ኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንቨስትመንት በቀላሉ የሚቀላጠፍባት አገር እንድትሆን መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ተንታኞች በበኩላቸው፤ አገሪቱ ንግድ በቀላሉ የሚጀመርባት እንድትሆን የዘርፉን ህጎችና መመሪያዎች በአግባቡ መተግበርና የኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ (ሮድማፕ) ማዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የካናዳ ክርስቲያን ህፃናት ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር እና የኦሮሚያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጉቱ ቴሶ አንድ ኢንቨስተር ወደ አንድ ሀገር ሄዶ ትርፋማ ለመሆን በቅድሚያ አካባቢው ለንግድ ሥራ ይቀላል ወይ ? ያለምንም ውጣ ውረድ መስራት የሚያስችል ሁኔታ አለን ? የሚሉት ጥያቄዎችን ያነሳል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ መመሪያዎች እንዳሏት የሚጠቅሱት ዶክተር ጉቱ፣ ኢንቨስተሮቹ እስከሚደራጁ ድረስ ግብር እንዳይከፍሉ መደረጉ፣እቃ ያለቀረጥ እንዲያስገቡ መመቻቸቱ እንዲሁም መሰረተ ልማቱ መዘርጋቱን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ጥምጥም አካሄድ የሞላበት ነው፡፡ አንድ ባለሀብት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በአፈፃፀም ረገድ መልካም ነገር ባለመኖሩ ተመልሶ እንዲሄድ እንጂ መዋዕለ ንዋዩን ሥራ ላይ እንዲያውል አይገፋፋውም፡፡በዘርፉ ያሉ አብዛኛዎቹ አካላት ኢንቨስተሩን ተቀብሎ በማስተናገድና ማራኪ ሆኖ በመቅረብ በኩል ብቃቱም ችሎታውም የላቸውም›› ሲሉ ዶክተር ጉቱ ያብራራሉ፡፡ ዶክተር ጉቱ ፤አንድ መታወቅ ያለበት ነገር መንግሥት ፈጥኖ ከችግሩ ለመውጣት በማሰብ ብቻ የአጭር ጊዜ እቅድ መያዝ የለበትም ይላሉ፡፡
ለጥቂት ጊዜ ብቻ ችግር እንዲፈታ ታስቦ የሚደረገው አካሄድ አዋጭ ባለመሆኑ ለሚቀጥሉት 50እና60 ዓመታት የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት መሰረት ሊያስይዝ የሚችል ነገር ነው መደረግ ያለበት፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ኢትዮጵያ በዘርፉ የአጭር ጊዜ እንጂ የረጅም ጊዜ እይታ ያላት አገር አለመሆኗ ነው ያሉት ዶክተር ጉቱ፣ የዛሬ 30 እና 40 ዓመት ኢንቨስትመንቶች ምን መሆን አለባቸው? የትስ ቦታ መሆን አለባቸው? እንዲሁም በየትኞቹ ዘርፎች? የሚሉ ጉዳዮችን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ መኖር እንዳለበት ያብራራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፍኖተ ካርታ የታለ ሲባል የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ነው ለማሳየት የሚፈለገው፤ይህ ግን ፍኖተ ካርታ መሆን አይችልም፡፡
ባለሀብቱም ቢሆን ፍኖተ ካርታ እንዳልሆነ ያውቃሉ ይላሉ፡፡ ዶክተር ጉቱ፣ ‹‹አንድ ኢንቨስተር ወደ አገራችን ከመጣ በኋላ ዞር ብሎ ያለማየት ችግር ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ባለሀብት አስፈላጊውን ነገር ከማሟላት ጀምሮ እስኪደራጅ ድረስ ሁሉ ከጎኑ መሆን ይገባል፡፡ መሬት፣ ውሃና መብራት ብቻ ሰጥቶ ዞር ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ተከታታይ ድጋፍ ማድረግ ይገባል›› ብለዋል፡፡ ‹‹የዚህ አገር የኢኮኖሚ ጥያቄ የሚፈታው መንግሥት በሚሰራው አሊያም ግብረሰናይ ድርጅቶች በሚሰሩት ሳይሆን ባለሀብት በሚሰራው ነው›› የሚሉት ዶክተር ጉቱ፣ መንግስት ለኢንቨስተሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለበት ይላሉ፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ዘላለም እጅጉ እንደሚሉት፤በሀገሪቱ ቢዝነሱን በተሻለ መልኩ ለመቅረፅ እንዲያስችል የትኛው ዘርፍ ከየትኛው ይሻላል አሊያም የትኛው ዘርፍ ወደ ኋላ ቀርቷል የሚለው እምብዛም ደረጃ ሲወጣለት አይታይም፡፡ለምሳሌ የፋይናንስ አቅርቦቱ ላይ ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ ዘርፉን ከሚመለከቷቸው ቢሮዎች ጋር በተያያዘ ቢሮክራሲ መኖሩ ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው፡ ፡ እናም እነዚህን ለማሻሻል በተለይ ከባንክ በሚገኘው ብድር ላይ በአግባቡ መስራትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ዙሪያ መንግሥትም ማሻሻያ (ሪፎርም) በማድረግ ላይ መሆኑን ዶክተር ዘላለም ጠቅሰው፣በተለይ ብድር ለማግኘት ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በማስያዝ የሚከናወነውን ተግባር ማፋጠን ይገባል ይላሉ፡፡
