የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን 500 /አምስት መቶ/ የዋልያዎቹ ደጋፊዎችን ወደ ካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ።
የሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አድርሴና የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ በሰጡት መግለጫ ‹‹የአፍሪካ ዋንጫው የአገርን መልካም ገጽታ የምናሳይበትና ኢትዮጵያን ይበልጥ ለዓለም የምናስተዋውቅበት መድረክ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል።
ዋልያዎቹ ከስምንት ዓመት በኋላ የሚሳተፉበትና በመጪው ጥር በካሜሩን በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ‹‹ኢትዮጵያ የሰላምና የጀግኖች አገር መሆኗን የምናሳይበት፣ ምዕራባውያን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ በተሳሳተ መረጃ የሚያስተላልፉትን ውሸት የምናከሽፍበት መድረክ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተነዋል›› ሲሉ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልጸዋል።
መላው ዓለም ኢትዮጵያን በተመለከተ እንኳን 500 /አምስት መቶ/ ደጋፊ ወደ ካሜሩን ሊሄድ ቀርቶ ብሔራዊ ቡድኑ ራሱ ወደ አፍሪካ ዋንጫው መሄዱን እየተጠራጠሩ በሚገኙበት በዚህ ወቅት፣ ‹‹አዲስ አበባ ተከባለች፣ ጦርነቱ ቀጥሏል›› የሚለውን ወሬ ለማክሸፍ በማሰብ እነዚህን ደጋፊዎች ወደ ካሜሩን ይዞ ለመጓዝ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደሚሳካ እርግጠኛ መሆናቸውንም አቶ ባህሩ ተናግረዋል።
ከደጋፊዎች በተጨማሪ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሃያ አምስት ጋዜጠኞችን ይዞ ለመጓዝ የታሰበ ሲሆን፣ ‹‹ጋዜጠኞች አምባሳደሮቻችን ናቸው፣ ከዘገባ ውጪ በውድድሩ ላይ ከሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞች ጋር ተወያይቶ እንደ አገር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ መገንባትና ያለውን እውነታ መግለጽ ይጠበቅባቸዋል፣ ይህም ከውጊያው አውድማ በተመሳሳይ በሚዲያ ላይ ያለውን ጦርነት ሊዋጉ የሚሄዱ ያደርጋቸዋል›› በማለት አቶ ባህሩ የሚዲያውን ተልዕኮ ገልጸዋል።
የሲሳይ ፕሮሞሽን ባለቤትና የጉዞው ዋና አስተባባሪ አቶ ሲሳይ በበኩላቸው፣ ለጉዞው የአውሮፕላን የምግብና የማረፊያ፣ የአገር ውስጥ ትራንስፖርት እንዲሁም የስታዲየም መግቢያ ወጪን የሚሸፈን ሲሆን ለዚህም 55 ሺ 223 ብር እንደሚከፈል ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ 25 ጋዜጠኞች በነጻ የሚጓዙ ሲሆን ሙሉ ወጪያቸውንም በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች የሚሸፈን መሆኑ ታውቋል።
አቶ ሲሳይ ‹‹አገሬ አምናብኝ ፌዴሬሽኑም ለሰጠኝ ኃላፊነት ታማኝ ነኝ፣ አገሬን ለማገልገልም ዝግጁ ነኝ፣ ልዩነታችንን አጥበን እንደ አገር በርትተን ከሰራን ኢትዮጵያን የማኩራት ሥራ እንሠራለን ብዬ አስባለሁ›› ሲሉ አስረድተዋል። ‹‹በቀጣዩ ዓርብ ወደ ካሜሩን ስለምሄድ የ48 ሰዓት የኮቪድ ምርመራ ሂደቱን በተመለከተ እንዴት ማድረግ እንዳለብን ተወያይቼ ስለሚጓዘው ለልዑካን ቡድኑ የተሻለ ሥራ ሠርቼ እመለሳለሁ፣ እንደኔ 500 ዘማች ደጋፊዎች አሉን ብዬ ነው የማምነው›› በማለትም ተናግረዋል።
አቶ ሲሳይ እንደ አገር ብሔራዊ ቡድኑ አሸንፎ ሲመለስ ያቀባበል ኘሮግራሙን መሥራታቸው እንዲሁም ቀደም ሲል በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን ድጋፍ በተመለከተ የነበራቸውን ተሞክሮ በማሰብ ‹‹በርካታ የእግር ኳስ ወዳዱ ቤተሰብ ብሔራዊ ቡድኑን ለመደገፍ ወደ ካሜሮን ለምን ተበታትኖ ይሄዳል? ለምን ተሰባስበን አንሄድም? አንድነት ድምቀት ይሰጣል›› በማለት ከሦስት ወር በፊት ሥራውን እንደጀመሩና ወደ ካሜሮን ሰዎችን በመላክም ጥናት ማድረጋቸውን አስረድተዋል። አንድነታችንን እንዴት? በምን መልኩ ነው የሚገለፀው የሚለው ሀሳብ ረጅሙን ጊዜ እንደፈጀና ሰፊ ውይይት ከፌዴሬሽኑ ጋር በማድረግ ውሳኔ ላይ እንደተደረሰ የጠቆሙት አቶ ሲሳይ፣ በውሳኔው ‹‹ደጋፊው ሲሄድ የግሉን ወጪ ብቻ እንዲሸፍን፣ እኛ ደግሞ የእዛ ሁሉ ድምፅ የሆኑት የሚዲያ አካላት ወጪ የሚሸፈንበትና በአንድ ቦታ ሆነው የጎደለውን እየሞሉ የሚሰሩበት ሁኔታን ማመቻቸት›› በሚል ሀሳብ በፌዴሬሽኑ በኩል ቀርቦ በተደረገው መግባባትና በጥናቱ መሠረት የሆቴል፣ የምግብ፣ የትራንስፖርትና የስታዲየም መግቢያ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ያዘጋጀው የብሔራዊ ቡድን መለያን ሸፍኖ በአንድ ላይ ቢደረግ የተሻለ ገጽታ መገንባት ይቻላል በሚል እምነት እቅድ አዘጋጅተው ማቅረባቸውን አብራርተዋል።
በዚህ መንገድ አንድ ሆነን ብንሄድ የተሻለ አንድነት እንዳለን ለማሳየት ይረዳል በሚልም በካሜሮን ቆይታ የሦስት ቀን ጉብኝት ፣ የአስር ቀን ደርሶ መልስ ቆይታ ለአንድ ሰው 55ሺ ብር እንደሆነና አስር ቀን የሚለው በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት የሚወሰን ሆኖ በልዩነቱ ላይ ውይይት ተደርጎ እንደሚስተካከል አስረድተዋል ።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንና በሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ስምምነት መሠረት ሁለቱ ተቋማት ከተጣራው ገቢ 50 በመቶ እንደሚካፈሉ ተጠቁሟል። ሁለቱ ተቋማት የሰጡትን መግለጫ ተከትሎም ለተጓዦች ምዝገባ መጀመሩ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 30/2014