ሰዓቱ ወደዕኩለ ሌሊት እየተጠጋ ነው። ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ብዙ ዓይኖች በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ናቸው።በድንገት “ሰበር ዜና” የሚል አርዕስት የያዙ አጫጭር የጽሁፍ መልዕክቶች ማሕበራዊ ሚዲያውን አጥለቀለቁት።የመልዕክቱ መነሻ ደግሞ የሀገሪቱ መሪ ናቸው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚያ ሌሊት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በሕወሓት ስለተፈፀመው አስነዋሪ ተግባርና እሱን ተከትሎ ለሠራዊቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ይፋ አደረጉ::
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሙሉ መልዕክት፡-
ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን እዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው። በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሓት ግን እንደባዕድና እንደወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል።
መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፤ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል። ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም። የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ።”
የጥፋት ድግስ
ጥቅምት 24 2013 ሌሊት፣
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ
አባላት እንደመሰንበቻቸው ሁሉ የትግራይ ህዝብ የገጠመውን ችግር ለማስወገድ ሲለፉ ውለዋል።የአንበጣ ወረርሽኝ የገበሬው ወቅታዊ ስጋት ነው። እህሉም ደርሷል።በዚህ ወቅት የሠራዊቱ ትኩረት ከገበሬው ጋር ነው። ውሎውን አንበጣ ሲያባርር የደረሰ እህል ሲሰበስብ ይውላል።
በዚሁ ቀንም የሠራዊቱ ውሎ ተመሳሳይ ነበር። ማሳ ውስጥ ከገበሬው ጋር፤ በሌላ በኩል፤ የጥፋት ድግሱን ሲያሰናዱ የቆዩት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ሠራዊቱን ከኋላ ለመውጋት ስምሪት ሰጥተዋል። መሸ፤ ሠራዊቱ ወደካምፑ ተመልሶ የዛለ ሰውነቱን፤ የደከመ ጉልበቱን አሳረፈ።“ሀገሬ” በሚለው መሬቱ፤ “መመኪያዬ” ባለው ግዛቱ ውስጥ ነውና በእምነት ወደመኝታው አቀና።ያ ምሽትና የጥፋት ድግሱ እንዲህ ነበር። ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ ህዳር 02 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሁኔታውን ሲያብራሩ፣
ማታ አራት ሰዓት ላይ ሊያደርጉት የፈለጉትን ኦፕሬሽን ቀደም ሲል በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩትን ትግሪኛ ተናጋሪ አባላት ከሠራዊቱ እንዳይወጡ፣ በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት
አባላትም ከዚህ ቡድን ጋር ተናብበው እንዲሠሩ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል።አንደኛው ተልእኮ፤ በሠራዊቱ ውስጥ በመሆን ሠራዊቱን ማፍረስ ነው። ሁለተኛው ከሠራዊቱ ወጥቶ ሠራዊቱን መውጋት ነው። ሦስተኛው ሠራዊቱ እጅ እንዲሰጥ የሃይማኖት አባቶችንና ሽማግሌዎችን እያመጡ የሽምግልና ሥራ መሥራት ነው።
በውስጥ የራሳቸውን ሰዎች እያደራጁ መደበኛውን የሠራዊቱን የመገናኛ ሬዲዮ የዕዝ ሰንሰለት እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ወደራሳቸው አዞሩት። በዚህ ወቅት የመከላከያ መገናኛ ዋና መምሪያ ኃላፊው የራሳቸው ሰው ነው።የሰሜን ዕዝ በነበረባቸው አካባቢዎች ሁሉ የመከላከያ የሬዲዮ መገናኛ መስመር እነሱ በሚያውቁት ፕሮግራም ተለወጠ።እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሁልጊዜም ይደረጋል። የመገናኛ ሬዲዮ ፕሮግራም ለውጥ ሲደረግ የሚያጠራጥር ነገር የለውም።እኔም ወታደር ነኝ።በውትድርና እርስ በእርስ መጠራጠር የለም።በግልጽ ነው የምትሠራው፤ በምትሠራው ሥራ ላይ ኃላፊነት ተሰጥቶሃል።
