ባለፈው ሳምንት ያስተዋውቅናችሁ መንትዮቹ የዘመን ሀኪሞች ለመግቢያ እንዲሆናችሁ በአጠቃላይ የጤና ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠትን መርጠዋል። ከሰጡት ማብራሪያም ሆነ በአጠቃላይ የጤና ችግሮቻችሁ ዙሪያ ለምታነሱት ጥያቄዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል። መግቢያቸውን እነሆ!
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1948 የዓለም የጤና ድርጅት (WHO)ባወጣው የጤና ትርጉም መሰረት ጤና ማለት የህመም አለመኖር ማለት ብቻ ሳይሆን፣ በአካላዊ፣ በአዕምሮ እንዲሁም በማህበራዊ ስርዓት ውስጥ የደህንነት ስሜት ማለት ነው። የጤና አይነቶች የጤና አይነቶች በዋናነት በ3 የሚከፈሉ ሲሆን እነዚህም አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ማህበራዊ ናቸው። አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤና በስፋት ትኩረት ከሚሠጥባቸው የጤና አይነቶች ናቸው። አካላዊ ጤና በሀገራችን እንዲሁም በዓለማችን ከፍተኛውን የጤና አይነቶች ሲሆኑ፣ አካላዊ ጤና በሃገራችን እንዲሁም በዓለማችን ከፍተኛውን ትኩረት አግኝቶ እና በስፋት እየተሰራበት ያለው የጤና አይነት ነው።
እያንዳንዱ የጤና አይነት ማለትም አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ እና ማህበራዊ ጤና በአንድ ግለሰብ የሚኖራቸው ሚና አንዱ ከአንደኛው የሚያንስ ወይንም የሚበልጥ አይደለም። አካላዊ ጤና በቀደሙት ጊዜያት የዘመናዊ ህክምና ከመጀመሩ አስቀድሞ አካላዊ ጤና ተብሎ የሚታሰበው ወይም ትርጉም የሚሰጠው፤ አንድ ሰው በካባድ ህመም አለመታመሙ ወይም አለመያዙ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። የዘመናዊ ህክምና ከመጣ ወዲህ ግን አካላዊ ጤና አለው ተብሎ የሚታሰቡ የህመም አለመኖር ወይም አለመያዝ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ የሚከተሉትን የያዘ ይሆናል።
• አካል ብቃት እንቅስቃሴ(ማለትም ጥንካሬን፣ የመተጣጠፍ አቅም፣ አካላዊ ፅናትን)
• የአመጋገብ ስርዓትን (ማለትም የተመጣጠነ ምግብ፣ ፈሳሽን ጨምሮ፣ ጤናማ የምግብ አወሳሰድን ይጨምራል)
• እንቅልፍ እና እረፍት (የእንቅልፍ ጥራት፣ በቂ አካላዊ እረፍት)
• በመጨረሻም የራስን ጤና መጨመር እና እንደ አስፈላጊነቱ የህክምና አገልግሎትን ማግኘትን ያካትታል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የአካላዊ ጤና ግብአቶች በማይኖሩበት ግዜ የሚኖራቸው ጉዳት በምናየው የሰውነት አካል ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ህመምን ያስከትላሉ። የአካላዊ ጤናን ለመፈተሽ የተለያዩ መንገዶች አሉ። አንድ ግለሰብ ይህንን ለማድረግ በሚያስብበት ወቅት ወደ ሃኪም ወይንም የአካል ብቃት መምህር ጋር በመቅረብ የሚከተሉትን ማድረግ ያስፈልጋል።
• ክብድትን ከቁመትና ከፆታ ጋር ማነጻጸር /BMI/
• የሰውነት የስብ መጠንን እና ስርጭትን መመርመር።
የህመም ተጋላጭነትን መመርመር/ የደም ግፊት፣ የልብ አመታት፣ የአተነፋፈስ ሁኔታ፣ የደም ውስጥ የስኳር መጠን፣ የኮሌስትሮል መጠን ወ.ዘ.ተ
• የአካላዊ ጥንካሬን፣ የመተጣጠፍ አቅምን፣ አካላዊ ፅናትን መፈተሽ ያስፈልጋል።
