የኦቶማን ቱርክ የግብፅ አስተዳዳሪ ሆኖ በ18 12 ዓ.ም የተሾመው ሙሐመድ ዓሊ ወደ አፍሪካ መጣ። በወቅቱ የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር መዳከምን ያስተዋለው አልባኒያዊው ሙሀመድ ዓሊ ፓሻ የራሱን ግዛተ ዐፄ ወይም ኢምፓየር ከግብፅ ወደ ደቡብ እና ከሰሜን እስከ መካከለኛው ምስራቅ ለመዘርጋት ዕቅድ ነበረው። ይሁን እንጂ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሊያደርግ ያሰበው ዘመቻ በወቅቱ አካባቢውን ይቃኙ በነበሩት በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ኃይሎች ሳቢያ ተገታ።
ሆኖም በደቡብ በኩል ከልካይ ያላገኘው ሙሀመድ ዓሊ በ1821 ሰሜን ሱዳንን ተቆጣጠረ። ወደ ኢትዮጵያም ማማተር ጀመረ። ከ18 12 እስከ 18 57 በሥልጣን የቆየው ሙሐመድ ዓሊ በዋናነት ራሷን የቻለች እና ከኦቶማን ቱርኮች ነፃ የሆነች ግብፅን መሠረተ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የኦቶማን ግዛቶች የነበሩ የቀይ ባህር እና የህንድ ውቅያኖስ አዋሳኝ ጠረፎችንም በግብፅ ሥር ለማድረግ ጥሯል።
የግብፅ ሱዳንን መያዝ ተከትሎም ከኢትዮጵያ ጋር በዋድ ካልታቡ፣ በወልቃይት እና በጠገዴ አካባቢ የተደረጉ ጦርነቶች ነበሩ። ጠንከር ያለ ጦርነቶች የተካሄዱት ግን የሙሐመድ ዓሊ የልጅ ልጅ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ (1863-1879) ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ነው።
የአያቱን የመስፋፋት ሃሳብ ለማሳካት፤ በአሜሪካውያን እና በአውሮፓውያን አማካሪዎች እና በቅጥረኛ ወታደሮች ታጅቦ ግዛቱን ለማስፋፋት ፈለገ። የኬዲቭ ኢስማኤል ፓሻ ግቡ በግዛት ማስፋፋት ብቻ የተገታ አልነበረም። የታሪክ ሰነዶች እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያን ለመውረር ቆርጦ የነበረው በዋናነት በጣና ሐይቅ እና በጥቁር አባይ ላይ ያነጣጠረ የግብፅን ኢምፔሪያሊስታዊ ፍላጎት ለማሳካት ነበር።
የኬዲቭ እስማኤል ታሪክ ጸኃፊ እንደገለጸው እና በስቨን ሩቢንሰን (19 76) እንደተጠቀሰው «የኬዲቩን ቅኝ ግዛት ሥራ በአንድ አገላለጽ ማጠቃለል ይቻላል፤ ሁሉንም የናይል ተፋሰስ መሬት በሀገሩ ቁጥጥር ሥር በማድረግ የናይልን ወንዝ ግብፃዊ ወንዝ ማድረግ ይፈልግ ነበር።» ይህንን ለማሳካትም ተደጋጋሚ እና ያላቋረጡ የወረራ ሙከራዎችን አድርጓል። ነገር ግን ሁሉም ሙከራዎች እየከሸፉ በግብጾች ላይ መከራና ውርደት አስከተሉ።
በዋናነት ከሚጠቀሱት ሁለት ዓበይት ጦርነቶች አንዱ ከ146 ዓመት በፊት የተካሄደው የኅዳር 8 ቀን 1869 ዓ.ም (የጐንደት ጦርነት -ግብጾች ያለቁበት ያልተነገረለት አውደ ውጊያ ከተሰኘ የመረጃ ምንጭ የተወሰደ) የጉንደት ጦርነት ነው። በዓመቱ ደግሞ የተካሄደው የጉራዕ ጦርነትም ይጠቀሳል። የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሀንስ ግብፅ የኢትዮጵያን ግዛት መድፈሯን ለወቅቱ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ከጦርነቱ ቀድመው በተደጋጋሚ አስታውቀው ነበር።
ከዲቭ እስማኤል ግን ሲመቸው በትዕቢት ሳይመቸው ደግሞ በትሁት ዘዴ (በመቅለስለስ) የአፄ ዮሐንስ ራብዓዊን መልዕክትና ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ። አውሮፓውያኑ መንግሥታትም ለንጉሰ ነገስቱ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም ነበር። በሁለቱም ጦርነቶች ወራሪዎቹ ግብፆች እና አጋዥ ቅጥረኛ ወታደሮች እና አማካሪ ጄኔራሎች ሽንፈትን ተጎንጭተው ተመለሱ። ድልም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ሆነ።
