ዋልያዎቹ ከስምንት ዓመት በኋላ የሚሳተፉበት የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በካሜሮን ላይካሄድ እንደሚችል ከጥርጣሬ በዘለለ ስጋት ፈጥሯል። የአፍሪካ ታላቁ የስፖርት መድረክ የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ላይካሄድ እንደሚችል ስጋት የፈጠረው ካሜሮን ለአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር እያደረገች ያለችው ዝግጅት መጓተትና የውድድር ቅድመ ሁኔታን አለማሟላት እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የአፍሪካ ዋንጫው በካሜሮን የማይደረግ ከሆነም ካፍ ውድድሩን ኳታር ላይ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ሊጀምር እንደሚችልም ተጠቁሟል። የቀድሞው የካፍ የቴክኒክ ዳይሬክተር አብደል ሞኔም ሻታ ካሜሮን ከወር በኋላ የአፍሪካ ዋንጫውን ለማስተናገድ ባላት አቅም ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የግብጹ ኃያል ክለብ አል አህሊ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋች የነበሩት ሻታ የካሜሮን ዝግጅት አስተማማኝ አለመሆኑን በመግለጽ ውድድሩ ሊሰረዝ እንደሚችልም ጠቁመዋል። ሰላሳ ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዋናነት ሊካሄድ የታሰበው በ2020 ሰኔ ወር ላይ የነበረ ቢሆንም በዚያ ወቅት በካሜሩን ያለው የአየር ጸባይ ምቹ ባለመሆኑ ጥር ላይ እንዲካሄድ ካፍ ከሁለት ዓመት በፊት ውሳኔ ላይ መድረሱ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመትም ከኮቪድ19 ወረርሽኝ ስጋት ጋር ተያይዞ ውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሊራዘም ተገዷል። ይሁን እንጂ የውድድሩ ስያሜ ከስፖንሰርሺፕ ጋር በተያያዘ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ተብሎ የሚካሄድ ይሆናል።
የካሜሩንን ዝግጅት ለመገምገም በካፍ የተዋቀረው እርግጥ ከሆነ የአፍሪካ ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአህጉሪቱ ውጪ በተለይም በኳታር የሚካሄድበት እድል መኖሩን በተመለከተ ሻታ አስተያየት ሲሰጡም፣ ‹‹በአሁን ወቅት ካፍ በፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ ሳሙራ እየተመራ እንደመሆኑ የአፍሪካ ዋንጫው ከአፍሪካ ውጪ እንዲካሄድ ነገሮች ቀላል ሊሆኑ ይችላሉ፣ የሚያስፈልገው የፊፋ ውሳኔ ብቻ ነው›› በማለት አስረድተዋል።
ሃያ አራት አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሳተፉበት የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ካሜሮን የተሳካና በቂ መስተንግዶ ለማድረግ ቢያንስ በተለያዩ ከተሞች ስድስት ስታዲየሞች ያስፈልጓታል። ለዚህ ውድድር እየተዘጋጁ የሚገኙት ስታዲየሞች በካሜሮን መዲና የሚገኙት ኦሌምቤ ስታድየምና አህማዶ አሂጆ ስታዲየም የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በዱአላ ከተማ የሚገኘው ጃፖማ ስታዲየም፣ በሊምቤ ከተማ የሚገኘው ሊምቤ ስታዲየም፣ በባፉሳም የሚገኘው ኮይኮንግ ስታዲየም፣ በጋሩዋ የሚገኘው ሮምዴ አጂአ ስቴድየም ተጠቃሽ ናቸው። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አንድ የተደለደለችው ካሜሮንም የመክፈቻውን ጨዋታ ከቡርኪናፋሶ ጋር የምታደርገው በመዲናዋ በሚገኘውና ስልሳ ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው ኦሌምቤ ስታዲየም ይሆናል።
ይህ ሁሉ ግን ካሜሮን ለውድድሩ የምታደርገውን ዝግጅት ቢያንስ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ አጠናቃ አሁን የተፈጠረውን ስጋት በማስቀረት የአፍሪካ ዋንጫውን ማዘጋጀት ስትችል ብቻ ነው። የአፍሪካ ዋንጫ ከአፍሪካ ውጭ ሊካሄድ ይችላል ኮሚቴ አገሪቱ ውድድሩን ለማስተናገድ እያደረገች የምትገኘው መሰናዶና ውድድሩ ሊካሄድ የቀረው ጊዜ እንደማይጣጣም መገንዘቡን ሻታ ሰሞኑን ከአል ሃያህ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የገለጹ ሲሆን፣ ፊፋም ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተልና ዝግጅቱን ለማፋጠን በካሜሩን ጊዜያዊ ቢሮ መክፈቱ ታውቋል።
ካሜሩን ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ባቀረበችበት ወቅት በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥር አስራ ስድስት ነበር። አሁን ግን በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥር ወደ ሃያ አራት አድጓል። ይህም ካሜሩንን ተጨማሪ ስቴድየሞች የመገንባት ግዴታ ውስጥ አስገብቷታል። የተሳታፊ አገራት ቁጥር አስራ ስድስት እያለም የመክፈቻ ጨዋታውን በሚያስተናግደው ስቴድየም ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ውዝግቦች ሲነሱ እንደነበር ይታወሳል።
ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ ሳይካሄድ ለሶስትና አራት ወራት ቢራዘም እንኳን በካሜሮን ምትክ አስተናጋጅ አገር ማግኘት እንደማይቻል የጠቆሙት ሻታ፣ ውድድሩ በተያዘው ጊዜ ካልተካሄደ የመሰረዝ እድሉ ሰፊ መሆኑን አብራርተዋል።
‹‹በአፍሪካ ኅብረት በኩል ያለው ነገር ለእኔ ተቀባይነት የለውም፣ ለአፍሪካ ትኩረት የሚሰጥ አካል የለም፣ የክለቦች የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄዱበት ወቅት መጋጨቱ አንዱ ችግር ነው፣ አፍሪካውያን በተመሳሳይ ጊዜ ሁለት ውድድሮች እንዲያደርጉ መፍቀድ ትልቅ ንቀት ነው፣በዚህ ረገድ ለጉዳዩ መፍትሔ ለማበጀት ነገሮች ለፊፋ ፕሬዚዳንት ቀላል ናቸው››በማለትም ሻታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ካሜሮን ውድድሩን ማስተናገድ አለመቻሏ
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1/2014