• አዕምሯዊ ጤና ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ለተለያዩ የአዕምሯዊ የጤና እክሎች ይጋለጣሉ። አስተሳሰባቸው፣ ፀባያቸውን፣ ስሜታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ድርጊታቸውን በተለያዩ መንገድ እና መጠን ተፅዕኖ የማሳደር አቅም እና ጉልበት አለው። የአዕምሮ ጤና በተለያዩ ነገሮች እና ሁኔታዎች ይወሰናል። የተፈጥሮ ሁኔታ (Gene) የህይወት ተሞክሮ እና ልምድ፤ የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ግንኙነት ለአዕምሮ ጤንነት ወሳኝ ከሚባሉት ሁኔታዎች ይጠቀሳሉ። የአዕምሮ ጤንነት ሙሉነት ሰዎችን ሙሉ አቅማቸውን እንዲያውቁ እና እንዲተገብሩ ሲረዳ፤ በህይወታቸው ለሚፈጠሩ ማንኛውም ጫና የመቀበል አቅማቸውን ያጠናክራል።
በተጨማሪም በማህበረሰብ ውስጥ የስራ ምርታማነታቸውን እና አስተዋፅኦቸውን ይጨምራል። የአዕምሮ ጤና በውስጡ የተለያዩ የአዕምሮ ጤና አይነቶችን ይይዛል። ከነዚህም ውስጥ የስሜት ጤና /Emotional Health/ስነ ልቦናዊ ጤና /Psychological Health/ እና ማህበራዊ ጤና /Social Well-being/ ይጠቀሳሉ።
አንድ ግለሰብ ከላይ የተጠቀሱት የአዕምሮ ጤና አይነቶች በአንዱ ወይንም በሁሉም ሊታመም ይችላል። አዕምሮ ህመም እንደማንኛውም የጤና እክል ህክምና ማግኘት እና መታከም የሚቻል ሲሆን፣ ታካሚው ከህመሙ ሙሉ ለሙሉም ሊድን ይችላል። አንዳንድ ግዜ የአዕምሮ ህመም ከአካላዊ ህመም ጋር ሊያያዝ ይችላል። ይህም ማለት አዕምሯዊ የጤና እክል ለአካላዊ የጤና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። እንዲሁም በተገላቢጦሽ አካላዊ የጤና እክል ለአዕምሯዊ ጤና ችግር ካለን ከምንጠቅሳቸው ውስጥ ድባቴ(ድብርት) ጭንቀት፣ የስሜት መዋዠቅ/ Bipolar/ ወ.ዘ.ተ ናቸው።
ማህበራዊ ጤና ማህበራዊ ጤና ከአዕምሯዊ እና አካላዊ ጤና ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተዛማጅነት ያለው የጤና አይነት ነው። ማህበራዊ ጤና ማለት ሰዎች ከአካባቢያቸው እንዲሁም ከማህበረሰባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እና የግንኙነት አቅም፣ ችሎታ እና አይነት ነው። ማህበራዊ ጤና የራሱ መስፈርት ያለው ሲሆን ማህበራዊ ጤናማነት ከቦታ ቦታ፤ ከባህል ባህል፤ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ የሚለያይ ነው። ሆኖም ግን የሰው ልጅ በአንድ አካባቢም ሆነ በሌላ አካባቢ ቢኖርም ሰዎች በጋራየሚስማሙባቸው የማህበራዊ የጤና መስፈርቶች አሏቸው። አካላዊ ጤና እና አዕምሯዊ ጤና በማህበራዊ ጤና ላይ በአሉታዊም ሆነ አውንታዊ መልኩ ማህበራዊ ጤና ላይ የራሳቸውን ተፅእኖ አላቸው። ለምሳሌ ብንወስድ አንድ አካል ጉዳተኞች በአካል ጉዳት የሚያጋጥመው ችግር ለምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። እንዲሁም በአንዳንድ የካንሰር ዓይነት የተያዙ ሠዎች የሚኖራቸው የስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ችግርም ይጠቀሳል።
ቅድመ ጥንቃቄ (Preventation) ሰዎች በህይወታቸው ከሚያጋጥሟቸው የጤና እክሎች አብዛኛዎቹ የሚጠቁት ቀድመው ለበሽታ የሚዳርጉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ባለመገንዘባቻው የሚከሰቱ ናቸው። ተላላፊም ሆኑ ተላላፊ ያለሆኑ ህመሞች ቅድመ ጥንቃቄን በማድረግ ከሚከሰተው ህመም ራስን መጠበቅ ይቻላል። አንዳንድ ጊዜም ህመሙ ሲከሰት እንኳን ጥንቃቄውን በመውሰድ ህመሙን ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ የከፋ ደረጃ እንዳይሻገር ይረዳል። አልፎም ህመሙ ተላላፊ ከሆነ በዙሪያችን የሚገኙ ሰዎችን ከህመሙ ለመጠበቅ ይረዳል። ለአካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ህመም በሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች ከህመም ህመም የሚለያዩ ናቸው። በአጠቃላይ ግን ለተላላፊም ሆነ ተላላፊ ላልሆነ ህመም የሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን እንደሚከተለው ይሆናል።
