ራሲሞ ከባ ይባላል። የተወለደው በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ወረዳ ነው። ለቤተሰቡ አራተኛና የመጨረሻ ልጅ ሲሆን ሦስት ታላላቅ እህቶች አሉት። አባቱ ገና የዘጠኝ ወር ልጅ እያለ ነው የሞቱት። እንደአባትም እንደእናትም ሆነው ያሳደጉት እናቱ ናቸው።
ራሲሞ ሲወለድም ጀምሮ የጤና ችግር ነበረበት። እግሩ እንደማንኛውም ሕፃን ልጅ ለመዳህ የሚያስችለው አልነበረም። እጁም ተመሳሳይ ጉዳት ያለበት ነው። በዚህ የተነሳ እራሱን ችሎ መንቀሳቀስና መቀመጥ አይችልም። አብዛኛውን የሕፃንነት ጊዜውን በእናቱ ጀርባ ላይ ማሳለፉን ቤተሰቦቹ እንዳወጉት ይናገራል።
እያደገ ሲመጣ ግን እራሱን ችሎ ከወዲህ ወዲያ ማለት እንዲለማመድ ብለው እናቱ ከጀርባቸው ያወርዱታል። እርሱም ሙከራዎችን ማድረግ ይጀምራል፤ ግን አስቸጋሪ ይሆንበታል።
አብሮ አደግ ጓደኞቹ ሲሯሯጡና ሲጫወቱ አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ ከማየት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበ ረውም። እንደጓደኞቹ ከሰፈሩ ራቅ ብሎ በመሄድ የአካባቢውን መልክዓ ምድር መመልከት፣ መጫወትና መሯሯጥ አለመቻሉ ያስከፋው ነበር። እንደ አንድ የገጠር ልጅ ያደገበትን መንደር ዙሪያ ገባውን አያውቀውም፤ ጥጆች አላገደም፤ ማገዶ እንጨት አልሰበረም፤ አቀበትና ቁልቁለት አልወጣም አልወረደም፤ በለመለመው መስክ አልቦረቀም፤ ወንዝ ወርዶ አልዋኘም፤ አልተንቦጫረቀም። የልጅነት ጊዜውን በቤቱ ፤ ግፋ ቢልም በደጃፉ ተወስኖ ለማሳለፍ የተገደደ ብላቴና ነበር።
ከሰፈሩ ልጆች ሁሉ እርሱ ብቻ አካል ጉዳተኛ ሆኖ እንደልቡ መንቀሳቀስ አለመቻሉን እያሰበ ይከፋው ነበር። በተለይም እያደገ ሲመጣ አካል ጉዳተኝነቱን እያብሰለሰለ ይበሳጭ ነበር። ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ የሰፈሩ ልጆች ሁሉ ተለቃቅመው ወደ ትምህርት ሲሄዱ እርሱ ደጃፉ ላይ ቁጭ ብሎ ሲያያቸው ውስጡ ይረበሽ ነበር።
ራሲሞ ራሱን ችሎ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስና ከሰፈሩ ርቆ ሄዶ መመለስ ከቻለ ቤተሰቦቹ ትምህርት ቤት ሊያስገቡት እንደሚችሉ ቃል ይገቡለታል። ከጥገኝነት ተላቆ የወደፊቱን ህይወቱን ለማስተካከል ያለው አማራጭ እራሱን ችሎ መንቀሳቀስ መሆኑን የተረዳው ብላቴና አዘውትሮ መንቀሳቀስ ይጀምራል።
ቀን በቀን ሁለትና ሦስት ኪሎሜትር ከሰፈሩ ራቅ ወዳለ ቦታ በእንብርክኩ ተጉዞ ይመለሳል። እግሩ ብቻ ሳይሆን እጁም ጉዳት ያለበት ብላቴና አንድ ክንድ የምትሆን መመርኮዣ እንጨት አዘጋጅቶ በእርሷ እየታገዘ ከቦታ ቦታ መጓዝን የዕለት ተዕለት ሥራው አደረገው። እንቅስቃሴ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ፍጥነቱንም ከጤናማ ልጆች እኩል ለማስተካከል ይጥር ጀመር።
ራሲሞ እንዲህ ዓይነት ጥረት እንዲያደርግ ያበረታታው ቤተሰቦቹ እራሱን ችሎ ከተንቀሳቀሰ እንደሚስተምሩት ቃል ስለገቡለትና እርሱም የትምህርት ፍልጎት ስላለው ነው።
እንደተባለውም ልክ የስምንት ዓመት ልጅ ሲሆን፤ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን ተለማምዶ በተገባለት ቃል መሰረት ትምህርት ቤት እንዲገባ ይደረጋል። እዚያው መንዲ ወረዳ ከትውልድ መንደሩ ራቅ ብላ በምትገኘው አለልቱ ጎምቢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዝግቦ መማር ይጀምራል።