የጉንደት ጦርነት የተካሄደው በግብፁ ከዲብ እስማኤል ፓሻ እና በኢትዮጵያው አፄ ዮሐንስ ራብዓዊ (አራተኛ) መካከል ነው። ንጉሡ የነገሡት በጥር 18 72 ዓ.ም ሲሆን፣ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ኢትዮጵያ በሦስት አቅጣጫ በወራሪዎች የተወጠረችበት ወቅት ነበር። ይኸውም በሰሜን አቅጣጫ ግብፅና ጣሊያን በስተምዕራብ ደግሞ መሀዲስት ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸሙበት ወቅት እንደነበር ታዬ ቦጋለ የጻፉት መራራ እውነት የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ያስረዳል።
ንጉሡ በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ከግብፃውያን ጋር ተፋልመዋል። በ1870ዎቹ የግብፁ ከዲቭ እስማኤል በሚያስተዳድረው የሱዳን ግዛትና በኢትዮጵያ ድንበር መካከል ግጭቶች ነበሩ። በተለይ የትግራይና ኤርትራ ግዛትን የሚዋሰኑት አካባቢዎች ስጋት የተጋረጠበት ነበር። ምፅዋም በወቅቱ በግብፅ ሥር መሆኗ አንዱ ስጋት ሆኖ ነበር፤ ምፅዋን የተቆጣጠረው የግብፅ ጦር በዘመናዊ መንገድ የታነፀ ጥብቅ ወታደራዊ ኃይል እንደነበረው ሃሮልድ ጂ. ማርኩስ የጻፉት እና ሙሉቀን ታሪኩ የተረጎሙት የኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ ያስረዳል። በወቅቱ ወርነር ሙዚንገር ምጽዋን ያስተዳድር ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ነገር እንዳይገባ በመጠበቅ ከንጉሥ ዮሐንስ ሊቃጣበት የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ይጥር ነበር።
ዐፄ ዮሐንስ ከነገሡ በኋላ በ18 73 ወደ ጎንደር ሄደው የበጌምድርን ዕውቅና አገኙ፤ የጎጃሙን ራስ አዳል በኋላ ንጉሥ ተክለሃይማኖት እና የየጁውን ራስ ወሌ በማስገበር በሥራቸው አዋሉ፤ የሸዋው ምኒሊክም ለመገበር ተስማሙ። በዚህም በ18 75 ወደ ትግራይ ሲመለሱ አገሪቱን በአንድ ላይ አስተባብረው ጨርሰው እንደነበር ከላይ የጠቀስነው መጽሐፍ ያስረዳል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግብጻውያን ክፍተቱን ተጠቅመው ገላባትን እና የምፅዋን ደቡባዊ ግዛቶች ተቆጣጥሩ። በወቅቱ የግብፁ ካዲቭ እስማኤል ፓሻ ጀርመናዊውን ወርነር ሙዚንገርን የምስራቅ ሱዳንና የቀይ ባህር ዳርቻ አስተዳዳሪ አድርገው ሾመው። በሙዚንገር ተተክቶም አራኪል ቤይ ኑባር ምፅዋን ማስተዳደርም ጀምሮ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ ሙዚንገር የአቅጣጫ ማሳያ ካርታ፤ ጥቂት የጦር መሪዎችና ከ3ሺህ እስከ 4ሺህ የሚደርሱ ወታደሮች በቂ መሆናቸውን ለካዲቭ እስማኤል አስረዳ። በ18 75 ላይ ሁሉም ነገር ከተሟላ በኋላ ካዲቭ እስማኤል መላው የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አራት ዘመቻዎች አዘዘ። በዘመቻዎቹ ግብፅ ሐረርንና የሱማሌን ጠረፎች ያዘች።
በሙዚንገር የተመራው ዘመቻ በታጁራ በኩል አድርጎ ሸዋን እንዲቀላቀል የታለመ ነበር። ነገር ግን ጥቅምት 14 ቀን 18 75 ዓ.ም ላይ በአውሳ አፋሮች በደረሰበት ጥቃት ዘመቻው ከሸፈ። አፋሮች በወቅቱ በግብጽ ጦር ላይ በሰነዘሩት ጥቃት የጦሩን አዛዥ ሙዚንገርን ጨምሮ ሁለት ሦስተኛውን የግብጽን ጦር ደመሰሱት።
ከሽንፈቱ በኋላ ግብፅ በአራኪል ቤይ ኑባር እና ኮሬን አሬንድሮፕ ፓሻ የሚመራ ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ በማዝለቅ የሠራዬንና የሀማሴን ግዛቶች ተቆጣጠረች። አፄ ዮሐንስ ጥቅምት 15 እና 16 ምሽት ላይ ወደ 70 ሺህ የሚጠጋ ጦራቸውን በማንቀሳቀስ ከመረብ ዳርቻ በምትገኘው ጉንደት የተባለች ቦታ ላይ የግብፅን ጦር ደመሰሱት። በወቅቱ የግብጽ ወራሪ ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስ የጦር መሪዎቹ አራኪልና ኢሬንድሮፕ ሳይቀር ተገደሉ። በወቅቱ የግብጽ ጦር የታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ ሁሉ በንጉሡ እጅ ገባ።
