ኢትዮጵያና ቻይና የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም እንደ አሁን የሁለቱ ግንኙነት፣ ትብብርና ትስስር ተጠናክሮ የሚያውቅ አይመስልም። ከማንም በበለጠ የሁለቱ ግንኙነት ጥብቅ ብቻ ሳይሆን በጋራ መስራት፣ መልማትና ማደግን ያካተተ ሆኖ ነው የሚታየው።
ይህንን ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳየት ማስረጃ እናቅርብ ቢባል የቱ ተጠቅሶ የቱ ይተዋልና በአንዱ፤ በትምህርቱ፣ ከትምህርቱም ኮቪድን ከመከላከልና ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘትን የተመለከተው ፕሮጀክት (ስፕላሽ/Splash ይባላል) ላይ ብቻ አተኩረን የተሠሩ ሥራዎችን እናመልክት።
ፕሮጀክቱ በሙሉ ስሙ ስፕላሽ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ (Splash International Ethiopia) ይባላል። በ2007 የተቋቋመ ቻይናዊ ተቋም ሲሆን አላማው ማህበራዊ ፍትህ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን ማከናወን ነው። ይህ በአመቱ (በ2008) ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ በቀዳሚነት በኢትዮጵያና ካምቦዲያ በረድኤት ድርጅትነት የተቋቋመ ሲሆን፤ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች ንጽህናቸውን በመጠበቅ እራሳቸውን ከኮቪድ-19 እንዲከላከሉና ንፁህ የመጠጥ ውሀን እንዲያገኙ በማድረግ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ በማተኮር ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚ ተግባሩ ነው።
ይህ ፕሮጀክት ለአራት አመታት በተከታታይ የሚከናወን ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ተጠናቆ በመመረቅ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህም በመጀመሪያው ዙር የተማሪዎች በትምህርት ቤት ንፅህና አጠባበቅና ንፁህ ውሀ ተጠቃሚነት ፕሮጀክት (School Wash Project) በአዲስ አበባ የሚገኙ 20 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዕድሉን ያገኙ ሲሆን፣ 23 ሺህ ተማሪዎችም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ኅዳር 11 2014 አ.ም ዕድሉን ካገኙት 20 ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በሆነውና ፈረንሳይ በሚገኘው «ሕዝባዊ ሰራዊት ቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት»፣ በቻይና በኩል በኢትዮጵያ ካንትሪ ኦፊስ ዳይሬክተር ኢማ ዢኦሽን ሁዋንግና በሳቸው የሚመራ ቡድን፣ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አምባሳደር አማካሪ፣ በኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ቀልቤሳ ዳባ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህራንና መምህራንና ተማሪዎች፤ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለፀው ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ደረጃ የተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ከፍተኛ ችግር ፈትቷል፤ የመማር ማስተማሩን ሥራም የተቃና እንዲሆን አድርጎታል።
መንግሥታዊ ያልሆነውና በ1989 የተቋቋመው ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፑቨርቲ አሊቬሽን (China Foundation for Poverty Alleviation – CFPA) ባለፉት 32 አመታት በRMB 34.09 ቢሊዮን በጀት ለ33 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ተደራሽ መሆን የቻለ ለጋሽ ድርጅት መሆኑ በዕለቱ የተነገረለት ይህ ተቋም፤ “China Foundation for Poverty Alleviation Ethiopia Country Office” ወይም “SPLASH INTERNATIONAL ETHIOPIA” በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ ከ2008 (እ.አ.አ) በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ ሕፃናት ማሳደጊያዎች፣ መጠለያዎች ወዘተ ውስጥ ተመሳሳይ ከጤና፣ ንፅህና አጠባበቅ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሀ ማውጣት፣ ዘመናዊ የተጣራ ውሀ ማጠራቀሚያ (ultrafiltration water filter System) መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ አካባቢ ጥበቃ ወዘተ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን እስከ ፕሮግራሙ (ፕሮጀክቱ) ማለቂያም ይኸው ፕሮግራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተነግሯል።
ይህ የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከሆነው XCMG ጋር በመተባበር እየተከናወነ ያለው ፕሮጀክት ለአራት አመታት የሚዘልቅ ሲሆን በአጠቃላይም $16.8 ሚሊዮን በጀት የተያዘለት መሆኑ ታውቋል።
ይህ XCMG፣ CFPA እና Splash International በጋራ የሚያከናውኑት ፕሮጀክት አሁን በ20 ትምህርት ቤቶች ባከናወናቸውና ለ23 ሺህ ተማሪዎች ተደራሽ ባደረጋቸው ስኬቶች ብቻ የሚቆም አይደለም። ካንትር ዳይሬክተር አቶ ቀልቤሳ ዳባ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ ፕሮጀክቱ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚከናወንና ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራ ሲሆን፤ይህ እንደተጠናቀቀም ፕሮጀክቱ ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስፋፋና ተማሪዎችንና የየትምህርት ቤቶቹን ማህበረሰብ በሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።
ከዚህ በፊት፣ የዘንድሮው አመት ትምህርት ቤት መከፈቻ ወቅት «የቻይና መንግሥት»፣ «ፓንዳ ፋውንዴሽ»፣ «አሊባባ ፋውንዴሽን» እና የመሳሰሉት በአገራችን የትምህርት ጥራትን ከማምጣትም ሆነ አገር ተረካቢ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን፤ ኮቪድ-19ን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ከቻይና መንግሥት በርካታ ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውን፤ በዚህ አመት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የቻይና መንግሥት ከ3000 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን የኮቪድ ክትባት መድኃኒቱን በማምረት ድጋፍ ማድረጉን፤«ኢትዮጵያ ፓንዳ ፓክ ፕሮጀክት» የታቀፈና ላለፉት ሦስት ዙሮች ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቶ የተጠናቀቀ ፕሮግራም በድምሩ 118ሺህ የተማሪ ቦርሳዎች ታድለዋል።
በ2019 43ሺህ፣ በ2020 55ሺህ፤ እንዲሁም ዘንድሮ (2021) 20ሺ ዘመናዊ፣ የቻይናንና የኢትዮጵያን ባህል ባስተሳሰሩ የፊት ለፊት ምስሎች የተጌጡ፤ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ዘመናዊ (46 ዋና ዋና ኪሶች ያሏቸው) ቦርሳዎችን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለተጠቃሚ ተማሪዎች ማድረሱን በዚሁ አምድ ላይ ማስፈራችን ይታወሳልና የሁለቱ አገራት ትብብር የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2021