ራሲሞ ዘወትር ማለዳ ከሰፈሩ ልጆች ቀድሞ እየተነሳ ወደ ትምህርት ቤቱ ይገሰግሳል። ከቤቱ እስከ ትምህርት ቤቱ ያለው ርቀት ቢያንስ አስር ኪሎ ሜትር ይሆናል። ይህን ርቀት እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ይጓዘዋል። ደርሶ መልሱ ሲታሰብ በቀን ሦስት ሰዓት ይጓዛል ማለት ነው።
ራሲሞ ትምህርት በጀመረ በቀናት ውስጥ ረዥም ጉዞ የሚጓዝ መሆኑን ተከትሎ እግሮቹና እጆቹ እየተላላጡ ያመው ጀመር። ይሁንና የመማር ፍላጎቱን ለማሳካት ስለሚጓጓ ህመሙ አልበገረውም። በጣም ፈታኝና አድካሚ ሂደቶችን አልፎ ትምህርቱን አስከ ሰባተኛ ክፍል ይማራል። በኋላ ግን የጉዞው ሁኔታ አንገፍግፎት ትምህርቱን ለማቋረጥ እስከመገደድ ይደርሳል።
ደብተር የሚገዛለት፣ የሚከታተለውና የሚያበ ረታታው መምህሩ ውሳኔው ትክክል አለመሆኑን አስረድቶት ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪን መውሰድ እንዳለበት ይመክረዋል። ባለውለታው የቀለም አባቱ መምህር ጉዲና ጫሊ ይባላል። ሁልጊዜም በራሲሞ ጭንቅላት ውስጥ ልዩ ቦታ አለው። ትምህርቱን እንዳያቋርጥ ብቻ ሳይሆን መመላለሱን ትቶ እዚያው እርሱ አጠገብ ተቀምጦ እንዲማር ዕድል ሰጥቶታል። ራሲሞ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን መምህሩ ቤት ተቀምጦ መማሩ እፎይታ ሰጥቶት እንደነበርም አይረሳውም።
ራሲሞ ከቤቱ ወደ ትምህርት ቤት እየተመላለሰ በሚማርበት ወቅት ዝናብ ሲዘንብ የሚገጥመውን ፈታኝ ሁኔታ ሁሌም እንደማይረሳው ይናገራል። አንዳንድ ጊዜ በዝናብ ክፉኛ ይደበደባል፤ ዝናቡ ሲያባራ ደግሞ ያልታሰበ ጎርፍ ይመጣና መንገዱን ይዘጋበታል፤ አርሱን በሰዎች ዕርዳታ ሲያልፍ ጭቃው አላላውስ ይለዋል። በበጋ ወቅትም ቢሆን ፀሐይና አቧራ ሲያስቸግረው ነበር። ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል እየተመላለሰ ሲማር በጣም የሚሰቃይበትን ያን ወቅት አይረሳውም። አንድ ዓመት ከዚህ ሁሉ መከራ የታደገውንና ትምህርቱን እንዳያቋርጥ የመከረውን መምህሩን ዛሬም ድረስ የሚያመሰግነው ከዚህ ሁሉ ስቃይ የገላገልው ስለሆነ ነው።
ራሲሞ የተማረበት ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ የሚያስተምር ነበር። የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ አልፎ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን ለመቀጠል ሲያስብ በአቅራቢያው ሌላ ትምህርት ቤት አልነበረም። ትንሽም ቢሆን የሚቀርበው በወለጋ ዞን አጎራባች፤ በቤኒሻንጉል ክልል ቢልዲጊሉ ወረዳ የሚገኘው ዳለቲ ትምህርት ቤት ነበር። ትምህርት ቤቱ ከራሲሞ የትውልድ አካባቢ እስከ ሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ነበረው። ያም በመሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ በእንብርክኩ ተመላልሶ ለመማር የማይሞከር ይሆንበታል። መጓጓዣ መጠቀም፤ ካልሆነም ቤት ተከራይቶ መማር ነበረበት። ይህንኑ ችግሩን አስቀድሞ የተረዳው ታዳጊ እራሱን በኢኮኖሚ ለማጠናከር ሲል ክረምት ክረምት እንደማንጎ፣ አቦካዶ፣ ፓፓዬ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን ቢተክልም የምሥራች ፍሬ ለመስጠት ዓመታትን ስለሚፈጁ ለችግሩ ሊደርሱለት አልቻሉም።
ቤተሰቦቹም ሆኑ የአካባቢው ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከሚማር ትምህርቱን ቢያቋርጥ እንደሚሻል ሃሳብ ይሰጡት ነበር። እንደውም አንዳንዶች ወደ መሀል ሀገር ሄዶ ምጽዋት ቢጠይቅ ጥሩ ገቢ ሊኖረው እንደሚችል ይመክሩታል። ልመናን የሚጠየፈውና ተምሮ አንድ ደረጃ ላይ መድረስ ያሰበው አካል ጉዳተኛ ግን በሃሳባቸው ሳይስማማ ይቀራል። ያለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅሞ ትምህርቱን መማር እንደሚፈልግ ግልጽ አቋሙን ያሳውቃቸዋል።
የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን በዳለቲ ከተማ መማር እንዳለበት ይወስናል። ይሁንና ቤት ተከራይቶ ምግብ እያበሰለ መማር አይችልም፤ እንደከዚህ ቀደሙ በእንብርክኩ እየተመላለሰ መማርም አይችልም። ግን አንድ አዲስ ሃሳብ መጥቶለታል። እናቱና እህቶቹ ተጋግዘው አህያ ቢገዙለት እርሱ ላይ ተቀምጦ ቀን በቀን እየተመላለሰ መማር እንደሚችል ያስረዳቸዋል። እነርሱም የመጨረሻ አቋሙን ስለተረዱ ሃሳቡን ሳይነቅፉ በሰባት መቶ ሃምሳ ብር አህያ ገዝተው ይሰጡታል።
በአካባቢው ባህል አህያን ለጭነት እንጂ ለመጓጓዣ መጠቀም የተለመደ አለመሆኑ ለራሲሞ ቁብ አልሰጠውም። ማለዳ አህያው ላይ ተቀምጦ ከሃያ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ በሰዓቱ ትምህርት ገበታው ላይ እየተገኘ ተምሮ ወደ ቤቱ ይመለሳል። አህያ ላይ የሚያወጡትና የሚያወርዱት አብረውት የሚማሩ ጓደኞቹ ናቸው። ለከፋ ነገር የተጋለጠበት አጋጣሚ ባይኖርም በርካታ ጊዜ ከአህያ ላይ ይወድቅ ነበር።
ራሲሞ በዚህ መልክ ተምሮ ነበር የዘጠነኛ እና የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው። ባሳለፋቸው የትምህርት ዓመታት ሰዎች ከሌሎች ተማሪዎች ይልቅ አትኩረው ሲመለከቱትና አንዳንዶቹም ከንፈራቸውን ሲመጡ ሲያይ ይሰማው አንደነበር ያስታውሳል።
የአስራ አንደኛ እና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን የተማረው በአሶሳ ከተማ ነው። ቤት ተከራይቶ በወር አንዴ ወደ ቤተሰቦቹ እየሄደ ቀለብ በማምጣት መማር ይጀምራል። ቀደም ሲል የተከላቸው ፍራፍሬዎች ደርሰው እየተሸጡ የኢኮኖሚ አቅሙን ይደጉም እንደነበር ይናገራል።
ራሲሞ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ካጠናቀቀ በኋላ አዚያው አሶሳ ሬፍት ቫሊ ኮሌጅ ገብቶ በኮምፒተር ሳይንስ ትምህርቱን ይከታተላል። ሦስት ዓመት ከተማረ በኋላ በዲፕሎማ ይመረቃል።
በአሶሳ የትምህርት ቆይታው እስከሚመረቅ ድረስ እናቱ ስንቅ በማቀበል፤ አንዳንዴም ከመቀነታቸው እየፈቱ ያለቻቸውን በመስጠት ትልቅ እገዛ ያደርጉለት እንደነበር ይገልጻል። ተምሮ አንድ ደረጃ ላይ መድረስ ከሚፈለግበት ጉዳይ አንዱ እናቱን መርዳት በማሰብ ነው።