ልታጠፋ ትችላለህ፤ ነገር ግን ስታጠፋ ትጠየቅበታለህ።ስለዚህ የሬዲዮ ፕሮግራም ሲደረግ ጥርጣሬ አልነበረም። እነሱን ጥርጣሬ ውስጥ ሊከትት የሚችል ነገር አልነበረም።በራሳቸው ያደራጁት ኃይል በዚህ ሬዲዮ መገናኛ ሲገናኝ ድምጹ አይሰማም።ኦፕሬሽኑን እስከሚጀምሩ ድረስ ክፍት አላደረጉትም።ኦፕሬሽኑ ሲጀመር ብሎክ ለማድረግ ነው።ኦፕሬሽኑ መቼ ነው የሚጀመረው? “የሠራዊቱ ራሽን ሲገባ“ብለው ተዘጋጅተዋል።ያለፈው ሳምንት፣ ማክሰኞ ነው ዕለቱ[ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ማለት ነው]፤ ስለዚህ የሠራዊቱ ራሽን እና ደሞዝ እንደገባ ኦፕሬሽኑ ተጀመረ።
የሰሜን ዕዝ ሀገሪቱ ካሏት እዞች መካከል ጠንካራው እና በሜካናይዝድ ክፍለጦሮች ጭምር የተደራጀ ነው።ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ከ20 ዓመት በላይ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በምሽግ ውስጥ የኖረ፤ ከራስ በላይ ለሀገር ክብር ዋጋ የከፈለ፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጠንካራ ማህበራዊ ውህደት የፈጠረ የህዝቡ አንድ አካል ነው ማለት ይቻላል።ለዚህም ህዝቡ ሲጠማ የውኃ ጉድጓድ ሲቆፍር፤ ጤናው ሲጓድል ሃኪም ቤት ሲያሰራ፤ ልጆቹ እንዲማሩ ትምህርት ቤት ሲገነባ ኖሯል።በመጨረሻም ሰብሉን አንበጣ ሲወርረው መሳሪያውን አስቀምጦ ውሎአዳሩን በገበሬው ማሳ ውስጥ አድርጓል።
ይህ ሠራዊት አብረውት በኖሩ ጓዶቹ “ከጀርባዬ እወጋለሁ” ብሎ እንዴት ይጠብቃል? ሌ/ጀነራል ባጫ ቀጥለዋል፣
ማታ አራት ሰዓት ኦፕሬሽኑ ተጀመረ።ቀን የሠራዊቱ ኃላፊዎች ድግስ ተደግሶ ሁሌ እንደሚደረገው አብረው በልተው ጠጥተው ሌሎቹ አባላት ሲሄዱ የሚፈልጉትን እዚያው አፈኑ።የሃያኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ጄነራል ኑሩም ታፍኗል፣ የአሥራ አንደኛ ክፍለ ጦርም፤ ከአራተኛ ሜካናዝድ ክፍለ ጦርም እንደዚሁ፤ በዕለቱ የቀድሞው የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ ወደ ድግሱ ስላልሄደ አልታፈነም።
ሬሽኑ ተወሰደ፤ የሬዲዮ ግንኙነት ተቋረጠ፤ የብርጌድ አዛዥ ሻለቃውን ማግኘት አይችሉም፤ የክፍለ ጦር አዛዥ ብርጌዱን ማግኘት አይችሉም፤ መከላከያ ክፍለ ጦሩን ማግኘት አይቻልም።ሙሉ በሙሉ ነው የተቆረጠው፤ ይሄ በመከላከያ ውስጥ የተሠራ ሴራ ነው።እነሱ ተመሳሳይ ሬዲዮ ተሰጥቷቸው በተመሳሳይ ሬዲዮ ሌላ ፕሮግራም ተደርጎላቸው ጃም ማድረግ የሚችሉበት ተፈጥሯል።
ይሄ የእነሱ ሰው ከሀዲው ሄዶ ነው [የመገናኛ መምሪያው ዋና ኃላፊ] ፕሮግራሙን በዚህ መንገድ ያስተካከለላቸው እንጂ ማንም የውጪ ኃይል ገብቶ ጃም ማድረግ አይችልም።በመከላከያ ይሄን ማድረግ ማለት የሠራዊት የዕዝ ሰንሰለቱን ጣስክ ማለት ሙሉ በሙሉ ሠራዊቱ ተዋሕዶ እንዳይሰራ አደረግህ ማለት ነው።
የሠራዊት ዋናው ምሰሶ ደግሞ ተዋሕዶ መሥራት ነው። መቶም ይሁን መቶ ሺህ በአንድ ቃል፣ ሁሉም አንድ ዓይነት ነገር ማድረግ ይችላል።ሠራዊቱን ልዩ የሚያደርገው ይሄ ነው። በአንድ ቃል፤ ሁሉም በአንዴ አንድ ዓይነት ነገር ያደርጋል።ቦታቸው የትም ይሁን የት የታዘዘውን ነገር ብቻ መስማት ነው።ስለዚህ ተዋሕዶ መሥራት የሚባለው ነገር በእዝ ሰንሰለቱ የሚተላለፍ ነውና፣ [በወቅቱ] የእዝ ሰንሰለቱ ነው የተበጠሰው፤ ከዚያ በኋላ ራሽኑም ተወሰደ፤ ብሩም ተወሰደ።ራሽኑን አግበስብሰው ላሰለጠኗቸው ሚሊሻዎችና ልዩ ኃይል ለሚሏቸው ሰጡ።ብሩን ለራሳቸው ወሰዱ።
በሌላ በኩል፤ ይሄ ግንኙነት የሌላቸውን ሻለቆች ባሉበት ለየብቻ ሄደው ከበቧቸው።ከብበው ሲያበቁ “እጃችሁን ስጡ፤ ጠመንጃችሁን አስረክቡ እና ወደፈለጋችሁበት ትሄዳላችሁ።እኛ ጠመንጃ እንጂ እናንተን አንፈልግም።የእኛ መንግሥት ‘የተመረጠ’ መንግሥት ነው፤ የአዲስ አበባ መንግሥት የተመረጠ ስላልሆነ ፈርሷል።ስለዚህ እጃችሁን ስጡ” የሚል ቅስቀሳና ማስፈራሪያ ሰነዘሩ።
ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ፤ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ መዘርዘራቸውን ቀጥለዋል።የጥፋት ቡድኑ በሠራዊቱ ላይ የፈፀመውን ግፍ በምን ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንዳስፈፀመው አስረጂ በመጥቀስ የዕለቱን የግፍ ተግባር እንዲህ ይገልፁታል፡-
እጅ መስጠቱ አልቻል ሲል የጁንታው አባላት ቀድመው ያፈኑትን ጄነራል ኑሩ የሚባል የሃያኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ወደመገናኛ ሬዲዮ አምጥተው ሬዲዮ ከፍተው ትእዛዝ እንዲሰጥ አደረጉት።ጄነራል ኑሩ “ጦርነት ይቅርብን፤ ደም መፋሰስ የለበትም፤ እኔም ትጥቄን ሰጥቻለሁ፤ እናንተም ትጥቃችሁን ስጡ፤ እኔን ካሁን በኋላ አታገኙኝም” አስባሉት።በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ “አንተ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፤ አንተ ትጥቅህን ስጥ እኛ ግን ትጥቅ አንሰጥም” አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ “ትጥቁን ከሰጠ ታዲያ ከዚህ በኋላ እኔን አታገኙኝም ያለው ለምንድነው? ለምንድነው የማናገኘው? ይገድሉታል ማለት ነው፤ ስለዚህ ሞት የእኛም እጣ ፈንታ ስለሆነ ጠመንጃችንን ሰጥተን አንሞትም” አሉ።
ሌሎቹ “አንተ ብትሰጥም እኔ ሀገር ጠብቅበት የተባልኩትን ትጥቅ ለማንም ግብስብስ ሚሊሻ አልሰጥም” በሚል ሁሉም አንድ ሆነው ተዋጉ። በዚህ ቅስቀሳ መሣሪያ ሰጥቶ ወደፈለገበት ቦታ ለመሄድ ዝግጁ የሆነ ሰው የለም።በሁሉም የ20ኛ፣ የ11ኛ፣ የ4ኛ ሜካናዝድ፣ የ7ኛ ሜካናዝድ፣ የ8ኛ ሜካናይዝድ እና የ31ኛ ክፍለ ጦር አባላት በሙሉ ያደረጉት ይሄንን ነው።
ጄነራል ኑሩን እንደዚያ ወደሬዲዮ ያመጡበት ምክንያት “ሰሜን ዕዝ ከእኛ ጋር ተባብሯል” የሚለውን ለማረጋገጥ ነበር።የሰሜን ዕዝ አዛዥን ግብዣ ጋብዘህ ከአንተ ጋር 21 ዓመታት የኖረ፣ አብረህ ስትሠራ፤ አብረህ ጠላት ነው ያልከውን ስትዋጋ የነበረ፣ አጉርሶህ ሲያበቃ፤ ስትወጣ ካቴና እጅህ ላይ የሚያስገባ ፍጡር እሱን እዚህ ጠመንጃ አስቀምጠውለት በመናገሩ ‘ከእኛጋር ተባብሯል’ የሚል ነገር አመጡ።
የሰሜን ዕዝ እንኳንስ ከጁንታው ጋር ሊተባበር ይቅርና ለሀገሩ ክብር፣ ለመለዮው ፍቅር በከባድ መስዋዕትነት እና ጽናት እየተዋጋ በብርታት እንዳገኙት በመግለጫቸው አንስተዋል።ሌተናል ጀነራል ባጫ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ክህደት፣ የደረሰበት ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት ግፍ፣ ግፉን የተቋቋመበት እና ራሱን ለማደራጀት የሞከረበትን ሁኔታ ሲገልጹ በከፍተኛ እልህ፣ ቁጭትና ወኔ ውስጥ ሆነው ነው።የሳቸው እና የሌሎች የጦር መኮንኖች ተልእኮ ምን እንደነበር በማብራራት ገለጻቸውን ቀጥለዋል፣
አንዱም የእኛ ተልእኮ ሠራዊቱን አደራጅቶ፤ የእዝ ሰንሰለቱን አስተካክሎ ወደ ውጊያው ማስገባት ነበር።በጁንታው በኩል በውጊያው የተሳተፉት አንደኛ፤ ልዩ ኃይል ብለው በተለያየ ምክንያትና ጊዜ ያሰባሰቧቸው ናቸው። ሁለተኛው፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የትግራይ ሚሊሻ ተብለው የተሰበሰቡ፤ ሦስተኛው፤ ከሀገሩ ጋር ቃልኪዳን የገባበትን ከእኛ ጋር ዩኒፎርም እና መለዮ ለብሰው የነበሩ፤ትግሪኛ የሚናገሩ፣ የገቡትን ቃልኪዳን አፍርሰው ሠራዊቱን ክደው ከሚሊሻውና ከልዩ ኃይሉ ጋር ሆነው መልሰው ሠራዊቱን ወጉት።በሁሉም ቦታዎች ይሄ ኃይል [በሠራዊቱ ውስጥ ተልእኮ የወሰደው] ተሳትፏል።አራተኛውና አስደናቂው ኦሮምኛ የሚናገሩ የኦነግ ሠራዊት አባላት ከእነሱ ጋር ሆነው መዋጋታቸው ነው።እነዚህ አራቱ ናቸው በጋራ ሆነው ይሄንን ሠራዊት ሲወጉ የነበሩት፤
