በአምቦ ከተማ 16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 12ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል «የባህል ስፖርት ተሳትፎአችን ለሰላምና ለአንድነታችን» በሚል መሪ ቃል በአምቦ ስታዲየም ዛሬ በይፋ ተጀመረ።
የዕለቱ ፕሮግራም መከፈትን በይፋ ያበሰሩት ክብርት ዶክተር ሂሩት ካሳዉ የስፖርት ፋይዳዎች ዘርፈ ብዙ መሆናቸዉን በማስታወስ የብሔራዊ ስፖርት ፖሊሲያችን ባስቀመጠ አቅጣጫ መሠረት ህብረተሰቡን የበለጠ በባህል ስፖርቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በጥናት ላይ የተመሠሰተ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመናገር ዉድድሩና ፌስቲቫሉ በይፋ አስከፍተዋል።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተፈራ በዳዳ፣አና የኦሮሚያ ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ናስር በበኩላቸው ፤አምቦ የሠላም እና የፍቅር ከተማ አንዲሁም ዉጤታማ አትሌቶችን እና ተዋቂ መዑራንን በማፍራት በመጥቀስ መልካም የቆይታ ግዜ ይሆን ዘንድ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ባህል ስፓርቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አሰፋዉም በመቀጠል የዘንድሮዉ የባህል ስፓርቶች ፌስቲቫልና ዉድድር ዕድሜና ጾታ ሳይገድብ ህብረተሰቡን ባህል ስፖርቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድድረግ በተለይ ስፖርቱ በሚፈጥርልን መልካም አጋጣሚ የአገራችን ሠላም በጋራ ለማክበርና ለማስከበር ነዉ ብለዋል።
በአምቦ ከተማ በድምቀት እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር በ13 የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ይሆናል ።የስፖርት አይነቶቹም ትግል፣ ገና ፣ ገበጣ፣ ፈረስ ጉግስ፣ ፈረስ ሸርጥ፣ ኮርቦ፣ ድብልቅ ኮርቦ፣ ሻህ፣ቡብ፣ ሁሩቤ ፣ ቀስት ፣ ድብልቅ ቀስት እና በባህላዊ ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ:፡
በውድድሩ አዲሰ አበባ ፣ድሬደዋ፣አማራ፣ደቡብ ብሔር ብሔረሰብ እና ህዝቦች፣ሐረሪ እና ኦሮሚያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።በአምቦ ስታዲየም ድምቀቱን እንደጠበቀ ከካቲት 16 እስከ 24 ዓ.ም በአምቦ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።
በዳንኤል ዘነበ
ፎቶ ሃዱሽ አብርሃ