በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው አገራችን በተያዘው በጀት ዓመት የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ብቻ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ዘይት፣ ስኳርና ስንዴ ከውጭ ለማስገባት ተዘጋጅታለች፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2011 በጀት ዓመት 400 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት፣ ሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ስኳርና ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማስገባት ሁኔታዎች እየተመቻቹ ናቸው፡፡
መንግሥት ለእነዚህ ምርቶች ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ከመመደብ በተጨማሪ ከቀረጥ ነፃ ከመፍቀድ አልፎ በተለያዩ ምክንያቶች በሽያጭ መካከል የሚፈጠሩ የዋጋ ልዩነቶችን በመደጎም ጭምር ምርቶቹን በገፍ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የውጭ ምዛሪን ሳይወድ በግድ እያጣ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ምርቶች ውስጥ ግን ስንዴን በአገር ውስጥ በማምረት ፍላጎትን ከማሟላት አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ቢታወቅም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ያለመሆኑን በዘርፉ ከአስር ዓመታት በላይ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡
በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ አገራት ከፍተኛ የስንዴ ምርት የሚመረትባት አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባዎራዎች አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በማልማት በአመት ከአራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያልበለጠ ስንዴ ያመርታሉ፡፡
ተመራማሪዎቹ እንዳስገነዘቡት ስንዴን በመስኖ ለማምረት ከስድስት ዓመት በፊት አዋጭነቱ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ከሦስት ሺ 500 በላይ ሄክታር መሬት ላይ በሚያረካ መልኩ እየለማ ይገኛል::
አገሪቱ 75 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎቷን በአገር ውስጥ ብትሸፍንም ቀሪውን 25 በመቶ ግን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመግዛት ተገድዳለች፡፡ ከዚህ ሀቅ ጎን ለጎን ግን በአገሪቱ ባሉ 12 የሚደርሱ ተፋሰሶች ዙሪያ በመስኖ ሊለማ የሚችል አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ጦሙን እያደረ ነው፡፡ ከአራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 500ሺ ሄክታር ብቻ ብናለማ አሁን ባለው አማካይ የምርት መጠን (40 ኩንታል በሄክታር) ሲሰላ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በዓመት ማምረት ይቻላል፡፡
ይህ ምርት አገሪቱ በዓመት ወደ አገር ውስጥ የምታስገባውን 14 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ፍላጎት ሸፍኖ ቀሪውን ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ወደ ውጭ በመላክ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያስችላታል፡፡ ይህ በእርግጥ ቁጭት የሚፈጥር ነው:: ምክንያቱም የሚለማ መሬት ተይዞ፣ በዘርፉ እድሜ ጠገብ ምሁራንና ተመራማሪዎች ‹‹ዝግጁ ነን›› የሚለው የቁጭት ስሜታቸው ከውጭ የምናስገባውን ስንዴ ማስቀረት ካላስቻለ ፋይዳ ቢስ ያደርጋል፤ ድካማቸውም ከንቱ ይሆናል፡፡
በሰፊው ለማልማት ግን ዘርፉ ሊያሟላ የሚገባው ግብዓቶች በትኩረት ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ የስንዴን ምርት በስፋት ለማምረት እርሻውን ሜካናይዝድ ማድረግ፣ በመስኖ ስራው የውሃ ስርጭቱ የተስተካከለ እንዲሆን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና የምርት ሂደቱን ከጅምሩ እስከ ምርት ስብሰባው ድረስ ያለውን ሂደት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መቃኘት ወሳኝ ነው፡፡
ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ‹‹ምቹ ሁኔታ እየፈጠርኩ ነው›› የሚለው ንግድ ሚኒስቴር ስትራቴጂም አዘጋጅቻለሁ ሲል ተናግሯል:: እርሱ ይህንን ይበል እንጂ በዚህ ረገድ ምንም አይነት ስራ ሲከናወን አይታይም፤ የጀመረው ጉዞም የለም፡፡ እናም ስንዴን ከውጭ የማስገባቱን ስራ ማስቆም ጊዜው ሩቅ ቢመስለንም መንገዱን ዛሬ ካልጀመርነው መዳረሻችን ሩቅ ሆኖ ይታየናል፡፡
ስለዚህ ንግድ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ ባለሙያ እና እድሜ ጠገብ ተመራማሪዎችን በማቀናጀት ሩቁን መንገድ ዛሬ ሊጀምሩ ይገባል፡፡ ለዚህም ስኬታማነት የግብርና ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲዎቹ ይህን የተቀደሰና ልንኮራበት የሚገባንን ተግባር ያለምንም ክፍተት ሊደግፉት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011