ሠራዊት ምንጊዜም በመለዮው ያመነ፤ ለሀገሩ የገባውን ቃልኪዳን የሚጠብቅ፤ አንድ ሻምበልም ይሁን፣ አንድ ቲምም ይሁን ከዚያ በላይ የሚሰጠውን የሚያውቀውን ትእዛዝ ከላይ እስኪመጣለት ለጠላት እጁን አይሰጥም።ብዙዎቹ ቦታቸውን ያልለቀቁበትና በአንዳንድ ተባራሪ ወሬ “ቦታውን ልቀቁና ተሰባስባችሁ ልትደራጁ ወደምትችሉበት ነጻ ቀጣና ውጡ” ሲባሉ፤ “አንወጣም” ያሉት ወታደር ይሄንን ጠብቅ ብለህ ካስቀመጥክብት ሥፍራ ዝም ብሎ በመልዕክተኛ ስለማይነሳ ነው። መለዮው ነው እንደዚያ ያደረገው፤ ጀግና ሠራዊት ተፈጥሯል።ጀግንነቱን ሊያኮላሹ የፈለጉት እነዚያ መቀሌ የከተሙ ማፊያ ቡድኖች ናቸው።ጀግንነቱን ለመስለብ የፈለጉትም እነሱ ናቸው።
አንድ ሠራዊት፣ ከእዚያው ከውስጥ የራስህ ጓደኛ ሲመታህ መጀመሪያ ትረበሻለህ። ምን ተፈጠረ ብለህ ውሳኔ ላይ ሳትደርስ ነው በሌላ የምትገደለው፤ [በሰሜን እዝ] ያ አልተፈጠረም፤ የሠራዊት አባላት የነበረውን ሁኔታ ያነብቡ ነበር።እዚያው ያሉ የማፊያው ቡችሎች አፋቸው ስለማያርፍ ምን ማድረግ እንደፈለጉ ይናገሩ ነበር። ያ ለኢትዮጵያ ሠራዊት! ለሰሜን ዕዝ ምልክት ሰጥቶታል።
ለምሳሌ፣ አንዱ ሻለቃ የራሱ ክፍል ደሞዝ እንደመጣ አውቆ “ለሠራዊቱ እንድናከፋፍል ደሞዙን ቶሎ ላክልን ይለዋል።” የተጠየቀው ሰው “ዛሬም ደሞዝ ታስባለህ እንዴ?” ይለዋል።“ለምን አላስብም?” ይላል፤ “መማረክንም አስብ” ብሎ ይመልስለታል።ይሄ ግጭቱ ከመነሣቱ በፊት ነው።ይሄ “መማረክንም አስብ” የሚለው ሰውዬ ከዚያ በፊት የሁሉንም አመራሮች ዘር እየቆጠረ ይጽፍ ነበር።
ይሄንኑ ደሞዝ የሚጠይቀውን ሻለቃም “አንተ የትኛው ብሔር ነህ?” ብሎ ይጠይቀዋል፤ “የእኔ ብሔር ምን ያደርግልሃል፤ እኔ ወታደር ነኝ፤ ከሁሉም ብሔር ድብልቅልቅ ያልኩ ልሆንም እችላለሁ። ለምን ትጠይቀኛለህ?” ይለዋል።በዚህ ጊዜ ጠያቂው “አባት የሌለው እኮ አህያ ነው” ይለዋል።
በእዙ ውስጥ፣ አፍኖ ለመውሰድ እንዲመቻቸው “ማን ምንድነው?” የሚለውን [አስቀድመው] ለይተዋል።“ማን ጠንካራ ነው? ማን ለስላሳ ነው?” የሚለውንም ለይተዋል።“ማን ምን ይዟል” የሚለውም ተለይቷል።እንዲህ ዓይነት ሴራ ለሰው አይገለፅም። ያም ሆኖ ግን ምልክት ሰጥቷቸዋል።
ሬሳችንን ጅብ አስበሉት
የሀገርን እምነት በመናድ፤ የህዝብን አደራ በመካድ በሠራዊቱ ውስጥ በተሰገሰጉ ቅጥረኞች የታገዘው የህወሓት ልዩ ሀይልና ሚሊሻ በሠራዊቱ ላይ ተኩስ ከፈተ።ቀድሞ ተዘጋጅቶ ነበርና በአንድ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት አደረሰ።የሠራዊቱን አባላት ያለርህራሄ መግደል ጀመረ።በእዚያ ስፍራ እጅግ ዘግናኝ ወንጀል ተፈፀመ።
ከጥቅምት 24፣ 2013 ምሽት አንስቶ በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመውን የሕወሓት ጁንታ የጭካኔ ተግባር በተመለከተ ሌ/ጄነራል ባጫ እንዲህ ይላሉ፤-
በምድር ላይ መደረጋቸውን አለመደረጋቸውን እርግጠኛ ባልሆንም የተደረጉ መጥፎ ነገሮችን ልጥቀስላችሁ፤ የ20ኛ ክፍለ ጦር አራተኛ ብርጌድ ድጋፍ ሰጪ ብርጌድ ነው።ያለውም ሴሮ አካባቢ ነው።ይሄ ብርጌድ ሞርታሮች፣ ሮኬቶች፣ የአየር መቃወሚያዎች መድፎች የሚታጠቅ ነው።ክላሽ ለዋርድያ [ጥበቃ] ካልሆነ በስተቀር እያንዳንዱ ወታደር ክላሽ አይታጠቅም።ግፋ ቢል ቢታጠቅ ሽጉጥ ነው።እነርሱን ከበቧቸውና ተታኮሱ፤ እስከመጨረሻው ተዋጉ፤ ተዋደቁ።የእኛ ጥቂት ሰው ነው የተረፈው፤ ጠመንጃ እየቀሙ፣ የቀማው ገድሎ እየሞተ ውጊያው ቀጠለ።
ከጠላት ኃይልም ብዙ ሞቷል።መጥፎው ነገር የእኛን ኃይል የሚወጉት እዚያው ሴሩ አካባቢ አብረው በምሽግ ውስጥ የነበሩ፤ አብረው በሻዕቢያ ውጊያ የነበሩ፤ ምሽግ የሚጠብቁ ሚሊሻዎች ናቸው።የማይታወቁት የኦነግና አዲስ ልዩ ኃይል የሚባሉት ናቸው።ከሌሎቹ ጋር ግን ይተዋወቃሉ።በአካባቢው ያለውም ሕዝብ ያውቃቸዋል።በእነዚህ ብዙ ወታደሮች ተሰው።
እነዚያ የተሠውትን የመከላከያ አባላት ግን ልብሳቸውን አውልቀው ሬሳቸውን ራቁታቸውን ፀሐይ ላይ አሰጡት።ሬሳቸው አልተቀበረም።ሬሳቸው እዚያው ፈንድቶ የአሞራና የጅብ ሲሳይ ነው የሆነው፤ ይሄ አይደልም ሃያ አንድ ዓመት አብሮ በቀበሮ ጉድጓድ አብሮ የኖረ ሰው፤ የሚያውቁት በእጃቸው ያደገ፣ ሁሉ ነገራቸው፤ እርሻ ሲመጣ የሚያርስ፤ ጉልጓሎ ሲመጣ የሚጎለጉል፤ እህል ሲደርስ የሚያጭድ፤ያጨደውን ወቅቶ ጎተራ የሚያስገባ፤ አንበጣ የሚከላከልላቸው፤ ኮቪድ ሲመጣ ኮቪድን የሚከላከል፤ ትምህርት ቤት የሚሠራላቸውን ሠራዊት መግደል ብቻ አይደለም ሬሳችንን ነው ጅብ ያስበሉት!!
