አውሮፓውያን በ18ኛው ክፍለ ዘመን ላስፋፉዋቸው ኢንዱስትሪዎቻቸው ጥሬ ዕቃን ለማግኘትና ምርታቸውንም ለመሸጥ እንዲያመቻቸው የአፍሪካን አህጉር በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ በመወሰናቸው በበርሊኑ የአውሮፓ መንግስታት ጉባዔ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ሲወያዩ ኢትዮጵያም ቅኝ እንድትገዛ ከተወሰነባት አገሮች አንዷ ነበረች፡፡
ይህንኑ ዕቅድ ለመፈፀም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጀችው ጣሊያን ድንበር ጥሳ ስትገባ አፄ ምኒልክ ውቅያኖስ ተሻግሮ፣ ድንበር ሰብሮ የገባን ወራሪ ጠላት ለመደምሰስ “ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት” ብለው አወጁ፡፡ አዋጁ ኢትዮጵያን የማዳን ጥሪ ነውና ከንጉሱ የተኳረፈውም ሆነ የተወዳጀው አገሩን ከጠላት ወረራ ሊታደግ ስንቁን ሰንቆ በቀጠሮው ቦታው ወረኢሉ ላይ ከተመ፡፡ ጀግኖች አባቶቻችን ጎራዴ፣ ጋሻና ጦር ይዘው በአገር ፍቅር፣ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ ሆነው ለነፃነት ሊሞቱ ተሰለፉ፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ማለዳ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ የጠላት መድፎች አጓሩ፣ መትረየሶች አሽካኩ፣ ከመሳሪያ ላንቃ ጥይት እንደ ዝናብ ዘነበ፣ ጎራዴ ተመዘዘ፣ ጦር ተሰበቀ፣ እግረኛውም፣ ፈረሰኛውም ወደ ጠላት ምሽግ ገባ፡፡ ጦርነቱም በአንድ ቀን ውሎ ተጠናቀቀ፡፡ ወራሪው ኢጣሊያ ኪሣራና ውርደትን፤ አገራችን ኢትዮጵያም ክብርና ኩራትን ተጎናፀፈች፡፡
ዛሬ የምናወድሰው ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ተሰራ፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን መራር የትግልና የመስዋዕትነት ፍሬ ሲሆን፤ድሉ ለጥቁር ሕዝቦች ምሣሌ የሆነ ሐውልት ነው፡፡ ይህ የድል በዓል ዘንድሮ ለ123ኛ ጊዜ ነገ ይከበራል፡፡
በእርግጥም የአድዋ ድል የአፍሪካውያንና የመላው የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ነው፡፡ አፍሪካ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ያላት ስፍራ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሺህ ዘመናትን ከሚያስቆጥረው የአህጉሪቱ ታሪክ ውስጥ አፍሪካውያን እንደተቀሩት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በታሪካቸው አያሌ የብርሃንና የጨለማ ዘመናትን ሲያሳልፉ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀው ያሳለፉት ዘመናቸው ዋናው ነው፡፡
መላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝብ በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቆ በሚማቅቅበት በዚያ የሰቆቃ ዘመን መላውን የሰው ልጆች ያስደመመ፣ በደስታ ያስፈነጠዘ ድል ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከኢትዮጵያ ተሰማ፡፡ ነጻነታቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውን፣ ሃይማኖታቸውንና ክብራቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች በአፍሪካ ምድር አዲስ ታሪክ አስመዘገቡ፡፡
ዓድዋ ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ፣ ሰብአዊ ክብርንና ልእልናን የተጎናጸፉ፣ ለሰው ልጆች ፍቅርንና አክብሮትን የሚሰጡ ሕዝቦች ሁሉ የተቀዳጁት ታላቅ ድል እንጂ የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ አይደለም፡፡ የዓድዋ ድል የነጻነት ድል ብቻ ሳይሆን ፍቅርና ይቅርታ የታዩበትም ዓውደ ግንባርም ነው፡፡ ዓድዋ በአውሮጳውያኑ ዘንድ ያልሰለጠነና አረመኔ ሕዝብ ነው ተብለው የተገመቱት ኢትዮጵያውያን በምርኮኛ አያያዛቸው ለሰው ልጆች ያላቸውን ሰብአዊነትና አክብሮት ያሳዩበት ታሪክ ነው፡፡
አድዋ አውሮፓውያን ከአፍሪካ ምድር እነርሱን ሊቋቋም የሚችልና በሃይል የማይገዛ ጀግና ሕዝብ እንዳለ ያስገነዘበ ሕያው ታሪክ ቢሆንም እኛ የታሪኩ ባለቤቶች የራሳችንን ታላቅ ታሪክ አክብረንና ጠብቀን ሳናስተዋውቀው ባዕዳን ታሪካችንን ‹‹የአፍሪካን ታሪክ ማወቅ ከፈለግን የዓድዋ ድል እውቀቱ ሊኖረን ይገባል››፣ ‹‹አቢሲኒያውያን ኢጣሊያውያንን አሸነፉ፣የዓድዋ ጦርነት የአፍሪካ ታሪክ አካል በመሆኑ የዓድዋ ድል ያልተካተተበት የአህጉሪቱ ታሪክ ሙሉ ታሪክ አይሆንም»፣‹‹አፍሪካን ያስገረመ ታላቅ ድል›› በማለት አድናቆታቸውን መግለፃቸው ይሁን ቢያሰኝም፤እኛ ራሳችን ታሪካችንን የማስተዋወቅ ስራን እንዴት እያከናወንን ይሆን? በተለይም በየአገራቱ ኢትዮጵያን ወክለው በዲፕሎማትነት የተቀመጡት ሁሉ የአገራችንንና የሕዝቡን ታሪክ የሚያጎላ፣ ቱሪዝምን የሚያስፋፋ፣ በአጠቃላይ ገፅታችንን የሚገነባ በቂ ስራን እያከናወንን ለመሆናችን ምን ማረጋገጫ ይኖረን ይሆን?
የድሉን ዓለም አቀፋዊነት ድምቀት በተለይ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አምባሳደሮቻችን እንደ አንድ ስራ አድርገው ሊሰሩበት ይገባል፡፡ ዩኒቨርቲዎቻችንም ጥናትና ምርምር በማካሄድ የአድዋ ድል በአህጉር እና በዓለም ደረጃ ይበልጥ እንዲታወቅ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2011