይላሉ በአፍሪካ ሄልዝ ሪሰርች ኢንስቲትዩት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክስ ሲጋል። ተመራማሪው እንደሚሉት ከዚህ በፊት የተያዙ ሰዎች እንዲሁም ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ኦሚክሮንን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ ነው ካሉ በኋላ ሶስተኛ ዙር ክትባት መውሰድ ደግሞ ይበልጥ የመከላከል አቅምን ከፍ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። አዲሱ ኦሚክሮን እስካሁን ከ30 በላይ አገራት ውስጥ የተገኘ ሲሆን ሰዎች በክትባትም ሆነ ኮሮና ቫይረስ ሲይዛቸው የሚያዳብሩትን በሽታ የመከላከል አቅም ሊቋቋም የሚችል ነው። ነገር ግን ከዚህ በፊት ከነበሩት የኮሮና ቫይረስ አይነቶች አንጻር እስካሁን ቀላል የሚባሉ ምልክቶችን ብቻ ነው ያሳየው።
በዚህም ምክንያት ስለ ቫይረሱ፣ ስለ ስርጭቱ እና ስለሚያደርሰው ጉዳት በርካታ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው። መነሻውን በደቡብ አፍሪካ አገራት ያደረገው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ አይነት ለዓለማችን ተጨማሪ ስጋትን ፈጥሮ ቆይቷል።
ይህ አዲስ ዝርያ እስካሁን ከታዩት የኮሮና ቫይረስ አይነቶች እጅግ የተለየው ነው ተብሏል። በበርካታ ብዙ የዘረመል ለውጥ ውስጥ በማለፉ በአንድ ሳይንቲስት “አሰቃቂ” ተብሎ ሲገለጽ ሌላው ደግሞ እስካሁን ከታዩት የከፋ ዝርያ ነው ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካው ሴንተር ፎር ኤፒዴሚክ ሪስፖንስ ኤንድ ኢኖቬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ቱሊዮ ዴ ኦሊቬራ ስለዚህ አዲስ ዝርያ ሲናገሩ፤ “ያልተለመደ የዘረ መል ለውጥ ያለው” ሲሆን ከተሰራጩት ሌሎች ዝርያዎችም “በጣም የተለየ ነው” ብለዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ የፋይዘር ክትባት ኦሚክሮን ላይ የሚኖረው ጥንካሬና ድክመትን በተመለከተ መረጃዎች ይፋ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። እስካሁን ድረስ እንደ ሞደርና፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ያሉ እንዲሁም ሌሎች ክትባቶች ከአዲሱ ኦሚክሮን አንጻር ያላቸው ውጤታማነትን በተመለከተ ምንም ጠቃሚ መረጃ አልተገኘም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014