ይህ ብቻ አይደለም። ከገደልከኝ በኋላ ልብሴን አውልቀህ ሬሳዬ ላይ እንዴት አድርገህ ነው ከብበህ የምትጨፍረው!? በሠራዊቱ ሬሳ ላይ እያጨበጨቡ ነው የጨፈሩት፤ የእነሱን ወገን ሬሳ አንሥተው፤ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሬሳ ላይ ነው የጨፈሩት፤ ሬሳ አትቅበር፤ ልብስ ማውለቅ ግን ምንድነው!? ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ተዋግተው ሰው ገድለው አያውቁም ማለት ነው።ተዋግቶ የገደለ የተዋጋውን በጀግንነት ይቀብራል።21 ዓመታት በትግራይ ለነበረ የሰሜን እዝ የሰጡት ክብርና ምላሽ ይሄ ነው።
ያ፤ ራቁቱን ያስቀረውና ሬሳ መቅበር ያልቻለ ወራዳ እርሱ ይፈርበት እንጂ ሠራዊቱ የተሰዋው በጀግንነት ነው።እኛ አንኮራበታለን! የትም ቦታ ከተሰዋ በኋላ ከፈለጉ ዘልዝለው ይስቀሉት፤ ወራዳው ግን ጀግናውን ያልቀበረው ነው።ያፈኗቸውን ደግሞ ዩኒፎርማቸውን አውልቀው ራቁታቸውን ነው ወደሻቢያ ሂዱ ያሏቸው፤
በዓይኔ በብርቷ ነው ያየኋቸው።ህሊና ያለው ሰው ራቁቱን ለሚሄድ ሰው የራሱን ልብስ አውልቆ ነው የሚሰጠው፤ ህሊና ያለው ግን አለበሰው። እኛ ጠላታችን ብለን የወጋነው የኤርትራ ሠራዊት ግን ራቁታቸውን የተሸኙትን የሠራዊት አባላት ልብሳቸውን አውልቀው አለበሷቸው።ወዳጃችን ነው ብለን የተዋጋንለት፤ ሕይወታችንን የሰጠንለት ወገን የነበረ፤ ልብሱን አውልቆ አባረረው።ስለዚህ በቁማችንም፤ ሞተንም ከባንዳ ያለን ክብር ይሄ ነው።ከእንደነዚህ ዓይነት ማፊያዎች ክብራችን ይሄ ነው።
ሰብስቤ ሳነጋግራቸው አንድ ሻለቃ ያለውን ልንገራችሁ።“እነዚህ ሰዎች የወጉን ወገኖቻችን ናቸው።አብረን ነው የኖርነው ብለን እንደሰው ነበር የምናያቸው፤ ነገር ግን የሰው መልክ ያላቸው፣ ከገሃነም ያመለጡ ሰይጣኖች ስለሆኑ በምድር ላይ ሰው መስለው መኖር የለባቸውም።ሰው መስለው እንዲኖሩም ልንፈቅድላቸው አይገባም።ወደገሃነም ልንመልሳቸው ይገባል” ነው ያለኝ።በሄድኩባቸው ቦታዎች ያየሁት ይሄንን ነው።
የሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ጋዜጣዊ መግለጫ
ህዳር 02፣ 2013 ዓ.ም.አዲስ አበባ
ሰሚ ያጣው የኢትዮጵያ እናቶች ልቅሶ
የሕወሓት አመራሮች መቀሌ መክተማቸውን ተከትሎ በሕወሓት አመራሮችና በማዕከላዊ መንግስቱ መካከል የነበረው መካረር የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሀይማኖት አባቶችን፣ እናቶችን እና ሴቶችን እጅጉን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።ታዋቂውን አትሌትና ባለሃብት ኃይሌ ገብረስላሴና ሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦች የተካተቱበት የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ሰኔ 08 ቀን 2012 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ተገኝቶ ስለሰላም ልመና አቅርቧል። የሰላም ዘንባባ የያዙ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ እናቶች የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በተገኙበት፣ ጦርነት ለማንም አይበጅም ብለው ወልዶ ባጠባ ጡታቸው
በመማጸን ህዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ልመና አቅርበዋል።ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ያ የሀገር ሽማግሌዎች ልመና፣ ያ እናቶች ልቅሶ ከንቱ መሆኑን ሁሉም አወቀ።የሀገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን ዋነኛ ትኩረት አደረጉት።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጣ
ሕወሓት በሠራዊቱ ላይ የፈጸመውን ጥቃት መነሻ በማድረግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ ሆነ።
ምክር ቤቱ በዕለቱ ባካሄደው ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ መንግሥት አዋጁን ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት፤ የሀገርን ሰላምና ሕልውና፤ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥና ሀገሪቷን ወደሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶች የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ እንደሆነ አስታወቋል።
ምክር ቤቱ በዚህ መግለጫው፤ በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን፤ እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ ጉዳዮች መከሰታቸውን፤ እነዚህም ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ መሆናቸውን አትቷል።
አያይዞም፤ በክልሉ ውስጥ በሕገወጡ ቡድን አማካይነት የፌዴሬሽንን ምክር ቤት ውሳኔዎች ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤ ይህንንም ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በመሆኑም፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ ርምጃ መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።ይላል በዚሁ ቀን የተሰጠው መግለጫ፤
በዕለቱ የወጣው ዓዋጅ ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው። ዓዋጁን ለማስፈምም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ግብረ ኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን፣ ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ሀይል’’ ተብሎ ይጠራል የሚል መረጃም በመግለጫው ተካትቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ ሲሆን፣ እንዳስፈላጊነቱ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎች ግብረ ኃይሉ በሚያወጣው መመሪያ ይወስናል መባሉ በዕለቱ በመገናኛ ብዙኃን ተነግሮ ነበር።