ነገር ግን ይህ ምኞቱ አልተሳካም። እናቱ እርሱ ትምህርቱን እንደጨረሰ በደንገት ታመው ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። ራሲሞ ልቡ በኀዘን ይሰበራል። በአካባቢው የመኖር ፍላጎትም ያጣል። እንደውም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በተማረበት የኮምፒውተር ሳይንስ ሥራ ለመሥራት ያስባል። ስድስት ወር ያህል ቡራዩ ከተማ ዘመድ ጋር ተቀምጦ ሥራ ማፈላለግ ይጀምራል። በሳምንት አንድ ቀን ከቡራዩ ወደ መሃል አዲስ አበባ እየመጣ የሥራ ማስታወቂያዎችን ይከታተላል። አንዳንዴ የትራንስፖርት ገንዘብ እያጣ የሥራ ውድድሮች ሳይመዘገብ እንደሚያመልጡት ይናገራል።
ራሲሞ ሰዎች በቅንነት የሚያደርጉለት ነገር ደስ ቢያሰኘውም ሲደጋገምና ሲበዛ ግን እንደሚያሳቅቀው ይገልጻል። በዚህም ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእንግድነት ለስድስት ወራት ከኖረበት ቤት ወጥቶ ብቻውን መኖር ጀምሯል። አሁን ቤት ተከራይቶ እያኖረው ያለው በአጋጣሚ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተመለከተው አንድ ሰው ነው።
ልመናን ተጠይፎ በትምህርት እራሱን አሸንፎ ለመኖር ያለመው ወጣት ዛሬ ምንም ዓይነት ሥራ የለውም። እንደሌሎች ጤናማ ሰዎች ተሯሩጦ ሥራ የማፈላለግ ዕድልም የለውም። የዕለት ጉርሱንም ሆነ የቤት ኪራይ የሚሸፍኑለት ችግሩን የተረዱ ቅን ሰዎች ናቸው። እርሱ ግን ከመጀመሪያው መማር የፈለገው ከሰዎች ጥገኝነት ለመላቀቅ ነበር። አማራጭ አጥቶ በሰዎች እጅ መውደቁ አላስደሰተውም።
ራሲሞ ሃሳቡን እንዲህ ይገልጸዋል። ‹‹በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የተቀመጡ በርካታ ሥራ አጦች አሉ። እነዚህ ሰዎች ያለሥራ ሲቀመጡ ሳይ ተስፋ እቆርጣለሁ። ምክንያቱም ከእኔ የተሻለ መንቀሳቀስ የሚችሉ ሰዎች ሥራ ሳያገኙ እኔ እንዴት አገኛለሁ እያልኩ ተስፋ እቆርጣለሁ። ነገር ግን መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረት መስጠት አለበት እላለሁ። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞች የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል። ለምነን እንዳንኖር ሊያደርጉን ይገባል። መንግሥት ሠርተን ለመኖር የምናደርገውን መፍጨርጨር ማገዝ አለበት። በተማርነው ዘርፍ ያለውድድር ልንቀጠር ይገባል። ምክንያቱም አኛ በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፈን እዚህ ከደረስን በኋላ ለማህበረሰቡ ሸክም መሆን የለብንም። ጤናማ ሰዎች ብዙ የሥራ አማራጭ ሊኖራቸው ይችላል። እኛ ግን ሥራ የመሥራት ዕድላችን ውስን ነው። ስለዚህ የግል ድርጅቶችም ይሁኑ የመንግሥት ፤ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩልን ይገባል፤ ካለበለዚያም መስፈርቱን የምናሟላ ሲሆን ቅድሚያ ቢሰጡን የሰው እጅ ከማየት ሊታደጉን ይችላሉ›› ይላል ራሲሞ።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፎ እዚህ የደረሰው አካል ጉዳተኛ በሰለጠነበት ሙያ ሠርቶ እንዲኖር ማናኛውም አካል እገዛ እንዲያደርግ አዲስ ዘመን ያሳስባል። ለዛሬ ከሲራሞ ጥንካሬ የተማርነውን ለህይወታችን ስንቅ እናድርግ። ሳምንት ከሌላ ባለታሪክ ጋር እስከምንገናኝ መልካም ሳምንት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014