የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ተጀመረ

22ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል “ባሕላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በሆሳዕና ከተማ ተጀምሯል።

ውድድሩና ፌስቲቫሉ ትናንት ሲጀመር በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር እንዳሻው ጣሰው፣ ስፖርት ማኅበረሰብ እንዲቀራረብ ከማድረጉ ባሻገር ሀገራዊ ገጽታን በመገንባት ብቁና ጤናማ ዜጋ መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ማኅፀነ ለምለም ናት የተባለው በምክንያት ነው። ብዝኃ የባሕል ስፖርቶችን የታደለችው የብዝኃነት ሀገር ስለሆነች ነው። በስፖርት ማኅበረሰብ ይቀራረባል፣ ሀገራዊ ገጽታ ይገነባል፣ ብቁና ጤናማ ዜጋ ይፈጠራል። ስለዚህ በየአካባቢያችሁ ስለሀገራችን ኢትዮጵያ ተመካከሩ፣ ስለአንድነትና አብሮነት ተወያዩ። በእርግጥም ሀገራችን ማኅፀነ ለምለም ስለሆነች የሁሉም ችግሮቿ መፍቻ እና የአንድነቷ ማጠናከሪያ አላት” ሲሉም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልፀዋል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ ሙሐመድ በበኩላቸው፣ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ዓላማ ኅብረተሰባችንን በባሕል ስፖርቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግና ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባት መሆኑን ተናግረዋል። የባሕል ስፖርቶች ከባሕል ጨዋታነታቸው ባሻገር ለዘመናዊ ስፖርቶች መነሻ ስለሆኑና ለሀገር ያላቸው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ተገቢው ጥናትና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ባሕላዊ ስፖርቶቻችንን በማልማት በሀገር ውስጥ እንዲዘወተሩ ማድረግ፤ እንዲሁም በአሕጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት እንዲኖራቸው በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም አክለዋል።

ሁሉም ሀገራት የየራሳቸው ባሕላዊ ስፖርቶች እንዳሏቸው የጠቆሙት የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሐመድ፣ ኢትዮጵያም ብዝኃ ባሕላዊ ስፖርትን የታደለች ሀገር መሆኗን አስረድተዋል። የባሕል ስፖርቶች በኢትዮጵያ የመሰብሰቢያና የማኅበረሰብ አብሮነት ማጠናከሪያ ሆነው ማገልገላቸውንም ገልፀዋል።

የባሕል ስፖርቶችን በሥርዓተ ትምህርት እና በዩኒቨርስቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በማካተት የተሻለ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልፀውም፣ የባሕል ስፖርቶች ባሕልን በማስተዋወቅ በቱሪዝም ዘርፉ የሀገርን ገጽታ እየገነቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል። የዘንድሮው ውድድርና ፌስቲቫልም በጠንካራ ስፖርታዊ ጨዋነት በስኬት ይጠናቀቃል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለፁት፣ ስፖርት የማኅበረሰባዊ ትስስርና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሣሪያ ነው። የስብዕናና የሀገር ገጽታ መገንቢያም ነው። የዚህ ባሕላዊ ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ዓላማም የባሕል ስፖርትን ለማሳደግና የሀገራችንን ሕዝቦች ለማቀራረብ ነው። በዝግጅቱ ሁሉንም እንግዶቻችንን በሰላም፣ በደስታና በጤና አስተናግደን እንደምንሸኝ እተማመናለሁ ብለዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ እንየው በበኩላቸው፣ የሆሳዕና ከተማ በዕድገት ጎዳና ላይ ያለች ጥንታዊ ከተማ ናት ብለዋል። የሀገር አቀፉን የባሕል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ለማስተናገድ በሁሉም ዘርፍ ሰፊ ዝግጅት አድርጋለች። “መርሐ-ግብሩ ከተማችንን፣ ቱባ ባሕላችንንና ዕሴቶቻችንን ከማስተዋወቁም በላይ የሕዝባችንን እንግዳ ተቀባይነት ያሳያል።” ሲሉም ተናግረዋል።

በሆሳዕና ከተማ አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም በሚካሄደው የ2017 ዓ.ም የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል፤ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች፣ በድምሩ ከ1386 በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ከእነዚህም መካከል 789 ወንድ እና 596 ሴት ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡ 5 የባሕል ስፖርት ኢንስትራክተሮች እና 5 የባሕል ፌስቲቫል ዳኞችም ይመሩታል፡፡

ትናንት የተጀመረው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል በ11 የባሕል ስፖርቶችና በባሕል ስፖርት ፌስቲቫል ውድድር እያስተናገደ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You