የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት ትኩረቱን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ማስቆም እንጂ በኃይል የተያዙ ቦታዎች ላይ አያደርግም ተባለ

የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት ትኩረቱን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ማስቆም እንጂ በኃይል የተያዙ ቦታዎች ላይ አያደርግም ተባለ፡፡

ለአንድ ሳምንት ተብሎ የተጀመረው የሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ የገንዘብ እና ጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ናት፡፡

አሜሪካ እስካሁን 64 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ድጋፍ ደረገች ሲሆን፤ ይህ ገንዘብ በአሜሪካዊያን ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሱን ተከትሎ የምርጫ መከራከሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡

ይህን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነት የምርጫ ቅስቀሳ አጀንዳ ያደረጉት ሲሆን፤ ጦርነቱን አንድ ቀን አስቆመዋለሁ ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ቅስቀሳቸው ለውጥ አምጥቶም ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ማሸነፋቸው ይፋ የሆነ ሲሆን የፊታችን ጥር ወር ላይ ስልጣን ይረከባሉ፡፡

ይሁንና ፕሬዚዳንቱ ስልጣን ከመረከባቸው በፊት ስለ ዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት መቆም ጉዳይ እየሰሩበት እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡

የሪፐብሊካን ፓርቲ ዋና ስልት ነዳፊ እና የዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባል የነበሩት ብሪያን ላንዛ እንዳሉት፤ አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በኃይል ስለተወሰዱ የዩክሬን ግዛቶች አያተኩርም ብለዋል፡፡

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚያተኩረው ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን እንዲያቆሙ ማድረግ ነው ያሉት ብሪያን፤ እንደ ክሪሚያ ያሉ ቦታዎች ወደ ሩሲያ ተካለዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያም ሆነ የዩክሬን ጦር አሁን ባሉበት ሆነው ከአንድ ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር ርቀት ከሁለቱም ተፋላሚዎች ነጻ ሆኖ እንዲቆይ የሚል እቅድም ቀርቧል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሩሲያ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኗን የሀገሪቱ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ሪያብኮቭ ተናግረዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ሩሲያ በኃይል ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ጦሯን ካላስወጣች ሰላም እንደማይሰፍን በተደጋጋሚ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You