ወደኋላ በዐይነ ህሊናችን መለስ ብለን የዛሬ 123 ዓመት አካባቢ የነበረችውን ኢትዮጵያን ለመቃኘት ስንሞክር አገራችን ኢትዮጵያን እንደሚከተለው ሆና እናገኛታለን። በተደጋጋሚ በተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች የደቀቀች ይህንን ተከትሎ ኢኮኖሚዋ የተዳከመ፣ ህዝቦቿ በኋላቀር የአኗኗር ዘይቤ የሚኖሩና ዕውቀት ገና ያልተስፋፋባት፤ የተደራጀ ሰራዊት ያልነበራትና ከኋላቀር መሳሪያ ውጪ እዚህ ግባ የማይባል ትጥቅ የሌላት ምስኪን አገር።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የያኔዋ ጣሊያን እንዲህ ነበረች። በአውሮፓ የተስፋፋው የኢንዱስትሪ አብዮት የጎመራባት ይህንን ተከትሎም ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅሟ የፈረጠመ፤ በዘመኑ አለ የተባለውን የጦር መሳሪያ እስከአፍንጫዋ የታጠቀች ይህንንም ተማምና ማንንም በጡንቻ ደፍጥጦ መጨፍለቅ እችላለሁ የሚል ትምክህት የተጠናወታት ሃያል አውሮፓዊ አገር። ይህ ቁሳዊ ንጽጽር ነበር ፋሽስት ጣሊያን የማይነካውን የንቦች ቀፎ እንድትነካ የገፋፋት።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን! ከዚህም ባሻገር ጎረቤቶቿና ሸሪኮቿ የነበሩ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት መውረር የፈለጉትን አገር ያለምንም ከልካይ ዘው ብለው ገብተው መቆጣጠራቸው በኢትዮጵያስ ምን የተለየ ነገር ይገጥማል የሚል የተሳሳተ ስሌትን እንድታሰላ ገፋፍቷታል። አርግጥ ነው ከቁሳዊ ነገር ንጽጽር አንጻር የያኔዎቹን ኢትዮጵያና ጣሊያንን ለማነጻጸር መሞከር ዳዊትን እና ጎሊያድን እንደማነጻጸር ሊቆጠርና ሊያስገርም የሚችል ነገር ነው።
ዳሩ ግን ወራሪው የጣሊያን ፋሽስት ግልጽ ያልሆነለት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያውያን ምንም ይራቡ፣ ይጎሳቆሉና ይኮሰምኑ እንዲሁም በምንም ዓይነት የውስጥ ችግርና አለመግባባት ውስጥ ይኑሩ የሀገራቸውን ሉኣላዊነት የማያስደፍሩ ተርብ የሆኑ ዜጎች አገር መሆኗ ነበር። ስለሆነም በውጫሌ ውል የአጉል ብልጣብልጥነት አባዜ የተደረገው የፋሽሽት ጣሊያን የአገር መውረር ተግባር ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ አስቆጣ።
ዓለም ከዚህ በፊት ይደረጋል ብላ ልትገምተው የማችለውን ክንውን እንድታይም መልካም የታሪክ አጋጣሚ ተከሰተ። ኢትዮጵያውያን ትግሬ አማራ፣ አፋር ኦሮሞ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ ሶማሊ፣ ሁሉም ማንም ከማን ሳይለይ ውስጣዊ ችግሩንና ጉሰቁልናው ወደጎን ትቶ የትዕቢተኛ ወራሪዎችን እኩይ ተግባር ለመመከት ሚስቴ፣ ልጆቼ እርሻዬና ኑሮዬ ሳይል አድዋ ከተተ።
ግፍ እንደተፈጸመበት እንጂ በማንም ላይ ግፍ እንዳልፈጸመ፤ ድንበሩ እንደተገፋበት እንጂ የማንንም ድንበር እንዳልገፋ ብጥርጥር አድርጎ የተረዳው ኢትዮጵያዊ የአገሩን ህልውና በደሙ ሊጠብቅ ወድ ህይወትና አካሉን መተኪያ ለሌላት አገሩ በኩራት ሊሰዋ በንጉስ ሚኒሊክ ወኔ አነሳሽ ጥሪ የአድዋ ተራሮችን የታሪክ ምስክር አድርጎ ይፋለም ገባ።
ይህ ጦርነት የድል ሚስጥር እውነት ትክክለኛ ዓላማና የሀገር ፍቅር ስሜት እንጂ ከአፍ እሰከ አፍንጫ መታጠቅና የኢኮኖሚ አቅም ልቀት እንዳልነበረ አፍ አውጥቶ የመሰከረ ጥቁር በነጭ ላይ ድል ሊቀዳጅ አይችልም የሚለውን ስንኩል አስተሳሰብ የቀበረና ውጤቱን ዓለም አስሬ አድምጦ እውነት መሆኑን ለመቀበል የተቸገረበት ነበር።
አዎ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና እንድትቀጥል ኢትዮጵያ መሆንን በመረጡ ውድ ልጆቿ ደም የንቦቹን አገር መዳፈር እሳትን በእጅ ከመጨበጥ የበለጠ አደገኛና የማይሞከር መሆኑን ኢትዮጵያውያን በጋራ በፈሰሰ ደማቸው አረጋገጡ። በእለቱ በአድዋ የፈሰሰው ደም አንድም የሰውን አገር ለመውረር መጥተው በከንቱ ደማቸው የፈሰሰ የጣሊያን ሰራዊት ደም ሌላው የአገራቸውን መደፈር ከሚያዩ ሞታቸውን የመረጡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የህብር ደም ነበር።
እናም ዛሬ ላይ ቆመን የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁሮችና ነጻነታቸውን የተቀሙ ማንኛቸውም ህዝቦች ድል የሆነውን የአድዋን ድል ስንዘክር ድሉ በመላ ኢትዮጵያውያን ህብር ደም የተገኘና የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል መሆኑን ሳንዘነጋ ሊሆን ይገባል። ለአገራቸው ፤ሉዓላዊነትና ለነጻነት ረሃብና ጥም ሳይበግራቸው አብረው ዘምተው አብረው ተፋልመው የህብር ደም በጋራ አፍስሰው ለዚህ ኩራት ያበቁንን እንቁ ጀግኖቻችን የምንዘክረውም በጋራ እንደፈሰሰ ደማቸው አንድነታችንን አጥብቀን ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011