• ራስን ከታካሚ ሰውነት የሚወጣን ፈሳሽ መጠበቅ (ጓንት ማድረግ፣ የፊት ማስክ ማድረግ እና ወ.ዘ.ተ)
• የመመገቢያ ሳህኖችን፣ የመጠጥ እቃዎችን፣ የመኝታ እና የመታጠቢያ እቃዎችን እና አከባቢን በንፅህና መጠበቅ።
• የራስን ስሜት ማዳመጥ እና ከወትሮው የተለየ አካላዊ ወይም አዕምሯዊ ለውጥ ባለ ግዜ ወደ ህክምና መሄድ። • የህመም ስሜት ሲመጣ፣ የስሜቱን መጠን፣ የሚመጣበትን ፍጥነት፣ ማበበሻ ምክያቱን ማጤን እና ለሃኪም በአግባቡ ማስረዳት።
• እድሜን እና የጤና ሁኔታን ያገናዘበ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ። • በየጊዜው አጠቃላይ የጤና ምርመራን እና ክትትል (General Medical Checkup) ማድረግ።
• በአግባቡ እና በንፅህና የመፀዳጃ ስፍራዎችን መጠቀም።
• የአመጋገብ ስርዓት እንዲሁም የሃኪም ትዕዛዝን መተግበር።
• ቁመት ከክብደት (BMI)፣ ከፆታ ጋር ያገናዘበ አቋም እና ወ.ዘ.ተ ናቸው።
ህክምና ህክምና ማለት ሰዎች ካጋጠማቸው አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ እክል በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ ነው። የህክምና አይነቶች የተለያዩ ናቸው። እንደ ህክምና ማግኛው ዘዴ እና መንገድ (method) ፣ እንደ ህክምናው ዓለማ (objective) እንዲሁም እንደ ህክምናው አሰጣጥ (mode) ይለያያል።
• ህክምና በመስጫው ዘዴ እና መንገድ በሁለት ይከፈላል። እነዚህም ዘመናዊ ህክምና እና ባህላዊ ህክምና ናቸው። ዘመናዊ ህክምና ማለት በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፈ ምርመራ እና ህክምና ማለት ነው። በአንፃሩ ባህላዊ ህክምና ማለት በሳይንሳዊ መንገድ ያልተረጋገጠ ነገር ግን ሰዎች በጊዜያት እና በልምድ ፈዋሽነታቸውን ያረጋገጡባቸው የህክምና አይነት ነው።
• የህክምና አይነት በህክምና ዓለማ (objective) ይከፈላል ስንል፣ ፈዋሽ (curative) ህክምና እና ፈውስ የሌላቸው ህክምና (supportive Treatment) ናቸው። ፈውስ ያላቸው ህክምናዎች ታካሚው ካለበት የጤና እክል ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው ነፃ የሚሆንበት ነው።
ባንፃሩ ደግሞ ፈውስ ያሌለው ህክምና የምንለው ታካሚው ያለው ህመም ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው ነፃ የማይሆንበት ነገር ግን የበሽታው መጠን፣ ስርጭት እንዲሁም የሚደረገው የህክምና አይነት ነው።(ለምሳሌ፦ ደም ግፊት፣ ስኳር)
• ህክምና በአስጣጥ ይከፈላል ስንል፣ አብዛኛው ማህበረሰብ ህክምና ማለት መድሃኒቶችን በመስጠት ብቻ የሚደረግ ነገር አድርገው ይመለከታሉ። ነገር ግን ህክምና በሚሰጥ ሁኔታ ለሁለት መክፈል ይቻላል። እነዚህም መድሃኒት ነክ ህክምና (pharmacological) እና መድሃኒት ነክ ያልሆኑ(non-pharmacological) በመባል ይከፈላሉ። የተለያዩ መድሃኒቶችን በመጠቀም በሚዋጥ እንክብል መልክ፣ በሽሮፕ፣ በመርፌ እንዲሁም በሚቀባ መልክ ለተለያየ ህመም ሊሰጥ ይችላል። መድሃኒት ነክ ያልሆኑ የህክምና አይነቶች ደግሞ በውስጣቸው ብዙ የህክምና ዘርፎችን ይይዛሉ። ለምሳሌ የቀዶ ህክምና፣ የምክር አገልግሎት፣ የጨረር ህክምና፣ የአካል ብቃት ህክምና(physiotherapy)፣የደረቅ መርፌ ህክምና (acupunctute) ወ.ዘ.ተ ናቸው። አንድ ግለሰብ እንደ ህመሙ አይነት አንዱን ወይንም ሌሎቹን በማጣመር ህክምናውን ሊያደርግ ይችላል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011