
በአምቦ ከተማ 16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 12ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል «የባህል ስፖርት
ተሳትፏችን ለሰላምና ለአንድነታችን» በሚል መሪ ቃል በአምቦ ስታዲየም በስፖርታዊ ጨዋነት ታጅቦ በድምቀት መከበሩ ቀጥሏል። በውድድሩም
አማራ፣ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን በማሳተፍ ትናንት አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
በትናንት ውሎው በሁለቱም ጾታዎች የሻህ፣ ቡብ፣ ገበጣና የገና ጨዋታ ተከናውነዋል። በዚህ መሰረት በሻህ ወንዶች ኦሮሚያ ሀረሪን እንዲሁም ድሬ ዳዋ ደቡብን 2ለ0 በመርታት ወደቀጣዩ ዙር አልፏል።
በተመሳሳይ ዕለት የሴቶች ሻህ ተካሂዷል። አዲስ አበባና ኦሮሚያ ተገናኝተው አዲስ አበባ ኦሮሚያን 2ለ1 ረትቷል። በአማራ ክልል ከሀረሪ ባገናኘው ጨዋታ ደግሞ አማራ ሀረሪን 2ለ0 በመርታት ቀጣዩን ዙር በድል ተቀላቅሏል። በውድድሩ እየተካሄዱ ከሚገኙት 13 የስፖርት አይነቶች አንዱ የሆነው የቡብ ጨዋታም ተከናውኗል። በወንዶች ድሬዳዋ ደቡብን 2ለ0፣ አዲስ አበባ ኦሮሚያን 2ለ0 በመርታት ባለድል ሆኗል። ቡብ በሴቶች አማራ አዲስ አበባን እንዲሁም ኦሮሚያ ድሬ ዳዋን 2ለ0 ረትቷል። በገበጣ ባለ 18 ጉድጓድ በሴቶች አዲስ አበባ ደቡብን እንዲሁም ኦሮሚያ ሀረሪን 2ለ0 አሸንፏል።
በወንዶች ገበጣ ባለ 18 ጉድጓድ ኦሮሚያ ሀረሪን እንዲሁም አማራ አዲስ አበባን 2ለ0 አሸንፈዋል፡፡ የውድድሩ ድምቀት በሆነው የገና ጨዋታ በገና የወንዶች ውድድር ደቡብ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተጫውተዋል። ከፍተኛ ፉክክር በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ ደቡብ ከድሬዳዋ አቻ ሲለያዩ አማራ አዲስ አበባን 1ለ0 አሸንፏል፡፡
ሌላው የኮረቤ ውድድር በነጠላ ሴቶች አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ከአንድ እስከሶስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ በወንዶች ነጠላ ውድድር ደቡብ የመጀመሪያውን ደረጃ በመያዝ ኦሮሚያና አማራ 2ኛ እና 3ኛ ሆነዋል፡፡ በድብልቅ ኮረቤ ውድድር አማራ 1ኛ፣ አዲስ አበባ 2ኛ እና ኦሮሚያ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የቀስት ውድድር በሁለቱም ጾታዎች የተካሄደ ሲሆን በነጠላ በሴቶችም በወንዶችም የአንደኛነቱ ስፍራ አማራ በመያዝ አጠናቅቋል። በተመሳሳይ አዲስ አበባ በሁለቱም ጾታዎች ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደቀጣዩ ዙር በቀጥታ አልፏል።
በሌላው የውድድር ሁለትና ሶስት ቀናት ውሎ የድብልቅ ቀስት ውድድር የሚጠቀስ ሲሆን የድብልቅ ቀስት የወንዶች ውድድር አማራ 23 ነጥብ፣ አዲስ አበባ 16 ነጥብ፣ ኦሮሚያ 11 ነጥብ እና ድሬዳዋ 5 ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡ በድብልቅ ቀስት የሴቶች ውድድር አማራ 10 ነጥብ፣ አዲስ አበባ 9 ነጠብ እንዲሁም ደቡብ 4 ነጥብ አስመዝግበዋል።
16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 12ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በስፖርታዊ ጨዋነት በመታጀብ እስከየካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በ13 የባህል ስፖርት አይነቶች ይካሄዳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በዳንኤል ዘነበ