የጉንደት እና ገራዕ ጦርነት በዓመት ልዩነት በኢትዮጵያ እና ግብፅ መካከል 1875 እስከ 76 የተካሄደ ጦርነት ነው። በጦርነቱ በጉንደትና በዓመቱ በጉራ ላይ ኢትዮጵያ በግብፅ ጦር ላይ ድል ብትቀዳጅም የተሟላ ድል መሆን እንዳልቻለ የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፤ ዐፄ ዮሐንስ ከ18 76 እስ 18 85 ባሉት አስር ዓመታት ግብፅ ከያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ጠራርጎ ለማስወጣት ሙከራ አላደረጉም። የምፅዋ ወደብና የዳህላክ ደሴቶች እና የሰሜኑ ግዛት በዚህ ጊዜ በግብፆች እጅ ነበሩ።
ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ በ19 01 ዓ.ም የጻፉት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ መፅሐፍ « የምስር (ግብፅ) ንጉሥ ወዳጤ ዮሐንስ ብዙ ጦር ለመዋጋት ላከ … ዐጤ ዮሐንስ በቱርክ መምጣት ደንግጠው የድፍን ኢትዮጵያን ጦር ክተት አሉ። … የምስር ጦርም ጉንዳጉንዲ ደረሰና ምሽጉን አበጀ።
ጦርነቱ እስማኤል ፓሻ ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜትና ድልአድራጊነት ተስፋ ሰጥቶት ነበረ። ይህም የሆነው ብዙ ሰራዊቱ ይመራ የነበረው ሠፊ ወታደራዊ ስልጠና በወሰዱ አውሮፓውያን እና የአሜሪካን የጦር መኮንኖች ነበር።
ህዳር 8 ቀን 1869 ዓ.ም አጤ ዮሐንስ የእስማኤል ባሻን ሠራዊት ገጠሙ። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች በኮረብቶችና ምሽጎች ተሸሽገው ሲዋጉ የነበሩ ግብፃውያንን በመግደልና በመማረክ ድልን ተጎናፀፉ። ወሬ ነጋሪም ሳይቀር ቱርክን እንደ ካንቻ (በጎራዴ እንደ መጨፍጨፍ) መቱት።
ባውሳ የወጣውም የምስር ጦር ያውሳው ንጉሥ መሐመድ ሃንፈሬ ወዳጅ መስሎ ፍሪዳውን ወተቱን ሰጥቶ እንግድነት ተቀብሎ አሳድሮ ሌሊት ምንም የለብን ብሎ ከተኛበት ለዘር ሳይቀር አርዶ አርዶ ጣለው ። » ሲል መጽሐፉ ያትታል።
በዘናመዊው ዘመን በሁለቱ አገሮች የተካሄደ ጦርነት ነው። በጦርነቱ የተገኘው ድል አፍሪካን ለመቀራመት ለሚያስቡት ነፃነቱዋን ጠብቃ የኖረችን ኢትዮጵያን ለመቀራመት የማይቻል መሆኑን አመላከታቸው። በአንፃሩ ራስዋን የአፍሪካ ኢምፓየር አድርጋ ስላ የነበረችው ግብፅ በጦርነቱ በደረሰባት ምጣኔ ሀብታዊና ስነ ልቦናዊ ኪሳራ ልታንሠራራ አልቻለችም፤ ከአስር ዓመታት በኋላም የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ለመሆን በቃች።
የጉንደት ጦርነት በኢትዮጵያና በግብጽ ከተደረጉ ዘመናዊ ጦርነቶች አንዱ ሲሆን ግጭቱ ለኢትዮጵያ አሻሚ ያልሆነ ድልን ያጎናጸፈ ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነቷን አስከብራ ለዘለቀችው ኢትዮጵያ ቀጥሎ የመጣውን አፍሪካን የመቀራመት የአውሮፓውያን ዕቅድ እንዳትታሰብ ያደረጋትም ነው። በተቃራኒው ከላይ እንደገለጽነው ጦርነቱ ግብፅ በኢትዮጵያ ጦር ሽንፈትንና ውርደትን መጎናጸፍዋ ዕዳና ፍዳ አምጥቶባታል። ከ10 ዓመት በኋላ አቅመቢስ ሆና በባርነት ቅኝ እንድትገዛ አድርጓታል ሲሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ኢምፓየር ለመሆን ያሰበችው ግብፅ በጦርነቱ በደረሰባት ምጣኔ ሀብታዊና ስነልቡናዊ ጉዳት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት ተዳርጋለች። የግብፅ ሃሳብ የነበረው የአባይ ሸለቆን አካባቢና የጥቁር አባይን ምንጭን መያዝ ቀጥሎም የነጭ አባይን ተፋሰስ ሀገሮች መቆጣጠርና ምንጩን መያዝ ነበር። ማለትም ቻድንና ጅቡቲን ጨምሮ እስከ ዑጋንዳ ያሉ አገሮች በማጠቃለል ለመዝለቅ እና ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ጋር ለመፎካከር ነበር። ሁሉም ግን ቅዠት ሆኖ ቀረ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም