
-ከተመዘገቡት ከ23ሺ በላይ መሳሪያዎች ውስጥ 42 በመቶ ፍቃድ የላቸው
አዲስ አበባ:- በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ባለው የከተማውን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ግለሰቦች በማንነታቸው ሳይሆን በተጠረጠሩበት ወንጀል ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና በከተማዋ መሳሪያ በአዲስ መልክ ከአስመዘገቡት ከ23ሺ በላይ 42 በመቶዎቹ ፍቃድ እንደሌላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዮናስ ዘውዴ ገለጹ።
ኃላፊው የጸጥታ ሥራን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በተጠረጠሩበት ወንጀል ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ነው።
እየተያዙ የሚገኙት ብሄርንና ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው በሚል እየተነገረ የሚገኘው ወሬ መሰረት የሌለው መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው፤ እየተካሄደ የሚገኘው አገርን የማዳን ሥራ ነው፣ ተጠርጣሪዎች ንጽህናቸው ከተረጋገጠ ለተንገላቱበት ይቅርታ እየተጠየቁ ይለቀቃሉ ብለዋል።
ወቅቱ አገርን ለማዳን በሚደረግ ርብርብ ላይና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመሆኑ የጸጥታ አካላት የተጠናከረ የጸጥታ ሥራ እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ በተደረገውም አሰሳ አሸባሪን ሲደግፉ፣ መረጃ ሲሰጡና ገንዘብ ሲያዘዋውሩ የተገኙ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ቢሮ ተጠርጣሪ ባለሙያን በምሳሌ በማንሳትም ግለሰቡ ተጠርጥሮ ሲፈተሽ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ሲያዘዋውር መያዙን አመልክተዋል። አንዳንድ የሸገር አውቶቡስ አሽከርካሪዎችም ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ ተጠርጥረው የተያዙ እንዳሉ ጠቁመዋል።
የጸጥታ ሃይሉና የሕዝቡ ቅንጅታዊ ሥራም የዓለም አቀፍ ሚዲያው የሚያሰራጩትን ምኞት እንዲከስር ማድረጉንም ገልጸዋል። ‹‹ሌቦችም እጅ ከፍንጅ እየተያዙ ናቸው፣ ወንጀልም እየቀነሰ መጥቷል፣ ሕብረተሰቡ ተባባሪነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል›› ሲሉም አሳስበዋል።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ አዲስ አበባ ከተማን የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የሰላምና ጸጥታ መዋቅሩ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የሪፐብሊካን ጋርድና የኦሮሚያ ፖሊስ የከተማዋን ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በ11 ክፍለ ከተሞች፣ 121 ወረዳዎች የተከፋፈለች ነች፤ ለጸጥታ ሥራው እንዲያመች በቀጠናና በብሎክ ጭምር በመለየት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
ከተማዋ በአንድ ሺህ 610 ቀጠና ተለይቷል፣ ሰባት ሺህ 916 ብሎኮች አሉ በመንደር ደረጃ 33 ሺህ 378 መንደሮችን (እያንዳንዳቸው ዘጠኝ አባወራዎችን የያዘ) በመያዝ ተለይተዋል።
ከአጎራባች ከተሞች ጋር በመቀናጀት የጸጥታ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሱሉልታ ከተማ ጋር፣ ለሚ ኩራ ከጣፎ ጋር፣ ንፋስ ስልክ ከሰበታ ጋር፣ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከዱከም፣ ከገላንና ከቢሾፍቱ ከተሞች ጋር በመቀናጀትና በመናበብ እየተሠራ መሆኑን በአብነት አመልክተዋል።
መሳሪያ ምዝገባን አስመልክቶ የከተማው ጸጥታ ቢሮ ያስተላለፈውን መረጃ ተከትሎ በጥቆማና በፍቃደኝነት ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከ23 ሺህ 300 በላይ መሳሪያዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።ከተመዘገቡት ውስጥም 42 በመቶ ፍቃድ እንደሌላቸው ጠቁመዋል።
በፍተሻ በርካታ የጦር መሳሪያና ተቀጣጣይ ነገሮች፣ ስለታማ መሳሪያዎች፣ በርካታ የባንክ ደብተሮች፣ ፓስፖርቶችና ካርታዎች እንደተያዙ አመልክተዋል። ዩሮ፣ ፓውንድና ዶላር፣ በሚሊዮን የሚቆጠር አሮጌው የኢትዮጵያ ብር፣ የውጭ ገንዘቦች፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ ሳተላይትና ኮምፓስ መያዙን አስታውሰዋል።
በተደረገው ፍተሻ 27 ሺህ ጣቃ የትግራይ ልዩ ሃይል ልብስ፣ የአፋር ልዩ ሃይል፣ 94 የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ልብሶች መያዛቸውን አመልክተዋል። በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜናም አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም በምዕራቡ ዓለም ጫና እና አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ የሚፈጽሟቸው ድርጊቶችን ለማውገዝ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ትዕይንተ ሕዝብ አስደናቂና አስደማሚ እንደነበር ገልጸዋል።ለውጭ ሃይሎች ታላቅ መልዕክት እንደተላለፈበትም ጠቁመዋል፡፡
በማግስቱ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው የእራት ገቢ ማሰባሰቢያም ከፍተኛ ገቢ የተገኘበት እንደነበር አመልክተዋል። አንድ ቢሊዮን 540 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል። ተግባሩ ባለሀብቱ ከአገሩ ጎን መሰለፉን፣ ሀብት ማፍራት የሚቻለው አገር ስትኖር መሆኑን የሚጠቁም መልዕክት እንዳዘለም ገልጸዋል።
የገቢ ማሰባሰብ ሥራው እንደሚቀጥል የጠቆሙት ሃላፊው፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን የሚወዱ የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበረሰብም አለኝታነታቸውንና አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከ30 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰልፍ በመውጣት የምዕራቡ ዓለም የሚዲያ ጫና እና የሸኔና ትህነግ ተጽእኖን በማስመልከት ተቃውሟቸውን እያሰሙ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም