
‹‹ያለ አፈር ምርት ፤ ያለሴት ዘር አይታሰብም ›› በሚል በአንድ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ አድምጫለሁ። ስለ አፈር ጥቅም የጠየቅኳቸው ግለሰቦችም በአፈር ዙሪያ ያላቸው አስተሳሰብና ግንዛቤ ከባለሙያዎቹ እና አርሶ አደሮች ብዙም የተለየ አይደለም ። በአፈር ጠቀሜታ ሁሉም ተግባብቷል። ይሁን እንጂ እንዴት እንጠቀምበት? ሲጎዳስ እንዴት ይታከም በሚለው ዙሪያ የዘርፉን ምሁራን ምክረ ሃሳብ መቀበል ያስፈልጋል። አፈር ምርታማነቱንና ተፈጥሮውን በማመጣጠን በእንክብካቤ የምንይዘው ከሆነ እንደታዳሽ ኃይል የሚቆጠር መሆኑን ከኢንሳይክሎፒዲያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ አፈር በቀለምና በባህሪ የተለያየ ሲሆን አይነቶቹም ወደ አስር ይደርሳሉ። ከነዚህ መካከልም ጥቁር እና ቀይ አፈር ይካተታል። የሚሰጡት ጥቅምም እንደ አይነታቸው ይለያያል። አይጠቅምም የሚባል የአፈር ሀብት የለም። ለምርትና ምርታማነት ወይንም ለተክሎች የማይውል ቢሆን እንኳን ለግንባታ አገልግሎት ይውላል። ይህም የሚሆነው አፈር በተለያየ መልኩ በውስጡ ያለው ንጥረ ነገር ሲወጣና ለምነቱን ሲያጣ ብቻ ነው።
በደብረዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በቤተሙከራ ውስጥ የሚሰሩት የአፈር ባለሙያ አቶ መሐመድ ይማም እንዳስረዱት፤ አፈር ከምድር በረከቶች መካከል አንዱና 99 ከመቶ የሚሆነው ብዝሀ ህይወት ከአፈር ጋር የተገናኘ ነው። 99 በመቶ እንዲሁ ምግብ የሚገኘው ከአፈር ነው። አፈር እንደ አንድ ነዳጅ፣የከበሩ ማዕድናት ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ሲሆን የሰው ልጅን ጨምሮ ለፍጥረታት ሁሉ የህይወት መሠረት ነው። አፈር ከሶስት ነገሮች የተዋቀረ ወይንም ኮፓናንት አሉት።እነዚህም ኬሚካል፣ ባዮሎጂካልና ፊዚካል ናቸው። አንዱ ለሌላው መኖር በጣም አስፈላጊ ነው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ቢጎድል ወይንም የመቀያየር ሁኔታ ከተፈጠረ የአፈሩ ይዘት ይቀየራል።
ባለሙያው ምሳሌ ጠቅሰው እንዳስረዱት፤ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ሲባል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል። ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ የሚውለው አፈር ውስጥ ያለው ንጥረነገር (ሚኒራል) በተለያየ ምክንያት እየቀነሰ ሲሄድ ነው። ይሄ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ኬሚካል ስላለው አፈር ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ንጥረነገሩን ይገለዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ የተፈጥሮ አፈሩ ያለማዳበሪያ እገዛ ምርታማነትን ማሳደግ አይቻልም። ኬሚካል የሚባለው በአፈር ውስጥ ያለውን ሚኒራል የሚያሳይ ሲሆን በውስጡም ናይትሮጂን ፣ ፎስፈረስ የተባሉ ንጥረነገሮች ይይዛል። ባዮሎጂካል የሚባለው ደግሞ በአፈር ውስጥ የሚገኙ ህይወት ያላቸውን ነገሮች ለማብላላት የሚረዳ ነው። ይህ ሂደት ካልተከናወነ ህይወት ያላቸው ነገሮች ይሞታሉ ወይንም ይጠፋሉ።
ፊዚካል ወይንም ውጫዊው በእጅ ተዳስሶ የሚታየው ጠጣሩ ነገር አፈር ነው። ይህ የሚታየው ወይም የሚዳሰሰው አካል በግብርና ሥራ ወቅት በቀላሉ የሚታረስና የማይታረስ፣ በውስጡም ውሃ የሚያቁር ነው። አፈር በአግባቡ ካልተያዘ በጎርፍ፣በንፋስና በተለያየ መንገድ ተጠርጎ የአፈር መራቆት ወይንም መመናመን የሚባለውን ችግር ያስከትላል። አፈር አላቂ ሀብት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። አንድ አፈር ለማግኘት አንድ ክፍለዘመን ይፈልጋል። አፈር መፍጠር በሚገባበት ክፍለዘመን ካልተተካ እንደአላቂ ሀብት ነው የሚወሰደው። በመሆኑም አፈር በተለያየ መንገድ እንዳይመናመን እንክብካቤን በማድረግ መታደግ ይገባል። ለዚህም ነው ኬሚካል፣ፊዚካልና ባዮሎጂካል የተባሉት ግብአቶች ሳይነጣጠሉ መጠበቅ አለባቸው የሚባለው።