ወደ ቤታችሁ ተመለሱ! ጄነራሎቹ ተጠሩ
ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቀንሰው የነበሩ ሦስት ከፍተኛ መኮንኖች ወደመከላከያ ሠራዊቱ እንዲመለሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ ቀረበ።ጥሪ የተደረገላቸው የጦር መኮንኖች ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፣ ሌተናል ጄነራል ዮሐንስ ገ/መስቀል እና ሌተናል ጄነራል አበባው ታደሠ ናቸው።
ከመቀሌ እስከአሶሳ ሊፈጸም የነበረ ጥቃት ከሸፈ
ከሕወሓት ጋር ድብቅ ግንኙነት በመፍጠር በአሶሳ ከተማ ጥፋት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንደሆኑ የተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች በዚሁ ዕለት (ጥቅምት 25/2013) በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱላዚዝ መሐመድ አስታውቀዋል።
ግለሰቦቹ በአሶሳ ከተማ ኢንቨስትመንትን ሽፋን በማድረግ ጥፋት ለመፈጸም ከሕወሓት ድብቅ ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው። በክልሉ በመተከል ዞን የተፈጸመውን ጥቃት ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ ግለሰቦቹ ይህንን ጥፋት ዳግም ማስቀጠል ዋነኛ ግባቸው እንደነበር ጠቁመዋል።የተያዙት ግለሰቦች “ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ መንግሥት የለም” በሚል ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ከሚሠራው የጥፋት ኃይል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የፖሊስ ኮሚሽነሩ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።እነዚህ ግለሰቦች የአካባቢውን ወጣቶች በድብቅ በመመልመል ተጨማሪ ግጭት ለማስከተል ገንዘብ እና ሌሎች ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ነበር፤ ብሎ ፖሊስ በሰጠው መረጃ አሳውቋል በማለት ኢዜአ በዕለቱ ዘግቦታል።
የጋምቤላው ድግስ፤ በሕወሓትና በኦነግ ሸኔ
በዚሁ ዕለት በወጣ ተመሳሳይ መረጃ፤ “የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው በተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ብሔረሰቦችን ለማጋጨት አሲረው ሲንቀሳቀሱ ነበር” በሚል የተጠረጠሩ የህወሓትና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገልጿል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከሕወሓት የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው በጋምቤላ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችን ለማጋጨት አሲረው
ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል የተጠረጠሩት እና በቁጥጥር ስር የዋሉት ጸጋዬ መብርሃቱ (ካህሳይ)፣ ገብረ ማሪያም አናንያ፣ ዋስትና ተሾመ (ጃል ሴና)፣ አብርሃም መሃሪ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ (ባሌስትራ) እና ሌሎች 19 የሕወሓትና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ኃይሎች እንደሆኑ አሳውቋል።
እነዚህን በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተሰማሩ የጥፋት ኃይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋልና ሴራቸውን ለማክሸፍ በተካሄደው ኦፕሬሽን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ እንዲሁም የየክልሎቹ የጸጥታ አካላት በቅንጅት መሳተፋቸው በዕለቱ የተሰጠው መግለጫ ያመለክታል።
መትረየስ ወደባህር ዳር
በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ ለጥፋት ተልእኮ ማስፈጸሚያነት በድብቅ ሲጓጓዝ የነበረ አምስት የብሬል መትረየስ በአለፋ ወረዳ ፍንጅት በተባለው የጥበቃ ኬላ ፈታሾች ባደረጉት ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ያሳወቀው በዚሁ ዕለት ነው።
በዚሁ ዕለት ማለትም፤ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፖሊስ መምሪያው የኮሚኒኬሽንና ሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ውብነህ አስናቀው በሰጡት መረጃ፤ የጦር መሳሪያው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2- 55523 አዲስ አበባ በሆነ ቶዮታ ፒካፕ መኪና በድብቅ ተጭኖ በአለፋ በኩል ወደባሕር ዳር ሊገባ የነበረ ነው።የጦር መሳሪያዎቹን በድብቅ ጭኖ ሲያጓጉዝ ነበር የተባለ አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል።
የእንደራሴዎች ቁጣ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከህግ ማስከበር ዘመቻው አስቀድሞ በነበረው አንድ ወር በመተከል፣ በወለጋ እና በጉራፈርዳ የተካሄደው ግድያ አስቆጥቷቸዋል።ማንነትን መሰረት አድርጎ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ ሊቆም ይገባል የሚል ጥያቄ አንስተዋል።በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ አስቀድሞ በመተከል የአማራና አገው ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ እንደራሴዎችን አስቆጥቶ ከጉምዝ ታጣቂዎች፣ ከኦነግ ሸኔ እና ከሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ጀርባ ያለው ሕወሓት እንደድርጅት በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባል የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም.