ከፋይናንስ እጥረት የተነሳ ችግር ያጋጠማቸውንም በጥናት የመለየት ሥራዎች ሊሰሩ እንዲሁም የባንክ ሥርዓቱን በማሻሻል ሥራዎች ቀና እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ፡፡ ዶክተር ዘላለም ገንዘብ ያለውን ባለሀብት ብቻ ማሰባሰብ ላይ መጠመድ እንደማይገባም ያስገነዝባሉ፡ ፡ሐሳብ ያለውን አካል ማቅረብ ያስፈልጋል ፤ከትንንሽ ኢንቨስትመንት መነሳት እንደሚቻል በማሳወቅ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይገባል ያሉት ዶክተር ዘላለም፣ እነዚህ ሐሳብ የያዙ ግለሰቦች የሚነሱት ከትንሽ ቢሆንም፣በሂደት ግን ወደ ትልቅ ኩባንያ መሸጋገር የሚችሉ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
የዶክተር ጉቱን ሃሳብ በማጠናከርም አገሪቱ የፖሊሲና የመመሪያዎች ችግር እንደሌለባት ይገልጻሉ፡፡ከዚህ ጎን ለጎን መጠናከር የሚገባው በእኩል ዓይን መታየትና ጤናማ የውድድር ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል አሰራር መከተል እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ አሳሪ የሆነውን የካፒታል እጥረት በመፍታት ባለሀብቶችን ለመሳብ የብድር አቅርቦቱን ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣የኢንቨስትመንቱ ማነቆ የሆኑት የቢሮክራሲያዊ መብዛትና የአሰራር ክፍተቶችን የመፍታት ሥራ ሊታሰብበት እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጎን ለጎን ደግሞ ሰላማዊ የሆነ አካባቢ ማመቻቸት ወሳኝ ነው፡፡
አዲስ ለማምጣት ብቻም ሳይሆን ያለውን ለማስቀጠልም የሰላም መኖር ግድ ይላል ሲሉ ነው ዶክተር ዘላለም የሚናገሩት፡፡ ዶክተር ዘላለም እንደተናገሩት፤የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ችግር ነው፡፡ ሸቀጦችን ከወደብ ለማምጣት የትራንስፖርት አገልግሎቱ እምብዛም ምቹ አይደለም፡ ፡ቶሎ ወደ አገር ውስጥ የማስገባትና ወደ ውጭ መላክ ላይ ችግሮች አሉና መስተካከል ይገባቸዋል፡፡ ከኢንቨስትመንት አኳያ ቢሮክራሲ ከማይበዛባቸውና ባለሀብቶችን በመሳብ በኩል የተሻሉ ከሆኑት ኬንያ፣ ዑጋንዳ ፣ደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ ተሞክሮ መቅሰም ይገባል፡፡
የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ የ2019 ሪፖርቱ ንግድ በቀላሉ የሚጀመርባቸው ሀገሮችን ደረጃ በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡በዚህ ደረጃ መሰረትም ኢትዮጵያ ከ190 አገራት 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ባንኩ የሀገሮችን አዲስ የንግድ ሥራዎች ቶሎ መጀመር ለመለካት ከሚጠቀምባቸው መካከል ጊዜ፣ የመነሻ ሀብት መጠን፣የንብረት ምዝገባ፣የአነስተኛ ንግድ ሥራ ጥበቃ (ፕሮቴክሽን)፣የገንዘብ አቅርቦት የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡በዚህ መለኪያ መሰረትም ነው ሀገሪቱ በቀላሉ ንግድ ከማይጀመርባቸው ሀገሮች አንዷ የሆነችው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ንግድ ቶሎ እንዳይጀመር ደንቃራ ከሆኑት መካከል አዲስ ንግድ ለመጀመር 32 ቀናት እንዲሁም ኤሌክትሪክሲቲ ለማስገባት 93 ቀናት ይወስዳል፡፡ከታክስ ህግጋት ጋር ያለውን ሂደት ለማለፍ 300 ሰዓቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ዜጎች የንግድ ሐሳብ ቢኖራቸውም አሳሪ በሆነው ህግ ምክንያት ወደተግባር ለመቀየር እንደሚቸገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መናገራቸውም ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለመፍታት የአጭር፣የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ማስቀመጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ለዚህም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ መስራት ከጀመረም አንድ ወር አልፎታል፡፡ አዲስ ንግድ መጀመርን ቀላል እንዲሆን ለማስቻልም በ80 አሰራሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን በአጭር ጊዜ መፍትሄነት ማስቀመጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ የንግድ ሥራ ጀማሪዎች ፈጥነው ወደ ሥራ ለማስገባት የተጀመረው ሥራ በምእራፍ በምእራፍ ተግባራዊ መደረግ ሲጀመር አዲስ ሥራ የሚፈልጉም ሆኑ አስቀድሞ በሥራ ውስጥ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎችና ባለሀብቶች ይበልጥ ተበረታትተው እንዲሰሩ ያስችላል፡፡ወደ ውጭ የሚላከው ምርትና የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ ይጨምራል፡፡ እነሱ ሰሩ ማለት የሀገር ኢኮኖሚ ይነቃቃል፡፡ ሌሎች የውጭ ባለሀብቶችና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንቱን መቀላቀል ይጀምራሉ፡፡በዚህም የሀገር ኢኮኖሚ ከማደጉ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ለዚህ ሁሉ የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለማስወገድ የተጀመረውን ሥራ ማጠናከር ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
አስቴር ኤልያስ