ይህ የተፈጥሮ ፀጋ በተለያየ መንገድ ለምነቱን የሚያሳጣ ጉዳት ያጋጥመዋል። በዚህ ላይም አቶ መሐመድ በሰጡት ማብራሪያ፤ አንዱ ችግር ተክሎችን ሙሉ ለሙሉ ከመሬት ውስጥ ማውጣት አፈሩ እንዲጎዳ ያደርገዋል። ለአየር መበከልም መንስኤ ይሆናል።ለእጽዋት እድገት ካርቦን ወሳኝ በመሆኑ ተክሎች አስፈላጊ ናቸው። የአፈር መሸርሸርም ለምነትን ከሚቀንሱ መካከል ይጠቀሳል። ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ከሚያጋጥማቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
በአፈር መሸርሸር አፈር ለምነቱን የሚያጣው እንደካልሼየም ፣ማግኒዚየም ፣ ናይትሮጂን የመሳሰሉት ንጥረነገሮች በጎርፍ ወይንም በተለያየ መንገድ ታጥቦ ሲሄድ ወይንም ሲሸረሸር ነው። እነዚህ ንጥረነገሮች አፈርን እንደ አንድ የማዕድን ሀብት ተደርገው እንዲወሰድ የሚያስችሉ ናቸው። በተለይም በኬሚካል ውስጥ ወደ 16 የሚሆን ንጥረነገሮች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አንዱ ንጥረነገር ቢጎድል እጽዋት አያድግም።ለእጽዋቱ እድገት ንጥረነገሮቹ መመጣጠን ይኖርባቸዋል።
ይህ ሲባል አፈሩን፣ አየሩንና ውሃውን ባካተተ መልኩ ነው። ንጥረነገሮቹ ከአፈሩ ውስጥ ከወጡ ወይንም ካለቁ አፈሩ ወደ አሲድነት ይለወጣል። የአፈር መሸርሸር በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች አሲዳማ አፈር እየሆነ ምርታማነታቸውን ይቀንስባቸዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በሚኖርበት አካባቢ፣ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራዎች፣ ማዳበሪያና ፀረተባዮችን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ከመጠን በላይ ለግብርና ሥራ መጠቀምም ከጉዳቶቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አቶ መሐመድ ይናገራሉ።
አፈር በተለያየ ምክንያት ይታመማል። በውስጡ ያሉ ንጥረነገሮች በተለያየ ምክንያት ሲወጡ ወይንም ሲጠፉ ነው ጉዳቱ የሚታወቀው። ጉዳቱ ተለይቶ ከታወቀም በማከም ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለስ ይቻላል። በተለያየ ምክንያት ከውስጡ ንጥረ ነገሩ ወጥቶ ወደ አሲድነት የተቀየረ አፈር ንጥረ ነገሮቹ ተመልሰው የቀድሞ ይዞታውን እንዲይዝና ምርታማ እንዲሆን በኖራ በማከም ንጥረ ነገሩ እንዲመለስ ይደረጋል። ንጥረነገሮቹ ከአፈር ውስጥ ከወጡ በኋላ ለመመለስ ከሚደረገው የማከሚያ ዘዴ ይልቅ ንጥረነገሮቹን ከአፈር ውስጥ እንዲወጡ የሚያደርገውን መከላከል በተሻለ ይመረጣል።
አሲዳማነትን ለመከላከል አንዱ ዘዴ የአፈር ጥበቃ ወይንም የእርከን ሥራ ማከናወን ነው። በአሁኑ ጊዜም በደጋ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጎልቶ የሚታየው የአፈር አሲዳማነት ነው። ሞቃታማ በሆኑት አካባቢዎች ደግሞ ጨዋማ አፈር እንዲሁ በስፋት ይገኛል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው ሞቃታማ መሆን ነው።በሙቀቱ ምክንያት የውሃ እጥረት ያጋጣማል። ይህ ደግሞ በተቃራኒው ነው ንጥረነገሮቹ በአንድ ቦታ ተከማችተው ወደ ጨዋማነት ይቀየራል። ይሄ በሚፈጠረው የውሃ አለመመጣጠን የሚከሰት ችግር ነው። በመሆኑም ጂብሰም በተባለ ግብአት ታክሞ ለምነቱ እንዲመለስ ይደረጋል። ከአፈር ጋር ተያይዞ
ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉትና እንደችግር የሚገለጹት ጨዋማና አሲዳማ የአፈር አይነቶች ናቸው። አቶ መሐመድ በሰጡት ምክረሃሳብ ሁለቱም ልዩ ትኩረት ይፈልጋሉ። በአካባቢ የአየር ንብረት እና ቀድሞ ሊሰራ በሚገባ ሥራ ምክንያቶች የሚፈጠር ችግርን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይጠበቃል። አሲዳማ አፈርን ለማከም ጥረት ከማድረግ ቀድሞ ለአሲዳማነት የሚያጋልጠውን መከላከል፣ጨዋማ የመስኖ አጠቃቀምን ማስተካከል ያስፈልጋል።