በከረመ ቁጭት ውስጥ የቆየው ምክር ቤት በመከላከያ ሠራዊቱ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በተፈጸመ ሁለተኛ ቀን ላይ ተሰብስቧል።አጀንዳው ደግሞ በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ሁኔታ በመገምገም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፅደቅ፤ አፈፃፀሙን የሚከታተል መርማሪ ቦርድ ለማቋቋም እና የመርማሪ ቦርድ አባላትን ለመሰየም የተጠራ 6ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባዔ ነው።ጉባዔው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ በስድስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል።በዚህም፤
21ኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት የተደነገገው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀስ 2/ሀ መሠረት ነው። በዚሁ ድንጋጌ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራ ላይ ባለ ጊዜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ48 ሰዓት ውስጥ ቀርቦ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ማግኘት አለበት። ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት የተደነገገው ትናንት ሲሆን፤ ዛሬ በ24 ሰዓት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቷል። በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ላይ “አንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲፀድቅ፣ እንዲቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሊያፀድቀው ይገባል” የሚል ደንብ ያስቀምጣል። በዚህ መሠረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አምኖበት ተቀብሎት አጽድቆታል። ስለዚህ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተፈፃሚ ይሆናል። ይሄንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ የሕግ መሠረት የሆነው የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ አንድ ሲሆን፤ ሕገመንግሥታዊ ሥርዐቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰጥቷል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያለው ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ አምኖበታል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ይህ ሁኔታ መደበኛ በሆነው ሕግ የማስከበር ሥርዓት ልንቋቋመውና ልንቆጣጠረው የማንችል መሆኑን ተገንዝቧል። ይሄንን ለመቆጣጠር ከመደበኛው አካሄድ ለየት ያለ ስልትና አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ አምኖበታል። ለዚህም አግባብነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተደንግጓል።
…አዋጁ ለስድስት ወራት የታወጀ ሲሆን፤ በዋነኝነት በትግራይ ክልል ይተገበራል።ነገር ግን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስተገብረው ግብረ ኃይል እንደአስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወሰን ሊያሰፋውም ሊያጠብበውም ይችላል። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ በትግራይ ክልል ውስጥ መፈፀሙ አስፈላጊ አይደለም ብሎ በሚያምንበት ጊዜ በከፊል ተፈፃሚ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። አስፈላጊ መሆኑን በሚያምንበት ጊዜ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈፃሚ እንዲሆን ሊያደርግም ይችላል።
አዋጁን የማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል ነው። የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ናቸው፤ ግብረ ኃይሉ እንደአስፈላጊነቱ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚሰየሙ ከተለያዩ ተቋማት የሚወከሉ አባላት ሊኖሩት ይችላል። የግብረ ኃይሉ ተጠሪነት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ወይም ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል አዋጁን ለማስፈጸም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን የጸጥታ ኃይሎች በሙሉ በአንድ ዕዝ አስተባበብሮ የመምራት ሥልጣን ተሰጥቶታል። እንዲሁም፤ እያንዳንዱ ዜጋና የትኛውም አካል ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ትብብር የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል። ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ግብረ ኃይሉ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች፤ የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች በመቀበል የመፈጸምና የመተባበር ግዴታ በሁሉም ዜጋ ላይ የተጣለ ነው።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማዕቀፍ ውስጥ የሚተገበሩ ርምጃዎች
አዋጁ በመደበኛው አውድ ተፈጻሚ የሆኑ የመብት ድንጋጌዎች ሳይገድቡት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ የተለያዩ ርምጃዎችን የመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቶታል። ትእዛዝ መስጠት፤ መከልከል፤ ማገድ እና መሰል ርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ በመደበኛው አውድ ውስጥ ዜጎች ያሏቸውን መብቶች ከግምት ሳያስገባ፤ በዚያ ሳይገደብ ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስፈላጊ ነው ብሎ ያሰበበትን ርምጃ ለመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቶታል። በዝርዝር የተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች በሚታዩበት ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚፈጸምበት ክልል ውስጥ ፖሊስ ወይንም ማንኛውም የጸጥታ ኃይል ትጥቁን እንዲፈታ ትእዛዝ መስጠት፤ አካባቢውን መቆጣጠርና ህዝቡ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲቀጥል ለማድረግ አስፈላጊውን ርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቶታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስተገብረው ግብረ ኃይል አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነ ጊዜ ማንኛውንም የትራንስፖርት መንገድ ወይም አገልግሎት ወደክልሉ እንዳይገባ ወይንም ከክልሉ እንዳይወጣ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል። ይህንንም በመመሪያ መደንገግ ይችላል። የሰዓት እላፊ ገደብ መወሰን ወይም መደንገግ ይችላል። የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ሊከለክል ይችላል። የተለያዩ የመገኛኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ ማዘዝ ይችላል።