የተለያየ ንጥረነገር ውህድ ስለሆነው የአፈር አጠቃቀም ደግሞ አቶ መሐመድ እንዳብራሩት፤ የአፈሩ አይነትና ባህሪ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ ቢሆንም የተፈጥሮ ክፍተቱን በማስተካከል ተስማሚ ሆነው ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይቻላል። ጥቁር አፈር በንጥረነገር የተሟላ ሆኖ ነገር ግን በባህሪው ውሃ ያቁራል። ያለውን ክፍተት በማሻሻል ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይቻላል።
ጥቁር አፈር በኢትዮጵያ በመጠንም ለምርትና ምርታማነትም ተፈላጊ ነው። ሌላው ቀይ አፈር ነው። በደጋው የሀገሪቱ ክፍል በስፋት ይገኛል።ከፍተኛ ዝናብ ያለበት አካባቢ በመሆኑ አፈር በቀላሉ ታጥቦ ይሄዳል ወይንም ይሸረሸራል።በዚህ የተነሳም በውስጡ ያለው ንጥረነገር ታጥቦ ይሄዳል። ከውስጡ ታጥቦ የሚወጣውን ንጥረ ነገር ማከም ከተቻለ ለእርሻ ምቹ ነው።
አፈር ለምርትና ምርታማነት ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ውሃ በማጣራትም ትልቅ አቅም አለው። ከተሽከርካሪ፣ ከአምራች ኢንዱስትሪዎችና በተለያየ መንገድ የሚፈጠርን የአየር ብክለት ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ ነው። እዚህ ላይ የአየር ብክለትን ለመከላከል የተቃጠለ አየር ወደራሳቸው በመውሰድ ኦክስጂን ወደ ውጭ የሚያወጡት እጽዋቶች ከአፈር በሚወስዱት ንጥረነገር ነው።እጽዋቶቹ የወሰዱትን የተቃጠለ አየር ወደ አፈር በመመለስ ነው ውህደቱ የሚከናወነው።
አፈር በተፈጥሮ በውስጡ በያዘው ንጥረነገር ህይወት እየሰጠ እንደ ዩሪያ፣ዳፕ የመሳሰሉ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች ለምን አስፈለጉ? ለዚህም ባለሙያው ማብራሪያ ሰጥተዋል። አፈር በተፈጥሮው አስፈላጊ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ሽፋን ያለው ምርታማ መሬት በተለያየ ነገር በመጎዳቱ የሚፈለገውን ያህል ምርት ለመስጠት አያስችልም።
አሁን ካለው የምርት ፍላጎት ማደግና የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ምርት መመረት ይኖርበታል። ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ደግሞ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ መጠቀም ግድ ነው። ዩሪያ የተባለው ማዳበሪያ ናይትሮጂን ፣ዳፕ ደግሞ ፎስፈረስ የተባሉ ንጥረነገሮችን በውስጣቸው የያዙ ሲሆን፣እንደ ዚንክ፣ኮፐር የተባሉና ሌሎችንም ንጥረነገሮች ለመተካት እንዲሁ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
ሰውሰራሽ ማዳበሪያ በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኘውን ንጥረነገር እንዲይዝ ተደርጎ ቢዘጋጅም በተፈጥሮ የዳበረውን አፈር ለምነት ያሳጣል እየተባለ በተለያዩ ሰዎች ይተቻል።የተፈጥሮን ያክል ይሆናል ለማለት ባይደፍሩም ምግብ ከማጣት ግን ሰውሰራሽ ማዳበሪያው የተሻለ እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አንዴ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ካልዋለ ምርት ስለሚቀንስ ምርታማነትን ለማሳደግ ተብሎ የተጀመረው ሥራ ይስተጓጎላል። በሂደት ግን የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም የሚቻልበትን ዕድል የመፍጠር ሥራ መሠራት እንዳለበት ምክረሃሳብ ሰጥተዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀሙ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስም ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል።
አቶ መሐመድ በሚሰሩበት የደብረዘይት ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ በሚያከናውኑት የቤተሙከራ ሥራ በአፈር ውስጥ ያለውን ፊዚካል፣ባዮሎጂካልና ኬሚካል ንጥረነገሮችን ነው የሚመረምሩት። በአፈሩ ውስጥ እነዚህ ንጥረነገሮች መኖራቸውና አለመኖራቸውን በመለየት እንዲመረመርለት ለፈለገ አምራች ኃይል እንዲሁም ለተመራማሪዎች በሚሆን መልኩ መረጃ ያዘጋጃሉ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 /2014