እንዲሁም፤ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል ወደጦርነት የሚገፋፉ፣ የሚቀሰቅሱ፣ የፌደራል መንግስቱ ተልዕኮ እንዳይሳካ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መግለጫዎች መስጠትን ሊከለክል ይችላል። በተጨማሪ፤ አዋጁን ለማስፈጸምና ተልዕኮውን ለማሳካት ሲል ሕገወጥ በሆኑ ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል ብሎ የሚጠረጥራቸውንና የሚያምናቸውን ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋል ይችላል። በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ሰዎች አዋጁ ተፈጻሚ አስኪሆን ድረስ ይዞ ማቆየት ወይም በመደበኛው ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑና ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ይችላል። ከመደበኛው አሠራር ወጣ ባለ መንገድ ቤት፤ ማንኛውንም ቦታ፤ መጓጓዣ መበርበር፤ መፈተሽ ይችላል። በፍተሻ የሚያገኛቸውን ነገሮች ለማስረጃ የማቅረብ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጣርቶ ለግለሰቦቹ የመመለስ መብቱ የተጠበቀ ነው። አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሌሎች መንገዶችንና መሰል መሠረተ ልማቶችን አስመልክቶ ለተልእኮው መሳካት አስፈላጊ ነው ብሎ በሚያምንበት ጊዜ በእነዚህ ላይ አስፈላጊውን ትእዛዝ መስጠት ይችላል። ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ቦታ እንዲቆዩ፤ በተወሰነ አካባቢ እንዲታቀቡ፤ እንዳይገቡ፤ እንዳይወጡ፤ አካባቢውን እንዲለቅቁ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል። በአጠቃላይ ኃላፊነቱን ለመፈጸም አስፈላጊ ነው ብሎ ያሰበውን፤ የሚያምንበትን ትዕዛዝና መመሪያ የማውጣት፤ የመስጠት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በአዋጁ ተመጣጣኝ ሀይልን የመጠቀም ርምጃዎችን ተግባራዊ የማድረግ ስልጣን ተሰጥቶታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአስፈላጊነትና በተመጣጣኝነት መርህ ተግባራዊ ይደረጋል። ይህንንም ለመከታተል፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈጻሚነት የሚከታተል ቦርድ በዛሬው ዕለት ተቋቁሟል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግብረ ኃይል ተልእኮውን ለመወጣት እንዲችል ይህንን ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የጸጥታ ኃይሎች (የመከላከያ ሠራዊትም) ተልእኳቸውን በአግባቡ መወጣት ይችሉ ዘንድ የሚዲያ አካላት፤ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ዜጎች የሚያሰራጩትን መረጃ በኃላፊነት ስሜት በጥንቃቄ፤ ትክክለኛነቱን እያጣሩ በማሰራጨት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ጌዲዮን ጢሞቲሞስ (ዶ/ር)
ጥቅምት 26፣ 2013
አዲስ አበባ
ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም፣
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሌሊት ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት እና ያደረሰውን ጥፋት የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አውግዘውታል።
አራተኛው ጄነራል ተጠሩ
ሜጀር ጄነራል አለም እሸት ደግፌ ወደመከላከያ ሠራዊት እንዲመለሱ ከጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ የተደረገላቸው ጥቅምት 26 ቀን 2013 ነበር።አንድ ቀን ቀደም ብሎም ከመከላከያ ሠራዊት ተቀንሰው የነበሩት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፣ ሌተናል ጄነራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል እና ሌተናል ጄነራል አበባው ታደሠ መጠራታቸው ይታወሳል።
ከጀርባ ሳንጃ ነቅሎ ማጥቃት
“የሰሜን ዕዝ በሕወሓት ጁንታ በክህደት ከጀርባው የተወጋበትን ሳንጃ ነቅሎ በጀግንነት ተዋግቷል”
ሌ/ጄነራል ባጫ ደበሌ
የመከላከያ ሠራዊቱ የሰሜን ዕዝ በሕወሓት የተፈጸመበትን ድንገተኛ ጥቃት እና ክህደት መክቶ ወደፀረማጥቃት ርምጃ መሸጋገሩን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያሳወቀው ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም. ነበር። በዕለቱ “ሠራዊቱ ተኩስ በተከፈተበት ካምፖች ሁሉ በጠንካራ የመከላከል ውጊያ የከሃዲውን ኃይል በጀግንነት መክቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰበት ይገኛል” ሲል የሀገር መከላከያ ሠራዊት አሳውቋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ሃይል ተቀናጅተው በሰሜን ጎንደር ዞን ቀራቅር በተባለ ቦታ እብሪተኛው ቡድን የሰነዘረውን የማጥቃት ውጊያ በብቃት በመመከት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሰውበታል።ሠራዊቱ በወሰደው ቅንጅታዊ የማጥቃት ርምጃ ከቀራቅር በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ከፍተኛ ቦታ ላይ የነበረውን የእብሪተኛውን አጥፊ ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃት ቦታውን በቁጥጥር ሥር አዋለ።የቡድን እና የነብስ ወከፍ መሳሪያዎች መማረካቸውን በእለቱ መከላከያ ይፋ አድርጓል።
ጄነራሉ በቴሌቪዥን መስኮት ተከሰቱ
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በሕወሓት ኃይል ላይ ሠራዊታቸውን ካዘዙ ገና ሁለተኛ ቀን ነው።በሰሜን ያለው ሠራዊት ከማዕከል ጋር የሚገናኝበት ሰንሰለት በሕወሓት ጥቃት ምክንያት ተቋርጧል።ያም ሆኖ ሕግ እንዲያስከብር ትዕዛዝ የተሰጠው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግዳጁን በመወጣት ላይ ይገኛል።
በዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በተለያዩ አቅጣጫዎች ግዳጁን በውጤታማነት እያከናወነ መሆኑን ገልጠዋል።“ሠራዊቱ ለሁለት አሥርት ዓመታት በዘለቀው የሀገሩን ዳር ድንበር የማስጠበቅና የህዝቡን ሰላም የማረጋገጥ ተግባር ላይ እያለ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባልጠበቀው ሁኔታ ከራሱ ወገኖች ለእኩይ ዓላማ በተዘጋጁ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞበታል።ሠራዊቱ ይህን ጥቃት በፍጥነት መክቶ ወደማጥቃት ተሸጋግሯል።” በማለት፤ በሕወሓት ተገድዶ ወደውጊያ የገባው የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻም ወደጎረቤት ሀገር በመሸሽ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።የሕግ ማስከበር ዘመቻውንም ፅንፈኞችን በለየና የሕዝቡን ደህንነት በጠበቀ መልኩ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጄነራሉ አረጋግጠዋል።
የሕወሓት የደም እጆች
የሰው ዘር ዕድገት ታሪክ እንደሚያረጋግጠው የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት እንዲሰፍን፤ ጉልበተኛው ደካማውን እንዳያጠቃ፤ ወስላታው የሌላውን ንብረት እንዳይዘርፍ፤ እንዳይመዘብር፤ መዝጊያ ገልብጥ ከክፉ ዓመሉ እንዲታቀብ እና አጥፊ በጥፋቱ እንዲጠየቅ፣ የሰላም እና የዕድገት ትልም እንዲሰምር፤ በየመስኩ ሥርዓት እንዲኖር፤ ሕግ እንዲደነገግ እና መንግሥት እንዲቋቋም ግድ ሆኗል።
በሰው የሥልጣኔ ጉዞ ውስጥ እያደገ እና እየዳበረ የሄደውን በሕግና በሥርዓት የሚመራ ማህበራዊ መስተጋብር በመጣስ ብዙ ሺህ ዓመታትን ወደኋላ ተመልሰው በ21ኛው ክፍለ ዘመን በእብሪት፣ በኃይልና በጉልበት ብቻ የሚያምኑ፤ ሰውን በመግደል፤ በማስፈራራት፤ በመቀማትና በመዝረፍ የተጠመዱ ሰዎች የሕዝብ ፍቅር፣ የሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት ጉዳያቸው አይደለም። በታወከ ሰላም ባልተረጋጋ ሀገር ውስጥ እኩይ አላማቸውን ለመፈጸም ይጥራሉ። ከሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ዋዜማ ጀምሮ በግልጽ የታየውም ይኸው ነው። ለእኩይ አላማቸው ማስፈፀሚያ አደንዛዥ እፅን፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ይፈጥራሉ። ሃይማኖትን፣ ብሔርን እና መሰል ጉዳዮችን ግጭት ለመፍጠር ይጠቀማሉ።ሕወሓት ይህንን የጥፋት ተግባሩን በተለያዬ ጊዜ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተግብሮታል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014